በወርቅ የተንቆጠቆጡ መፀዳጃ ቤቶች ባለቤት እና ምርጫ የማታውቀው አገር

6


 ክፍለዮሐንስ አንበርብር

 ተገረም ሲልህ!

ይህን ፅሁፍ ስታነቡ አግራሞት አጭሮባችሁ ‹‹እንዲህም ይኖራል ወይ›› ብላችሁ እንደምታነቡት እምነቴ ነው።ይኸው ግድ የለም ዝለቁት።የሃገሪቷ አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር 428ሺ962 ነው።ከሶስቱ የሃገሪቷ ዜጎች ውስጥ ሁለቱ መኪና አላቸው፣ 97 ከመቶ የሚሆነው ህዝቧ በሚገባ ተምሯል።የሃገሪቷ ዜጎች ከሚያገኙት ገቢ ውስጥ መንግስት የሚቆርጠው ምንም ዓይነት ታክስ የለም።አገሪቷ ሰባራ ሳንቲም ዕዳ የለባትም።መንግስታቸውም ድቡሎ ዱዴ ነገር ከሌሎች መቀበል አይመቸውም።ሲሆን ይለግሳል እንጂ እንዲች ብሎ ከሌላ አገር አይበደርም።ምና አጣና?

እዚህ አገር ‹‹ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል›› የሚለው ኢትዮጵያውን አባባል አይዋጥላቸውም።ለማን ብለው ኑሯቸውን የዘላለም እንቅልፍ ከሆነው ሞት ጋር ያወድጁት። ይልቅስ ጮማ ቆርጦ፤ ጠጅ ጠጥቶ ደልቀቅ ብሎ ኖረ የሚለው አባባል ሊገልጻቸው ይችላል። አንዳንዴ ህይወት እንዲህ ናት።በዚህች አገር እስልምና የአገሪቱ ዋነኛ ሃይማኖት ሲሆን፤ 79 ከመቶ የአገሬው ህዝብ ሙስሊም ነው።ዘጠኝ ከመቶ ክርስቲያን፤ ስምንት ከመቶ ቡዲሂስት እንዲሁም አምስት ከመቶ የአገሬው ሰው ደግሞ የሌሎች እምነት ተከታይ ነው።በአገሪቱ መጠጥ አይሸጥም።ነገር ግን ቱሪስቶች ለቆይታቸው የሚበቃ አልኮል አሳውቀው ይዘው መግባት ይችላሉ፡፡

የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር እና ሱልጣን (Sultan) ብቻ ሳይሆኑ የሃገሪቷ የፋይናንስ ሚንስትር፣ የመከላከያ ሚንስትር፣ የውጪ ጉዳዮች ሚንስትር፣ የፖሊስ ኃይል ኃላፊ እና የሃገሪቷ የንግድ ሚንስትር ጭምር እርሳቸው ናቸው። በተጨማሪም በአገሪቱ ቀዳሚ የሚባለው ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ናቸው።ምናልባትም በዓለም ታሪክ አንድ ግለሰብ ይህንን ሁሉ ስልጣን በአንድ ጊዜ እንዲህ ጠቅልሎ የተያዘበት አገር ይኖራል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።

አገሪቱ የት ትገኛለች?

የዝችህን አገር ካርታ ላይ ፈልገህ ለማግኘት ትቸገራለህ።ግን መታገስ አለብህ።በትልቁ የተሳለውንና ከግርግዳህ ላይ የተሰቀለውን የዓለም ካርታ ዛሬ በአንክሮ ታየው ዘንድ ግድ ነው።በየትኛው አህጉር ትገኝ ይሆን ብለህ ደጋግመህ ራስህን ትጠይቃለህ።ከዚያም ደግሞ ጥያቄህ ማባሪያ አይኖረውም።አጎራባች አገሮች እነማን ናቸው፤ ሃብታቸውስ፣ አኗኗራቸውስ እያልክ መረጃ ለማነፍነፍ የተቻለህን ሁሉ ትፋንናለህ፡፡

ይቺህ ሃገር ‹‹ብሩናይ›› ትሰኛለች።ምናልባትም የሃገሪቷን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ እየሰማችሁ ሊሆን ይችላል። ምስራቅ እስያ ውስጥ የምትገኘው ይችህ ደሴታማ ሃገር ከእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ከወጣች እንኳን 40 ዓመት አልሞላትም። ኢንዶኖዥያ፣ ማላዥያ እና ፊሊፒንስ ያዋስኗታል፡፡

