325 አዳዲስ የገጠር ከተሞች እና መንደሮች ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ማድረግ ተቻለ

14

 ምህረት ሞገስ

 አዲስ አበባ፡- በ2012 ዓ.ም ብቻ ምንም አይነት የኤሌክትሪክ ሃይል አግኝተው የማያውቁ 325 አዳዲስ የገጠር ከተሞች እና መንደሮች የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ተቋሙን በማዘመን ነባሩ ደንበኛ አስተማማኝ ኤሌክትሪክ እንዲያገኝ ከማስቻል በተጨማሪ ከኤሌክትሪክ ጋር ምንም አይነት ትውውቅ የሌላቸውን አካባቢዎች ኤሌክትሪክ በማዳረስ ትልልቅ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። በተጠናቀቀው 2012 በጀት ዓመት 168ሺህ 751 አባወራዎች አዲስ ቆጣሪ እንዲያገኙ ተደርጓል።

የገጠር ኤሌክትሪፍኬሽን ፕሮግራም ሲጀመር 667 ከተሞች ብቻ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ መላኩ፤ አንዳንድ የዞን ከተሞች ሳይቀሩ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ተናግረዋል። እስከ አሁን በገጠር ኤሌክትርፍኬሽን 6 ሺህ 759 የገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል።

እንደ አቶ መላኩ ገለፃ፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአጠቃላይ የደንበኛው ቁጥር ከ3 ሚሊየን የዘለለ አይደለም። ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥም 44 በመቶ ብቻ ነው የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኘው። 66 በመቶው ህዝብ ማለትም ብዛት ያላቸው ከተሞች አሁንም ከኤሌክትሪክ ሃይል ጋር እንደማይተዋወቁም ጠቁመዋል። ተቋሙ ይህን ሁኔታ ለመቀየር አዳዲስ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያልነበሩ የገጠር ከተሞች እና መንደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በከፍተኛ መዋለ ነዋይ ፕሮጀክቶች ነድፎ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ህዝቡ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የኤሌክትሪክ ሀይል እንዲዳረሰው ተቋማቸው ጠንክሮ የሚሰራ መሆኑን ተናግረው፣ ኤሌክትሪክ ሀይል ማስፋፋት ቢቻልም አሁንም ተጠቃሚ ያልሆኑ በርካታ የገጠር ከተሞች አሉ ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪ ነባሩ ደንበኛ በተለያዩ ምክንያቶች የሚዋዥቅ እና የሚቆራረጥ አገልግሎት ሲያገኝ ቆይቷል ያሉት አቶ መላኩ፤ አሁን ግን ኔትወርኩን በማሻሻል ነባሮቹ ደንበኞች በመደበኛነት ሃይል እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ለእዚህ ማሳያውም በዚህ ዓመት ክረምት ከፍተኛ ዝናብ ቢጥልም ሃይል የሚቆረጥበት ክስተት ውስን እንደነበር ጠቅሰዋል።

አዲስ ዘመን መስከረም 6/2013