ፎክሎር ነክ የክብረ በዓል ቅምሻ

11

አዲሱ ገረመው

በፎክሎር የስነ ቃል ዘርፍ ከሚመደቡ ጥበባት ውስጥ አንዱ ክብረ በዓል ነው።ክብረ በዓልን ሰዎች የተለያዩ ጉዳዮችን ምክንያት አድርገው በጋራ በመሰብሰብ ያከብሩታል።ደስታ ተክለወልድ መዝገበ ቃል ክብረ በዓልን እንደሚከተለው ያብራራዋል።

«ክብረ በዓል- የበዓል ክብር፣ ገናን፣ ጥምቀትን፣ ትንሣኤን፣ ጰራቅሊጦስን ፣ መስቀልን፣ ፍልሰታን፣ ኅዳር ሚካኤልን፣ ሚያዝያ ጊዮርጊስን ለመሰለ በዓል የሚደረግ ማህሌት፣ ዘፈን፣ ንግስ እልልታና ደስታ፣ ሥራ አለመስራት፣ መንገድ አለመሄድ »/ 1950 ፣ 636/ በማለት ይገልፁታል።

እንደ ደስታ ተክለወልድ አገላለፅ፤ ክብረ በዓላት እንደ ገና ወይም ጥምቀት እንዲሁም አረፋና መውሊድ የመሳሰሉት በዓሎችን ምክንያት በማድረግ መንፈሣዊ እርካታን ለማግኘት የሚከናወን ድርጊት መሆኑ ነው።ድርጊቱም በዘፈን፣ በጭፈራ፣ በሆታና በመሳሰሉት የሚገለፅ እንደሆነም መገንዘብ ይቻላል።

በደስታ ማብራሪያ ላይ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ።አንደኛው በማህበረሰቡ ውስጥ ትኩረት የተሰጣቸው እንደ ትንሣኤ፣ መስቀል፣ ኢድአልፈጥር የመሳሰሉ ዕለታት መኖራቸውንና ሁለተኛው ደግሞ ዕለታቱ የሚከበሩት እንደ ዘፈን፣ ንግስ፣ ነሺዳና መንዙማ በመሳሰሉት መንገዶች መሆኑን ነው።

ክብረ በዓላት እንዲከወኑ ልዩ ልዩ መነሻ ድርጊት አፈፃፀም ያላቸው በመሆኑ በየጐራቸው መድቦ ቁርጥ ያለ ክፍፍል ለማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ።ነገር ግን በጥቅሉ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ብሔራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ስፖርታዊ እያሉ መከፋፈል እንደሚቻል ይጠቁማሉ።

ፖለቲካዊና ብሔራዊ ክብረ በዓላትን ሁለት ንዑሳን ክፍሎች አድርጐ ማየት ይቻላል።ፖለቲካዊ በዓል አንድ የፖለቲካ ድርጅት የበላይነትን ያገኘበት ሊሆን ይችላል፤ ብሔራዊ ክብረ በዓላት ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሀገር ነፃነትና ድል ከማድረግ ጋር በተያያዘ የሚከበሩ ናቸው።

የመንግሥት ክብረ በዓላትም የፖለቲካ ዓላማን ለማራመድ ያገለግላሉ።አርበኝነትን ማበረታታትና ለዴሞክራሲ ጠንካራ የሆነ ስሜት እንዲፈጠር ኮሚኒስታዊ ወይም የሶሻል አኗኗር ስልት በክብረ በዓላት አማካኝነት እንዲኖር ማድረግ በሰለጠኑ ሀገራት ዘንድ እየተለመዱ የመጡ ጉዳዮች ናቸው።ክብረ በዓላት ከማስደሰትና ከማዝናናትም አልፈው ሀገራዊ ስሜትንና ለሙያ ፍቅር እንዲኖር የማድረግ ግልጋሎትም ይሰጣሉ።

ወደ ሀገራችን የበዓል አከባበር ስንመጣ በኢትዮጵያ በርካታ ክብረ በዓላት የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክስቲያን የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት ተጠቃሾች ናቸው።

አስራት ገብረማርያም «ቤተክርስቲያን የተለያዩ በዓላት እንዲከበሩ የደነገገችው እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያደረጋቸውን ቸርነቶች የሰጠውንም ፀጋና በረከት በመንፈሣዊ ስሜት ለማስታወስና ምስጋና ለማቅረብ ነው» ይላሉ።

እነዚህን ክብረ በዓላት ለማድመቅ ደግሞ የተለያዩ ቃል ግጥሞች ሲደረደሩ ማየት የተለመደ ነው።ክብረ በዓላቱ ሃይማኖታዊ ቢሆኑም እንኳን በክብረ በዓላቱ የሚከወኑ ቃላዊ ግጥሞች መንፈሣዊና ዓለማዊ ሊሆኑ ይችላሉ።

የክብረ በዓላት ዘፈኖች አንድ ማህበረሰብ ወይም ቡድን በበዓላት ቀናት የሚከውናቸው ወይም የሚያቀነቅናቸው ቃለ ግጥሞች ናቸው።የበዓሉ ተሣታፊዎች በዓሉን በዘፈንና በጭፈራ ማሳለፋቸው የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ያጠነክርላቸዋል፣ ማህበራዊ ሕይወታቸው ይበልጥ የተሳሰረ እንዲሆን ያደርግላቸዋል።

