“የማንነት እንቅስቃሴ እኩልነትን ማረጋገጫ መንገድ እንጂ በራሱ ፖለቲካ አይደለም” ዶክተር ብርሃነመስቀል አበበ የሕግና ፖሊሲ ባለሙያ

1194

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ አከባቢያቸው አርሲ አጠናቅቀዋል፤ የከፍተኛ ትምህርት ጉዟቸውንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ በሕግ ትምህርት ቤት አንድ ብለው፤ ወደ አሜሪካ በማቅናት በኒዮርክ እና ሚኒሶታ ዩኒቨርሲቲዎች የሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡ አገራቸውንም በከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኝነት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕግ አማካሪነት፣ እንዲሁም ኒውዮርክ በሚገኘው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ዲፕሎማት በመሆን አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካን አገር በሕግ ማማከርና ጥብቅና ስራ ላይ ተሰማርተዋል፤ ዶክተር ብርሃነመስቀል አበበ ሰኚ፡፡ እኛም ለዛሬው የፖለቲካ ገጽ ዕትማችን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ከእኚህ የሕግና የፖሊሲ ባለሙያ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ፣ ለውጡን ተከትሎም የተካሄደውን የፖለቲካና የአመራር ሪፎርም እንዴት አገኙት?
ዶክተር ብርሃነመስቀል፡- ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ በኦሮሚያ፣ በኋላ ደግሞ በአማራ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡ የዚህ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ዓላማ ደግሞ በህወሃት ኢህአዴግ ሲመራ የነበረውን ጨቋኝ ስርዓት ማፍረስና በምትኩ ህዝባዊ መንግስት ማቋቋም ነበር፡፡ እናም የጭቆና ስርዓቱን ለማፍረስ ህዝቡ ባደረገው ትግልና ከኢህአዴግ ውስጥ በወጡ የለውጥ ሃይሎች ወይም “ቲም ለማ” በምንላቸው ሃይሎች ድርጅታዊ አቅም አግኝቶ የህዋሃት ኢህአዴግ አመራር (ይሄን የምለው ህወሃት ኢህአዴግን እንደ መግዣ መሳሪያ ይጠቀምበት ስለነበር ነው) እንዲሸረሸር አድርጓል፡፡

ምክንያቱም በኢህአዴግ የጭቆና ስርዓት ሕወሃት እንደ ርዕዮተ ዓለም ሲከተል የነበረው የመከፋፈል ሂደት ሲሆን፤ በጥፋት ተግባሩም መሬት የመዝረፍ፣ ህዝብ የማሰርና የመግደል፣ ከአገር እንዲሰደዱ ማድረግና ሃብት የመዝረፍ፣ የጭቆና ስርዓቶችን ህዝቡ ላይ መዘርጋት፣ በሽብርና በፖለቲካ አስተሳሰብ መክሰስ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ሀሳብን በመጻ የመግለጽ መብቶችን ማገድና መሰል ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ስርዓትን ህዝቡ አፍርሶ ከለውጥ ሃይሎቹ ጋር ለውጡ እዚህ ደርሷል፡፡ አሁን ደግሞ የጭቆና ስርዓቱን የማፍረስ ምዕራፍ ላይ ነው ያለው፡፡ በዚህም የስለላ መዋቅሩ ፈርሶ ህዝብን ወደማገልገል እንዲመለስ፤ የፍርድ ቤት መዋቅሩም በአዲስ ሃይል እንዲተካና ህዝቡን ወደማገልገል እንዲገባ፤ የመከላከያ መዋቅሩም ህዝብን ወደማገልገል እንዲመለስ የማድረግ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው፡፡

እኔ ይሄንን ሂደት አራት ቦታ ከፍዬ ነው የማየው፡፡ የመጀመሪያው ምዕራፍ አሳሪ የነበሩትን የፕሬስ ሕጉን፣ የጸረ ሽብር ሕጉን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና መሰል የጭቆና ሕጎቹን የማረም፤ የጭቆና መዋቅሩን የማስተካከልና በጭቆናው አሉታዊ ሚና ሲጫወቱ የነበሩ ሰዎችንም ከቦታ የማንሳት፤ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች የማስፈታት፤ በጥቅሉ መዋቅራዊ ለውጦችን ማድረግ ነው፡፡ የዚሁ አካል የሆነውና በሁለተኛ ደረጃ የሚታየው፣ የተጠያቂነት ምዕራፍ ሲሆን፤ በዚህም በ27 ዓመት ውስጥ በብዝበዛውም፣ በግድያውም፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰትም፣ በማሳደድና በማሰሩም፣ የህብረተሰቡን ማህበራዊ እሴት በማፍረስ ደረጃ ሲሰማሩ የነበሩ ዋና ዋና ሰዎችን በተቻለ መጠን ተጠያቂ የማድረግ ምዕራፍ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አሁን ያለነው የጭቆና መዋቅሩን የማፍረስና የተጠያቂነት ምዕራፍ ላይ ነው፡፡

