ሆድና ጀርባ የሆኑት ፕሬዚዳንት ትራምፕና የደህንነት ባለስልጣናት

11

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከደህንነትና ስለላ ባለስልጣኖቻቸው ጋር ያላቸው አለመግባባት እየከረረ መጥቷል፡፡ የአሜሪካ የደህንነትና የስለላ መስሪያ ቤቶች ባለስልጣናት ቻይናና ሩስያ የአሜሪካን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተባብረው እየሠሩ ይገኛሉ በማለት ለአገሪቱ ሴኔት የደህንነት ኮሚቴ አባላት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ፕሬዚዳንቱ እ.አ.አ በ2020 በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ በመግባትና የአሜሪካን ተቋማት በመሰለል የአገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ውስጥ ለመክተትና ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኗቸውን ለማጉላት እየተሯሯጡ እንደሆነ፣ የደህንነትና የስለላ መስሪያ ቤቶቹ ባለስልጣናት ለሴናተሮቹ ነግረዋቸዋል፡፡

የአሜሪካ ማዕከላዊ ደህንነት ኤጀንሲ (Central Intelligence Agency – CIA)፣ የአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (Federal Bureau of Investigation – FBI)፣ የብሔራዊ ፀጥታ ኤጀንሲ (National Security Agency) እና የሌሎች የአገሪቱ የደህንነትና የስለላ መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎች በተለይ ቻይና በአሜሪካ ላይ ስለደቀነቻቸው ውስብስብ የምጣኔ ሀብት፣ ወታደራዊና የደህንነት ስጋቶች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተሩ ዳን ኮትስ ‹‹ሩስያና ቻይና ትብብራቸውን ሲያጠናክሩ አንዳንድ የአሜሪካ አጋሮች ደግሞ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በንግድና በደህንነት መስኮች በምትከተላቸው ፖሊሲዎች ምክንያት ከአሜሪካ እየሸሹ ነው›› በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡በተጨማሪም ቻይና፣ ሩስያ፣ ሰሜን ኮሪያና ኢራን የሳይበር ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአሜሪካን መረጃዎች የመመዝበርና በአሜሪካውያን ላይ ተፅዕኖ የማሳደር ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ላይ እንደተሰማሩም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ኅዳር ወር የተካሄደውን የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ (Midterm Election) ከውጭ ጣልቃ ገብነት መጠበቅ እንደተቻለና በ2020 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ግን የተደራጀ ጣልቃ ገብነት ይኖራል ብለው እንደሚጠብቁ ባለስልጣናቱ በማብራሪያቸው አመልክተዋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይም የብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተሩ ዳን ኮትስ ‹‹የአሜሪካ ጠላቶች የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማዳከምና አሜሪካ ከአጋሮቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማበላሸት እንዲሁም የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለማስቀየር ጣልቃ መግባታቸው አይቀርም›› ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ የደህንነትና የስለላ መስሪያ ቤቶቹ ባለስልጣናት ለሴኔቱ የደህንነት ኮሚቴ አባላት የሰጡት ማብራሪያ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ካላቸው አቋም ጋር የተራራቀ ነው፡፡ በተለይ ሁለቱ ወገኖች ሰሜን ኮሪያ፣ ሩስያና እስላማዊ መንግሥት (ISIS) በአሜሪካ ላይ ደቅነውታል የሚሉት ስጋት ደረጃው የተራራቀ መሆኑ የፕሬዚዳንቱና የደህንነትና የስለላ መስሪያ ቤቶቹ ባለስልጣናት ግንኙነት ሆድና ጀርባ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

የብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተሩ ዳን ኮትስ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ አልታጠቅም ብላ የተናገረችው ነገር ውሸት ነው ይላሉ፡፡ የመከላከያ ደህንነት ኤጀንሲ (Defense Intelligence Agency) ዳይሬክተሩ ሮበርት አሽሊም የብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተሩን ሃሳብ ይደግፋሉ፡፡ ‹‹በሰሜን ኮሪያ በኩል ከዓመት በፊት የደህንነት ስጋት የነበሩት ነገሮች አሁንም አሉ›› በማለት ሰሜን ኮሪያ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ስጋት እንደሆነች ይናገራሉ፡፡ የማዕከላዊ ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተሯ ጂና ሃስፐልም ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤትነቷን የሕልውናዋ ጉዳይ አድርጋ ስለምትመለከተው የጦር መሳሪያው ባለቤት ለመሆን የማትፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን ባለፈው ሰኔ ወር ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን ጋር ሲንጋፖር ላይ ተገናኝተው ከመከሩ ወዲህ ‹‹ሰሜን ኮሪያ ለአሜሪካ ስጋት የምትሆንበት ምክንያት የለም›› እያሉ ነው፡፡

በሌላ በኩል ራሱን እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራው ቡድን አሁንም ከሶሪያና ከኢራቅ በኩል ጥቃት ሊሰነዝር እንደሚችል ዳይሬክተር ዳን ኮትስ ይናገራሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግን ‹‹እስላማዊ መንግሥት የሚባለውን ቡድን ስላሸነፍነው ለደህንነታችን ስጋት አይሆንም›› ብለው አሜሪካ በሶሪያ ያሏትን ወታደሮች እንደምታስወጣ ተናግረዋል፡፡ ይህ ውሳኔያቸውም አንጋፋ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትን አበሳጭቶና አንዳንድ የአሜሪካ አጋሮችንም አስደንግጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ከአማካሪዎቻቸውና ከአሜሪካ ወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ትንታኔ በተፃራሪ የቆመ እንደነበርና አሸባሪው እስላማዊ መንግሥት ሙሉ በሙሉ ስላልከሰመና የሌሎች ታጣቂ ቡድኖች እንቅስቃሴም አስተማማኝ በሆነ መልኩ ስላልተገታ ወታደሮቹን ማስወጣት ተገቢ ውሳኔ እንዳልሆነ ባለሙያዎቹ ሲናገሩ ነበር፡፡ አንጋፋ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላትም ፕሬዚዳንቱ ስለውሳኔያቸው ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቃቸው የሚታወስ ነው፡፡

የኢራን ጉዳይም ፕሬዚዳንቱንና የደህንነት መስሪያ ቤቶቹን ሹማምንት ካላግባቧቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል፡፡ የደህንነት መስሪያ ቤቶቹ ባለስልጣናት ‹‹ኢራን የ2015ቱን የኢራን የኑክሌር ስምምነት (Iran Nuclear Deal) በመጣስ የኑክሌር ጦር መሳሪያ እየገነባች አልነበረም›› ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ግን ‹‹እስላማዊቷ ሪፐብሊክ በስምምነቱ ያገኘቻቸውን እድሎች ተጠቅማ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት ለመሆን እየተንደረደረች ነው›› ብለው አሜሪካን ከኢራን የኑክሌር ስምምነት አስወጥተዋታል፡፡ የአሜሪካ ደህንነት ስጋትም ናት ብለው ፈርጀዋታል፡፡
ምንም እንኳ ጠንከር ያለና በግልፅ የተለየ እርምጃ ባይወሰድም ፕሬዚዳንት ትራምፕ 17 ዓመታትን በእርስ በእርስ ጦርነት በቆየችው አፍጋኒስታን ውስጥ ከሚገኙት የአሜሪካ ወታደሮች መካከል ግማሽ ያህሉ ከአገሪቱ እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠታቸው የአሜሪካ የደህንነትና የሥለላ ተቋማት በጉዳዩ ላይ ካላቸው መረጃና ትንበያ ተቃራኒ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ የፕሬዚዳንቱና የደህንነት ተቋማቱ ባለስልጣናት አለመግባባት እየሰፋ ለመሄዱ ተጨማሪ ማሳያ ነው፡፡