ሁሉ ነገር በነፃ

ወዳጄ! ይህች አገር ህዝቦቿ በነፃ ትምህርት ያገኛሉ፣ በነፃ ይታከማሉ፣ መንግስት በነፃ ቀለብ ያቀርባል፣ ወላሃንቲ! ጭንቀት የሚባል በሽታ ሃገሪቷ ውስጥ የለም።ቤት ለመግዛት ብድር ብትፈልግ ያለ ምንም ወለድ የሃገሪቷ ባንክ የፈለከውን ያህል ብር ያበድርሃል፣ ለዚህ ደግሞ ተያዥ የሚሆኑት የሃገሪቷ ጠቅላይ ሚንስትር ናቸው፣ የሃገሪቷ ዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ 79ሺ ዶላር ሲሆን በዚህም እጅግ ሃብታም ከሚባሉ የዓለም ሃገራት ዜጎች ተርታ መሰለፍ ችለዋል።

ይህች አገር በየእለቱ ሃብት የሚፈስበት፤ ጓዳዋ እንዳሻችው የሚሞላላት አገር ናት ወዳጄ።ብሩናይ እ.ኤ.አ ከ 1999 እስከ 2008 ባሉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ አጠቃለይ የሀገር ውስጥ ምርታቸው በአማካይ በ56 በመቶ አድጓል። የአገሪቱ የሃብት ምሰሶ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ነው።የዓለም የገንዘብ ተቋም (International Monetary Fund) በዓለማችን እዳ የሌለባቸው አገራት ውስጥ ይመድባታል።

የአገሪቱ መሪ

የዚህች አገር (ብሩናይ) መሪ ከአባቱ የዛሬ 53 ዓመት በ21 ዓመት ስልጣን የተረከበው ሱልጣን ሙሉ ስሙን ለማንበብ ዘለግ ያለ ጊዜ ይወስዳል።ከስሞች ሁሉ ረጅሙ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ሙሉ ስማቸው ‹‹Sultan Haji Hassanal Bolkiah Mu’izzaddin Waddaulah ibni Al-Marhum Sul­tan Haji Omar ‘Ali Saifuddien Sa’adul Khairi Waddien Sultan and Yang di-Pertuan of Brunei Darussalam›› ይባላል።ታዲያ ይህን ሁሉ ለመፃፍ ምን ዓይነት ቦታ ይበቃ ይሆን፤ ፓስፖርታቸው አሊያም ደግሞ መታወቂያቸው ላይ ምን ተብሎ ሊፃፍ ይችላል የሚል ጭንቀት ሊጋብችሁ ይችል ይሆናል።ሰውየው የዋዛ አይደሉም።አጠር ያለ ስም አላቸው።

“Hassanal Bolkiah” ተብለው በአጭሩ ይጠራሉ።እኝህ ሰው የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር እና ሱልጣን (Sultan) ብቻ ሳይሆኑ የሃገሪቷ የፋይናንስ ሚንስትር፣ የመከላከያ ሚንስትር፣ የውጪ ጉዳዮች ሚንስትር፣ የፖሊስ ኃይል ሃላፊ እና የሃገሪቷ የንግድ ሚንስትር ጭምር እርሳቸው ናቸው። ሲያሻቸውም እራሳቸውን የሃገሪቷ ፕሬዝዳንት ብለው ይጠራሉ። ታዲያ ይህን ሁሉ ስልጣን ተቆናጠው አገሬው ምርጫ ቢያምረው፣ አሊያም ዴሞክራሲ ናፈቀኝ ቢል ወይንም ሰላማዊ ሰልፍ ቢያምረው ንጉሱ ካልፈቀዱ በቀር ወይ ፍንክች አንዳችም አይሆንም።በነገራችን ላይ እኚህ ሰው ሦስት ጊዜ ትዳራቸውን ፈትተዋል።በአሁኑ ወቅት በ33 ዓመት የምታንሳቸውን ኮረዳ አግብተው ዓለማቸውን እየቀጩ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሰውየው የተጣራ 40 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ አላቸው።ሱልጣኑ የራሳቸው ፀጉር ቆራጭ አላቸው። ፀጉር ቆራጫቸው የሚኖረው “London” ስለሆነ በየወሩ ወደ “Brunei” የአውሮፕላን ወጪው ተችሎት ይመጣና ፀጉራቸውን በመቀስ ነካ ነካ አድርጎላቸው ይሄዳል። ለዚህም 21 ሺ ዶላር ይከፍላሉ።

