በለውጡ ጉዞ ለተነሱ ጥያቄዎች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ

20

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመቅረብ በለውጡ ሂደት ዙሪያ ባለፉት 300 ቀናት ስለተከናወኑት አበይት ተግባራት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተነሱት ጥያቄዎች ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ በርእሰ ጉዳይ በመከፋፈል እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

ፓርቲዎችና ሀገራዊ ሰላም
ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ንግግሬን ሳደርግ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገንባት ስርዓቱን ለማሳደግ ዋነኛው ምሰሶ መንግሥት ስለሆነ መንግሥት አርቆ አሳቢና ሆደ ሰፊ መሆን ካልቻለ ዴሞክራሲን መገንባት ያስቸግራል የሚል ንግግሬን ታስታውሳላችሁ፡፡ ይህ ማለት አገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ውልደት ምጥ ማሳጠር ብቻ ሳይሆን ተንከባክባ ማሳደግ የምትፈልግ ከሆነ እድገቱ የሚረጋገጠው ዋነኛውን ጨዋታ መንግሥት የሚጫወተው ሆደ ሰፊ በመሆን እንደ አንድ ጀማሪ ዴሞክራሲ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከሃይል በመለስ በንግግር ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት ወሳኝ በመሆኑ ነው፡፡

የቀረበው የሰላም ጥሪ የሰላም መርህን የተከተለ ነው፡፡ ሌላ ምንም መርህ የለውም፡፡ መንግሥት 20 ከሚጠጉ ፓርቲዎች ጋር በተለያየ አገርና ቦታ ድርድር ሲያደርግ የመደራደሪያ መርሁ አንድ ነው፡፡ ከአንድ ፓርቲ ጋር የሚደራደርበትን መርህ ከሌላ ፓርቲ ጋር የሚቀይር ከሆነ መንግሥት መሆን አይችልም፡፡ መንግሥትን መንግሥት የሚያደርገው ከየትኛውም ሃይል ጋር በተናጠል የሚያደርጋቸው ድርድሮችና ንግግሮች መርህን መሰረት አድርጎ የሚነጋገር ከሆነ ነው፡፡ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀረበላቸው የሰላም ጥሪ እናንተ የምታውቁት በእኔና በብርሃኑ አስመስዬ እዚሁ ምክር ቤት የገለጽኩት ውጊያ አያስፈልገንም በሰላማዊ መንገድ እንታገል እኔ ገድዬ እናንተ ገድላችሁ የሚለው ፋሽን ጊዜው አልፎበታል፤ 50 ዓመት ሙሉ ተታኩሰናል፡፡ የዛሬ 50 ዓመት የነበረው የመሬት፣ የማንነት ጥያቄ ዛሬም አለ በበቂ ደረጃ ጥያቄ መመለስ ስንችል መዋጋት የለብንም፡፡ ጥያቄዎቻችን ምላሽ እንዲያገኙ አፈ ሙዛችንን ወደ መሬት ማድረግ አለብን፡፡ መሳሪያዎቻችን ድምጻቸው መሰማት የለበትም፡፡ ነገር ግን ብዕሮቻችን፣ ጭንቅላቶችን ሰርተው በሀሳብ ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠር የሚገባውን ዴሞክራሲ እንፍጠር የሚል ድርድር፣ ንግግር ነው የነበረው፡፡ ከዚህ ውጭ ንግግር የለም፡፡

አንዳንዶች ጥያቄ ያነሳሉ ፊርማው፣ ንግግሩ፣ ድርድሩ የታለ ይላሉ፡፡ ከመጡ በኋላ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገነባውን ዴሞክራሲ ለመገንባት ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡ አቅማቸው በፈቀደ መጠን በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት እየሰሩ ነው፡፡ ያውም የቢሮ፣ የትራንስፖርት ችግር እያለባቸው ቢሆን ዴሞክራሲውን መገንባት ወሳኝ ነው ብለው የሚሰሩ አሉ፡፡ ያንን የማያደርጉ ጉራማይሌ የፖለቲካ ስልት የሚከተሉም አሉ፡፡ አንድ እግራቸውን አዲስ አበባ አንድ እግራቸውን ውጭ አስቀምጠው በሁለቱም መንገድ መጫወት የሚያስቡ ሃይሎች አሉ፡፡ ለእነርሱ ትናንትና ዛሬም የምንናገረው ይህ ፋሽን ለድል አያበቃም የሚል ነው፡፡

ማንም ማንንም ወግቶ የበላይነት፣ስልጣን ወይም ኃላፊነት መያዝ አይችልም፡፡ መዋጋት ለሁላችንም እኩል የተሰጠን ብቃት ነው፡፡ አንዳንዶቹ የሚችሉት ሌሎቻችን የማንችለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ዘመናችንን ሙሉ ስንዋጋ ስለነበረ ነው፡፡ የተለየ ብቃት ስላለኝ ተዋግቼ አሸንፋለሁ ማለት ሳይሆን የተሻለ ብቃት ስላለኝ በሃሳብ አሸንፌ እመረጣለሁ ነው መባል ያለበት፡፡ ይህ የጉራማይሌ አቀራረብ ዴሞክራሲ ወደ ኋላ ይመልሳል ጸረ ዴሞክራሲ ልምምድንም መልሶ ያመጣል፡፡ መቆም አለበት፡፡ እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ከችግሩ ማትረፍ የሚያስቡ ሃይሎችም አሉ፡፡ የሆነ ቦታ ችግር እየፈጠሩ ከችግሩ ትርፍ የሚያስቡ ሃይሎች በተቻላቸው መጠን ችግር ለመፍጠር፣ ለማባባስ ከፍተኛ ሙከራ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ ዓመታት የጮሁት የጠየቁት ጉዳይ ወደ ኋላ እንዲመለስ የሚያደርግ ስለሆነ ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

