የፍቅር ዋሻ

4

ኃይለማርያም ወንድሙ

የዋሻ ትርጉሙና አገልግሎቱ ሰፍቷል። ዱሮ አንደሚታወቀው ብቻ አይደለም:: የምድር ውስጥ መኖሪያ ፣መንገድ፣ምሽግ ፣ወዘተ መሰራት በዚህ ዘመንም ቀጥሏል::ፍልስጤሞች ከጋዛ ወደ ግብጽ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የመሬት ውስጥ ለውስጥ ዋሻዎችን/ተነሎችን/ በመገንባት ይጠቀማሉ። እስራኤል ዋሻዎቹን እያገኘች ብታወድምም እነሱ በርካታ ዋሻዎች ስላሏቸው በዋሻዎቹ እያረጉ የፈለጉት ቦታ ከመሄድ አልተቆጠቡም::

ሜክሲኮም የመሬት ውስጥ ምስጢራዊ ዋሻ ድረግብር (network) ትስስር በመፍጠር ዝነኛ ከተማ ነች ።ዋሻውን አደንዛዥ እፅ እና እጅግ ውድ ግን ኢ-ሕጋዊ የሆኑ ጭነቶችን ለማጓጓዝ ይጠቀሙበታል ።

በሀገራችንም ጁንታው ትግራይን ዋሻ በዋሻ እንዳረጋት ይታወቃል::ምንም አላስጣለውም እንጂ። በርካታ ኪሎሜትሮችን የሚሸፍን ዋሻ ገንብቶ ነበር:: የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ መንግስት በወሰደው የሕግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ ዋሻውም ጁንታውም እንዳይሆኑ ሆኑ::

እነዚህ እንደመግቢያ የተጠቀምኩባቸው ናቸው። የጽሁፌ ዋሻ ደግሞ ለሌላ ዓላማ የዋለ ነው::አንድ ሜክሲኳዊ በሜክሲኮ ከመኖሪያ ቤቱ እስከ ውሽማው ቤት ድረስ መሬት ለመሬት ውስጥ የሚወስድ ዋሻ ሰርቶ ተገኝቷል ።የፍቅር ጉዳያቸውን በምስጢር ለመጠበቅና ለማስቀጠል ለፈለጉት እነዚህ ሂያጆች ዋሻው ምቹ መሣሪያ ሆኗቸዋል ይለናል የኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ዘገባ ።

ይህ ሰው አንቶኒዮ በደል ፕራዶ ይባላል ::በቲጁአና ከተማ አቅራቢያ በግንበኛነት ይሰራል::ይህ ስራው በዚሁ አካባቢ ነዋሪ ከሆነች ፓሜላ ከምትባል ሴት ጋር ለመተዋወቅ ምክንያት ይሆነዋል፡፤ሴትዮዋ ባለትዳር ብትሆንም ፍቅር ውስጥ ይገባሉ::የምስጢር ፍቅረኛውን አንድም ሰው እንዲያውቅበት ስላልፈለገ ከቤቱ እስከ ሴትየዋ ቤት የሚደርስ ዋሻ በመሬት ውስጥ ፈልፍሎ ሠራ።

አንቶኒዮ ዋሻውን ለመገንባትና ቱቦዎችን ለመቆፈር የግንበኛነት የሥራ ልምዱን በሚገባ ተጠቅሞበታል ። ከቤቱ እስከ ፍቅረኛው ደጃፍ በሚወስደው መንገድ መሬት ውስጥ ለውስጥ የሚያቋርጥ ሰርጥ በመቆፈር ነው ዋሻውን የሰራው ።

ፍቅረኛሞቹ ዋሻው ከተጠናቀቀ በኋላ የፓሜላ ባለቤት ጆርጅ ለሥራ በወጣ ቁጥር በየቀኑ በምስጢር ለመገናኘት ተመቻቸው::አንድ ቀን ግን ያላሰቡት ነገር ተከሰተ፤ ጆርጅ በሌላ ቀን ለሥራ ከሚመለስበት ከታሰበው ሰዓት ቀደም ብሎ መጣ ።

አንድ ቀን አንቶኒዮ እና ፓሜላ ዓላማቸውን እየቀጩ እያለ የፓሜላ አባወራ ቤት መጣና ወዳሉበት ደረሰ::ግንበኛው በንዴት ከጦፈው የፓሜላ ባለቤት ለመደበቅ ሞከረ::ዝግ ብሎ በአልጋው ሥር ተሸሽጎ በፍቅር ዋሻው ውስጥ በመግባት ጠፋ ።

በሚያሳዝን ሁኔታ ጆርጅ የቤቱን ዙሪያ ተመለከተ::ምንም የሚያስወጣ ቀዳዳ አጣ ።በአልጋቸው ሥር ሲመለከት ግን ያየውን ለማመን ከበደው::ጉድጓድ ተመለከተ፤ዋሻ መሆኑን ተረዳ ።የተናቀው ባል ዝግ ብሎ በምስጢራዊው ዋሻ ገባና መሄድ ጀመረ ።ዋሻውም አንቶኒዮ ቤት በራፍ አደረሰው ።

ተሰውሮ የነበረው ግንበኛው አንቶኒዮ ለጆርጅ በሚቀጥ ለው ክፍል ያለችው ሚስቱ እንዳትሰማበትና ዝም እንዲል ለመነው። ከጋብቻ ውጪ እየወሰለተ ስለ ሚፈጽመው ግንኙነት ሚስቱ እንዳ ታውቅ በሚል በጽኑ አስተዛዝኖ ተማጸነው::

ይህ ግን ጆርጅን በጣም አስቆጣው ፤በዚህም ሁለቱ ሰዎች ግብግብ ውስጥ ገቡ ።እንግዳ ሰው ባልዋን እገዛ ቤቱ መጥቶ ሲመታባት ያየችው የአንቶኒዮ ሚስት ፖሊስ ጠራች::አንቶኒዮ ሕገወጥነቱን ለማስተባበል አማራጭ ስላልነበረው ድርጊቱን ተናዘዘ ።

“የፍቅር ዋሻ” ዜናውና ምስሎቹ በሜክሲኮ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በቅርቡ ተለቀቁ ::ክስተቱን በብሔራዊና ዓለምአቀፍ ዜና ማዕከላትም አንቶኒዮን ከውሽማው ጋር በሚስጢር ለመገናኘት ብሎ የቆፈረውን ይህን ዋሻ የአደገኛ ዕፅ ተዋናዩ ኤል ቻፖ ከሚያስቆፍራቸው የዋሻ መመላለሻዎች ጋር በማነፃፀርም ሲዘግቡት ሰነበቱ ።

አዲስ ዘመን ጥር 03/2013