ቀጥሎ ሊሆን የሚችለውና መደረግ ያለበትም ባለፉት 27 ዓመታት የፈረሰውን አገራዊ የመንግስት ስትራክቸሩን፣ ማህበራዊ እሴቱን፣ እንዲሁም ህዝብ በራሱ አገር ባይተዋር የሆነበት ጊዜ አብቅቶ ወደ ብሄራዊ አገር ግንባታ ፖለቲካ መሸጋገር ነው፡፡ በዚህም ነጻ የሆነ ቢሮክራሲ፣ ነጻ የሆነ መከላከያ፣ ደህንነትና ፖሊስ ከተገነባና የፓርቲ ስርዓቶች እንደገና ከተዋቀሩ በኋላ ወደምርጫ የምንሸጋገርበት አራተኛው ምዕራፍ/ደረጃ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለውጡንና ሂደቱንም በዚህ መልኩ መረዳት ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለውጡን ተከትሎ መልካም ነገሮች የመምጣታቸውን ያክል ፈታኝ ሁኔታዎችም እየታዩ ነው፡፡ በለውጥ ሂደት ደግሞ እነዚህ ሁለት ነገሮች ተጠባቂ መሆናቸው ይነገራል፡፡ በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ?
ዶክተር ብርሃነመስቀል፡- ከጥንካሬው ስጀምር፣ ይሄ ለውጥ በህዝብ ግፊት የመጣ እንደመሆኑ የህዝብ መሰረት ያለው ለውጥ ነው፡፡ ያን የጭቆና ስርዓት ህዝብ አንገሽግሾት በፓርቲ ተመርቶ ሳይሆን ህዝብ ተናብቦ ያደረገው ህዝባዊ ለውጥ ነው፡፡ ይሄንን ህዝብ ተናብቦ ያደረገውን ለውጥ የትኛውም ሃይል ሊቀለብሰው አይችልም፡፡ ምክንያቱም በደቡብ አፍሪካ ውስጥ የህዝባዊ ተቃውሞው የአፓርታይድ ስርዓት ለውጥ እንዳደረገ ሁሉ፤ በኢትዮጵያም የህዝቡ ተቃውሞ እነዚህን የለውጥ ሃይሎች ወደፊት ማምጣት ችሏል፡፡ ስለዚህ ለውጡ ሰፊ ህዝባዊ መሰረትና ህዝባዊ ተቀባይነት ያለው፣ በህዝብም የመጣ ለውጥ ስለሆነ የጸና መሰረት ያለው፤ የጸና መንግስትና ለውጥ ነው፡፡ ይሄ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ውስጣዊ የሽግግር ሂደት ስለሆነ ሥርዓቱ ውስጥ የነበሩት፣ ገና ያልጸዳ ቢሮክራሲ ውስጥ ያሉት፣ ገና ያልጸዳ መከላከያ፣ ደህንነትና ፖሊስ ውስጥ ያሉት፣ ያልጸዳው የግል ሴክተር ውስጥ ያሉት፣ ባለፉት 27 ዓመታት እጃቸው ውስጥ የገባውን ገንዘብ ተጠቅመው ሲከተሉት የነበረውን የመከፋፈያ ሕግና ፖሊሲ ተከትለው በህዝቦች መካከል ግጭቶችን ለመፍጠር የሚሰሩ አሉ፡፡ ይሄም ቢሆን ተጽዕኖዎችን ፈጥሮ የለውጡን ግስጋሴ ለመጎተትና ለማቀዝቀዝ ካልሆነ በስተቀር ለውጡን ሊገታ የሚችልበት ወይም የለውጡን ጥምረት ሊያቋርጥ የሚችልበት ምንም እድል የለውም፡፡