ሌላው ምክር ቤቱ እንዲያስበው የምፈልገው ጉዳይ አሁን የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቷል፡፡ ይህ ማለት ረጅም ርቀት መጓዝ የማይችሉ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ትንፋሽ ያጥራቸዋል ማለት ነው፡፡ ጋዜጠኛ አስረህብኛል፣ አባል አስረህብኛል፣ እንዳልጽፍ አድርገህኛል፡፡ በሚል የፖለቲካ ጉዳይ አድርገህ ትከራከራለህ፡፡ በመንግሥት ድርጊት ላይ መሰረት አድርገህ ተቃዋሚ መሆን ትችላለህ፡፡ አሁን አይቻልም፡፡ አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረባት አገር ናት፡፡ በዚህ ጉዳይ መከራከር አይቻልም፡፡ የሚቻለው ማሰብ ብቻ ነው፡፡ የተሻለ ሃሳብ አምጥቶ፣ ህዝብን አስተባብሮ አንድ አድርጎ ኢትዮጵያ ካለችበት ድህነት ማውጣት፣ ሰላሟንና ሉዐላዊ አንድነቷን ማረጋገጥ የሚያስችል ሃሳብ ማፍለቅ ነው፡፡ ይህ ከባድ ነገር ነው፡፡ ጠባብ ሲሆን በመቶ ሜትር ውስጥ ሩጫ የለመዱ ፓርቲዎች በኪሎ ሜትር ረዝሞ ማራቶን ሲሆን ትንፋሽ ያጥራቸዋል፡፡ ይህ መጠበቅ አለበት፡፡ እንዲህ አይነት ልምምድ ያላቸው ፓርቲዎች ያላቸው ምርጫ ቶሎ ብሎ ሃሳብ ወዳላቸው መጠጋት ነው፡፡

በክስ መንግስትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማረጋገጥ አትሰራም ብሎ ተቃዋሚ መሆን የሚቻልበት ደረጃ አይደለም፡፡ የሰላም ንግግራችን ዋነኛ መነሻ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ አንድነትና ብልጽግና ብለን ነው ከፍተኛ ትዕግስት ያሳየነው፡፡ ሰላማችንም አንድነታችንን የሚያደናቅፍ ነገር ደግሞ ሲሆን የትዕግስታችንን ያክል የመረረ እርምጃ እንደምንወስድ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ሉዐላዊ ግዛት ከማንም ጋር አንደራደርም፡፡ የኢትዮጵያን ሉዐላዊ ግዛት፣ ሰላሟን፣ልማቷን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ጉዳይ ሲፈጠር ህግን ተንተርሰን የማያዳግም ርምጃ እንወስዳለን፡፡ ያንን ለመውሰድ ነው ይህ ምክር ቤት የተሟላ ሃይል የመጠቀም ስልጣን ለመንግሥት የሰጠው፡፡ ለመንግሥት ሃይል የመጠቀም ስልጣን የተሰጠው ምን ምን ጉዳይ ሲያጋጥም እንደሆነ በህገ መንግሥት ተቀምጧል፡፡ እነዛ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ከማንም ጋር ድርድር አይደረግም፡፡ ይህ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡

ልክ ለሰላም ኑ በሰላማዊ መንገድ እንታገል፣ ያንን እንዳታደርጉ የሚያደርጓችሁን አዋጆች አሰራሮች ባህሪዎችና አሰራሮች በእኛ በኩል እናስተካክላለን ብለን እንደጠራን ሁሉ የኢትዮጵያን አንድነት የሚገዳደር ጉዳይ የሚሰራ ማንኛውም ሃይል በቀጥታ ጦርነት አውጆብናል ማለት ነው፡፡ መንግሥት ራሱ የመከላከል ርምጃ ይወስዳል፡፡ በዚህ ጉዳይ ድርድር እንደሚኖር የሚያስብ ሃይል ካለ ደጋግሞ ማሰብ ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ሰላም፣ ዴሞክራሲና አንድነት ጉዳይ የዚችን አገር ነጻነትና ሉዐላዊነት ለመጠበቅ ለሚደረግ ፍልሚያ ጠቅላይ ሚኒስትር የፓርላማ አባል መሆን አይስፈልግም፡፡

ከዚህም ውጭ ቢሆን በነዚህ መሰረታዊ ጉዳይ ለሚገጥመን ችግር በህይወት መስዋዕትነት መፋለምና የአገር አንድነት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ማረጋገጥ የሁላችን ኃላፊነት ይሆናል፡፡ በዚህ ጉዳይ የሚደረግ ምንም አይነት ሆደ ሰፊነት እንደማይኖር ፓርቲዎች፣ግለሰቦችና ቡድኖች በደንብ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን የማይወቀስ፣ የማይከሰስ፣ የማይተች መንግሥት ነው ማለት አይደለም፡፡ ማንም ግለሰብ በንግግር፣ በጽሁፍና በፈለገው መንገድ መንግሥትን መተቸት ይችላል፡፡ በርግጥ አሁን ባለው ዴሞክራሲ ከትችት አልፎ በግለሰብ ደረጃ የሚሳደቡ አሉ፡፡ የሚሳደቡትን ጭምር ወደ ህግ የማናቀርብበት ምክንያት ህግ ስለሌለ ሳይሆን የዴሞክራሲ ምህዳሩ መስፋት ጅማሮ አንድ ተግዳሮት ተደርጎ ስለሚወሰድ ነው፡፡ መንግሥትን መተቸት ይውረድ፣ አይሰራም፣ አይችልምና ሌላም ሌላም ብሎ መተቸት የሚቻል ሲሆን ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተን መሆን የለበትም፡፡ ወደእዛ ሲሄድ ነገር መልኩን እንደሚቀይር ሁሉም መገንዘብ ይኖርበታል፡፡

