የጃንሜዳው የሃርሞኒካ የቃል ግጥሞች

32

በጥምቀት በዓል ሲከበር ጃንሜዳ ነበርኩ። ወትሮ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚታወቀው ስፍራው በበዓል አክባሪ ሰዎች ተሞልቶ ነበር። ሚሊዮኖችን ዋጥ አድርጎ አላየሁም በሚለው ሰፊው የጃንሜዳ ግቢ ደግሞ ከሃይማኖታዊ ክንውኖች ባሻገር የተለያዩ ዓይነት ጨዋታዎች ተስተናግደዋል። በጥምቀተ ባህሩ አካባቢ ሽብሸባ እና ዝማሬ ቢስተዋልም ሁለት እና ሦስት መቶ ሜትሮችን አለፍ ብሎ ደግሞ «አለ ሌላ፤ አለሌላ» የሚሉ ወጣቶች ቢዝነሳቸውን ሲያጧጡፉት ይታያሉ። የተለያዩ ዓይነት ጨዋታዎችን በማካሄድ በአንድ ብር አምስት ብር እና በሁለት ብር አስር ብር የሚያቋምሩ ጨዋታዎችን ለሦስት ቀናት አካሂደዋል።

አንዱ ሳንቲም ከርቀት ወርውሮ ውሃ በተሞላ ሳህን ውስጥ ማስገባትን ሲያቋምር ሌላው ዓይኑን ታስሮ የግብ አግዳሚ ላይ የታሰረች ጀበናን ለመስበር ገንዘብ አስይዞ ይጫወታል። አለፍ ሲሉ ደግሞ የቁጥር ግመታ ባለዕድል ጨዋታ እና የተጠቀለለ ቀበቶ መሃልን የማወቅ ጨዋታ እንዲሁም ሌሎች ጨዋታዎች የዕለቱ ትዕይንቶች ነበሩ። ከዚህ ማዶ ደግሞ ጭፈራቸውን የሚያስነኩ ሃርሞኒካ የተሰኘውን የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያ የያዙ ወጣቶች አሉ።

ክብ ሠርተው ያጨበጭባሉ፤ አንድ ሃርሞኒካ የያዘ ወጣት ደግሞ በእጁ የያዛትን መሳሪያ እየነፋ ቀጭን ድምፅ ያወጣል። ሌሎች ጓደኞቹ ደግሞ ሲያሻቸው «ዳራን ዳራራን» እያሉ የሃርሞኒካዋን ድምፅ ያስተጋባሉ፤ ሲያሻቸው ባሉበት ጎንበስ ቀና እያሉ ይወዛወዛሉ። መሃል ላይ ደግሞ በግምት አስራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንድ እና ሴት ተቃቅፈው የአፍሪካ ምት ያላቸው ሙዚቃዎች ላይ በብዛት የሚታዩ የዳንስ ዓይነቶችን ያሳያሉ።

