የ82 ዓመቱ የኦክስፎርድ ሰው የኮቪድ-19 ክትባት ለመውሰድ የመጀመሪያ ሰው ሆኑ

9

በኃይሉ አበራ

የ82 ዓመቱ የእድሜ ባለጸጋ እና ጡረተኛና የቀድሞ የጥገና ሥራ አስኪያጅ ብሪኣን ፒንከር ትናንት በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀውንና ክሊኒካዊ ሙከራ ያልተደረገበትን የኮቪድ ክትባት በመቀበል በዓለም የመጀመሪያው ሰው ሆኗል ሲል ዘ- ጋርዲያን ዘግቧል።

በዘገባው መሰረት የኩላሊት ህመምተኛ የሆኑትና የዲያሌሲስ ህክምና በመውሰድ ላይ የሚገኙት ብሪኣን ፒንከር ክትባቱን በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የኤን.ኤች.ኤስ ፋውንዴሽን ትረስት ቸርችል ሆስፒታል ነርስ ከሆኑት ሳም ፎስተር ተቀብለዋል።

ኦክስፎርድ ተወልደው ያደጉት ፒንከር በኤን.ኤች.ኤስ እንግሊዝ በሰጠው መግለጫ ክትባቱን መውሰዱ የአእምሮ ሰላም እንደሚሰጣቸውና ህክምናውን እንደሚቀጥሉበት የገለጹ ሲሆን በመጪው የካቲት ወር የ48ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን ለማክበር በጉጉት እየጠበቁ እንደሆነም ገልጸዋል።

«ዛሬ የኮቪድ-19 ክትባት በመውሰዴ በጣም ደስተኛ ከመሆኔም በላይ የኦክስፎርድ ግኝት ውጤት ከሆኑት አንዱ በመሆኑም ኩራት ይሰማኛል» ሲሉም ገልጸዋል። «ነርሶች ዶክተሮች እና የሥራ ባልደረቦች ዛሬ ሁላችሁም ብሩህ የሆናችሁ እኔም አሁን በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የካቲት ወር ላይ የ48ኛ ዓመትን የጋብቻ ክብረበዓሌን ከባለቤቴ ሺርሌይ ጋር ለማክበር በእርግጠኝነት ወደፊት እያየሁ ነኝ» ብለዋል።

ፎስተር እንዳሉት «የመጀመሪያው የኦክስፎርድ ክትባት እዚህ ኦክስፎርድ ውስጥ ከተሰራበት ቦታ በጥቂት መቶ ሜትሮች ርቀት ላይ ብቻ በሚገኘው ቸርችል ሆስፒታል ማድረስ መቻል እውነተኛ መታደል ነው። በመቀጠልም በመጪዎቹ ሳምንታት ሌሎች በርካታ ታካሚዎችን እና የጤና እና እንክብካቤ ሰራተኞችን በኦክስፎርድ ግኝት ክትባት ለመከተብ በጉጉት እንጠብቃለን፣ ይህም እኛ በምናገለግላቸው ማህበረሰቦች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች እና በሆስፒታሎቻችን ውስጥ ለሚንከባከቧቸው ሰራተኞች ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል።

 በእንግሊዝ ኤን.ኤች.ኤስ ሆስፒታል ብሔራዊ የሕክምና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ስቴፈን ፖዊስ የኦክስፎርድን (አስትራዜኔካ) ክትባት ስርጭት በተመለከተ «ከዚህ ወረርሽኝ የምንወጣበት ሌላኛው ለውጥ ነው» ሲሉ ገልፀዋል። ትናንት ጠዋት ለቢቢሲ እንደገለጹት «ከአራት ሳምንታት በፊት ለመጀመሪያው የፒፋይዘር ክትባት ኮቨንትሪ ውስጥ የመስራት እድል ነበረኝ፤ ማጊዬ ኬናን ያንን የመጀመሪያ ክትባት እንዳገኘች አስታውሱ፤ እውነቱን ለመናገር በዚህ ወረርሽኝ ወቅት ዛሬ ከጀርባዬ ባለው ሕንፃ ውስጥ በመጀመሪያውን

 የአስትራ ዜኔካ የክትባት ተግባር ስመለከት የወረርሽኙ መግቻ ትልቅ ቅጽበት እና ከዚህ ወረርሽኝ የምንወጣበት ሌላኛው ቅያሽ መንገድ ሆኖ ይሰማኛል።»

ንግግሩን በመቀጠልም «በታሪካችን ትልቁ ለሆነው የኤን.ኤች.ኤስ የክትባት መርሃ ግብር ለብዙ ወራት እየተዘጋጀን ነበር። እኛ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የፒፋይዘር ክትባቶችን አስገብተናል። አሁን የአስትራዜኔካ የሆነውን አግኝተናል፤ ስለሆነም ለእኛ እንደተሰጠን በፍጥነት ወደ ሰዎች ክንድ ማድረስ ዓላማችን ነው። በሳምንት 2 ሚ ዶዝ ካገኘን ዓላማችን በማድረሱ ተግባር ውስጥ 2ሚ ዶዝ በእነዚያ ከፊት ተሰላፊ ቡድኖች ክንድ እንዲደርስ ማድረግ ነው።» ብሏል።

የአስትራዜኔካ የኮቪድ-19 ክትባት አቅርቦትን በተመለከተ ፖዊስ እንደገለጸው «በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር መሰረት፣ ሚያዝያ ወር ድረስ በአስር የሚቆጠሩ ሚሊዮኖች ዶዞችን አቅደናል። ይህ አዲስ ክትባት ነው፤ ከመለቀቁ በፊት እያንዳንዱ ባች መታየት አለበት፤ ይህ ሲሆን በሚቀጥሉት ሳምንታት ያለው ድልድልም ግልጽ ይሆናል። ነገር ግን እንዳልኩት ለመቀጠል ተነሳሽነቱ አለን።»

አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013