ሆኖም እዚህኛው ላይ የለውጥ ሃይሉና ህዝቡ ማድረግ ያለባቸው ነገር አለ፡፡ በመጀመሪያ፣ ግጭት በመፍጠርና ህዝብን በማጣላት ችግር እየፈጠሩ ያሉትን ሃይሎች ተጠያቂ የሚያደርግበትን ሂደት ማጠናከር ነው፡፡ ለዚህም የመንግስቱን መዋቅር፣ የለውጡን መዋቅር፣ እንዲሁም የለወጡን ደጋፊዎች ጉልበት ማጠናከር አለበት፡፡ ሁለተኛም፣ ህዝቡ ህግና ስርዓትን ማስከበር የዴሞክራሲ ስርዓት አንዱ አካል መሆኑን ተገንዝቦ በየአከባቢው ህግና ስርዓትን ማስከበር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ከመንግስት ጋር መቆም አለበት፡፡ ይህ ሲሆን በህብረተሰቡ ውስጥ ህጸጾችን እየፈለጉና የህዝብን ቀዳዳ እያዩ ይሄንን አስታከው ህዝብን ለማጣላት ቦታና አቅም ያጣሉ፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የለውጥ ሃይሉ የለውጥ ሃይሎችን ከፌዴራል እስከ ክልል፤ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ የስልጣን መዋቅሮች ተራማጅ ሃይሎችን አቅፎና የለውጥ ሃይሉን አጠናክሮ ለውጡ በታለመለት ፍጥነት ለታለመለት ዓላማ እንዲገሰግስ ማድረግ፤ ግስጋሴውን የሚጎትቱትን ሃይሎችም መቁረጥ ነው፡፡ አራተኛም፣ ለውጡ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው በአገር ውስጥ ካለው ህዝብ ብቻ ሳይሆን በውጪ ባሉ ኢትዮጵያውያንም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ውጪ ያለው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በፊት የተቃዋሚ ሃይሎች ማዕከል ነበር፤ አሁን ግን ያ ቀርቶ የለውጥ ሃይሎች ማዕከል ሆኗል፡፡ ስለዚህ ይሄ ለውጥ ውጤታማ እንዲሆን በአገር ውስጥ ማደራጀት ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉትንም አደራጅቶ በእውቀት፣ በገንዘብና በሰው ሃይል የለውጡ ደጋፊዎች አድርጎ መንግስቱን ማጠናከርና ይሄ አገር እስከዛሬ ከነበረበት የጭቆናና ጥፋት ዑደት እንዲወጣ ማድረግ አለበት፡፡ በፖለቲካ ምክንያት ተሰድዶ በውጭ ያለውና በተለያየ ምክንያት የውጭ ዜግነት ያገኘውም ዳያስፖራ ጥምር ዜግነት በመስጠት አቅሙን ለአገሩ እንዲያውል ማስቻልም ያስፈልጋል፡፡

በአምስተኛ ደረጃ፣ አሁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነትና ብሔራዊ ጥቅም ቁልፉ የዚህ ለውጥ ከግብ መድረስ ነው፡፡ ይሄ ለውጥ ከግቡ ደርሶ ስኬታማ እንዲሆን ከውጪው ማህበረሰብ የዲፕሎማሲ፣ የገንዘብና የሞራል ድጋፍ የሚያስፈልገው መሆኑን ተረድቶ የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ እንዳለ ይሄንን ለውጥ ማሳካት ላይ እንዲያተኩርና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሃይልም የሚታየውን የውጪ መንግስታት ድጋፍ በማሰባሰብ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ፤ የሚደረጉ የመዋቅር ለውጦችን የሚደግፉ የሰው ሃይል፣ የእውቀትና ፋይናንስ ድጋፎች ከውጭ እንዲመጡም መንገዱን ማመቻቸት ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለውጡ የመላው ኢትዮጵያ ውያን ውጤት ቢሆንም፤ ሰፊ መስዋዕት በመክፈል ጭርም ጀማሪ እንደሆነ የሚታመነው ለኦሮሞ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ለእርሱ ነጻነት እንታገላለን የሚሉ ፓርቲዎች ጭምር ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሰላም እንዲታገሉ እድል የሰጠ ቢሆንም፤ የኦሮሞ ፓርቲዎች እርስ በእርሳቸው ባለመግባባት የኦሮሞ ህዝብ ተረጋግቶ የለውጡን ውጤት እንዳያጣጥም ሆኗል፡፡ እርሶ በዚህ ዙሪያ ምን ይላሉ? ችግሩንስ እንዴት መፈታት ይገባል?

