የጠፋው ቀለበት

ዳግም ከበደ

በአገራችን ትልቅ ስፍራ እየተሰጣቸው ከሚከበሩ በዓላት መካከል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በደማቅ ስነ ስርዓት የሚከበሩት የገናና የጥምቀት በዓላት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ክብረ በዓላት ለማክበር የእምነቱ ተከታዮች ሰፊ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተው ትናንት በአሉን በደማቅ ስነስርዓት አክበረውታል፡፡

የአመት በአል ዋዜማ በገበያና በሌሎች ዝግጅቶችና በግርገር የተሞላ ነው፡፡ የበአሉ አለትም መብላት መጠጣቱ ሙዚቃው መዝሙሩ ግብዣው ይጦፋል፤ በስልክ፣ በአካል፣ ወዘተ እንኳን አደረሳችሁ መባባል አለ፡፡ የትናንቱን እለት በእነዚህ ሁሉ ስሜቶች ውስጥ አሳልፈናል፡፡ ዘግይቼም ቢሆን እንኳን አደረሳችሁ እላለሁ፡፡ ሲቀር ነው መጥፎው፡፡

ዛሬ ደግሞ የድካም ስሜት ሊኖር ይችላል፤ በተለይ በዝግጅቱ የወጡ የወረዱ ብዙ ይደክማሉ፤በአመጋገቡ በመጠጡ የሚጎዱም ጥቂት አይባሉም፡፡ የበአሉ ስሜት እየተጫነንም እኛ እንደ ፈረንጆቹ አይደለንምና ስራ እንገባለን፡፡ዛሬ በሌላ አዲስ መንፈስ ውስጥ ነን ማለት ነው።

ዛሬ በአንዳንድ አስደናቂ ክስተቶችና አዝናኝ በሆኑ ጉዳዮች እፎይታ እንድናደርግ አስበናል፤ ከተለመደው አይነት ጉዳይ ወጣ ብለን ቀልባችንን የወሰዱ አስገራሚ ዜናዎች ላይ ልናተኩር ወደናል። እነዚህን ዜናዎች ከአገር ውስጥ ሳይሆን ወጣ ብለን ከወደ ምዕራቡ መንደር ነው ጨለፍ ያደረግናቸው። ለመሆኑ ያስገርማሉ፣ ቀልብን ወስደው አእምሮን ዘና ያደርጋሉ ያልናቸው ሃሳቦች ምን ይሆኑ?

የሚያደንቁትን ሰው ፊት ለመምሰል

የሮይተርስ የዜና ምንጭ የሚጋራበት ድረገፅ ውስጥ ዞር ዞር እያልን ወሬዎችን ስንመለከት ቀልባችን አንድ ጉዳይ ላይ አነጣጠረ። ከወደ ጃፓን አንድ አስገራሚ ጉዳይ እንዳለ ከዜና ምንጩ አነበብን። ጉዳዩ እንዲህ ነው።

ለመሆኑ የራሶ የፊት ገፅ ሰልችቶት ይሆን? ወይ ደግሞ የሚወዱትና የሚያደንቁት የፊት ገፅታን ለአንዴም ቢሆን እርሱን በመሰልኩ ብለው አስበው ያውቃሉ? ግዴለም አንድ ቆንጆ መፍትሄ አለ። በዚህ ጉዳይ ከአሁን በኋላ ሊጨነቁ አይገባም።

አንድ ጃፓናዊ የሱቅ ነጋዴ ይህን ሃሳቦንና ምኞቶን እውን የሚያደርግ ሃሳብ ይዞ ከተፍ ብሏል። ነገሩ እንዲህ ነው ፤ቁርጥ የሚፈልጉትን አይነት የሰው ገፅታ የሚመስል የማስክ ቴክኖሎጂ ይዞሎት ብቅ ብሏል። ታዲያ ከእርሶ የሚጠበቀው አንድ ነገር ብቻ ነው። ወደዚህ ጃፓናዊ ሱቅ ጎራ ብለው የሚወዱትን የፊት ገፅታ መራርጠው የፊት ገፅታዎን በማስኩ ቀይረው ሸብ ረብ እያሉ ወደ ጉዳዮት መሄድ ብቻ።