ለፓርቲዎች ያለኝ ምክር ጊዜ የላቸውም፡፡ እንግዶች ናቸው፡፡ ከወጡ በጣም በርካታ ዓመታት ቆይተዋል፡፡ የህዝቡ ባህል፣ የኢኮኖሚ ሁኔታና
አስተሳሰብ ተለውጧል፡፡ ቶሎ ህዝብ ጋር መተዋወቅና መለማመድ ያስፈልጋል፡፡ ቶሎ መደራጀት ያስፈልጋል፡፡ በህገ መንግስቱ መሰረትም እያንዳንዱ ድርጅት ጉባኤ አካሂዶ ሃላፊዎች፣ ሊቀመንበሮችና ሥራ አስፈጻሚዎች መምረጥ ይጠበቅበታል፡፡ መመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን ካላደረገ ምርጫ መወዳደር አይችልም፡፡

አንድ ፓርቲ በራሱ ድርጅት ውስጥ ጉባኤ አካሂዶ በዴሞክራሲያዊ መንገድ አመራር የማይመርጥ ከሆነ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመወዳደር ጥያቄ ማቅረብ አይችልም፡፡ በራሱ ፓርቲ ያልተለማመደውን ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ላይ መለማመድ አይችልም፡፡ የመጀመሪያው አሰራር እያንዳንዱ ፓርቲ በዴሞክራሲ አግባብ መሰረት ጉባዔውን የምርጫ ቦርድ፣ ታዛቢዎች አስቀምጦ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አመራረሮች መርጦ ህግዊ ስም፣ ዓርማና አመራሮችን ይዞ ምርጫ ቦርድ መመዝገብ ቀዳሚ ተግባር ነው፡፡

በሀዋሳው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ ታዛቢዎች ከዳያስፖራም ከጋዜጠኞችም የመጡ ሰዎች ሙሉ ጉባኤውን ተከታትለውታል፡፡ ኢህአዴግ በውስጡ ምን አይነት አሰራር ተከትሎ ያለፉትን እንደሚገመግም፣ ለሚቀጥለው አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥና ኃላፊዎችን እንደሚመርጥ በግልጽ አሳይተናል፡፡ ልክ በእዛ መንገድ እያንዳንዱ ፖለቲካ ፓርቲ ታዛቢዎች ባሉበት ጉባኤውን አካሂዶ ምርጫ ማካሄድ ይጠበቅበታል፡፡ እርሱ የኢትዮጵያ ህዝብ ብመርጠው ዴሞክራሲ ሆኖ ያገለግለኛል ወይም አያገለግለኝም የሚለውን እንደ ትንሽ ማሳያ ይወሰዳል፡፡ ይህንን ሳናደርግ ቆይተን ጊዜው ሲደርስ የጸብና የግጭት እንዳይሆን ፓርቲዎች ጊዜ የለንም ብላችሁ በፍጥነት ራሳችሁን ማደራጀት፣ ጉባኤ ማካሄድና ወደ ህግ መሄድ አለባችሁ፡፡ ከዛ ውጭ ላለው ጉዳይ ጊዜ ባታባክኑ የሚል መልስ አለኝ፡፡ የትኛውም ጫፍ የደረሰ ሃሳብ እዚህ ምክር ቤት እዚህና እዚያ ጫፍ ሆኖ ቢደመጥ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

የመከላከያ ሰራዊት
ይህ ምክር ቤት በደንብ እንደሚያውቀው የመከላከያ ሰራዊት በሰፈር ውስጥ አንድ ሌባ ቦርሳ ይዞ ሲሮጥ ለምን ቦርሳ አላስጣልክም ተብሎ የሚጠየቅ አይደለም፡፡ ስራው አይደለም፡፡ በህገ መንግሥት ለመከላከያ ሰራዊት የተሰጠው ስልጣን የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት ስልጣን ሊዳፈር የሚመጣ ሃይል ካለ መከላከል ወይም አለመከላከል ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን ለመውረር ለመድፈር ሞክሮ መከላከያው ሰንፎ ያሳለፈበት ጊዜ የለም፡፡ ከሱ የሚፈለገው ተግባር ይህ ነው፡፡

ሁለተኛው የክልሎችን ሰላም ማረጋገጥ ሌላው ተግባሩ ነው፡፡ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ጉዳት ሲቸገሩ ካቅማችን በላይ የሆነ ነገር ገጥሞናልና የፌዴራል የጸጥታ ሃይል ያግዘን ሲሉ ይገባል፡፡ በለፉት ወራት በሁሉም ክልሎች ጥያቄ ሲቀርብለት መከላከያ ገብቶ የህይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍሎ ማረጋጋት ችሏል፡፡ በወለጋ፣ በቦረናና በተለያዩ ስፍራዎች የሆነው ይህ ነው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ መከላከያን የሚያክል ተቋም በአንድ ዓመት ውስጥ አጠቃላይ ሪፎርሙን ጨርሶ የሚወለድ ተቋም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ተቋማት ግን በቀደም የ100 ቀናት ግምገማ ስናደርግ ያየነው ምርጥ ስራ ከሰሩ መካከል አንዱ መከላከያ ነው፡፡ በተዋጽኦ፣ በአሰራር፣ በአደረጃጀት በብዙ መልኩ ለውጥ አምጥቷል፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ በተሰጠው ተልዕኮም ህይወቱን እየገበረ የእዚህችን አገር ሰላም ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል፡፡

