የራስን እየጣሉ የሌላውን ማንጠልጠሉ ነገር

16

ይቤ ከደጃች ውቤ

ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕ ራይዞች በማደራጀት የስራ እድል ለመፍጠር ተሰርቷል። አምራቾቹን ለማበረታታት ሥልጠና መስጠት፣ ምቹ የሥራ ቦታ ማመቻቸትና ገበያ ለማፈላለግም ተሞክሯል።

በአዲስ አበባ መርካቶ ሸራ ተራ፣ መሳለሚያና ኳስ ሜዳ አካባቢዎች የቆዳ ጫማ አምራቾችና ለጫማው ግብአት የሚያገለግሉ ቁሳቁስ የሚሸጡ ሰዎች በብዛት ይገኛሉ። የጫማ ምርቶቻቸው በትልልቅ የጫማ መሸጫ መደብሮች ጭምር የሚሸጡ ናቸው። የሚያመርቱት በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነው። ከፊሎቹም መንገድ ዳር ተቀምጠው የሚሠሩ ናቸው። በእጅ እየተመረቱ በፋብሪካ ከሚመረቱት የሚወዳደሩ ናቸው ብል ማስታወቂያ እየሠራህ ነው እንዳልባል ፈራሁ።

ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማምጣት ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ለሆኑ የግብርና ምርቶች ትኩረት መስጠት፣የኮንትሮባንድን ቀዳዳ መዝጋት፣ የምጣኔ ሀብት መሠረት የሆኑ ምርቶች ላይ ዕሴት ጨምሮ ወደውጪ የሚላክበትን ሁኔታ ማመቻቸት ወሳኝ ነው። መንግስት በዚህ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ሲያረጋግጥ ቆይቷል።ይሁንና ውጤታማነቱ ያጠራጥራል።

በመርካቶ የማቀዝቀዣና የቴሌቪዥን ነጋዴዎች ለቴሌቪዥን ማስቀመጫ የሚሆኑ ተገጣጣሚ የእንጨት ምርቶችን ሳይቀር በውጭ ምንዛሪ እያስመጡ ያለበት ሁኔታ እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ማቅረብ አይደለም ለሀገር ውስጥ ማምረትም አለመቻሉን ይጠቁማል። የውጭ ምንዛሪ ላጠራት ሀገር በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶችን ከውጪ እያመጡ መቸርቸር ምን ይሉታል።ይህ ሁኔታ በሀገር የውጭ ምንዛሬ መቆመር ይመስለኛል ።

ሀገራችን የውጭ ምንዛሬ በምፅዋት እየተቀበለች፣ በንግዱም እዚህ ግባ የማይባል የውጭ ምንዛሬ እያገኘች፣ እርባና ቢስ ቁስም እየገዛች እንዴት ይዘለቃል። የውጭ ምንዛሬ እየረጨች የውጭ ምንዛሬ አጠረኝ የምትል ሀገር አተረፉልን። እነማን? የቀደሙት፤ፓርቲ ጠርታችሁ ደግሞ እንዳታስጨፍሩኝና እንዳታጋጩኝ ሰጋሁኮ! እኔ ፓርቲ ያልኩት የምታዘጋጁልን ጭፈራና ዳንኪራ ካለ ብዬ ነው እንጂ የፖለቲካ ድርጅት አልጠራሁም።

የሀገራችን ባለሙያዎች እነዚህም ምርቶች እንዲያመርቱ ለምን አይደረግም? የቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች፣ ባለሀብቶች በእነዚህ ምርቶች ማምረት ላይ ለምን በስፋት እንዲሰማሩ አይደረግም። ገቢዎችና ጉምሩክም ቀረጥ በመጫን ለሀገር ውስጥ ምርቶች ጥላ ከለላ በመሆን ለምን አይንቀሳቀስም ትላላችሁ፤ የብድርና ታክስ ሥርዓቱም አምራቾችን ለማበረታታት ትኩረት አይሰጥም እንዴ የሚሉት ጥያቄዎቼ ናቸው።

