ኢንቨስትመንቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ስራዎች በኦን ላይን እየተከናወኑ ነው

5

 መርድ ክፍሉ

 አዲስ አበባ፡- ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ተቀዛቅዞ የነበረውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ በኦን ላይ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገለፀ። በጸጥታ ችግር ምክንያት የኢንቨስትመንት ቦታዎችን እንዳይወድሙ ልዩ የኢንቨስትመንት የፌዴራል ፖሊስ መዘጋጀቱም ተጠቆመ።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፕሮሞሽንና የፖሊሲ ጥናት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናሩት፤ ባለፉት ስድስት ወራት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የኢንቨስትመንት ስራዎች ተቀዛቅዘዋል። የኢንቨስትመንት ስራዎችን ወደነበሩበት ለመመለስ ስራዎች በኦን ላይን እየተከናወኑ ይገኛሉ።

እንደ አቶ ተመስገን ገለፃ፤ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ኢንቨስትመንትን ከማበረታታት አንፃር የተለያዩ ዘዴዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። የኢንቨስትመንት የመሳብ ስራዎች በአዲስ መልክ እየተሰሩ ናቸው። ቀድም ብሎ የነበረውን ወደ ኢንቨስተሮቹ በመሄድ የመደራደር ስራ በኦን ላይን ከኢንቨስተሮች ጋር በመገናኘት መረጃ መስጠት ስራ እየተሰራ ነው። ለዚህም አዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል።

ወረርሽኙ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ያለፉት አራት ወራት ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሮ እንደነበር የተናገሩት አቶ ተመስገን፤ በሌሎች አገራት የቫይሱ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅት ከኢትዮጵያ ሲገዙ የነበሩ ተቋማት ትዕዛዛቸውን ሰርዘው እንደነበር አስታውሰዋል። አጠቃላይ እንቅስቃሴው ላይ እክሎች ተፈጥረው እንደነበርና በዚህም የጥሬ እቃ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱና ከውጭ አስፈላጊ የሚባሉ እቃዎች ወደ አገር ውስጥ ቢገቡም ማከፋፈል ላይ የነበሩ ችግሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ችግር ለመፍታት መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን በመጥቀስ፤ ከዚህ ውስጥ ከውጭ አገር ውስጥ የገቡ እቃዎችን በነፃ ትራንስፖርት መስጠትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳያጋጥም ድጋፍ በማድረግ ለውጦች መምጣታቸውን ገልፀዋል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተመረቱ ምርቶች በአገር ውስጥ በመሸጣቸው ሰራተኞቻቸውን እንዳይቀንሱ መደረጉን ጠቅሰዋል። አንዳንድ ፋብሪካዎች ማስክና ሳኒታይዘር ወደ ማምረት ገብተው ለውጭ ገበያ እስከማቅረብ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በብጥብጥ ወቅት የኢንቨስትመን ስፍራዎች ዋነኛ የተቃውሞ መግለጫ ቦታ ተደርገው እየታዩ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተመስገን፤ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ደህነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ጥናት ተደርጎ የህዝብ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የመንግስት ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል የሚለው አቋም ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

እንደ አቶ ተመስገን ማብራሪያ፤ ይህ ሁኔታ ከተከናወነ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ይቻላል። በየጊዜው ኢንቨስትመንቶች በወደሙ ቁጥር የሚፈጠረው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው። ችግሮች በተፈጠሩ ቁጥር አዳዲስ ኢንቨስተሮች ወደ አገሪቱ ለመምጣት ፍላጎት አይኖራቸውም። ከኢትዮጵያ አምራች ድርጅቶች ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶች ላይም መቀዛቀዝ ያመጣል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የአበባ ፋርሞች እንዲሁም የማኒፋክቸሪንግ ፋብሪካዎች የተለየ ጥበቃ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚህም የፌዴራል ፖሊስ ልዩ የኢንቨስትመንት ፖሊሶች ያዘጋጀ ሲሆን በዚህም የሚፈጠሩ ችግሮችን መቀነስ እንደሚቻል አመልክተዋል።

አዲስ ዘመን መስከረም 6/2013