በየቀበሌው በየወረዳው የሚፈጠረው የሰላም ችግር በቀጥታ ከአገር መከላከያና ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ ክልሎች ይህንን ማድረግ ኃላፊነታቸው ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ እንደሚታወቀው የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ ያደርጋል፡፡
በተለይ በዚህ ዓመት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ የበጀት ድጎማ ተደርጎላቸዋል፡፡ ወለጋ ውስጥ የክልሉ መንግሥት ሰላም ለማረጋገጥ ጥረት ባደረገባቸው ጊዜያት ውስጥ መከላከያ ምንም አይነት ሥራ አልሰራም፡፡ የክልሉ መንግሥት በነዚህ ወረዳዎችና ዞኖች ከአቅም በላይ ሆኖብኛል ሲል መከላከያ ሰራዊት ምዕራብ ወለጋን ሙሉ ለሙሉ ነጻ አድርጎ የመንግሥት እንቅስቃሴዎች እንዲካሄዱ ለማድረግ ሁለት ወር አልፈጀበትም፡፡ ለዚህ ሊመሰገን፣ ሊከበር እንጂ ሊወቀስ አይገባውም፡፡

የለውጥ ጉዞአችን ማዳን እንጂ ማድከም አይደለም፡፡ ለማዳን መርፌ በሚያስፈልግበት ጊዜ መርፌ፣ ታብሌት በሚያሰፈልግበት ጊዜ ታብሌት፣ ማረፍ በሚያስፈልግበት ጊዜ ማረፍ ያስፈልጋል፡፡ ማዳን የጀመርነውን መድኃኒት መሃል ላይ ማቋረጥም በሽታ እንደሚያገረሽ ሁሉ ሃኪም ቤት ስለሄድን፣ መድሃኒት ስለጀመርን ፈውስ አይገኝም የተሟላ መዳን እንዲረጋገጥ ሃኪም የሚያዝዘውን ጊዜውን፣ ሰዓቱንና ህጉን ጠብቆ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በሁሉም የፖለቲካ እሳቤ ውስጥ የሚሳተፉ ሃይሎች የሚያስፈልገን እውነትና የሃሳብ ልዕልና ነው፡፡ ሻጥር አሁን አንፈልገውም፡፡ የዛሬ 30ና 40 ዓመታት የነበረው የፖለቲካ ስርዓት የከሰረ ሃሳብ ነው፡፡ እንደከሰረ ተቀብሮ መቅረት አለበት፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሰላምና እውነት ነው፡፡ የሃሳብ ልዕልና ነው፡፡ በሃሳብ ንግግር በእውነት ላይ መሰረት የሆነ ነገር መፍጠር ነው፡፡ ያንን ማድረግ ካልቻልን ጠንካራ ዴሞክራሲ መገንባት አንችልም፡፡

የታችኛው መዋቅር
የፌዴራል መንግሥት፣ አስፈጻሚው አካል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የካቢኔ አባላትን ካልያዘ በስተቀር ለውጥ ሊመራ አይችልም፡፡ ከህግ አውጭው የፖርላማ አባላትን ሙሉ የቁጥጥርና የክትትል ድጋፍ ካላገኘ በስተቀር ሃሳቦቹን ሊያሳካ አይችልም፡፡ ሃሳብ ግለሰቦች ያመነጫሉ እንጂ ለውጥ የሚመራው በተቋም ነው፡፡ ላይ ተቀይሯል ታች አልተቀየረም፤ የሚባል ነገር በድምሩ አልተቀየረም የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ ለብቻ የሚመራ ለውጥ የለም፡፡ በየደረጃ ያለ ኃላፊ እያንዳንዱ ዜጋ በርብርብ በሚደረግ ለውጥ ብቻ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት የሚያስችለው፡፡

ሰዎች ሳይመቻቸው ሲቀር ቀጥታ እየሄዱ አልሰራህም፣ ለለውጡ አጋዥ አይደለህም፣ አልተደመርክም፣ ውጣ ብለው ከቢሮ ከጎተቱ ለውጥ እያደናቀፉ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ሰው የሚጠበቀው እነዚህን ሰዎች መደገፍና ማገዝ ነው፡፡ እንጂ ህገ ወጥ ናቸው ብሎ ያመናቸውን የሥራ ኃላፊዎች በህገ ወጥ መንገድ ከቢሮ አንጠልጥሎ ካወጣ በህገ ወጥ መንገድ ህጋዊነትን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ይህ ማለት በየደረጃው ያለው አመራር እንከን አልባ ነው እርማት አያስፈልገውም ማለት አይደለም፡፡ ችግሮች ባሉበት እርማት በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ተነጋግሮ ችግሩን ማስተካከል ይቻላል፡፡ ህዝቡ የታችኛውን የመንግሥት እርከን በማገዝና በመደገፍ ካቅም በላይ ሲሆን ደግሞ ህግን ተከትሎ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ህዝቡ በዚህ ልክ ካልደገፈን በስተቀረ የታችኛውን እርከን አጠናክሮ መምራት ያስቸግራል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋም
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን እንደ ጦር ቤዝ የመጠቀም ዝንባሌ በዚህ ዓመት ሊያጋጥም እንደሚችል ተማሪዎች ከመግባታቸው ከአንድ ወር በፊት እናውቅ ነበር፡፡ የክልል፣ የዩኒቨርሲቲና የቦርድ ሰብሳቢዎች ባሉበት ውይይት ተካሂዷል፡፡ ተማሪዎች ሲገቡ እንዲህ አይነት እቅድ ስላለ ከወዲሁ ዝግጅት መደረግ አለበት፡፡ የአገር ሽማግሌዎችና ህዝቡ ውይይት ማድረግ አለበት ባልተገባ ሁኔታ የወጣቶች ህይወት መቀጠፍ የለበትም ብለን ውይይት አካሂደናል፡፡ በዚህ ሳናበቃ ተማሪዎች ሊገቡ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው ለሁሉም በሚዲያ መልዕክት አስተላልፈናል፡፡ ይህ ሁሉ ተሰርቶም አስተሳሰቡንና ሙከራውን የሚገዛ የሚያስተናግድ ሃይል አልጠፋም፡፡