ዶክተር ብርሃነመስቀል፡- ያልከው ነገር እውነት ነው፡፡ እንቢተኝነቱን አቀጣጥሎ ለውጥ እንዲመጣ ከማድረግ አኳያ የኦሮሞ ፕሮቴስት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፤ የአማራ ይቀጥላል፤ ሌሎች በደቡብና በሌሎችም የኢትዮጵያ ክልሎች ያሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለለውጡ የራሳቸውን ግፊት አድርገው ለዚህ አድርሰዋል፡፡ ለውጡ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ዘሩን መዝራት ላይ ግን በ1966ቱ አብዮት ውስጥ የተሳተፉ የኢህአፓ፣ የኦነግና ሌሎችም ትውልዶች ድርሻ አላቸው፡፡ ምክንያቱም አንዱ ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም የሚለው ያኔም ሲተላለፍ ነበር፡፡
አሁን ግን ይሄንን ለውጥ እዚህ ያደረሰው አሁን ያለው ወጣቱ ትውልድ ነው፡፡ በተለይም የኦሮሚያ ቄሮ ሰፊ ድርሻ አለው፡፡ በመታሰርም፣ በመገደልም፣ ለሽብሩና ጥቃቱ አልገዛም፣ እንሞታለን እንጂ የአገራችን ባለቤት እንሆናለን በሚል እሳቤም ነው የመጣው፡፡ የኦሮሞንም ፖለቲካ የመሃል ፖለቲካ ያደረገ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ነው የተደረገው፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ራሳችንን እናስተዳደር ብቻ ሳይሆን በአገራችን በኢትዮጵያ ላይ እኩል ድርሻ አለን፤ በሚል ነው የኦሮሞ ህዝብ በአገር ውስጥም በውጪም ሰፊ እንቅስቃሴ ያደረገው፡፡

በዛም እንቅስቃሴ በዝባዥና ጨቋን ስርዓቱን አስወግዷል፡፡ ከታች ወደላይ የህዝብ እንቅስቃሴ፣ ከላይ ወደታች ደግሞ በቲም ለማ (በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ያሉ) የሕወሃትን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲን አፍርሰው የአማራና የኦሮሞን ህብረት፣ የኦሮሞና የሌሎችንም ህብረቶችን በማጠናከር ህዝቡ አንድ መንፈስና አንድ ልብ ሆኖ በአገራዊ ጉዳይ ላይ እንዲመክር አድርገው ለውጡ መጥቷል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘሩን በመዝራት ሚና ነበራቸው፤ እንቅስቃሴውን የመራው ግን ህዝቡ ራሱ ነው፡፡ ስለዚህ የዚህ ለውጥ ባለቤት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይሆኑ የኦሮሞ ህዝብ ነው፡፡ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ህዝቡ የጭቆና ስርዓቱን እንዲጥል ነበር እስከዛሬ ሲታገሉ የነበረው፡፡ ያ ምዕራፍ አሁን አልቋል፤ የሚቀጥለው ምዕራፍ የኦሮሞ ህዝብ በኦሮሚያ ውስጥ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር ኢትዮጵያን በጋራ የሚያስተዳድርበት፤ በምስራቅ አፍሪካ ደግሞ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ህዝብ (የሴሜቲክና ኩሺቲክ) አንድ ባህል ያለው ህዝብ፣ በፖለቲካው፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚ የተሳሰረውን ህዝብ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ወደማድረግ የምንሄድበት ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ነው የጠቅላይ ሚንስትሩ ራዕይ፡፡ የኦሮሞ ህዝብም ወደዛ ነው መሸጋገር ያለበት፡፡

የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ህዝቡን አሁን መርዳት የሚችሉት አዲስ ራዕይ ይዘው እስከመጡ ድረስ ነው፡፡ ምክንያቱም እስካሁን ባላቸው መንገድ የጉዞ ምዕራፋቸው አልቋል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ደግሞ አሁን ባለበት ሁኔታ በፖለቲካ አስተሳሰብ፣ በማህበራዊና በአከባቢ፣ እንዲሁም በሃይማኖትም መከፋፈል አይፈልግም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ አንድ ሆኖ በእውቀትና ችሎታ ሊያስተዳድሩት የሚችሉ ሰዎች ሁሉ አንድ ላይ መጥተው፣ የምሑራኑ የጋራ መግባባት ተደርሶ እንዲያስተዳድረው ነው የሚፈልገው እንጂ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በኦሮሚያ ውስጥ እንዲባሉ አይፈልግም፡፡ ሌላውም የኢትዮጵያ ህዝብ ከዚህ የተለየ እሳቤ ያለው አይመስለኝም፡፡

