ፈተና የማያጣው የሊባኖስ መንግስት ምስረታ

11

በመካከለኛ ምስራቋ ሀገረ ሊባኖስ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ መንግስት ለመመስረት መቸገር አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ምርጫ በተካሄደበት ማግስት የመንግስት ምስረታ ተግባር መጀመር የሚጠበቅ ቢሆንም በሊባኖስ የፓርላማ ምርጫን ተከትሎ ከአንድም ሶስቴ ለዓመት ገደማ መንግስት ሳይመሰረት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ እ.አ.አ በ2009 የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የፓርላማ ወንበር ባሸነፉ ፓርቲዎች መካከል በዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ላይ መድረስ ባለመቻሉ ለበርካታ ወራት መንግስት ሳይመሰረት ሀገሪቷ በባለአደራ መንግስት ለመተዳደር ተገዳለች፡፡ በሊባኖስ ከ2009 ዓ.ም በፊት የነበሩ ምርጫዎችንም ተከትሎ እንዲሁ መንግስትን መመስረት ቀላል ሆኖ አያውቅም፡፡ ቢያንስ እስከ አምስት ወር ሲፈጅ እንደነበር የኋላ ታሪኮቹ ያሳያሉ፡፡

በሀገሪቱ የምርጫ ህግ መሰረት የፓርላማ ምርጫ በየአራት አመቱ እንዲካሄድ የሚያዝ ቢሆንም፤ በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ምርጫው በተደጋጋሚ ሲራዘም ቆይቶ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ በግንቦት 2018 ምርጫ የተካሄደ ቢሆንም ለድፍን ዘጠኝ ወራት መንግስት መመስረት ባለመቻሉ ሀገሪቷ በባለአደራ መንግስት ስትተዳደር ሰንብታለች፡፡

አልጀዚራ ከቤይሩት እንደዘገበው፤ ምርጫ ከተካሄደ ከዘጠኝ ወራት አለመግባባት በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ሳድ ሃሪሪ መሪነት ከትናንት በስቲያ አዲስ የሊባኖስ መንግስት ተመስርቷል፡፡ ለዘጠኝ ወራት የዘለቀውን አለመግባባት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ድቀት ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት በዜጎች ዘንድ አድሮ የነበረ ቢሆንም ከትናንት በስቲያ የተመሰረተው አዲሱ መንግስት ሀገሪቷን ከዚህ ስጋት ይታደጋታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

የምዕራባዊያን ድጋፍ እንዳላቸው የሚነገ ርላቸው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳድ ሃሪሪ፤ የህዝቡን ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ ማሻሻያዎችን ማድረግ ግን አልጋ በአልጋ አይሆንላቸውም፡፡ በተለይም አሳሳቢውን የመንግስት ፋይናንስ ችግሮችን መቅረፍና የሀገሪቱን እድገት ለማነቃቃት በቢሊየኖች የሚቆጠር ብድርና እርዳታ በሮችን መክፈት ፈታኝ ስራ እንደሚሆንባቸው ከወዲሁ ተገምቷል፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ ባደረጉት ንግግር በከባድ ዕዳ ውስጥ ያለችውን ሀገር እያጋጠማት ካሉ ችግሮች ዋና ዋናዎቹን ለመቅረፍ በአፋጣኝ የማሻሻያ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ አብራርተዋል፡፡ ያለፉት ጊዜያት በተለይም ከምርጫው እስከ መንግስት ምስረታ የነበሩ ጊዜያት እጅግ ከባድ ነበር ያሉት ሃሪሪ፤ ‹‹ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች የሀገሪቱ ዋነኛ ችግሮች ናቸው፡፡ ይህን የመከራ ምዕራፍ ዘግተን አዲስ የተስፋ ዘመን መጀመር አለብን፡፡ ›› ብለዋል፡፡

በቅርቡ ከሲቪል ማህበርነት ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት የተሸጋገረው የሳባ ፓርቲ አባል ቪኪይ ክኻሪይ እንዳሉት፤ የሀገሪቱ ዜጎች በተደጋጋሚ አመጾች ባሰሙት ቅሬታ የተሻለች ሊባኖስን ማየት እንደሚፈልጉ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ህዝቡ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው እንዲሻሻል፣ መሰረታዊ ፍላጎቱ እንዲሟላ፤ ነጻ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ፣ መሰረተ ልማቶች እንዲሟላ፣ ነጻ የትምህርት እድል እንዲሰጥ፣ ወዘተ ፍላጎት አለው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አዲሱ የሀገሪቱ መንግስት ከምንም አስቀድሞ ምጣኔ ሃብቱን ለማነቃቃት እገዛ ለሚኖረው ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ማሻሻያዎች ትኩረት መስጠት አለበት፡፡

