የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ስልጣን በቃኝ አሉ

3

 በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለስምንት ተከታታይ ዓመታት ሀገራቸው ጃፓንን የመሩት ሺንዞ አቤ ከስልጣናቸው መልቀቃቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ያጋጠማቸው የጤና ችግር ስልጣናቸውን ለመልቀቅ እንዳስገደዳቸውም እየተነገረ ነው ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን መልቀቅ አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በከባድ የጤና እክል ምክንያት ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን አስታውቀዋል። “ያለሁበት ሁኔታ በእርግጠኝነት እየተሻሻለ እንደሚሄድ ምንም ዋስትና የለም ” ብለዋል ።

ከስልጣን በመልቀቄ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ውሳኔያቸው በጃፓን የውስጥ ፖለቲካ ላይ ችግር ሊፈጥር እንደማይገባ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ጃፓንን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ቀዳሚ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የቻሉት የ66 ዓመት ባለጸጋ የሆኑት ሺንዞ አቤ፣ ‹‹አቤኖሚክስ›› በተሰኘው የምጣኔ ሃብት መርሃቸው ጃፓን ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘገብ አስችለዋታል።

የተረጋጋ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት፣ በማደግ ላይ ያለ ምጣኔ ሃብትና ስኬታማ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሀገራቸው ትተውት የሚያልፉት አመርቂ ሥራ እንደሆነ ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።

ሮይተርስ በበኩሉ እ.ኤ.አ. በ2012 መገባደጃ ላይ ሶስት ዋና ዋና የሂሳብ አያያዝንና ስርዓት፣ የፋይናንስ ወጪንና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ጃፓንን የዓለማችን ግዙፍ ሦስተኛ ኢኮኖሚ መገንባት ችለዋል ፤ በዚህ ሥራቸው በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አግኝተውበታል በማለት ዘግቧል።

የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባው ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ዘመናቸው የመሬት መንቀጥቀጥ፣ሱናሚና የኒውክለር አደጋ ጃፓንን አጋጥሟት የነበረ ቢሆንም ከአደጋው እንድታገግምና ኢኮኖሚዋ እንዲነቃቃ ከፍተኛ አስተዋፆኦ ማድረጋቸውን አመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪ የጃፓን መከላከያ ኃይልን በማጠናከር እና ወታደራዊ በጀቱን በማሳደግ አድናቆት አትርፈዋል።

በሆድ ውስጥ ህመም ሲሰቃዩ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ፣ ወግ አጥባቂ ፖለቲከኛ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

ህመማቸውን አስመልክቶ በኦስካ ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ህክምና እስፔሻሊስት ፕሮፌሰር ሺሮ ናካማራ ከሜድካል ኦፍ ሄልዝ መጽሔት ጋር በነበራቸው ቆይታ ፣በእንዲህ ዓይነት ህመም የተያዙ ሰዎች ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት መድኃኒቶችን በመጠቀም አሁናዊ ሁኔታቸውን በአንፃራዊነት ማረጋጋት ይችላሉ ብለዋል ።

ይሁን እንጂ ለታካሚው የሚደረገውን ህክምና ለመምረጥ አስቸጋሪ የሚያደርገው ጉዳይ በሽታ አምጪ ተህዋስያን ከሰው ሰው የሚለያዩ መሆናቸው ነው ፤ይህም ህመሙን ከባድ እንደሚያደርገው አመልክተዋል።

የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመው በነበረበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ2007 ከስልጣናቸው መልቀቃቸውን በዘገባው ያስታወሰው የህንዱ ኤክስፕሬስ፣ በዚያን ጊዜ ከስልጣናቸው መልቀቃቸው የሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገራት ያለውን ጫና መቋቋም ባለመቻላቸው፣ በተለይም በጃፓን ውስጥ የተፈጠረውን የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የፖለቲካ ሹማምንት የስልጣን ፍላጎት እንዲሁም አሜሪካ አፍጋኒስታንን እንድትወር ድጋፍ ማድረጋቸው እንደነበር አመልክቷል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን በመልቀቃቸው የተሰማውን ሀዘን በመግለጽ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለውን አክብሮት በመግለጽ ላይ መሆኑንም መገናኛ ብዙሃን በስፋት እየዘገቡ ይገኛል ።

የታይዋኑ ፕሬዚዳንት “ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ በፖሊሲም ይሁን በታይዋን ህዝብ መብትና ጥቅም ዙሪያ ሁል ጊዜ ተሰሚነታቸው የጎላ ፣ በጣም ጥሩ ሰው እንደነበሩ አስታውቀዋል ። ለታይዋን ህዝብ ያለውን ወዳጅነት ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን ። ጤናቸው መልካሙን እንዲያጋጥመው ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው በቲውተር ገጻቸው ፣ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ለሀገራቸውም ለዓለምም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በሳቸው የአመራር ዘመን እንግሊዝና ጃፓን በንግድ፣ በመከላከያና በባህል ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር የሰሩ ጥልቅ ሰው ናቸው ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ሺንዞ አቤ ሀገሩን በጣም የሚወድ ሰው ነው ብለዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አክብሮት እንዳላቸው ሮይተርስ አስነብቧል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቻይናና በጃፓን መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ትክክለኛው ጎዳና መመለሱን አስታውቋል፣ አዳዲስ ዕድሎችም መገኘታቸውን አስታውቋል ። ለዚህም የጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ያላሰለሰ ጥረት ወሳኝ ነበር ብሏል ። ከገጠማቸው የጤና ችግር በፍጥነት እንዲያገግሙ ያለውን ተስፋም ገልጸዋል ።

የሀገሪቱ ገዥው ሊብራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ እስኪሚደረግ ድረስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራውን ተክተው እንደሚሠሩ አስታውቋል።

ሺንዞ አቤ እ.አ.አ በ2007 በተመሳሳይ የጤና ዕክል ምክንያት ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸው አይዘነጋም። የሺንዞ አቤ የስልጣን ማብቂያ ጊዜ መስከረም 2021 እንደነበር ኒወርክ ታይምስ በዘገባው አስታውሷል።

አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2012