ዝናብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን በመስራት ውሃ ማጠንፈፍ እንደሚገባ ሚኒስቴሩ አሳሰበ

7

 አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ አበባ፡- ዝናብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩ የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን በመጠቀም ጎርፉን እንዲከላከል የግበርና ሚኒስቴር አሳሰበ። የዘንድሮው ክረምት ወቅት ዝናብ በስርጭትና በመጠን ከአምናው የተሻለና ለግብርናው ምቹ መሆኑን አስታወቀ።

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የመኸር ወቅት የሀገሪቱ 90 ከመቶ በላይ የሚሆነው ምርት የሚሸፈንበት ከመሆኑ አኳያ የዘንድሮው የዝናብ አጀማመር መልካምና በስርጭትና በመጠንም የተሻለ ነው።

በዚሁ የመኸር ወቅት 12 ነጥብ 85 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር እንደሚሸፈን አስታውቀው፣ከዚህ ውስጥ 335 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። ይህም ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ምርት 92 ከመቶ ያህሉን እንደሚሸፍን አስታውቀዋል።

የዘንድሮው የክረምት ወቅት በግብርናው ላይ አወንታዊም አሉታዊም ተፅእኖ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ አሉታዊ ተፅኖዎቹ በአብዛኛው ከዝናብ መብዛት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን አመልክተዋል።ጎርፍ በተከሰተባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የእርሻ ማሳዎች መጎዳታቸውን ጠቅሰው፣የዝናብ መብዛቱ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ የዘር ወቅት ማስተጓጎሉንም ጠቁመዋል።

በአወንታዊ ጎን የዘንድሮው ክረምት ወቅት በሁሉም አካባቢዎች ላይ ስርጭቱና መጠኑ ጥሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ የክረምትና የበልግ ወቅት በመግጠሙ በረጅም ጊዜ ለሚደርሱ ማሽላ፣ በቆሎና ዳጉሳ የመሳሰሉ ሰብሎች መልካም ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።አብዛኛው አርሶ አደርም በዚህ ወቅት ማሳውን በዘር መሸፈኑን ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።

ከብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የወጣውን የክረምት ወቅት አየር ትንበያ መሰረት በማድረግ ሚኒስቴሩ ምክረ ሃሳቦችን ማውረዱንና የክረምት አገባቡን መሳወቁንም ዳይሬክተሩ አስታውሰው፤ በዚህ ወቅት ሊኖሩ የሚችለውን የዝናብ መብዛት ተከትሎ የሚፈጠረውን ጎርፍ ለመቆጣጠር አርሶ አደሮች የጎርፍ መቀልበሻዎችን እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል።

‹‹የክረምቱ ወቅት በተለይ በደጋማው የሀገሪቱ ክፍል በስንዴ የዘር ወቅት ላይ መጠነኛ ማስተጓጎል ፈጥሯል›› ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ዝናብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩ የመቀልበሻ ቦዮችን፣ ከማሳ ውስጥ ውሃ የማጠንፈፍ ስራዎችን እንዲሰራና የዘር ወቅትን ጠብቆ ማሳውን እንዲሸፍን ምክረ ሃሳብ በመገናኛ ብዙሃንና በግብርና መዋቅር አስከቀበሌ ድረስ መውረዱን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሰብል በእድገት ደረጃ ላይ ያለና በአንዳንድ ቆላማ አካባቢዎች ላይ ደግሞ ሰብል የሚደርስበት ሁኔታ መኖሩንም አያይዘው የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በተወሰኑ የአማራ ክልል ምእራብ አካባቢዎች እህል የአድገት ደረጃ የሚደረስበት መሆኑና አርሲና ባሌ አካባቢዎች ደግሞ በነሃሴ መጀመሪያ ላይ የሚዘሩበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰዋል።

አብዛኛው ሰብል መጠነኛ እንጂ ብዙ ዝናብ አንደማይፈልግ ጠቅሰው፣በሃምሌ መጨረሻ አካባቢ የነበረው አስጊ ዝናብ በማለፉ በአሁኑ ወቅት ያለው የዝናብ መጠን የተስተካከለና ለግብርናው አመቺ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አዲስ ዘመን መስከረም 6/2013