ሰላሳ ካቢኔን ያቀፈው አዲሱ የሳድ ሃሪሪ መንግስት የሊባኖስን ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎችንና የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩትን ጭምር ያካተተ ነው፡፡ በኢራን የሚደገፈው የህዝቦላህ ቡድንም የመንግስት አካል መሆን ችሏል፡፡ ለመንግስት መረጃ ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደገለጹት፤ ህዝቦላህ የሺያ እምነት ተከታይ የሆኑትን የቡድኑ አባል ያልሆኑትን ዶክተር ጃሚል ጃባክ ቡድኑን በመወከል የሀገሪቱ ጤና ሚኒስትር እንዲሆኑ በእጩነት አቅርቧቸዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር በሀገሪቱ ከፍተኛ በጀት ከሚመደብላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አንዱ ነው፡፡ ህዝቦላህ ይህን ቁልፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የመምራት እድል ማግኘቱ ቡድኑ በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ይጫወት የነበረው ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አመላካች ነው፡፡ በዋሽንግተን በአሸባሪነት የተፈረጀው ህዝቦላህ፤ በካቢኔው ውስጥ ሌሎች ሁለት መቀመጫዎች ይኖሩታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አዲሱ መንግስት ጽንፍ የያዙ ሀይሎችን በአንድ ላይ የሰበሰበ ከመሆኑም በላይ አንጻራዊ የጾታ ምጥጥንም የታየበት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከካቢኔ አባላቱ መካከል አራቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ሴቶች በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ቁልፍ የሚባሉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት የመምራት እድልም አግኝተዋል፡፡ በሴቶች ከተያዙ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኤነርጂ ሚኒስቴር ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች በጊዜው ምርጫ ሊካሄድ ባለመቻሉ፤ የሃሪሪ መንግስት ሀገሪቱን በባለአደራ መንግስትነት ሲመራ የቆየ ሲሆን፤ ባለፈው ግንቦት በተካሄደው ምርጫ የሃሪሪ ፓርቲ ከፓርላማ መቀመጫ አንድ ሶስተኛውን ለማጣት የተገደደ ቢሆንም ሃሪሪ የሱኒ ሙስሊም ቡድን መሪነታቸውን እንደያዙ በመቀጠላቸው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታቸውን ይዘው ሊቀጥሉ ችለዋል፡፡

በአንጃዎች በተከፋፈለችው ሊባኖስ መንግስት መመስረት እጅግ አዳጋች እንደሆነ የሚናገሩት የጉዳዩ ተንታኞች በተለይም የፓርላማ ወንበር ክፍፍሉ እጅግ ፈታኝ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የሊባኖስን መንግስት ምስረታ በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩት ቡድኖችና ግለሰቦች የሀገሪቱ የቀድሞ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ የመንግስት ምስረታው ከላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች፡፡

የኢራንና የሶሪያው ፕሬዝደንት ባሻር አል አሳድ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚደረግለት የሚነገርለት ህዝቦላህ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ እጅግ ተፅዕኖ ፈጣሪ ቡድን ነው፡፡ ህዝቦላህና አጋር ሀይሎች በፓርላማው ውስጥ ከፍተኛ መቀመጫ ማግኘታቸው የሀገሪቱን ፖለቲካ እንደፈለገው ለመዘወር እድል ከመፍጠሩም በላይ በሀገሪቱ ላይ የኢራንና የሶሪያ መንግስት ጫና እንዲበረታ እገዛ እንደሚኖረው ተገምቷል፡፡
እጅግ ውስብስብ በሆነው ስርዓት በምትመራው ሊባኖስ ውስጥ የሃይማኖትና የፖለቲካ ማህበረሰብ ፍላጎት ሚዛን ማስጠበቅ ከባድ የቤት ስራ ነው፡፡ የአሁኑ የመንግስት ምስረታም እጅግ እንዲዘገይ ካስገደዱት ምክንያቶች አንዱ መሆኑ ይነገርለታል፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 25/2011

መላኩ ኤሮሴ