የዛሬውን ጽሑፍ የምንቋጨው፤ በኢትዮጵያ ረጅም ዓመታትን ካስቆጠሩ ሃይማኖታዊ በዓላት ውስጥ አንዱ ስለ ሆነው የገና በዓል አከባበር በመርሐቤቴ ወረዳ አባይን በጭልፋ ያህል በማስቃኘት ይሆናል።

የገና በዓል ግጥሞች አከዋወን በመርሐቤቴ ወረዳየገናን በዓል ከታኅሣሥ 27 እስከ 29 ለተከታታይ 3 ቀናት በመርሐቤቴ ወረዳ ከተማ በዓለም ከተማ ኦፍና አማኑኤል ቤተክርስቲያን የወረዳዋ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎችና ሌሎችም ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ይከውኑበታል።

ይህን ክብረ በዓል ልጃገረዶች እጃቸውን አንሶስላ አሙቀው፣ ሽንሽን ቀሚስ ለብሰው ነጠላ በመደረብ ተውበው ይውላሉ።ወጣት ወንዶችም ቁምጣና ጃኬት ለብሰው ሸበጥ በመጫማት በዓሉን ያከብሩታል።

በክዋኔው ወቅት ወጣት ወንዶች ክብ በመስራት ያ ሆ፣ አይናማ፣ ሆይ መላ የሚባሉ ዘፈኖችን ሲጨፍሩ ከ50-100 ተቀባዮች፣ ከ5-10 ጨፋሪዎች፣ ከ1 እስከ 6 አውራጆች (ድምፃዊዎች) ሲሳተፉ፣ ሴቶች ወጣቶች ሸሙናዬ፣ ሆይ መላ፣ ደርባባ የመሳሰሉትን ይጫወታሉ፤ በወቅቱም ከ50 – 100 እና ከዚያ በላይ በመሆንና ክብ በመስራት ከ2 እስከ 4 አውራጆችና ከ2 እስከ 6 ጨፋሪዎችን ያሣትፋሉ።

በዚህም ጊዜ የሚጫወቱት የሚከተለውን ይመስላል።

ሻሙናዬ

አውራጅ ተቀባይ

ሻሙናዬ /2/ ጓድዬ አባባዬ ሻሙናዬ

ጓዴ ባንጀሬ ሻሙናዬ

ግሽልጡን የማሸው ሻሙናዬ

እያወራሽ ነው ወይ ሻሙናዬ

ኋላ የማይሆን ነው ሻሙናዬ

እንዳታስለምጂው ሻሙናዬ

ይህ ጨዋታ እርስ በእርስ ስለ ግሽልጡና ስለ ንፍሮው እያስመሰሉ ለወንዶች አጉል ወሬ እንዳታወሩ እየተባባሉ በምስጢር ይነጋገራሉ።

ወንዶች ለበዓሉ የሴቶቹን ያክል ቅድመ ዝግጅት ባያደርጉም እንኳን ሴቶቹ በተሰበሰቡበት በመገኘት እንዲህ በማለት ይዘፍናሉ።

አንቺዬ

አንቺዬ የማሽላ እንኮይ አላፈራም ወይ

አንቺዬ ስትግደረደሪ ፆምሽን እንዳታድሪ

አንቺዬ ስትሄጂ ቦይ ለቦይ አገኝሽ የለም ወይ/2/

በዚህ ጊዜ ጨዋታው እየደመቀ ሲሄድ በግልፅ ፍላጐታቸውን በመግለፅ ዋዜማውን ያሣልፋሉ።በንጋቱም ሴቶቹ የታሰረላቸውን ግሽርጥ በመፍታት ታጥበው ሎሚ ይቀቡታል።ከዚያም መዋቢያቸውን አድርገው ወደ ከበራው ይሄዳሉ፡፡

የክብረ በዓሉ ቃል ግጥሞች ተስተላልፎ

ተስተላልፎ ማለት የቃል ግጥሞቹ ከቦታ ቦታ ከዘመን ዘመን፣ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉበትን ስልት ይመለከታል።በዚህም መሠረት የመርሐቤቴ ወረዳ ወጣት ወንዶችና ሴቶች የቃል ግጥሞቹን በየበዓላቱ በመገኘት ይለምዳሉ።የለመዱትንም በየበዓላቱ ተገኝተው በመከወን ቃል ግጥሞቹ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ።

በቃል ግጥሞቹ ተስተላልፎ ላይ ከዋኞቹ ትልቁን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን፣ ታዳሚዎችም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።በአንድ ወቅት በአካባቢው በነበረኝ የመስክ ቆይታ ከዋኞች ከቀበሌያቸው ውጭ በመሄድ ቃል ግጥሞችን ሲከወኑ ተመልክቻለሁ።ከከዋኞቹ በተጨማሪ በርካታ ተሣታፊዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ራቅ ብለው በመሄድ ሚናቸውን ይወጣሉ።በአካባቢው በዓሉ ከታኅሣሥ 27 እስከ 29 ይከበራል።ይህን በዓል ራቅ ካሉ የገጠር ቀበሌዎች ድረስ የሚመጡ ሰዎች ኦፍና አማኑኤል ቤተክርስቲያን በመሄድ ይጫወታሉ።በዚህም ከዋኞችና ተሳታፊዎች ቃል ግጥሞቹ ከቦታ ወደ ቦታ ተስተላልፎ እንዲኖራቸው ያደርጋሉ።

አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013