ሲነገረን የቆየው የአነስተኛና ጥቃቅን አምራቾችን ማበረታታት ብዙም አልተተገበረም ።ያ ሆኖማ ቢሆን መዝጊያ መስኮት፣ የቢሮ እና የቤት እቃዎች ገበያችንን ባላጨናነቁት ነበር። የመሥሪያ ቤት፣ የትምህርት ቤትና የቤት ወንበርና ጠረጴዛ፣ ሶፋ ጭምር ከውጭ ማስመጣት የማደግ ምልክት አይመስለኝም። ደብተር ከውጭ ይመጣልናል። በርግጥ አቅም ያለው ከአሜሪካ አይደለም ከጨረቃም ቢያስመጣ አንቀየምም፤ አንመቀኝም። በዚህ ላይ ግን ጉምሩክ ቀረጡን ቆልሎ ይታደገን ዘንድ እንጠይቃለን። የምናድገው በዜጎቻችን የተመረቱ ምርቶችን ስንሸምት ነው።

አምራቾችና ባለሙያዎችም በማኅበር ተደራጅተው የጉልበትና የሙያ ውጤት የሆኑ ምርቶቻቸውን ከውጭ ምርቶች መከላከል ይኖርባቸዋል። ችግሩ አብዛኞቹ ነጋዴዎች ባላቸው አማራጭ ወደ ሥራ የገቡ የዘልማድ አምራቾችና ነጋዴዎች መሆናቸው ላይ ነው። ለነገሩ እንደራጅም ቢሉ ለይስሙላ ካልሆነ በቀር በጥርጣሬ ነው የሚታዩት። በአገዛዙ ሥር በነበረው ቢሮክራሲያዊ ጫና ይከስማሉ። ለነገሩ የተደራጁትም ቀደም ሲል በቃል አቀባይነት ሲሠሩ የነበሩ ናቸው።

ያ አውራ ፓርቲ ንግዱንም/የራሱን/ሀገርንም እየመራ ስብሰባም እየመራ ጊዜ አጠረው፤ አይፈረድበትም። በስብሰባ ጊዜ ስላጠረው የዜጋውን ችግር ሊረዳው አልቻለም። አንድ ጋዜጣ በሀገሪቱ በጣም ስብሰባ ስለበዛ የአንድ ለአምስት ጥርነፋን ጨምሮ ማለት ነው ስብሰባን የሚቀንስ ስብሰባ ይደረግ ብሎ ጽፎ ነበር። ነጋዴዎችን እናበረታታለን እያለ የበላው አደራ ከወንበሩ አስነሳው። አውራው ፓርቲ ከሰው ስለራቀ አውሬ ሆነ ነው ያሉኝ አንድ የውቤ ሠፈር ነጋዴ።

ከውጭ የሚገቡ የህንፃ የሴራሚክ የወለል ንጣፎች አይቻለሁ፤ ቀደም ሲል ከማቃቸው የወለል ንጣፎች ያምራሉ፤ የውሃ ብርጭቆ ይዛችሁ የሴራሚክ ወለሉ ላይ ቢወድቅ ግን ብርጮቆው ተሰበረ ብላችሁ ብታዝኑም ብርጭቆው ወድቆ ሳይሰበር የወለል ሴራሚኩ ይሰነጣጠቃል፤ አልያም ብርጭቆውም ይሰበራል የወለል ንጣፉም ይሰነጣጠቃል። ይህ ነገር አጋጥሞኝ ባየሁባቸው ህንፃዎች የተገጠመው የወለል ስዕል ነው እንዴ? አስብሎኛል።

 ባህላዊ ጥበብ መሳይ አልባሳትም ከውጭ ማስመጣት ተጀምሮ ነበር፤ ተባነነበት፤ ገበያ ሲያጣ በራሱ ጊዜ ከገበያ ወጣ። በሴራሚክ የተሠሩ የውጭ የቡና ጀበና፣ የፕላስቲክና መስታወት ሥሪት ረከቦት አይቻለሁ፤ ባህልንም ሸክላ አምራችንም ማዳከም ስለሆነ መገታት አለበት።

