ከመሸሸጊያ ወደ እውነታ

ተገኝ ብሩ

ወይ አመል! አይጣል ነው ጎበዝ፤ ዞረው ገቡበት አሉ። ያ ገደላ ገደል የዝንጀሮ መክረሚያ የአራዊቱ መፈንጫ ለጉብኝት ሳይሆን ለመደበቂያ ተመለሱበት መባሉ ደነቀን። ከፊሎቹ ሌላ ሆነው ከመነሻቸው ተገኙ። በወጣትነታቸው ከተኙበት ታዝለው ገብተው ታዝለው ወጡ። ቀለማቸው ተቀይሮ፣ መጎናፀፊያቸው ወይቦ፣ መታያቸው ጠልሽቶ እንዳልነበሩ ሆነው ወደ መዳኛቸው ተጓዙ፤ ገርጥተው ወደ ፍትህ መድረክ ቀረቡ።

አይጣል ነው ወዳጄ ወደነበሩበት በውርደት መመለስ፤ ወደ ተነሱበት በግዳጅ መዳረስ ህመም ይፈጥራል። እራስን ወደ መቀመቅ መዶል ፈቅዶ አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ ከባድ ነው ። ወዳጄ ክፉ ተግባርህ ይከተልሀል፤ እኩይ ምግባርህ ያድንሀል። ስትነሳ መልካምን ካላቀድክ ወደመነሻህ ይወስድሀል። ውሳኔህ ፍትህ ከሌለው ዓላማህ በጎ ካልሆነ እመነኝ የቱንም ያህል አዛዥ ናዛዥ ብትሆን ጊዜ ወደ ጅምርህ ይመልስሃል።

ጅምር ላይ እዚያው ነበሩ፤ ቆይተው መቀሌ ሰንብተው አዲስ አበባ ገቡ። አገር በግራ መጋባት ውስጥ የነበረችበት ጊዜ ነበረና ይበልጡን ግራ አጋብተው ከፊት ቁጭ አሉ። ለዓመታት ባሻቸው መንገድ አገርና ህዝብ ላይ ግፍ ሲፈፅሙ ከዚህች ደሀ አገር ጉድለት ላይ ነጥቀው ኪሳቸው ሲሞሉ ቆዩ። ሰላሳ ሊሞላ በጣት የሚቆጠር እድሜ ሲቀራቸው ግን እውነት ተገለጠ። ህዝብ እንቢኝ መንገዳችሁን ስታችኋል ሲል እንደገና ወደ መቀሌ ተሰባስበው ከተሙ። ውለው አድረው የማይሞከር ሞክረው የማይታለም ክፉ ህልም አለሙና ወደ መነሻቸው ከተቱ።

ምን ዋጋ አለው፤ መነሻቸው እንደ ቀድሞ ሳይደላቸው እንደ መጀመሪያው መንደርደሪያቸው ሳይሆን ማብቂያ የውርደት ማቅ መልበሻ መድረካቸው ሆነ። ያኔ የገቡበት ገደል ዛሬ ግፍ ስለሰሩ አላስተናግድ አለ፤ ያኔ ቁጭ ብለው ያሴሩበት ጫካ ግፋቸው በተግባር ሲገለጥለት ለቀናት እንጂ እንዳሰቡት ለቆይታ አልሆነላቸውም።

ወዳጄ አመልህን ግራው፤ ያልተገራ አመል ክፉ ነው፤ ከከፍታህ ዝቅ አድርጎ ከመንበርህ ቁልቁል ይከሰክስሃል። እንደው የነበረህን ነስቶ የሆንከውን ለውጦ ከላይ ወደ ታች የሚያንሸራትት የዝቅታን መዳረሻ የሚያስጎበኝ ቅብጠት ምንኛ ክፉ ነው ጎበዝ።