ተማሪዎች የፖለቲካ ነጋዴዎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ማስተዋል መጠንቀቅ በመጀመሪያ የእነርሱ ሥራ ይሆናል፡፡ ቀጥሎ ተማሪዎችን እሳት አስጨብጦ ለፖለቲካ አላማ የሚማግድ ጨካኝ የፖለቲካ ሃይል ያለው በተጨባጭ ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የፖለቲካ አጀንዳውን ዩኒቨርሲቲ አስገብቶ ሰውና ሰው የሚያጋድለው እንጂ ኬንያ፣ደቡብ ሱዳን፣ አሜሪካ ደቡብ ሱዳን የለም፡፡ ተማሪዎች ተደራጅተው መንግሥትን የሚቃረኑበት ጊዜ አለ፡፡ ለፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ህይወታቸውን የመገበር ዝንባሌ ግን በዓለም ላይ ያለው አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡

ተማሪ በማንኛውም ጉዳይ አንድ የውሸት መረጃ ሲያገኝ ሲጨቃጨቅ ቢወያይ ችግር የለውም፡፡ መረጃውን ሳያጣራ የራሱንን ህይወት ገብሮ የጓደኛውን ህይወት ዋጋ አስከፍሎ ፖለቲካ ባልሰለጠነ መንገድ የሚያካሂድ ዓለም አሁን ብዙ የለም፡፡ ይህ አሳዛኝ ነው እናቶች ወገባቸውን አጉብጠው አሳድገው ለወግ ማዕረግ በቃልኝ ሲሉ አስከሬን መቀበል እጅግ አሳዛኝና የሰው ሞራል የሚሰብር ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ እንዲቀየር ወላጆች፣ መምህራን፣ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ተማሪዎች ሁሉ በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሃሳብ ልዩነት መፍጠር፣ መከራከር ችግር የለውም፡፡ በጣም መጥፎው ነገር በቡድን ሆኖ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ማጥቃት አስነዋሪ ነው፡፡

ከተማሪዎች የሚጠበቀው ሃሳብና ሃሳብ አጋጭተው የተሻለ ሃሳብ ማፍለቅ ነው፡፡ ድንጋይና ድንጋይ አጋጭቶ የጋርዮሽ ዘመን እሳት ማውጣት ዘዴ በክብሪት ተተክቶ አይተናል፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ሃሳብና ሃሳብ በማጋጨት የተሻለ ሃሳብ የሚያመጣ ተማሪ ነው፡፡ እንደ ድሮ ድንጋይና ድንጋይ የሚያጋጭ ከሆነ መማር አያስፈልግም፡፡ ተማሪዎች ጊዜያቸውን ባያባክኑ ጥሩ ነው፡፡ እነ ኢብሳ ጉተማ ንጉሱ ፊት ቀርበው ኢትዮጵያዊ ማነው ያሉት፣ እነ ዋለልኝ ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰብ እስር ቤት ናት በማለት አዲስ ትርክት ያመጡት፣ የጻፉትና የተከራከሩት ተማሪዎች ናቸው፡፡

በዛ ጊዜ የነበራቸው ሃሳብ መንግሥታት አልነበራቸውም፡፡ ዛሬ ደግሞ መንግሥታት ያልደረሱበትን አዳዲስ ሃሳብ እያመጡ መከራከር ከሁሉም ይጠበቃል፡፡ ድንጋይ ተወራውሮ መጋደል ግን አሳፋሪ ስለሆነ ሁላችንም ከዚህ ጉዳይ መጠበቅ ይኖርብናል። በዚህ በኩል በትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆን ክልሎችን በሚመለከትም ተመሳሳይ ችግር አለ። በተለይ ታዳጊ የሚባሉ ክልሎች አካባቢ በደንብ አልተደራጁም በሚል እሳቤ የመረበሽ ፍላጎት እንደነበር ቀድመን ስለደረስንበት በሁሉም ታዳጊ ክልሎች ሰፋፊ ስራ ስንሰራ መቆየታችን ይታወሳል። በመሆኑም ታዳጊ ክልል ሆነው በፖለቲካውም በመንግሥትም ሥራ ያልተሰራበት መስክ አልነበረም። ለምሳሌ የኢህአዴግ ጉባኤ በወሰነው መሰረት ድርጅቱን ወደ አንድ የማምጣት ሥራ እየተሰራ ስለሆነ የታዳጊ ክልል አመራሮች ፖለቲካውን ማወቅ አለባቸው ተብሎ በስራ አስፈጻሚ እንዲሳተፉ በድርጅት ተወስኗል። በመንግሥት ደግሞ ድርጅቶች በለውጥ ውስጥ ገብተው ራሳቸውን ከቀየሩ በኋላ በየደረጃው አመራር የማስተካከል ሥራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።