በጨፋሪዎቹ ዘንድ የሃርሞኒካ ጭፈራ የሚል ስያሜ የተሰጠውን ጨዋታ በብዛት በወጣትነት ዕድሜ ላይ ያሉት ናቸው የሚጫወቱት። ከጭፈራው ይልቅ ግን በዜማ አውጪው የሚጠቀሱ የተለያዩ ዓይነት ግጥሞች ስበውኛል። ግጥሞቹ በአብዛኛው ተቀባይ ያላቸው እና የሙዚቃ ዜማ ተወስዶ ግጥሞቻቸው የተቀየሩ ናቸው።
ካገር ያወጣኝ እንጀራ
ማሚዬ ሚስቴን አደራ
ከፍከፍ ከፍ /አዝማች/
ካገርያወጣኝ መንግሥት
መለሰኝ አብይ ከስደት
ከፍከፍ ከፍ የሚለውን ዜማ ብንመለከት ካገር ያወጣኝ እንጀራ እናት ሃገሬን አደራ የሚለውን የብርሃኑ ተዘራን ሙዚቃ ዜማ ተጠቅሟል።
በዚሁ የጥምቀት ወቅት የሃርሞኒካ ጨዋታዎች እና ግጥሞች ላይ ጥናት ያደረጉት ወይዘሮ ሕሊና ሰብስበው በጥናታቸው እንዳስነበቡት፤ ጥናቱ «ወደዘመናዊነት ሽግግር እና ባይተዋርነት በጃንሜዳ ሀርሞኒካ ቃል ግጥሞች አውዳዊ ክንዋኔ» ይሰኛል። በሃርሞኒካ ጨዋታዎች ላይ ያሉ ግጥሞችን ፎክሎራዊ ትንታኔ ሲሰጡ፤ አብዛኛዎቹ ግጥሞች ከማህበረሰቡ ወጣ ያሉ የቃላት አጠቃቀም እና አንዳንድ ጊዜም ልቅ የቃላት አጠቃቀምን እንደሚከተሉ ይገልጻሉ። ይሁንና ሂስ የሚሰጡ እና መልዕክት አስተላላፊ ግጥሞችን እንደሚ ያዘወትሩ ያስረዳሉ። ለአብነት
ባናገርኩሽ ቁጥር አትበይ ባሌ ባሌ
አታካብጂ ነገሩን ልክ እንደቀበሌ
የሚለውን ግጥም ብንመለከት በአንድ በኩል ልጅቷን ሲያናግራት ባል እንዳላት ብትነግረውም ልሰማት መሆኑን ሲገልጹ በሌላ በኩል ጉዳዩን ከቀበሌ አሠራር ጋር ያያዙበት መንገድ ትችት አዘል ነው። ቀበሌ ጉዳዮችን ያንዛዛል፣ ያራዝማል በማለት የልጅቷን መልስ እያገኙ ዜማቸውን ያወርዳሉ።
አንድ ፍትህ ያጣ የወንጀለኛ ታዳጊን ታሪክ የያዘ የሃርሞኒካ ግጥም በተጨማሪነት እንመልከት። በዚህ ቃል ግጥም ውስጥ ከእስር እስከ መፈታት ያለውን ሂደት እና በእስር ላይ ያለውን መከራ በግልጽ ይናገራል።
ሸንበቆ ቢረዝም ወንዝ አይሻገርም /አሀ አሀ ይላሉ ተቀባዮች/
የታሰረ ሁሉ መፈታቱ አይቀርም አሀአሀ ይልና የአስቴር አወቀን ሰኞ ዕለት የሚለውን ዘፈን ዜማ ይዞ የሚከተለውን ግጥም እየደነሰ ያዜማል፡፡
ሰኞ ለት ጋማ አሉኝ በድንገት
ማክሰኞ ቀረብኩኝ ፍርድ ቤት
ሮብ ቅልጥ ያለው እራብ
ሀሙስ ውደቅ ተኛ ተነስ
ዓርብ ላይ ለወሱኝ አንድ ላይ
ቅዳሜ ተኛሁኝ ታምሜ
እሁድ ዋስ አቅርብ አሉኝ
ግጥሙ በተለይ ወደመጨረሻ ቤት አይመታም ነገርግን ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልዕክት በዜማ ያስተጋባል። ይህን የሃርሞኒካ ጭፈራ የቃል ግጥም አጥኚዋ ሲያብራሩት በመጀመሪያው ቀን «ጋማ አሉኝ» ማለቱ ጥፋት አጥፍቶ ተያዝኩ ለማለት መሆኑን ይገልጻሉ። ከዚያ በኋላ የእስር ቤቱን መከራ ለመግለጽ እራብ እና ውደቅ ተነስ ተብሎ ስፖርት መሥራቱን እንዲሁም ለወሱኝ ሲል የደረሰበትን መከራ ያሳየናል። የእስር ቤቱን ችግር በአግባቡ ይተቻል።
ከዚያ ደግሞ ከእስር ሲወጣ የደረሰበትን ተስፋ መቁረጥ እና ለሱስ ጥገኝነት መጋለጡን የሚያሳይ ግጥም ያስከትላል።
ስወጣ ከእስር ቤት
ገባሁኝ በርጫ ቤት
ሲጋራ ሳጣ ከኪሴ
ያበሳጨኛል ያሱሴ
ከገዛህልኝ ሲጋራ
እንዳሻህ አርገኝ ዲያስፖራ እያለ የገባበትን ማጥ ቁልጭ አድርጎ በጨዋታ መልክ ያቀርበዋል።
የሀርሞኒካ ግጥም ተጫዋቾች ከሌላው የማህበረሰብ ክፍል ይለያሉ፡፡ ለአብነትም የአለባበስ እና የጸጉር ቅብ እንዲሁም ቁርጣቸው ይለያል። በተለይ ሱሪ ዝቅ ማድረግ እና አንድ እጀታን ቆርጦ በአንድ እጀታ ብቻ ካናቴራ መልበስ እንዲሁም ቀይና ነጭ ቀለማትን ጸጉራቸውን መቀባትና ሴት ልጅን ጎትቶ በግድ የማስደነስ ተግባር መለያቸው ነው። አንዳንዴም የነውረኛነት እና የመገለል ምልክት የሆኑ ቃላትን እያወጡ የሃርሞኒካ ጭፈራ ላይ የሚካፈሉ ወጣቶች በርካታ ናቸው።
የተስፋ መቁረጥ ምልክት የሆኑ እና ውጥንቅ ጣቸው የጠፋ ግጥሞችን ለጨዋታ ብቻ ብለው ቢያቀርቡም በብዛት ግን ተወዳጅ የሆኑት መልዕክት ያላቸው ናቸው። ምክንያቱም በጃንሜዳ ያለው ታዳሚ መጥፎ ቃላት በግጭት መልክ ሲቀርቡለት ቀስ በቀስ ከበባውን ትቶ ይበተናል። ይሁንና መዕክታቸው ከሳበው ደግሞ ልክ እንደእኔ ቆሞ ሊያዳምጣቸው እና አለፍ ሲልም በጭብጨባ ሊያግዛቸው ይችላል።
ግጥም አቅራቢዎቹ ደግሞ የሰፈራቸውን ስም ማሞጋገስ ይቀናቸዋል። ለምሳሌ ከጃንሜዳ ብዙ ጊዜ የቀበና፣ የመነን፣ የፈረንሳይ ለጋሲዮን እና የቤላ እንዲሁም ሌሎች በአቅራቢያ ያሉ ወጣቶች ይመጣሉ። መንደራቸውን ከሰው ባህሪ እና መልክ እንዲሁም የተለያየ ሁኔታዎች ጋር እያዛመዱ ያወድሳሉ። ለአብነት የሚከተለውን ግጥም ማየት ይቻላል።