እርግጥ ገጠመኙ በጥሩነት አይነሳም። አሳስተውት እሳቱን የሞቀ አደናብረውት አብሯቸው የተወቀጠ ብዙ ነውና ስለዚያ ገጠመኝ ስለዚያ ሁነት ሲነሳ ብዙው ደስ አይልም። ግን ደግሞ ለትውልድ ታላቅ ማሳያ ትምህርት ነው። እጅግ በአጭር ጊዜ የሆነ ለዘመናት ትምህርት ለዕድሜ ዘመን መመከር የሚሆን እውነት ነው።

ደግሜ ላስታውስህ ባሻዬ ሰዎቹ መነሻቸው እዚያ ነበር። አሁን መልሰው የከተሙበት። ሰዎች ለኑሮ የማይመርጡት የአውሬ መኖሪያ፤ ያ የዝንጀሮ መጠሊያና የአራዊት መፈንጫ ጫካ፤ ገዳላ ገደል ስፍራ።

ዛሬ የሚታደኑበት እግሬ አውጪኝ ብለው የፈረጠጡበት፣ የሰሩት ሴራና ያደረሱት በደል በዝቶ ማስነው የገቡበት። ወደ መነሻቸው ነው ያመሩት። ችግሩ ትላንት ዛሬ አይደለምና ወጥተው የሚነግሱበት ሳይሆን ወደ መቀመቅ ከመውረዳቸው በፊት የመጨረሻ መቆያቸው ሆኗል።

እርግጥ ነው፤ የተነሱበት ዓላማ ስውር፣ ርቀው ሊጓዙበት ያሰቡት መዳረሻ እኩይ ቢሆንም፣ ዓላማዬ ብለው እዚያ ተጠለሉ። መልካም ያልሆነን ምኞት ለማሳካት በጎ ያልሆነን ተግባር እውን ለማድረግ ብዙ አሰቡ። የወቅቱ አንድ እውነት ደገፋቸው። አገሪቱ መልካም መሪ ያልታደለች ምቹ አስተዳዳሪ የተነሳችበት የእርስ በርስ ግጭትና ፍጅት የበዛበት ነበርና ለእነሱ ዓላማ ማሳኪያ ምቹ ሆነ።

ያኔ ጊዜው የእነሱ ነበረና እንዳሻቸው ሆኑ። አራት ኪሎ ላይ ሆነው ወደ ምስራቅ ደውለው ምቹ መንፈላሰሻ ያለ ጥያቄ ይግባልኝ አሉ። ወደ ምዕራብ ደውለው መሄጃዬን አደላድሉልኝ ሲሄድ እንዲመቸኝ የሚል ማስጠንቀቂያ አስተላለፉ፣ ወደ ሰሜን ደውለው ከኔ የሆነን ከስሬ ሹሙልኝ አልሰማ ያለውን መቀመቅ ወርውረው የሚል ትዕዛዝ ሰጡ፣ ወደ ደቡብ ደውለው እኔ እንዳሻኝ ካልሆንኩ ዋ!ልህ አሉ። ያኔ ያሻቸውን በሻቸው መልክ ሾመው ያልተመቻቸውን ሻሩ። ተንፈለሰው በምቾት ቀበጡ።

የህዝብ መበደልን ከቁብ አልቆጠሩም፤ የአገር መጎዳት ግድም አልሰጣቸው አለ። ብቻ የሚፈልጉትን አደረጉ። ቀድመው ያለሙት ትክክለኛነት የራቀው ይህቺን አገር ከመሰረቱ የሚለውጥ አልነበረም። አገርና ህዝብ ከመለወጥ ይልቅ ራሳቸውን መለወጥ ያገኙትን ሁሉ በሴራ በዘረጉት መረብ ማጋበስ እንዴት ኧረ ነውር ነው ያለውን ማሸማቀቅና ማግለል ተያያዙት። በምቾት ፍራሻቸው ላይ ተንጋለው ሙቅን አኘኩ፤ በውስኪ ተራጩ።