ከተቃዋሚ ሃይሎች እስከዛሬ ድረስ ጨቋኙን ስርዓት ለማፍረስ ከሚያደርጉት ጥረት ባለፈ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ራሳቸውን አላሸጋገሩም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ የሃሳብ ማፍለቂያ መድረክ ነው፡፡ የአገር አስተዳደር ዘይቤዎችን፣ ፍልስፍናዎችን፣ የያዙ የሃሳብ መድረኮች ናቸው፡፡ ያን አይነት አስተሳሰብ በተለያዩ ምክንያቶች በኢትዮጵያ የለም፡፡ ይህ ደግሞ አንድም አፋኝ ስርዓት ስለነበረ፤ ሰዎች የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ሃሳባቸውን የመግለጽ ነጻነትና መብቶች ተከልክለው የነበረበት አገር ስለነበረ የፖለቲካ ፓርቲ እስከዛሬ ባለመፈጠሩ የይስሙላና የስም ፓርቲዎች ናቸው ያሉት፡፡

ወደ አገራዊ ግንባታ/ኔሽን ቢዩልዲንግ/ ሂደት ገብተን አሁን ያለውንም የማንነት ፖለቲካ ወደ የሃሳብ ፖለቲካ አሸጋግረን ይህችን አገር ያደገችና የበለጸገች ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲ ሥርዓቱ ወደ አስተሳሰብ ግንባታ መሸጋገር አለበት፡፡ ምክንያቱም የማንነት እንቅስቃሴ እኩልነትን ማረጋገጫ መንገድ እንጂ በራሱ ፖለቲካ አይደለም፡፡ አማራነት ፖለቲካ አይደለም፤ ኦሮሞነት ፖለቲካ አይደለም፤ ትግሬነት ፖለቲካ አይደለም፤ ሌላም ማንነት ፖለቲካ አይደለም፡፡ ፖለቲካ የሕዝብ አስተዳደር ዘይቤ ከሆነ በማንነት ላይ ያለ ጭቆና በሕግና ፖሊሲ ተቋማዊ ምላሽ አግኝቶ ህዝቡን ወደ አስተሳሰብ ፖለቲካ ማሸጋገር ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው የጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር ያንን እንዲያመጣ ነው የምትፈልገው፡፡

ከዚህ አኳያ የኦሮሞም ሆነ የአማራ መላው የኢትዮጵያ ምሑራንም በዚህ ላይ ምሑራዊ መግባባት ፈጥረው አገሪቱን ማሸጋገር፣ ራሳቸውንም ማሸጋገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ከነበረችበት የፖለቲካ አዙሪት ወጥታ ጠንካራ አገር እንድትሆን ሁሉም መስራት አለበት፡፡ የሚጠበቀውም ይሄ ነው እንጂ ህዝቡን ከፋፍሎ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በአከባቢና በሌላም መልኩ ለማባላት የሚደረገው ጥረት የኦሮሞን ህዝብ አይጠቅምም፤ የኢትዮጵያንም ህዝብ አይጠቅምም፤ አልፎም የምስራቅ አፍሪካን ህዝብ አይጠቅምም፡፡ በኦሮሚያ ክልል የሚታየው ህዝቡን ሰላም የመንሳት ሂደትም በዚሁ አግባብ ተቃኝቶ መታረም አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የመንጋ ፖለቲካና ፍትህ በመስፋፋቱ በህዝቦች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩና ለሕግ የበላይነት አለመከበር መንስኤ መሆኑ ይነገራል፡፡ ታዲያ ይሄን የመንጋ ፖለቲካና ፍትህ ከሕግ የበላይነት ጋር እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?
ዶክተር ብርሃነመስቀል፡- “የመንጋ ፖለቲካ” ባንለው ጥሩ ነው፡፡ ህዝቡ በአንድ ወገን በአብዮት ስሜት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ገና ስምንት ዘጠኝ ወሩ ነው፡፡ ህዝብ ተረጋግቶ ወደሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ የለውጥ ሃይሉም በሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ በፖለቲካ ትርክቱና ሃቲቱም፣ በተለያዩ ምሑራንና አክቲቪስቶችም የሚደረጉ ነገሮች ህዝቡን አረጋግቶ የለውጥ ሃይሉን ወደመገንባት፤ ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ወደመስጠት እንዲመጣና የለውጥ ሃይሉን አደራጅቶ የለውጥ አጋሮችንም ወደራሱ ወስዶ ወደስራ ማድረግ በቀጣይነት መሰራት ያለበት ነገር ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ይሄንን ለውጥ የሚቃወሙ የህዝቡን ችግር እያራገቡ ህቡን ወይ እርስ በእርሱ ሊያጋጩት፣ ወይም ደግሞ የለውጥ ሃይሉን እንዲቃወም ለማድረግ የሚሰሩ ሃይሎች መኖራቸው ታውቆ በዚህ አከባቢም የለውጥ ሂደቱን ራሱ ተሰልፎና ራሱ ሞቶበት ያመጣውን ህዝብ መልሶ ራሱን እንዳይቃወም፤ ራሱን በራሱ እንዳያሰናክል ሚዲያውም፣ የለውጥ ሃይሉም፣ ህዝቡም፣ ምሑራንም መስራት አለባቸው፡፡ ከመንግስት ደግሞ ሕግና ስርዓትን ማስከበሩን፣ የፍትህ ተቋማትን፣ የደህንነት፣ ፖሊስና መከላከያን አይነት የሕግ ማስከበሪያ ተቋማትን አሁን በጀመረው መልኩ ህዝብን ሊያገለግሉ በሚችሉበት አግባብ በማደራጀት ለውጡ እስከታች እንዲወርድ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ህዝብን በተለያየ መልኩ ሲመዘብሩ፣ ሲገድሉ፣ ሲያስሩና ሲዘርፉ የነበሩትን ደግሞ በየእርከኑ ከሲስተሙ ውስጥ ማውጣትና የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እያደረጉ የመሄድ ስራዎች ይጠበቃሉ፡፡

