የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ለሚያስተላፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊነት በጋራ እንደሚሰሩ አጋር ሊጎች ገለጹ

38

ሐዋሳ፡ የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ወጣቱ በአገሩ ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ድጋፋቸው እንደማይለይ አጋር ሊጎች ተናገሩ፡፡

በአራተኛው የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ጉባኤ ላይ ተገኝተው የአጋርነት መልዕክታቸውን ባስተላለፉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በአንድ አገር ሁለንተናዊ ለውጥ ውስጥ ወጣቶች ጉልህ ድርሻ አላቸው፡፡ ወጣቶች ለዚህ ተግባር የድርሻቸውን እንዲወጡ ከማድረግ አኳያ ደግሞ የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ጉልህ ድርሻ ተወጥቷል፡፡ አሁንም ይሄንኑ ተግባሩን ከማጠናከር አኳያ በጉባኤው የሚያስተላልፈው ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆን በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ከጎኑ ሆነው በመደገፍ የድርሻቸውን ይወጣሉ፡፡

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዘቦች ደሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) ወጣቶች ሊግ በተወካዩ አማካኝነት ባስተላለፈው መልዕክት እንደገለጸው፤ የወጣቶች ተጠቃሚነት ካለው በተሻለ እንዲጎለበት የወጣቱ ፍላጎት ነው፡፡ በዛው ልክ አገር ከወጣቱ ብዙ ትጠብቃለች፡፡ የተገኘው ለውጥም ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት፣ ጊዜና ገንዘብ ተከፍሎበታል፡፡ እናም ወጣቱም የሚፈልገውን እንዲያገኝ፣ አገር የምትጠብቅበትንም እንዲወጣ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከማህበራዊ ሚዲያ ጀምሮ የሚነዙ አፍራሽ አጀንዳዎችን ተገንዝቦ የወጥመዳቸው ተገዢ ባለመሆን ሊሰራ ይገባል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወጣቶችም በዚሁ አግባብ የሚሰሩ እንደመሆናቸው፤ ሊጉ ከኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ልምዶችን በመቅሰም ለላቀ ተጠቃሚነትና ተሳትፏቸው የሚሰራ ይሆናል፡፡ በዚህ ጉባኤም የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ከኢህአዴግ ተራማጅ አካሄድ በመማር በቀጣጥ አጋር ሊጎች አጋር የሚሆኑበትን ውሳኔ እንደሚያሳልፍ መልዕክት ያስተላለፉት ተወካዩ፤ በቀጣይ ሊጉ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎችን እንደሚያሳልፍ ያለውን ተስፋ አስቀምጧል፡፡

የቤጉህዴፓ ወጣቶች ሊግም በዚህ ጉባኤ የሚተላለፉ ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ከኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ጎን በመሆን የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ወጣቶች ሊግም በተወካዩ አማካኝነት ባስተላለፈው መልዕክት እንዳለው፤ ለውጡ የተበተኑ ወገኖችን ያሰባሰበ ነው፡፡ ይህ ለውጥ ከዳር እንዲደርስና የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ሊጉ ይሰራል፡፡

የክልሉ መንግስትም አብዴፓ በቅርቡ ባካሄደው ጉባኤ ወጣቶችን ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚያደርጉ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፤ ወጣትና የተማሩ ሰዎችንም ወደሃላፊነት አምጥቷል፡፡ ይህ ደግሞ ወጣቱ በአገሩ ልማትና ሰላም በባለቤትነት እንዲሰራ የሚያደርግ እንደመሆኑ፤ በዚህ ጉባኤ የሚወሰኑ ውሳኔዎችና የሚቀመጡ አቅጣጫዎች ከዳር እንዲደርሱ የአፋር አብዴፓ ወጣቶቸ ሊግ በአጋርነት ይሰራል፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ወጣቶች ሊግ በበኩሉ ባስተላለፈው መልዕክት እንደገለጸው፤ ወጣቱ በአገሩ ጉዳይ ተሳታፊና ከጥቅሙም ተጋሪ ለመሆን የሚፈልገውን ያክል አገርም ከእርሱ ብዙ ትጠብቃለች፡፡ የአገር ልማትና ሰላምም የተመሰረተው በዚሁ ወጣት ላይ ነው፡፡ እናም ወጣቱ ይሄን ተገንዝቦ መስራት ያለበት ሲሆን፤ በዚህ ጉባኤም ለዚህ ተግባር አጋዥ የሚሆን ውሳኔ የሚጠበቅ እንደመሆኑ የኢሶዴፓ ወጣቶች ሊግ ለተፈጻሚነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡

የጋምቤላ ህዘቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህአዴን) ወጣቶች ሊግም በተመሳሳይ ባስተላለፈው መልዕክት እንዳመለከተው፤ ለውጡ በሰላምና በፍቅር የመደመር እንደመሆኑ፣ ወጣቱ ልዩነቶቹን ወደጎን በመተውና አንድነቱን በማጠናከር ከመንግስት ጎን በመቆም የልማትና የሰላም ባለቤትነቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግም በጉባኤው ይሄን ሊያግዙ የሚችሉ ተግባራትን መፈተሽ የሚገባው ሲሆን፤ አዳዲስ አባላትን ወደሊጉ ማስገባትም ይኖርበታል፡፡ የጋህአዴን ወጣቶች ሊግም በጉባኤው የሚደረሱ ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ከሊጉ ጎን በመሆን ይሰራል፡፡

የሀረሪ ብሄራዊ ሊግ (ሀብሊ) ወጣቶች ሊግም በተመሳሳይ ባስተላለፈው መልዕክት እንዳለው፤ ለውጡን መቀበል ብቻ ሳይሆን ራስን የለውጡ አካል ማድረግ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ሊጉም በጉባኤው በዚህና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በተለይም ለውጡን ከማስቀጠልና የወጣቱን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚነት የሀብሊ ወጣቶች ሊግ ያላሰለሰ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

በወንድወሰን ሽመልስ