ስለቻይና ጉዳይ ከኮሚቴው አባላት ብዙ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው የደህንነት ባለስልጣናቱ በሰጡት ምላሽ ቻይና በአሜሪካ ላይ የደቀነችው ስጋት አንድ ሁለት ተብሎ የሚቆጠር እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ ዳይሬክተሩ ክርቶፈር ሬይ ‹‹ቻይና በአሜሪካ ላይ የደቀነችው ስጋት ከሌሎቹ ሁሉ የበለጠ ጥልቅ፣ ሰፊና አስቸጋሪ ነው›› ብለዋል፡፡

የብሔራዊ ደህንነት ዳይሬክተሩ ዳን ኮትስ በበኩላቸው፣ የደህንነትና የስለላ ባለሙያዎች በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ተዘዋውረው ቻይና በታላላቅ ኩባንያዎች ላይ እያካሄደችው ስላለው ስለላ ከኩባንያዎቹ ሥራ አስፈፃሚዎች ጋር መወያየታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ቻይና ባለፉት ዓመታት ኃይልና እውቅና ያገኘችው የአሜሪካን መረጃዎች በመመዝበር ነው›› ብለዋል፡፡

የደህንነትና የስለላ መስሪያ ቤቶቹ ባለስልጣናት ማብራሪያ አሜሪካ ሁዋዌ (Huawei) በተባለው ግዙፉ የቻይና የቴሌኮም ኩባንያ ላይ የወንጀል ክስ መመስረቷን ባሳወቀችበት ማግስትና ዋሽንግተንና ቤጂንግ በንግድ ጉዳይ ላይ ሊመክሩ ከያዙት ቀጠሮ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የተሰጠ ነው፡፡

የደህንነትና የሥለላ መስሪያ ቤቶቹ ባለስልጣናት ለሴኔቱ የደህንነት ኮሚቴ የሰጡትን ማብራሪያ የሰሙት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባለስልጣናቱን በድጋሚ ወርፈዋቸዋል፡፡ ‹‹ኢራን በአሜሪካ ላይ የደቀነችው ስጋት ሊታያቸው ያልቻለ የዋሆች›› ብለዋቸዋል፡፡ ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካ ደህንነት ስጋት ናት የሚለውን የደህንነትና የሥለላ መስሪያ ቤቶቹን ባለስልጣናት ዕይታም አጣጥለውታል፡፡

‹‹የደህንነትና የሥለላ ባለስልጣናቱ ኢራን በአሜሪካ ላይ የደቀነችው ደህንነት የማያስጨንቃቸው ናቸው፡፡ እንደገና ትምህርት ቤት ገብተው መማር ይጠበቅባቸዋል›› በማለት በነገር ነክተዋቸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከአሜሪካ የደህንነትና የሥለላ ተቋማት ጋር ውዝግብ የፈጠሩት ገና የፕሬዚዳንት መንበሩን ሳይረከቡ ነበር፡፡ ተቋማቱ ሩስያ በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጣልቃ ስለመግባቷ ይፋ ያደረጉትን ጥናት ውጤት ዶናልድ ትራምፕ ማጣጣላታቸው የፕሬዚዳንቱን የቅርብ ሰዎች ጭምር አስገርሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሩስያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በጋራ የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ተመልክተው ‹‹ተግባራቸው ሁሉ ከሀገር ክደት አይተናነስም›› ብለው የወቀሷቸው የቀድሞው የማዕከላዊ ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጆን ብሬናን፣ ‹‹ትራምፕ የደህንነትና የሥለላ ተቋማት ምክረ ሃሳቦችን ለመቀበል አለመፈለጋቸው እጅግ አሳፋሪ ነው›› ብለዋል፡፡

ጎበዝ ናቸው ብለው ከሾሟቸው ባለስልጣናት ጋር አለመግባባትና እነርሱንም ማባረር መታወቂያቸው እየሆነ የመጣው ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ አሜሪካን የዓለም ሁሉ አለቃ አድርገዋታል ከሚባሉት ከደህንነትና ከሥለላ ተቋማት ጋር አለመግባባታቸው የት እንደሚያደርሳቸው ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡

ጥር 24/2011

አንተነህ ቸሬ