በዋነኛነት ግን ህዝቡ ይሄን ሲያይ መረዳት ያለበት የአስተዳደራዊ ስራው የቀረ ቢሆንም፤ ስትራቴጂክ ለውጡ መጥቷል፡፡ ህዝቡን የሚሰሙ፣ ለህዝቡ ጥያቄ መልስ ለመስጠት እየሰሩ ያሉ፣ ህዝቡን የአገሩ ባለቤት እያደረጉ ያሉት የለውጥ መሪዎች ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩም በዚህ ላይ ቁርጠኝነታቸውን እያሳዩ ነው ያለው፡፡ ሌሎቹም በየቦታው ያሉት የለውጥ ሃይሎች ይሄንኑ እያጠናከሩ ነው፡፡ ነገር ግን 27 ዓመት ወይም ያለፉትን መቶ ዓመታት የተዘረጉ የብዝበዛ መዋቅሮችን ግን በስምንት ወር ይስተካከላል ብሎ ህዝቡ መጠበቅ የለበትም፡፡ ምክንያቱም በፌዴራል ደረጃ ወደ 1ነጥብ5 ሚሊየን የሚጠጋ ቢሮክራሲ ያለባት አገር (በኦሮሚያ ብቻ ወደ 700ሺ የሚጠጋ ሰራተኛ አለ) ይሄንን ለማጽዳት ጊዜ ይፈልጋል፡፡ የለውጥ ሃይሉ ግን ፍጥነቱን ጨምሮ የመዋቅር ለውጦቹን፣ የአስተዳደርና የፍትህ ጥያቄዎችም ምላሽ እየሰጠ መቀጠል አለበት፡፡ ሁሉም ዜጋ ተቀናጅቶ እንደ ቁልፍ ብሄራዊ ጥቅም ወስዶም ነው መስራት ያለበት፡፡

ምክንያቱም አገርን ለማፍረስ የሚችሉ ሃይሎች እኛ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉባቸው ቀዳዳዎች አሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ለውጦች ሲደረጉባቸው የነበሩ አገሮች በጥንቃቄ ካልተመሩ የሊቢያን፣ የሶሪያ፣ የየመንና መሰል አገራትን ሂደቶች መመልከቱ በቂ ነው፡፡ ህዝቡ ባልተረጋጋበት ሁኔታ በርካታ የኢትዮጵያ ወዳጅ ያልሆኑና የዚህችን አገር አንድነትና እድገት የማይመኙ፣ በግል ጥቅምም ዓይናቸውና አዕምሯቸው የታወሩ ሰዎች አገር የሚያፈርስ ስራ፣ ህዝብ ከህዝብ ጋር የሚያጋጭ ስራ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ህዝብ ደግሞ ከግጭትና ከአገር መፍረስ የሚጠቀመው ነገር የለም፡፡ ይሄ የጋራ ቤታችን መኖር አለበት፤ መጠበቅም አለበት፤ አገራዊና የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ወኔ ዳግም መመለስ አለበት፤ የሕዝብ ጥያቄዎች የተመለሱባትና ለሁሉም ምቹና የጋራ የሆነች የፍትህና ርትዕ አገር ለማድረግ ሁሉም መስራት አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለውጡ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ ለውጥ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ይሁን እንጂ ለውጡና ለውጡን ተከትሎ የተካሄደው ሪፎርም በሕግና ፖሊሲ ማሻሻያዎች ሊታገዝ እንደሚገባ ይነገራል፡፡ ታዲያ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎቹስ በምን መልኩ መሆን ይኖርባቸዋል?

