ሞፋራህ ለሦስተኛ የኦሊምፒክ ድል እየተዘጋጀ ነው

7

ብርሃን ፈይሳ

 በለንደንና ሪዮ ኦሊምፒኮች በተለይም ኢትዮጵያ በምትታወቅባቸው የረጅም ርቀት ውድድር እንግሊዛዊው አትሌት ሞሐመድ ፋራህ የበላይነቱን መውሰዱ የሚታወስ ነው።በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረክም ከአንድ ውድድር በቀር በተመሳሳይ የክብር ባለቤት ቢሆንም፤ ከመም ወደ ጎዳና ላይ ውድድሮች ራሱን ማሸጋገሩን አስታውቆ ነበር።ይሁን እንጂ በሁለት ዓመታት ቆይታው እንዳሰበው ስኬታማ ባለመሆኑ በድጋሚ ወደ መም ውድድሮች ተመልሷል።ከሳምንታት በፊት በተካፈለበት የአንድ ሰዓት ውድድርም በኢትዮጵያዊው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እጅ የነበረውን ክብረወሰን በማሻሻል በመልካም ውጤት ጀምሯል።አሁን ደግሞ በኦሊምፒክ ለሁለት ጊዜያት ባለ ድል በሆነበት 10 ሺ ሜትር አሸናፊ በመሆን ታሪክ መስራት እንደሚፈልግ አስታውቋል።

በ5ሺ እና 10 ሺ ሜትር ርቀቶች የኢትዮጵያውያን ተቀናቃኝ የሆነው ሞሃመድ ፋራህ፤ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ተጨማሪ ስኬት ለማስመዝገብ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።የ37 ዓመቱ ትውልደ ሶማሊያዊ አትሌት ፊቱን ዳግም ወደ መም ውድድሮች መመለሱን ተከትሎ በተለይ በ10 ሺ ሜትር ለሶስተኛ ጊዜ ቻምፒዮን በመሆን ለመጪው ትውልድ መነሳሳትን መፍጠር እንደሚፈልግም ጠቁሟል።‹‹በአንድ ውድድር (ርቀት) ብቻ በማተኮር ውጤታማ መሆን እፈልጋለሁ።ስለዚህም በ10 ሺ ሜትር ለተከታታይ ሶስት ኦሊምፒኮች የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት በመሆን የመጀመሪያው አትሌት መባል እፈልጋለሁ›› ሲልም አትሌቱ ጠቁሟል።

አትሌቱ እኤአ ከ2010 ጀምሮ ነው የምስራቅ አፍሪካዊያኑ ሃገራት ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች የበላይነቱን በያዙበት የ5ሺ እና 10 ሺ ሜትር ውድድሮች ውጤታማነቱን ማሳየት የጀመረው።ከመም ውድድሮች እስከተሰናበተበት እኤአ 2017 ድረስም በተሳተፈባቸው የኦሊምፒክ፣ የዓለም ቻምፒዮናዎችና ሌሎች ውድድሮች ላይ የክብረወሰን ባለቤት መሆን ባይችልም የበላይነቱን ግን ጠቅልሎ መያዝ ችሏል።በተሳትፎዎቹም 17 የወርቅ፣ 2 የብር እና 1 የነሃስ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ውጤታማነቱን አስመስክሯል።በዚህም በሃገሩ ታላቅ ድሎችን ለተቀዳጁ ሰዎች የሚሰጠውን ‹‹ሰር›› የሚል የክብር ማዕረግ ከስሙ ማስቀደም ችሏል።

ሞ ፋራህ በሁለት ተከታይ ኦሊምፒኮች (በለንደን እና ሪዮ) ኦሊምፒኮች በተካፈለባቸው ሁለቱም ርቀቶች ሌሎቹን አስከትሎ በመግባት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ነው።በቀጣዩ ዓመት በጃፓን ቶኪዮ አዘጋጅነት በሚካሄደው ኦሊምፒክም ተጨማሪ የክብር ባለቤት ለመሆን ማቀዱን ‹‹ከዚህ ቀደም ታሪክ ሰርቻለሁ፤ በእንግሊዝም በሁለት ተከታታይ ኦሊምፒኮች ሜዳሊያ በማግኘት ቀዳሚው አትሌት ነኝ።ነገር ግን በዚሁ ማቆም አልፈልግም፤ የምወደውን ነገር ማድረግ እፈልጋለሁ።ከባድ ቢሆንም ለማቅለል እሞክራለሁ›› ሲልም ነው ያብራራው።

ለቀጣዩ ትውልድም በጠንካራ ስራ ሁሉን ማቅለል እንደሚቻል መክሯል።አሰልጣኙ አልቤርቶ ሳላዛር ከስፖርት በአበረታች ንጥረ ነገር ምክንያት ከመታገዱ ጋር በተያያዘ ለቀረበለት ጥያቄም ‹‹ይህ የስፖርቱ አካል ነው›› ሲልም ምላሽ ሰጥቷል።

አዲስ ዘመን መስከረም 6/2013