ሹሂ አኮዋ ይባላል። በጃፓን ቶኪዮ ይሄን በሶስት አንግል (3 ዳይሜንሽን) ከእውነተኛው የሰው ልጅ ጋር በእጅጉ የተቀራረቡ የፊት ገፅታዎችን በማተም ለሽያጭ ያቀርባል። አሁን አሁን በርካታ ደንበኞቹ በማህበራዊ ድረ ገፅ ምስላቸውን እየላኩ እንዲታተምላቸው ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ። ሱቁ ድረስ በመሄድም በትዛዝ የፊት ማስኩን እየሸመቱ ናቸው።

የዚህ ፈጠራ ባለቤት የሆነው ሹሂ ማስኮቹ በብዛት ለፓርቲና ለመዝናኛ ስፍራ ሊውሉ እንደሚችሉ ይናገራል። በኮሮና ዘመን የተፈጠሩት እነዚህ የፊት ገፅን ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን ሌላ ምስልን የሚሰጡ ማስኮች የኮቪድ ወረርሽኝን የመከላከል አቅም ግን የላቸውም።

የጠፋው ቀለበት

ሁላችንም በአንድ ወቅት አንድ የምንወደው ነገር እንደሚጠፋብን እርግጥ ነው። ሆኖም ከአመታት በፊት የጣልነውን በህይወታችን ትርጉም ያለው ጉዳይ ቁስ በድጋሚ ባልተጠበቀ መንገድ ብናገኘው ምን ይሰማን ይሆን?

እንደኛ ግምት ግራ መጋባት፣ የመደነቅ ስሜት አሊያም በጊዜው እቃው ለእኛ የነበረውን ቦታ ለማስታወስ በትዝታ ወደ ኋላ መለስ ብለን በፈገግታ ሃሳብ ውስጥ ልንሰምጥ እንችል ይሆናል። ማን ያውቃል። ሰሞኑን የሆነውም ይሄው ነው። ጉዳዩ ደግሞ በማሳቹሴት ግዛት ነበር የተፈጠረው። በዩናይትድ ስቴት ማሳቹሴት ትንሿ ራሂም ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆነው ጃክ ሄሊ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት የሃይስኩል ተማሪ በነበረበት ወቅት ነበር የሚወደው የጣት ቀለበት የጠፋበት።

ጃክ ቀለበቱ መጥፋቱን ያወቀው ከራሂም መኖሪያ ቤቱን ቀይሮ ወደ ብሊትሮር ምትባል ከተማ ከሄደ በኋላ ነበር። ቀድሞ ይኖርበት የነበረው ቤት ውስጥ የገቡ ቤተሰቦች ግን የዚህን ሰው ቀለበት አግኝተው ለዓመታት በአንድ ትንሽ ሳጥን ውስጥ አስቀምጠውት ነበር።

አንድ ቀን ግን ከቤተሰቡ መካከል አንዱ ይህን ንብረት ለባለቤቱ የመመለስ ሃሳብ ይመጣለታል። ታዲያ ለማህበራዊ ድረገፅ ምስጋና ይግባውና ቀለበቱን ፎቶ አንስቶ ባለቤቱን የሚያውቅ ካለ በሚል ጥሪ ያደርጋል።

በዚህ ጊዜ ታዲያ የጃክ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጓደኛ የሆነችውን ሄሊ ትኩረት ይስባል። ወዲያውኑም ለቀድሞ ጓደኛዋ የመልክት ሳጥን ውስጥ ቀለበቱ እንደተገኘ በመንገር ከ50 ዓመት በኋላ የሚወደውን ንብረት በድጋሚ በእጁ እንዲያስገባ አድርጋለች። ጃክም በአደራ ለዚህ ሁሉ ዓመት ቀለበቱን አስቀምጠው ለመለሱለት ቤተሰቦች ምስጋናውን አቅርቧል።

አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2013

Ad Widget

Recommended For You