ዶክተር ብርሃነመስቀል፡- ለኢትዮጵያ ችግር የሆኑ የአስተሳሰብ መሰረቶችን የመከለስ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ቋንቋ፣ ሃይማኖትና ባህል በሚል ብዝሃነትን አጥፍቶ ወጥ አድርጎ አንድ አገር የመመስረት ሂደት አልሰራ ስላለ የ1966ቱ አብዮት ተከሰተ፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄም ዋና ጉዳይ ሆኖ ቀረበ፡፡ ይሄን የተካው የደርግ ስርዓት ሲወድቅም የቀደመውን ጥያቄ እንደመመለስ የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ውስጥ ተገባ፡፡ ይህ ደግሞ ሕወሃት አናሳ ድርሻ ያለው ስለነበረ ስልጣን ሲይዝ ህዝቡን በመከፋፈል ካልሆነ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የበላይ ሆኖ መምራት ስለማይችል የተተገበረ ነበር፡፡

አሁን የሚፈለገው በህዝቦች መካከል መከባበርና መቀባበል ያለባት፤ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካም ሆነ የማህበራዊ ኑሮ መገለሎች በህግና በፖሊሲ በተቋማት ተሻሽለውና እልባት አግኝተው ኢትዮጵያ የሁሉም የእኩልነትና የፍትህ አገር እንድትሆን ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የሕግ ማውጣቱም ሆነ የፖሊሲ ማሻሻያው ብሎም ተቋማት የመገንባት ሂደቶች ማስተካከያው በዚህ መሰረት ላይ መቆም ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የዴሞክራሲ ተቋማትን የማጠናከርና ህዝባዊ መንግስት የማቋቋም ህዝብን ለዛ የማዘጋጀት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ የማድረግ ስራ ነው የሚሆነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መነሻ የሚሆኑ እርምጃዎች ተወስደዋል፤ እየተወሰዱም ነው፡፡ በሂደት ላይ ቢሆንም ጨቋኝ የሆነው ስርዓትም እየፈረሰ ነው ያለው፡፡

ስለዚህ የብዝሃነት አገር ለመገንባት የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ማድረግ ይገባል፡፡ ለአብነት፣ የቋንቋ ክፍፍሉን ለመግታት ወደ 80 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ የሚናገራቸው አማርኛና ኦሮምኛን የፌዴራሉ የስራ ቋንቋ በማድረግ በህዝቦች መካከል እንደ ድልድይ አገልግሎት ለዚህች አገር አንድነት የጸና መሰረት እንዲሆን ማድረግ አንዱ የፖሊሲ ምሰሶ መሆን ይገባዋል፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ የሌላት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለመሬት ወረራና ለዜጎች መፈናቀል በተለይም በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ለነበረው አሰቃቂ መፈናቀል እልባት በሚሰጥ መልኩ የመሬት ወረራው አገራዊ ምላሽ መስጠትም ሌላው የፖሊሲ ማጠንጠኛ ሊሆን ይገባዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአንድ አገር ሁለንተናዊ ሂደትና እድገት ውስጥ ምሑራን ጉልህ ድርሻ ያላቸው ቢሆንም፤ አሁንም ሆነ ቀድሞ የኢትዮጵያ ምሑራን በተለይም ከፖለቲካው መድረክ የራቁ መሆናቸው ይነገራል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን? ተሳትፏቸውስ በምን መልኩ መምጣት ይችላል?
ዶክተር ብርሃነመስቀል፡- ላለፉት 27 ዓመታትም ሆነ በደርግ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩት ምሑራን በአገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ እንዳይሰጡና ህዝብን ተከራክረውም የተሻለ ፖሊሲ እንዳያወጡ በሩ የተዘጋ ነበር፡፡ የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብቶች ስላልነበሩ የፖለቲካ ስደቶች ነበሩ፤ በዩኒቨርሲቲዎችም ቢሆን ከአካዳሚክ ምርምር ባለፈ ለህዝቡ ድምጽ የሚሆኑ ህዝባዊ ምሑራን አልነበሩም፤ አሁንም ቢሆን ህዝቡና ምሑራን አልተዋወቁም፡፡ እናም የህዝብ ድምጽ የሚሆኑና የከተማውንም ሆነ የገጠሩን ህብረተሰብ ችግር ፈቺ ምሑራን እየተፈጠሩ መሄድ አለባቸው፡፡