በሀረር አካባቢ ያሉ ዜጎች ማወቅ ያለባቸው የውህዳንን/ አናሳ መብት ማክበር የመሰልጠን ምልክት መሆኑን ነው፡፡
ይሄንን በሚመለከት በፖሊስ በኩልም በተባለው ደረጃም ባይሆን ከፍተኛ ችግር ነበር በተደረገው ግምገማም የፖሊስ ኃላፊዎች ከሥራ እንዲለቁ ተደርገዋል በህግም እየተጠየቁ የሚገኙ አሉ የማስተካከያም እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል። ነገር ግን ፖሊሶች ባጠቃለይም የታጠቀ ሀይል ካጠለቀው መለዮ በታች የሚያመዛዝን ጭንቅላት ያለው ከቆለፈው ሸሚዝ ስር የሚራራ ልብ ያለው መሆን አለበት። ሳያመዛዝን ሳይራራ እርምጃ የሚወስድ ከሆነ መታጠቁ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ፖሊሶች ባጠቃላይም የታጠቃችሁ ሀይሎች ህግን ለማስከበር ህይወታችሁን እንደምትሰውት ሁሉ ህግ ተጥሶ ደግሞ አላግባብ እናንተንም መጠቀሚያ ለሚያደርጉ ሁኔታዎችንም የመከላከል እኩል ኃላፊነት እንዳለባችሁ መገንዘብ ያስፈልጋል። እንደዚህ ከተደረገ በሂደት ሁሉም ችገር ይፈታል። ለሀረሪም ጉዳይ በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል። ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርና ኮንትሮባንድ
ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርና ኮንትሮባንድን
በሚመለከት ኮንትሮባንድ ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ህጋዊ እስኪመስል ድረስ ሲካሄድ የነበረ ጉዳይ ነው። የተሀድሶው ዋናው መነጋገሪያ ሀሳብም ኮንትሮባንድ ነበር። አሁን አዲስ የሆነው ከተሀድሶው በኋላ ትኩረት ማግኘቱ ነው። ኮንትሮባንድ ካልቆመ የሀገሪቱን ሰላምም ኢኮኖሚም የሚያናጋ በመሆኑ በአደረጃጀትም በአሰራርም ትኩረት ያስፈልገዋል የሚል አቋም ተወስዶ እርምጃ መወሰዱ ብቻ ነው አዲሱ ነገር። ከዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከህዝብ ብዛታቸው በላይ መሳሪያ ከታጠቁ ሀገራት መካከል አንዷ ነበረች። ሰው በመሳሪያ ንግድ ውስጥ የሚሳተፈው ደግሞ በሦስት ምክንያት ነው። አንደኛው እንደማንኛውም ንግድ ነግዶ ለማትረፍ እንደሥራ እየተወሰደ ነው። ሁለተኛው ደግሞ አርሶ አደሩ በገፍ መሳሪያ እየገባ ሰዎች እየታጠቁ ስለሆነ ካልታጠቅኩ ራሴንና ቤተሰቤን መከላከል አልችልም ከሚል እሳቤ ሲሆን እዚህ ላይ በሬውን ሸጦ ከባንክ ተበድሮ መግዛቱ አንዱ ችግር ነው። ሦስተኛው መሳሪያ በማስገባት ችግር መፍጠር የሚያስበው ሀይል ነው።

እነዚህ ሦስት ሀይሎች የተለያየ አላማ ቢኖራቸውም በተግባር እየተጋገዙ ያሉ ናቸው። በዚህ ምክንያት ኮንትሮባንድ በገቢም በወጪም ንግድ የኢትዮጵያን ሰላም እያናጋ ያለ ጉዳይ ነው። ከወጪ ንግድ አንፃር ከብት የቅባት እህል ወርቅ የከበረ ድንጋይ ከዚህ ወጥቶ የጎረቤት ሀገራት እንደራሳቸው ሀገር ምርት አድርገው ወደ ውጪ ይልኩታል። ለነሱ ዶላር ያመጣል ለኛ በምላሹ ከመጋዘን የተረፈ መሳሪያ ግዜው ያለፈበት መድሀኒት ጠንካራ ያልሆነ ልብስ ይልካሉ። ይህንንም ትልቅ ችግር እያመጣ መሆኑን በማወቅ በግምገማ ተቋሙ መጠናከር እንዳለበት በመንግሥት በተወሰነው መሰረት ገቢዎች ባለስልጣን ባለፉት ጥቂት ወራት ከሰባት ሺ በላይ ሠራተኞች በአዲስ መዋቅር በአዲስ ድልድል በማስቀባት ራሱን እያደራጀ ይገኛል። ያደራጀበት ምክንያት ደግሞ ተቋሙ ራሱን አጠናክሮ ካልሰራ የኢትዮጵያ ልማትም ሰላምም አደጋ ውስጥ ይገባል የሚል እምነት ስላለ ነው።

መሳሪያን በተመለከተ ህገ ወጥ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን ህጋዊም ቢሆን አደገኛ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ መሳሪያ የያዘ ሰው ዛሬ ራሴን ልከላከል ቢልም የከፋው ቀን ጎረቤቱን አልያም ባለቤቱ ላይ ሊያዞር ይችላል። በመሆኑም መታጠቅ ብቻ ሳይሆን የሚያስከትለውንም አደጋ መመልከት አስፈላጊ ነው። በገፍ መሳሪያ ሲገባ እርስ በእርስ የሚያባላ በመሆኑ በጋራ መከላከል ያስፈልጋል። ለዚህም የጉምሩክ ቁጥጥርና ፍተሻን ማጠናከር የኮንትሮባንዲስቶችን የፋይናንስ ምንጭ ማድረቅ፣ የጠረፍ ንግድ ስምምነትን ማድረግ፣ በወረቀት ላይ ያለውንም የንግድ ስርዓት ማጠናከር ያስፈልጋል። ከጎረቤት ሀገራት ጋርም ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ለመስራት አሁን የሚታየውን ችግር መፍታት የሚቻልበትን መንገድ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ፖለቲካል ገበያውን መፈተሽና ማስተካከል ይጠይቃል።

