የታዋቂ አትሌቶች የአበረታች ቅመሞች ምርመራ እየተካሄደ ነው

4

ብርሃን ፈይሳ

 በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ለሚሳተፉ አትሌቶች የስፖርት አበረታች ቅመሞች ምርመራ በመካሄድ ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጸረ አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።ምርመራው የሚከናወነው ከአለም አትሌቲክስ የኢንተግሪቲ ዩኒት ጋር በመተባበርም ነው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የጸረአበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት በአትሌቲክስ ስፖርት ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለውን የአበረታች ቅመሞች ለመከላከል ምርመራ ማካሄድ መጀመሩን በድረገጹ አስነብቧል።ናሙናዎችን በመውሰድ ምርመራው የሚካሄደው በቀጣይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከናወኑ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ለሚሆኑ አትሌቶች ነው።በምርመራውም ከ150 በላይ በሚሆኑ ታዋቂ አትሌቶች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ ከመስከረም 04/2013 ዓም ጀምሮ የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነትን የሚለየው ምርመራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የጸረ አበረታች ቅመሞች ጽህፈት ቤት ምርመራውን የሚያካሂደውም ከአለም አትሌቲክስ የኢንተግሪቲ ዩኒት (AIU) ጋር በመተባበር ነው።በመርሃ ግብሩ ላይም በግላቸውም ይሁን በብሔራዊ ቡድን ታቅፈው አገራቸውን በተለያዩ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ ወክለው የሚሳተፉ ታዋቂና ልምድ ያላቸው አትሌቶች ቅድሚያ እንደተሰጣቸውም ታውቋል።ማህበሩ በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የአትሌቲክስ ስፖርት በአንጻራዊነት ልምምድና ውድድር መጀመራቸውን ተከትሎ በአበረታች መድኃኒቶች ቁጥጥር ላይ የሚሰሩ ተቋማት ወደ ኃላፊነታቸው እንዲመለሱ አስታውቋል።መደበኛውና በታዋቂ አትሌቶች ላይ የሚተገበረውና የት እንዳሉ ክትትል የሚደረግበት የቁጥጥር መንገድም ወደ ስራ ተመልሰዋል።

ምርመራው በዋናነት የአትሌቶች ባዮሎጂካል ፓስፖርት ፕሮግራምን (ABP) በተጠናከር መንገድ ተግባራዊ በማድረግ የተከለከሉ የስፖርት አበረታች ቅመሞችን የተጠቀሙ አትሌቶችን በቀጥታ የቤተሙከራ ትንተና ይለያል።ከዚህም ባሻገር የአትሌቶችን ግለ ታሪክ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በተከታታይ ጥናትና ትንታኔ በማካሄድ በተራቀቀ መንገድ የህግ ጥሰት የሚፈፅሙትን አካላት ለመለየት የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት እንደሚያስችልም ተጠቁሟል።

ጽህፈት ቤቱ በአትሌቶች ላይ የሚደረገው የምርመራና ቁጥጥር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያመላከተ ሲሆን፤ በተያዘው የ2013ዓም በጀት ዓመት ኦሊምፒክን ጨምሮ ለተለያዩ ውድድሮች ተሳትፎ ዝግጅት የሚያደርጉ አትሌቶች በቂ የሆነ ክትትል እንደሚደረግባቸው ገልጿል።ኢትዮጵያ ንፁህ ስፖርተኞችን ብቻ ይዛ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የምትሳተፍበትንና አስቀድማ የገነባችውን መልካም ገፅታ ማስቀጠል የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም ጥረት ይደረጋል።

አዲስ ዘመን መስከረም 6/2013