በዚህ መልኩ ከምሑራን በሚወጡ ሀሳቦች የህግና ፖሊሲ አማራጮች በሚዲያ ጭምር ወደ ህዝብ ደርሰው ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ከእኛም ምሑራንን ያገለለ አካሄድ መስበር ይጠበቃል፡፡ ያሉት ጅምሮችም አገራዊ እንዲሆኑ የተለያዩ የመገናኛ አውታሮችን ጨምሮ አማራጭ የሃሳብ ማንሸራሸሪያ መድረኮች ሊፈጠሩ ይገባል፡፡ “ፖለቲካና እሳት በሩቁ” የሚለው የምሑራን ብሂልም ሊሰበር፤ ለአገሩ ጉዳይ ተሳታፊ ሊሆን፤ መንግስት ለዚሁ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይጠበቃል፡፡ በዚህ መልኩ እውቀት ሲመነጭ ነው የማንነት ፖለቲካውን የአገሪቱን ችግር ባገናዘበ መልኩ ወደ የአስተሳሰብ ፖለቲካ ማሸጋገር የሚቻልበት እድል የሚፈጠረው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የለውጡ ከዳር መድረስ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ካለው ፋይዳ አኳያ መንግስት፣ ድርጅቶች፣ ምሑራንና ህዝቡ በምን መልኩ መስራት አለባቸው?
ዶክተር ብርሃነመስቀል፡- ለለውጡ ከዳር መድረስ ሁሉም አካላት የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ ትልቁ ሃላፊነት ግን የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ላይ ነው፡፡ መንግስት ደግሞ የተበላሸውን የአሰራር መዋቅር ከመናድ ባለፈ በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመሰብሰብ ላይ ያለፉትን ወራት አሳልፏል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ለውጡን ስር ለማስያዝ የዘሩትን ወደመሰብሰብና የለውጥ ሃይሉን ወደማደራጀት ወይም ወደመደመር ፖለቲካቸው መመለስ አለባቸው፡፡ ይሄ ለውጥ መሰረት እንዲኖረውና በእውቀት፣ በገንዘብና በሰው ሃይልም መደገፍ የሚፈልጉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ብዙ ኢትዮጵያዊ እንደመኖራቸውም ከኢህአዴግ መዋቅር አጥር ወጥተውም መመልከትና ማሰባሰብ ይኖርባቸዋል፡፡

በዚህ መልኩ የሕዝብ ድምጽ መሆን የሚችለው የህዝብ ድምጽ እንዲሆን፤ መዋቅር መዘርጋት የሚችለው መዋቅር እንዲዘረጋ፤ ስራ መፍጠር የሚችለው ስራ እንዲፈጥር፣ ወዘተ. በአገር ግንባታ ፖለቲካ ውስጥ በማሳተፍ ህዝቡ ወደ አገር ግንባታ ፖለቲካ እንዲገባ የለውጥ ሃይሉን መሰላል ማድረግና ህዝባዊ መንግስት ወደማቋቋም መሻገርም ይገባቸዋል፡፡ ምሑራንም ሆኑ ህዝቡ ብዙ የፈራረሱ ነገሮች ለማቃናት ከመንግስት ጎን በመቆም መደገፍ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም፣ የሃይማኖት ተቋሞቻችን የሌባ ጎሬ ሆነዋል፤ የግል ቢዝነሶችም ሰርቆ ማግኛ ሆነዋል፤ የመንግስት ቢሮክራሲውም በስብሶ ህዝብ የሚያገለግል ሳይሆን ህዝብ የሚዘርፍ የሌባ ጎሬ ሆኗል፡፡ እነኚህን ነገሮች መስመር ለማስያዝ ደግሞ ትልቁ ሃላፊነት መንግስት ላይ ቢሆንም፤ ሌላው ህብረተሰብ በዚህ ሂደት ውስጥ የድርሻውን ለመወጣት በእውቀትም፣ በገንዘብም ሆነ በጉልበት ተሳታፊ ለመሆን ራስን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡

ተቃዋሚ ሃይሎችም ገና ለገና ለፖለቲካ ስልጣን ከመቋመጥ ይልቅ፣ የፖለቲካ ስልጣን የህዝብ ነውና ይህች አገር ተመልሳ በሁለት እግሯ እንድትቆም፤ የፈረሱ ተቋማት እንዲገነቡ፤ የህዝብ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎች እንዲመለሱ፤ ኢኮኖሚው እንዲጎለብትና ብሄራዊ ደህንነት እንዲረጋገጥ፤ ከመንግስት ጎን ቆመው አገር ወደመገንባት መሸጋገር አለባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ አገርን የጸና መሰረት ላይ ካቆሙ በኋላ ወደ ምርጫ ፖለቲካ ምግባት እንችላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ እጅጉን አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ብርሃነመስቀል፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 20/2011

ወንድወሰን ሽመልስ