የዓለም ትልቁ ቤተመንግስት ባለቤት

ዓለም ላይ ትልቁ “Presidental palace” እንግሊዝ፣ አሜሪካ ወይም ሌላ የአውሮፓ ሃገር ውስጥ ሳይሆን እዚህች ሃገር ውስጥ ነው ያለው! ለዚህ “palace” ግንባታ ከአንድ ቢልዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርገውበታል።257 ሽንት ቤት አለው።

የዓለማችን ውዱ የግል አውሮፕላን የሚገኘው የ”Brunei” ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ነው።“Boeing 747-430” የተሰኘውን የግል አውሮፕላንን ለመግዛት ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሰውየው አውጥተዋል። አውሮፕላኑ ውስጡ የሚገኙ አብዛኛው ነገሮቹም በወርቅ የተለበጡ እንዲሆኑ አድርገዋል። ሰውየው ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እና ከሃገሪቷ ውጪ ለግል ጉዳያቸው ሲሄዱ ይህንን አውሮፕላን ራሳቸው እያበረሩ ነው።ሰውየው 220 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የግል አውሮፕላን አላቸው።የአውሮፕላኑ መደበኛ ዋጋ 120 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፤ 100 ሚሊዮኑ ግን በእንቁ ለማንቆጥቆጥ ያወጡበት ተጨማሪ ዋጋ ነው፡፡

7000 መኪና ለአንድ ሰው

ሰውየው በይበልጥ የሚመቻቸው መኪና ነው። የግል ጋራዣቸው ውስጥ ከ 7000 በላይ እጅግ በጣም ውድ መኪኖች አሏዋቸው። እነዚህ መኪኖች በትንሹ በአጠቃላይ አምስት ቢሊዮን ዶላር ያወጣሉ።በዓለማችን ቅንጡ የሚባሉ መኪኖች በሙሉ ከእርሳቸው ዘንድ አሉ። ከእነዚህ ተሽርካሪዎች ውስጥ ደግሞ 2ሺ100 የሚሆኑት በወርቅ የተለበጡ ናቸው፡፡

እኚህ ሰው ከራሽያው “Moscow state univer­sity for international relations” የክብር ዶክትሬት ወስደዋል። እስካሁን ከተለያዩ የዓለም አገራት 14 የክብር ዶክተሬት አግኝተዋል።

ምርጫ የማታውቀው አገር

የሃገሪቷን መንግሥት እና ሱልጣኑን ጋዜጣ፣ መፅሄት፣ ሬዲዮ ወይም ቴሌቪዥን ላይ ማብጠልጠል፣ መተቸት፣ መሳደብ፣ መንቀፍ ምናምን የማይታሰብ ነው። ትልቅ ወንጀል ነው። ይህ ሆኖ ከተገኘ ያው ‹‹ውርድ ከራሴ›› የሚለውን ብሂል ውጤት መጠበቅ ነው፡፡

በሃገሪቷ ፓርላማ ቢኖርም ምርጫ የሚባል ነገር ግን አይደረግም። ለመጨረሻ ጊዜ ምርጫ የተካሄደው የዛሬ 58 ዓመት ነበር። ለማንኛውም ሱልጣኑ አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ሃገራት ከ150 በላይ እጅግ ቅንጡ ቤቶች እና ከ 20 በላይ የግል አውሮፕላኖች አሏቸው፣ በወርቅ ላይ ይሄዳሉ፣ ወርቅ ላይ ይተኛሉ።እንደ “Forbes” ዘገባ የሱልጣኑ ሃብት በአንድ ሰከንድ ውስጥ 147 ዶላር ይጨምራል።በ 1 ሰዓት ውስጥ 52ሺ200 ዶላር ወደ አካውንታቸው ላይ ይገባል። መረጃውን ወንድዬ እንግዳ ከተሰኘ ፌስ ቡክ፣ ጎግል እና ዩቱዩብ የተጠናከረ ነው፡፡

አዲስ ዘመን መስከረም 2/2013