ዘዴ እየፈለጉ ሌላውን ዝቅ አድርገው ራሳቸውን ከፍ ማድረግ ላይ አዘወተሩ። ሲነሱ ማሳካት ያሰቡት መልካም አልነበረምና ውጤቱ ክፉ ሆነ። ዛሬ መንፈላሰሻ መኪናው እዚያ የለም፣፡ ማዘዣ ስልኩ ፈፅሞ አይሰራም፣ አንዳንዴ ለብሰው የማይደግሙት ልብሳቸው ማስቀመጫ ቁም ሳጥን የለም፤ ሙቅ ቀዝቃዛ የሚሉት መፅዳጃና ማፅጃ ከእነሱ ርቋል። መነሻ ሆኗቸው የተጠለሉበት የግፈኞቹ መሸሸጊያ ስርቻ ዛሬ ላንዳንዱ መቃብር ለሌላው መታደኛ ሆነ።

በዘመናቸው አገር ባይበድሉ በተሰጣቸው እድል ተጠቅመው ህዝብን ቢያገለግሉ መገኛቸው ዛሬ የት ይሆን ነበር። ግና የሰሩት ስራ ሳይሆን ሴራ ነበር፤ መልካም ሳይሆን እኩይ ነበርና ወደ ታች መውረድ ዕጣ ፋንታቸው ሆነ። የሰው ልጅ በብዙ መልኩ ራስ ወዳድ ነው። የተሻለ ነገር ወደራሱ እንዲቀርብ ይመኛል። ነገር ግን የተለየ ምኞት የስካር ነው። ከትክክለኛነት የራቀ ስግብግብነት።

ተው ይሄ አይበጅም፤ መንገዳችሁ አያዘልቅም ቢባሉ ያኔ አልሰማ አሉ። ዛሬ መስማትም ማሰማትም ወደማይችሉበት ወረዱ። ያኔ ሰው አትበደሉ ሀገር አታውድሙ ተብለው ነበር፤ አንሰማም ብለው ያሻቸውን አደረጉ። ዛሬ ጊዜ ተላልፏቸዋልና አገርና ህዝብ ያሻውን ህጋዊ እርምጃ የሚወስድባቸው ጊዜ ሆነ።

ለሁሉ መፍትሄ የሚሆነውን ሰላም ጠልቶ ፉከራ ማብዛት፣ ህብረትን ሸሽቶ ብቻዬን ማለት፣ ፍቅር ንቆ ጠብ መምረጥ ወደ ብቸኝነት የሚያዳርስ አስተማማኝ ትኬት ነውና። ቀድመው አንድ ላይ ሆነው በአንድ ቦታ የጀመሩት ሰርጥ ዛሬ ተነጣጥለው ከተሙበት፤ ውለው አደሩበት።

አዎን እውነት ተገልጦ የእነሱ ሀሰት ተረጋግቷል። የእነሱ ጊዜ አብቅቶ የተበዳዮች ቀን እውን ሆኗል። የራሴ ባሉት በአገር ላይ ማድረግ ቀርቶ ማሰብ የሚከብድ ደባ፣ በህዝብ ላይ ሊነገር የሚከብድ በደልና ሰቆቃ የፈፀሙና ያስፈፀሙ መነሻ ሰርጣቸው ገብተው ቢወሸቁም፣ እውነት ተገልጦ ህግ ፊት እየቀረቡ ነው፤ ሲቀጥፉት የነበረው ሀሰት የእውነት ቅጣት ውስጥ አስገኝቷቸዋል።

ወዳጄ ይህን ብሂል አትዘንጋ! ብልጥ በሌሎች ስህተት ይማራል የሚለውን። መልካም ተግባር ሲመሽ ምቹ ማደሪያህ ይሆናል፤ ስለመልካም ተግባር ተባበር መልካምነት ላይ አዘውትር። ለበጎነት ሁሌም ትጋ፤ መልካም የሆነው ነገር ወዳንተ ይቀርባል። ቸር ይግጠመን።

አዲስ ዘመን ጥር 04/2013

Ad Widget

Recommended For You