የማርገጃ /አሀሀ ይላሉ ተቀባዮች/
አለው ሳንጃ
የመነኗ
አቤት አይኗ
የዮሐንስ አለው ድግስ
በጃን ሜዳ የለምእዳ ከዚህ የሀርሞኒካ ግጥም ዜማ የራያ ባህላዊ ዘፈኖች ዜማ የተወሰደ ቢሆንም መልዕክቶቹ እና ዳንሱ ግን ለየቅል ነው። በሌላ በኩል የእራሱ የሃርሞኒካ ዜማ ማለትም ከሌላ ያልተወረሰ ተብሎ አይታሰብም፡፡ አንዳንዴም ከሃይማኖታዊ መዝሙራት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህን የሚያስረዳን ደግሞ የሚከተለውን ስንኝ የያዘው ነው።
ተወልደናወ ተወልደን አራዳ
አምልጠን የለም ወይ ቦንቡ ሲፈነዳ
ተወልደና ተወልደን ጉለሌ
መልሰን የለም ወይ የርዳታውን ስንዴ
ተወለደና ተወልደን ማርገጃ
እንቢ ያልን እንደሆን ማምለጫውን እንጃ
እንቢ እንጃ… እቢ እንጃ
እያሉ ዳንሳቸውን ይቀጥላሉ።
ስለፌዝ፣ ስለነውረኝነት እና ሌሎችም ቁምነገር አዘል ግጥሞች ሲያቀርቡ እና ሁካታ ውስጥ የነበሩ ወጣቶች ስለሰፈራቸው ሲዘፍኑ ደግሞ ረገብ ብለው ነው የሚሰሙት። ይህ ሁሉ የጥምቀት ቀናት በተለይም የበዓሉ ዕለት እና የቃና ዘገሊላ እለት የሚታዩ ክስተቶች ናቸው። የሃርሞኒካ ጨዋታ በበዓሉ ካልሆነ በአዘቦት ቀን ማንም አይከውነውም። ይህን የሃርሞኒካ ጨዋታ ታዲያ ለጥምቀት በዓል ጎራ ያሉ አንዳንድ ፈረጆችም ሊሳተፉበት ይችላሉ። ዳንሱን እንጂ ግጥሙ የማይገባቸው የውጭ ዜጎች ለጊዜያዊ መዝናኛነት በሚል ዓይተው እና አጨብጭበው ያልፉታል።
የሀርሞኒካ ግጥሞች ላይ ጥናት ያደረጉት ወይዘሮ ሒሩት ግን ነገሩን በዋዛ ብቻ ማለፍ እንደማይገባ ነው በጥናታቸው ያሰፈሩት። ይልቁንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በርካታ እቅዶቹን ከጨዋታዎቹ እና ከጥምቀት ክዋኔ ጋር ቢያስተሳስር መልካም ጥቅም እንደሚያገኝ ይጠቁማሉ።
የቀድሞ ነገሥታት እረኛ ምን አለ ብለው እንደሚያጠይቁ እና የህዝቡን ስሜት እንደሚረዱ ሁሉ በጃንሜዳም ምንተባለ? መባል ቢጀምር ከህዝብ ጋር መደማመጡ እንደሚያይል ያስረዳሉ። እኛም እንዳለፉት የጥምቀት ሃርሞኒካ ግጥሞች ሁሉ ቀጣዮቹም የአደማጩን ቀልብ ሳቢና ተቺ እንደሚሆኑ በመገመት እንሰናበታለን። መልካም ሰንበት!!

አዲስ ዘመን ጥር 19/2011

ጌትነት ተስፋማርያም