የተፈናቃዮች ጉዳይ
ተፈናቃዮችን በሚመለከት ሰው ማፈናቀል ከባህላችንም ከኛነታችንም ያፈነገጠ ኢሞራላዊና ኢ ህገ መንግስታዊ ነው። በእኛ ሀገር ሉአላዊ ክልል የለም ያለው ሉአላዊ ሀገር ነው። ክልል ለአስተዳደር እንዲመች የተሰራ ወሰን እንጂ ሉአላዊ ድንበር አይደለም። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት ቦታ ሄዶ ሰርቶ አግብቶ ንብረት አፍርቶ መኖር ይችላል የሚል እምነት በእያንዳንዱ ዜጋ ካልያዘ በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ጥያቄ አለ ማለት ነው። ድርድሩ የሚደረገው በውጪ ሀገራት መካከል አይደለም። ማንም ሰው በየትኛውም ቦታ የሚመቸው ነገር ካለ የትኛውም ክልል ሄዶ ለመስራት መብት አለው። ይሄም ሆኖ ከለውጡ በኋላ የተፈናቀሉ ሰዎች በጣም በርካታ ቢሆኑም ዘጠና በመቶ ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው። የተወሰኑ ከግጦሽና ከውሃ ጋር በተያያዘ ችግሮች ባሉባቸው ስጋት ያለባቸው አሁንም ያልተመለሱ አሉ፡፡ ለእነዚህም የተለየ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ይገኛል። ሁሉም በፈለገበት ተንቀሳቅሶ እንዲሠራ እንዲኖር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዘብ መቆም አለበት።

ግጭትን ለማስቆም እምቅ የግጭት አቅም ያላቸውን ማምከን እና ዘላቂ ሰላም ማምጣት ያልነውን ፖሊሲ ስንተገብርና ሰው ሰርቶ አምርቶ መብላት ሲጀምር ጉዳዩ እየቀነሰ የሚሄድ ይሆናል። አሁንም የሰላም ሚኒስቴር የሚያስተባብረው ኃይል እየሰራና ውጤትም እየተገኘ ነው። የሀይማኖት አባቶች ምሁራንና የተለያዩ የፖለቲካ መሪዎች በጣም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። በቅርቡ የሚጸድቀው የሰላም ኮሚሽን አባላትም ከሀይማኖት አባቶች ከምሁራን የተውጣጡ ስለሆነ ግዜ ወስደው ኢትዮጵያውያን ከራሳቸውም ከወንድሞቻቸውም ታርቀው በሰላም ለመኖር እንዲችሉ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።

ወንጀለኞችን ለፍርድ የማቅረብ ሂደት
ወንጀለኞችን ለፍርድ በማቅረቡ በኩል በሙስናና በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ታስረው ወደ ህግ የቀረቡ ሰዎችን ወንጀለኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ፍርድ ቤት ቢሆንም ያሉበትን ሁኔታ በሚመለከት የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በማረሚያ ቤቶች ምልከታ አካሂዷል። በዚህም በቤተሰብ እንደሚጠየቁ፣ ማንበብ፣ ስፖርት መስራት በሚችሉበት ሁኔታ መኖራቸው ተረጋግጧል መስተካከል ያለባቸውም እንዲስተካከሉ ተደርጓል። በክልሎች በኩል ሁሉም ክልሎች ወንጀለኞች ተብለው የታሰቡትን ወደ ህግ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። ተጠርጣሪዎችን ይዘው የሰጡ አሉ እየያዙ ያሉም አሉ፡፡ ጠፉብን ብለው የሚፈልጉም አሉ። ነገር ግን ወንጀለኛው በይፋ ሲንቀሳቀስ እያየ ይዞ ያላቀረበ ግለሰብም ይሁን ቡድን የወንጀል ተባባሪ በመሆኑ በህግ የሚጠየቅ ይሆናል። በኢትዮጵያ ገሎም ሰርቆም ተደብቆ መኖር አይቻልም ፍርድ አለ ሁሉም ሰው ከህግ በታች ነው ይሄ መታወቅ አለበት።

በዚህ በኩል ሁሉም ሰው ስልጣን ይፈልጋል ስልጣን ከያዘ በኋላ ግን መወሰን አይፈልግም ከወሰነ በኋላ ደግሞ መጠየቅ አይፈልግም፡፡ ነገር ግን ውሳኔው በህግ አግባብ ካልሆነ ማስጠየቁ አይቀርም። ስልጣን ተይዞ ሲወሰን ስህተት ሊያጋጥም ይችላል፤ ወንጀለኛ ተብሎ ተጠርጥሮ የገባ ሁሉ ግን ወንጀለኛ ነው ማለት አይደለም፡፡ ይሄንን የሚያጣራው የፍትህ ስርዓቱ ነው። ቀድሞ መደምደምም አያስፈልግም። ሁሉም ሰው ከህግ በታች እንደመሆኑ ያን የሚያጣራው ፍርድ ቤት ብቻ ነው። እርምጃው ብሔር ተኮር ይመስላል የሚባለውም ስህተት ነው ሌባ ብሄር ኢትዮጵያ ውስጥ የለም፡፡ እንኳን በብሄር በቤተሰብም ደረጃ የለም። ሌባ ሁሉም ብሄር ሁሉም ሰፈር ሁሉም ፆታ ውስጥ አለ። ሌቦቹ ሲሰርቁም ሲያዙም ብልጥ ናቸው፡፡ ሲሰርቁ ማንንም አያማክሩም ሊያዙ ሲሉ ደግሞ ያንተ ወገን ስለሆንኩ ይላሉ። ይሄ አዲስ ፋሽን አይደለም በየክልሉ እንኳ ቢታይ ከሰረቀ በኋላ የዚህ ዞን ብሎ ራሱን ለመከላከል ሙከራ ይደረጋል።

