ኮቪድ 19 እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖው

6


 ባሳለፍነው ዓመት ዓለም ከፍተኛ ፈተና የተጋፈጠችበት ወቅት ነው።የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በፈረንጆቹ 2019 ማብቂያ ላይ በቻይና ተከስቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዓለምን በማዳረስ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትሏል።አሁንም የጥፋት በትሩን ገና ከሰው ልጆች ላይ አላነሳም።አሁን ባለው ሁኔታም ቢሆን የሰው ልጅ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ የፈተነና የሳይንስና ቴክሎጂ እድገትንም መና ያስቀረ ክስተት መሆን ችሏል፡፡

በዛሬው የማህደረ ጤና ዝግጅታችንም ወረርሽኝኙ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ባደረሰው ጥፋትና ከዚህ ለመውጣት በቀጣይ ሊከናወኑ ይገባሉ በሚል ምሁራን ባስቀመጧቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡

ኮቪድ 19 ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው እአአ በህዳር ወር በቻይናዋ ውሃን ግዛት ነው።በርግጥ በበሽታው አነሳስ ዙሪያ የአሜሪካና የቻይና ሃሳብ የተለያየ እንደሆነ ሁላችንን ባለፉት አስር ወራት የታዘብነው እሰጣገባ ነው።አሜሪካ “በሽታው ቀድሞ ቢከሰትም ቻይና ደብቃለች፤ ለዚህም ተጠያቂ ናት” የሚል ጩኸት በተደጋጋሚ ታሰማለች። በዓለም ላይ በተለይ በአሜሪካ ለደረሰው ጥፋትም ቻይናና የዓለም የጤና ድርጅትን ተጠያቂ ታደርጋለች።ይህ ግን ውሃ የሚቋጥር መረጃ ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በተደጋጋሚ ገልፀዋል፡፡

ወረርሽኙ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም በፍጥነት ወደተለያዩ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የላቲን አሜሪካ አገራት በመዛመት ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ሲያስከትል በመቀጠል በአፍሪካም ቢሆን የቅጣት በትሩን ከማሳረፍ አልቦዘነም።በተለይ በአፍሪካ ዘግየት ብሎ የጀመረው የቫይረሱ ስርጭት አሁን አሁን በከፍተኛ ፍጥነት በመዛመት ከፍተኛ ስጋት እየሆነ ይገኛል።

 ቢቢሲ በድረገፁ ላይ እንዳሰፈረው ወረርሽኙ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለው ጉዳት ከ1987 ወዲህ እጅግ አስከፊ የሚባል ነው።በወቅቱ በዓለም ላይ በተለይ በግዙፎቹ የአሜሪካ የአክሲዮን ገበያዎች ላይ በደረሰ ኪሳራና ቀውስ ምክንያት የዓለም ኢኮኖሚ ክፉኛ ተናግቶ የነበረ ሲሆን በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ከስራቸው ተፈናቅለዋል።

በወረርሽኙ የተነሳ እስካሁን ባለው ሁኔታ ከኢኮኖሚ አንጻር ያስከተለው ጉዳት ከ2 ነጥብ 4 እስከ 3 ከመቶ የአጠቃላይ የምርት መቀነስ አስከትሏል።ይህ ደግሞ በዓለም ላይ 86.6 ትሪሊየን ዶላር እንደሚሆን መረጃው ያሳያል።በተለይ ግዙፍ በሆኑ የበለፀጉ አገራት ላይ የከፋ ጉዳት ማስከተሉ የችግሩን አስከፊነት የሚያሳይ ነው።ለምሳሌ በአሜሪካ ቫይረሱን ለመከላከል እስካሁን ባለው ሁኔታ ከሦስት ትሪሊየን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጓል።ይህ ደግሞ በቀጥታ ለድህነት ቅነሳ ቢውል በዓለም ላይ ድህነትን ለማጥፋት ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር መገመት ይቻላል።

ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኮቪድ 19 የተነሳ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ዘርፎች አንዱ ግብርና ነው።ይህ ዘርፍ በዓለም ላይ 80 ከመቶ የሚሆኑ ዜጎችን ህይወት የሚታደግ ሲሆን የዚህ ዘርፍ መጎዳት የሚያስከትለው ቀውስም በዚያው ልክ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚያስከትል ይታመናል።ከዚህ ጋር ተያይዞ የምርት መቀነስ ብቻ ሳይሆን እሴት ተጨምሮባቸው የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችም አቅርቦትና ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጎዳ ዘርፉ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እንደሚያጋጥመው መረጃው አመላክቷል።

ኮቪድ 19 ለከፍተኛ ኪሳራና ጉዳት ከዳረጋቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የመዝናኛ ዘርፍም ተጠቃሽ ነው።በተለይ በኪነጥበብ፣ በመዝናኛና ስፖርት ዘርፎች ላይ ወረርሽኙ ቀጥተኛ ተፅዕኖ በማሳረፍ በሙያው ላይ የተሰማሩ አካላትን ገቢ በእጅጉ አዳክሟል።አንዳዶቹንም

 ለድህነት ዳርጓል።ከዚህ እንፃር በአገራችንም የተከሰተው ችግር አንድ ማሳያ ነው።በተለይ አርቲስቶች በወረርሽኙ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ መዳከም እንዳስከተለባቸው በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡

እንደሚታወቀው ዘርፉ በአንዳድ የዓለም አገራት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ነው።ለምሳሌ በአውስትራሊያ ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ምንጫቸው እስከ 6.4 ከመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል። በመሆኑም የዘርፉ መጎዳት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ቀውስ ማስከተሉ እውን ነው።ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሲኒማው ዘርፍም በወረርሽኙ ተጎጂ ከሆኑ ኢንዱስትሪዎች አንዱ ነው።ይህ ዘርፍ በተለይ በአሜሪካ የፊልም ኢንዱስትሪ የሚያንቀሳቅሰው ኢኮኖሚ ከፍተኛ ነው።ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ የሚያወጡ በርካታ ፊልሞች በሚመረቱባት አሜሪካ የዘርፉ መጎዳት ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡

ስፖርትም በተመሳሳይ የኮቪድ ሰለባ ከሆኑ የኢኮኖሚ ምንጮች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል።በዚህ ዘመን ስፖርት ያለው ተቀባይነትና የሚያንቀሳቅሰው ገንዘብ ሲታይ በተመሳሳይ ለአገራዊ እድገቱ የሚኖረውን አንድምታ የሚያሳይ ነው።ለዚህ ደግሞ የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦችን ማየቱ በቂ ነው።መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኮቪድ 19 የተነሳ የስፖርት ተቋማት ከ30 እስከ 60 ከመቶ ኪሳራ ገጥሟቸዋል።ከዚህ ጋር ተያይዞ የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችም ትልቅ የአኮኖሚ ኪሳራ ምንጮች ሆነዋል።

የአየር ትራንስፖርትም ባለፉት ስድስት ወራት ከ80 እስከ 90 ከመቶ ኪሳራ አስተናግዷል።በዚህ የተነሳም አብዛኞቹ የዓለም ትልልቅ አየር መንገዶች የመንግሥቶቻቸው ድጎማ የግድ አስፈልጓቸዋል።

ከዚህ አንጻር የአገራችን አየር መንገድ ይህንን አስከፊ ወረርሽኝ ያለኪሳራ ለማለፍ የሄደበት መንገድ ከአገራችንም አልፎ አለምአቀፍ እውቅናና አድናቆትን እንዲያተርፍ አድርጎታል።አየር መንገዶ በችግሩ ወቅት ለአፍሪካ አገራት

 ጭምር ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት እንዲያደርስ በመመረጥም አስቸጋሪ ወቅቶችን በመቋቋም ትልቅ አየር መንገድ መሆኑን ያስመሰከረ ነው፡፡

ስራአጥነትም ኮቪድ 19 ካስከተላቸው ችግሮች ውስጥ ተጠቃሽ ነው።ከዚህ አንጻር በቻይና አምስት ሚሊየን ዜጎች ስራ አጥ ሲሆኑ በአሜሪካም አስር ሚሊየን ዜጎች ከስራቸው እንደተፈናቀሉ መረጃዎች አመላክተዋል። ከዚህም ባሻገር በተለያዩ የአውሮፓ፣ የኤሽያ፣ የላቲን አሜሪካና የአፍሪካ አገራት በርካታ ዜጎች ለስራ አጥነት ተዳርገዋል።

በአገራችንም በቫይረሱ የተነሳ ስራቸውን ያጡ ዜጎች ቢኖሩም በበጀት ዓመቱ ከሦስት ሚሊየን ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠርም መንግሥት ችግሩን ለመቋቋም የሄደበት መንገድ ውጤታማ እንደሆነ አሳውቋል፡፡

የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም ሌላው የኮቪድ 19 ሰለባ ነው።እንደሚታወቀው ይህ ዘርፍ የሰዎችን ዝውውር የሚጠይቅ በመሆኑ ከወረርሽኙ ባህርይ ጋር ይቃረናል። በዚህ የተነሳ ለኪሳራ ተዳርጓል።በተለይ በየዓመቱ ከዘርፉ ከ200 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ የምታገኘው አሜሪካ ከዚህ የምታገኘውን ገቢ በማጣት ግንባር ቀደም ስትሆን አገራችንም ከዚህ ማግኘት የሚገባትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ አጥታለች፡፡

በአጠቃላይ ባለፈው ዓመት የኮሮና ቫይረስ ካስከተላቸው የኢኮኖሚ ቀውሶች ውስጥ ከላይ የጠቀስናቸው ችግሮች ዋና ዋናዎቹ ቢሆኑም በእያንዳንዱ አገር ላይ ያስከተለው ቀውስ ግን ዘርፈብዙ እንደሆነ መገመት ይቻላል።በተለይ በድህነት ውስጥ ባሉ አገራት ከእጅ ወደአፍ ኑሮ ባላቸው ዜጎች ላይ ወረርሽኙ ያስከተለው ቀውስ ቀላል አይደለም።በመሆኑም በቀጣይ ችግሩ የሚስከትለውን ፈተና ለመቋቋም በሽታውን እየተከላከሉ የኢኮኖሚ አማራጮችን ማስፋት እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።እኛም በአዲሱ ዓመት በሽታውን እየተከላከልን የኢኮኖሚ አቅሞቻችንን እንገንባ መልዕክታችን ነው።መልካም በዓል፡፡

አዲስ ዘመን መስከረም 1/2013