ለዘመናት ስናጣጥላቸው የነበሩት ሸክላ ሠሪዎችን ግንዛቤ ሰጥቶ ከውጭ የሚመጡ ሴራሚክ የፊት መታጠቢያ እና የመጸዳጃ መቀመጫዎችን ሊሠሩ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸትም ይቻላል። የግድ ቀለማቸው ነጭ ወይም ሌላ መሆን ካለባቸው ከተሠሩ በኋላ በቀለማት ማሳማመር መፍትሄ ነው። ዋጋውም ከውጭ ከሚመጡት ይቀንሳል።

በለውጡ ማግስት መንግሥት ለወጣቱ ሥራ ዕድል በመፍጠር እንደአብነት የሚጠቀሱ ክዋኔዎች ታይተዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአዲስ አበባ መስተዳድር ለሸክላ ሠሪዎች ለመሥሪያና ለመሸጫ ምቹ ቦታ ሰጥቷል።ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቦታውን ጎብኝተዋል። ይህም ሸክላ ሠሪዎችን ዐይንህ ላፈር እያለ እያጣጣለ ምርታቸውን እያንጠለጠለ ሲጠቀም ለነበረው ህብረተሰብ ሁሉ ሙያተኞች መከበር እንዳለባቸውና ማደግ የሚቻለው ስናበረታታቸው እንደሆነ ያስረዳናል።

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች ምርታማና ውጤታማ እንዲሆኑ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን ማበረታታት ይገባል። ይህም ብዙ ዜጎች ገቢ ከማግኘታቸው በተጨማሪ ባለሙያ ወጣቶችን እንዲቀጥሩ ተጨማሪ አምራቾችም እንዲፈጠሩ ያስችላል።

የምግብ ዘይት በአብዛኛው ከውጭ ይገባል። ለዘይት የሚሆነውን ምርት በጥሬ ወደ ውጭ ከመላክ የምግብ ዘይት አምራቾችን የታክስ ማሻሻያ በመስጠት መደገፍ ያስፈልጋል። ይህም ግብርናውና ኢንዱስትሪው እንዲመጋገቡ፣ አርሶ አደሮችንም እንዲያበለፅጉ ይረዳል። በጣም የምናሳስብ ሆነናል። ብርቱካንና እንጆሪ ከግብፅ፣ ሽንኩርት ከሱዳን እያስገባን ነው። በሀገር ውስጥ ሊመረቱ እንደሚችሉ በተረጋገጡ ምርቶች ላይ ውጤታማ መሆን አልቻልንም፤ ለምን? ማምረት እየቻልን ባለማድረጋችን የተነሳ ገበያዎቻችን በሌሎች ሀገሮች ምርቶች እየተጨናነቁ ናቸው።

መቼም የራሳቸውን እየጣሉ የሌላውን ምርት የሚያንጠለጥሉ ይወድቃሉ እንጂ ይመጥቃሉ የሚል እምነት የለኝም። ይህችን ድሀ ሀገር ለመታደግ የራሳችንን እየጣልን የሌላውን እንዳናንጠለጥል እናድርግ። ሰው የራሱን ከጣለ ለኔ ራሱን እንደጣለ (ህሊናውንም እንደሳተ) ይቆጠራል። ሰው የራሱ የሆነን አይጥልም።

መንግስት በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ምርቶች ወደ ሀገር ውስጥ ከማስገባት መቆጠብ አለበት። የሚያስገቡ ካሉም በቀረጥ ማጨናነቅ ይኖርበታል። አምራቾች ምርቶቻቸውን ከውጭ ምርቶች መከላከል ይኖርባቸዋል። ለእዚህ ደግሞ መደራጀት ይኖርባቸዋል። እርግጥ ነው የንግድ ምክር ቤቶች አሉ። ምክር ቤቶቹ ነጋዴውን ከመንግስት ጋር በማገናኘት ድልድይ ሆነው እንደሚያገለግሉ ይታመናል። ይህን የሀገር እና የአምራቾች ችግር ለመፍታት መስራቱን ማጠናከር ይጠበቅበታል። ህዝቡ የዜጎቹን ምርቶች ሊጠቀም የሚችልበትን መንገድ ያስተምር።

አዲስ ዘመን ጥር 01/2013