አሁንም ባለው ሂደት በሜቴክ ጉዳይ ከትግራይ ከአማራ ከኦሮሚያ ከደቡብም ታስሯል ከደህንነቱም እንደዛው ነው። ነገር ግን ጥቃቱ ከአንድ ብሔር ነው የሚመስለው ይሄ ፖለቲካዊ እንድምታ ያለው ነው ብለው ሲናገሩ ደግሞ መደንገጥ የለበትም። ችግር የሚሆነው እየታሰሩ አትጠይቁ አትናገሩ ከተባለ ነው፡ ይሄ ጸረ ዴሞክራሲያዊና የሚፈለገውን የዴሞክራሲ ግንባታም የማያረጋገጥ አይሆንም። ሰው ትክክል ያልመሰለውን ድንጋይ ሳይወረውር ፎቅ ሳይደረምስ መንገድ ሳይዘጋ በሰላም ወጥቶ ተቃውሞ መሄድ መብቱ መሆኑን መታወቅ አለበት።
የተሰራው ሥራ በአንዳንዱ እይታ ልክ ነው በአንዳንዱ ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህም ትክክል አይደለም ያለው በህጋዊ መንገድ ተቃውሞውን ማሰማት ይችላል። እኛም ስንሞገስ የተቀበልነውን ያህል ስንወቀስም መቀበል አለብን። ምርቃቱን ፈልጎ እርግማኑን ሸሽቶ አይቻልም። ድጋፍ ሲደረግ በሩ ክፍት ሆኖ ሰልፉ የሚፈቀድ ከሆነ ተቃውሞ ሲካሄድ ግን የሚከለከል ከሆነ ይሄ ዴሞክራሲ አይደለም። ተቃውሞውን ሁሉም በህግ አግባብ በተሰጠው ቦታ በተፈቀደው ግዜ ማከናወን ይችላል። ካልሆነ እኔ ስቃወም ሰርግ የለም፣ ቀብር የለም፣ ትምህርት የለም ብሎ የሚቃወም ከሆነ ችግሩ እዚህ ላይ ይሆናል። ትናንት ሁሉም ነገር መጥፎ ሁሉም ነገር ጥሩ አልነበረም ወደኋላም ስንመለስ ጥሩ የሰራውን ማሞገስ ጥሩ ያላደረገውን መውቀስ አለብን። ጅምላ ሙገሳም ጅምላ ወቀሳም አይጠቅሙንም። ባለፉት ግዚያት በተሰሩት በርካታ ስራዎች የተሰሩ ስህተቶች ይኖራሉ።

ክልል የመሆን ጥያቄ
ክልል ከመሆን ጋር የሚነሱት ጥያቂዎች ህገ መንግሥታዊ ናቸው፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ ያልተማከለ የስልጣን ክፍፍልን በመፍቀድ ህዝቡ ራሱን እንዲያስተዳደር ውሳኔ አስተላልፏል። በመሆኑም ማንኛችንም ከህገ መንግሥት በላይ ሆነን የዚህ አይነት ጥያቄ አይነሳ ማለት አንችልም። ሁላችንም ከህግና ከህገመንግሥት በታች ስለሆንን ጥያቄው ሲመጣ በህግ አግባብ በምክክር ማስተናገድ ያስፈልጋል። ነገር ግን የክልል ጥያቄን መመለስ መፍትሄ አይሆነንም፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ደቡብ ውስጥ ከአስር በላይ ዞኖች ክልል እንሁን ብለዋል። በሀገር ደረጃ ያሉትን ዞኖች በሙሉ ክልል እናድርጋቸው ካልን ለክልል አዲስ ስም መስጠት ያስፈልጋል። ክልል የሚለው ስያሜ ብቻውን መፍትሄ አያመጣም።

ዋናው ነገር ክልል መሆን ያስፈለገው ለምንድንነው ከኋላ ያለው እሳቤ ምንድንነው? እስካሁንስ በክልል ምን ጥቅም አግኝተናል? በማለት ግዜ ወስዶ ምን ጥቅምና ጉዳት እንዳለውም ማጥናት ያስፈልጋል። ከዚያ በኋላ ጥቅም ኖሮት ክልሉ ቢበዛ ለመንግሥት ጉዳት አይኖረውም። ችግር የሚሆነው አንደኛውን ክልል ለማድረግ ሲሰራ የጎረቤቱን ክልል ጉዳይ የማያይ ከሆነ ነው። ክልል መሆን ሰላም የማያመጣ ዘላቂ ልማት የማያመጣ አንድነትን ፈተና ውስጥ የሚከት ከሆነ ትርፉ ኪሳራ ነው። ኮሚሽንም የተቋቋመው ያ እንዳይሆን እንጂ ክልል እንዲሸነሽን አይደለም። የተቋቋመው ኮሚሽን አይወስንም ይልቁንም ከክልል ጋር የተያያዘ በቂ ጥናት አጥንቶ ለመንግሥት እንዲያቀርብ ነው፡፡ የተቋሙ አባላት በሚቀጥለው ሳምንት ይጸድቃሉ።

አዲስ ዘመን ጥር 25/2011

በጋዜጣው ሪፖርተሮች