በአማራ ክልል ከ328 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሸፍን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ተጀመረ

7

ሰላማዊት ውቤ

አርማጮሆ፦ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በዘንድሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በሚገኝ ከ328 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን የአማራ ቤሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በሥራው 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች እንደሚሳተፉ ገለጸ።

በቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር ተወካይ እስመለዓለም ምህረት ለጋዜጣው ሪፖርተር እንዳስታወቁት ከትላንት ጀምሮ እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ ከ20 እስከ 30 ለሚደርሱ ቀናት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በሚገኙ ከ328 ሺህ ሄክታር በላይ በሆኑ የማሳ፣ የቦረቦር መሬቶችና የተራራ ሥፍራዎች ስነ ሕይወታዊ ሥራዎች ይከናወናሉ።

በተጨማሪም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተፈልተው ከ182 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የመትከል የስነሕይወታዊ ሥራ የሚሠራ

 መሆኑን የጠቆሙት ተወካዩ ፣ በሥራው 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን የክልሉ አርሶ አደሮች፣ ባለሙያዎች፣ ባለድርሻ አካላትና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይካፈላሉ ብለዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ከዚህ ቀደም የግብርና ሥራ ተደርጎ ይወሰድ እንደነበረ የጠቀሱት ኃላፊው፣ ሥራው የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ ይሄ ዓይነቱ አስተሳሰብ መቅረት እንዳለበት አሳስበዋል። ባለሀብቱ በእርሻ መሣሪያም ሆነ መኪናውን ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማጓጓዝ እንዲውሉ በመፍቀድ እንዲተባበርና የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራው ስነ አካላዊ፣ ስነ ሕይወታዊ፣ ዘላቂነትና ተጠቃሚነትን ያካተተ እንደሆነና የሥራው የመጨረሻ ግብም አፈር መቆለል፣ድንጋይ መካብና ጉድጓድ መቆፈር ሳይሆን ተጠቃሚነትን ማምጣትና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሆነ አመልክተዋል።

ሥራውን ለማከናወን ባለፉት ወራቶች ሥራው የሚሠራባቸውን አካባቢዎችና ከ8 ሺህ 300 በላይ ተፋሰሶች የመለየት፣ ክፍተት ያለባቸውን ባለሙያዎች የማሰልጠንና ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማዘጋጀትና ሕብረተ ሰቡን የማወያየት ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታው ሰዋል።

የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ሥራ መነሻው ታች ከተፋሰስ መሆኑን የጠቀሱት ተወካዩ ፣ ይሄው ዝግጅት እስከ ቀበሌ መውረዱን አስታውቀዋል። ባለፈው ሳምንት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የግብርናው ዘርፍ ኃላፊዎች ባሉበት መግባባት ላይ ተደርሶ የጋራ መደረጉንና ትላንትና በይፋ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል ቦረቦር የነበሩ፣የተራቆቱ መሬቶችና ተራራዎች የነበሩና በተፈጥሮ ሀብት ሥራው በመለወጥ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንሰሳት መኖ፣ለማገዶ እንጨት የሚውሉ ዝሪያዎች የለሙባቸውና የእንሰሳትና የንብ እርባታ እየተካሄደባቸው የሚገኙ ሥፍራዎች በፌዴራል፣ በክልል፣በዞንና ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ተጎብኝተውና ልምድ ተቀስሞባቸዋል ብለዋል።

“ሥራው ዓመቱን ሙሉ የሚሠራ ነው›› ያሉት ተወካዩ፣ በአማራ ክልል የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ በተደራጀና በንቅናቄ መልማት የጀመረዉ በ2003 ዓ.ም መሆኑን አስታውሰዋል።›› ‹‹ከንቅናቄው በፊት የክልሉ የደን ሽፋን 6 ነጥብ 5 በመቶ ነበር›› ያሉት ተወካዩ እስከ አሁን በተሠራዉ ሥራም የክልሉ የደን ሽፋን ወደ 14 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል። ዕድገቱን ዘላቂ ለማድረግ የዘመቻ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላም የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመር በቀጣይ በግል ማሳና በሌሎች አካባቢዎች በቋሚነት ተጠናክሮ የሚሠራ መሆኑን አመልክተዋል። የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ሥራ እንደ ሀገር ከጥር 1/2013 ጀምሮ በይፋ መጀመሩና እንደ አካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በተገኙበት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ላይ አርማጭሆ ወረዳ ችራ ቀበሌ በሶኒ ተፋሰስ ነው። በሥነ-ሥርዓቱ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ጨምሮ ሌሎች የፌዴራል፣ ክልልና ዞን ከፍተኛ አመራሮችም ተገኝተዋል።

አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2013  ዓ.ም