«ፍሪሊየን» በጥበብ

17

ከሰሞኑ በኪነጥበቡ ዘርፍ የተከሰተ አንድ ጉዳይ ለሳምንቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ይህም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በድንገትና ከአንድ ወይም ሁለት ግለሰቦች ማወቅ ውጪ ማንም በማያልምበት ሁኔታ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ የኪነጥበብ ምሽት ክዋኔ ላይ መገኘታቸው ነው። ይህንን ጥር 2 ቀን 2011ዓ.ም የተከሰተ ነገር በስፍራው የነበሩ በደስታ ስሜት፤ ክዋኔው እንደሚኖር አውቀው መገኘት ሳይችሉ የቀሩ ደግሞ በቁጭት፤ አልፎም በበራሪ ዜናውን የሰሙ በመገረም ስሜታቸውን አንጸባርቀውበታል።

ታዲያ ነገሬ ከእለቱ ሁነት ሳይሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር መነሻ ያደረገ ነው። ይሁንና ግን በብሔራዊ ቴአትር የነበረውን ድባብ መግቢያዬ ባደርግ ወድጃለሁ። ይልቁንም በዝግጅቱ ላይ ታዳሚ የነበረው የሙዚቃ ባለሙያው ሠርጸ ፍሬስብሐት በፌስቡክ ገጹ ላይ «የማትረሳ ድንቅ ምሽት» ሲል በእለቱ የነበረውን ስሜትና ሁኔታ በማራኪ ሁኔታ አስፍሮት ነበርና፤ ገለጻው በሃሳብም በቃልም ስለሚልቅ የተወሰነውን ቀንጭቤ ላካፍላችሁ። እንዲህ ይላል፤
«የኾነው እንዲህ ነው፦ ምስክር ጌታነው ሚዲያ እና ፕሮሞሽን በየሦስት ወራት በሚያዘጋጀው መርኀ ግብር ላይ የዛሬው ተረኛ ርዕስ «ስንዋደድ» ተሰኝቶ የሚቀርብበት መድረክ ነበር የተሠናዳው።…

የመድረኩ የመጨረሻ ተናጋሪ የነበሩት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ባልተለመደ ሁኔታ ከመድረኩ ጀርባ መጥተው፣ «የዛሬውን የእኔን ንግግር፣ አንድ ዘወትር በዚህ መድረክ ላይ ለመገኘት ፍላጎት ላለው፣ በቅርቡ ከውጪ ለመጣ ወዳጄ አስቀድሜ ዕድል ልስጥና ከእርሱ ንግግር በኋላ እመለሳለሁ።» ብለው፣ ገና ከመድረኩ አትሮንስ ሁለት እርምጃ ሳይራመዱ፣ የቴአትር ቤቱን ታዳሚ ልብ ቀጥ የሚያደርግ እንግዳ ወደ መድረኩ ፈገግታ በተመላ ትሁት የእጅ ሰላምታ እጁን እያውለበለበ በታዳሚው ሁሉ ፊት ድቅን አለ።

የሌሎችን ባላውቅም፣ እኔ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የማየውን ነገር ማመን አልቻልኩም። የታዳሚው ጭብጨባ፣ ጩኸት እና መውደዱን የገለጸበትን መንገድ፣ እንደ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ያለው «የቃል አንጥረኛ” ደራሲ በሥዕል መልክ የሚጽፈው እንጂ እኔ የምገልጸው ዓይነት አይደለም።…» አለና ተረከው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ ትውልድ «የእኔ» ብሎ ከሚመካባቸው መሪዎች መካከል ናቸው። ለዚህ ምክንያት ለማቅረብና ሰሚን ለማስረዳት፤ ለአገር ይህንና ያንን ሠርተዋል የሚል ሐተታ አያሻም። ለሚመሩት ሕዝብ ቅርብ መሆናቸውንና ከወገናቸው ጋር አብሮነታቸውን ለማሳየት አጋጣሚዎችን ሲጠቀሙ ስንመለከት ይህን እናውቃለን። ጥበብ ደግሞ እንዲህ ያሉ እውነቶች ይገዟታል። መሪ ራሱን ዝቅ አድርጎ፤ ንጉሥ ከከፍታው ወረድ ብሎ ከሚመራው ሕዝብ አጠገብ ሆኖ ሲታይ፤ «…ጻፍ ጻፍ…» ይለው ስሜት እንደሚዞረው ጸሐፊ የምትናገረው ይበዛላታል።

ወደተነሳሁበት ነገር አሁን ልመለስ እችላለሁ። ነገሬ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በእለቱ በብሔራዊ ቴአትር ባደረጉት አጭር ግን ሰፊ ንግግር ላይ መግቢያ ስላደረጉት «ፍሪሊየን» የሚል፤ የብዙ ሃሳባት ኩሊ የሆነ ቃል ነው። ቀጥሎ የምላችሁ ውሃ ያነሳ እንደሆነ ባላውቅም፤ «የምትጽፉና የምትናገሩ ሰዎች ሃሳቡን ወደፊት ይበልጥ እንዲሰፋ ማድረግ ትችላላችሁ» ብለዋልና ጠቅላዩ እድሉን ልጠቀምበት ነው።
ታዲያ በንግግራቸው መነሻ ያደረጉት ይኸው «ፍሪሊየን» የተሰኘው እሳቤ፤ አንድም በነጻ የተቀበሉትንና በስጦታ የተሰጠን ሀብት ለሌሎች መስጠትና አገልግሎት ላይ ማዋል ያለውን ጠቃሚነት የሚያነሳ ነው። እንግዲህ «ፍሪሊየን» አለን የምንለው የሀብታችን ብዛት ቢሆን «ፍሪሊየነር» ደግሞ ባለሀብቱ ነው እንደማለት ነው፤ በዚህ በእኛ አውድ ደግሞ ጥበብና ጥበበኛው በዚህ ይገለጣሉ።

ይህን ሃሳብ ከዚህ ቀደም የኪነጥበብ ባለሙያዎች በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ከነበራቸው መድረክ ጋር እናጎዳኝና እንመልከተው። በዛ መድረክ ላይ በተለይ አንጋፋ የሆኑና እውቅናቸው በቴሌቪዥን መስኮት የሆነ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፤ በትምህርት ቤቶች እየሄዱ ጥቂት መልካም ነገርን ዘርተው ለነገ በስማቸው የሚጠራና መልካም ሆኖ የሚበቅል ፍሬን እንዲያፈሩ ጥሪ ቀርቦ ነበር። ይህ ምን ያህል ተከናውኗል? ለባለመልሶቹ ይቆይልን!

ጥበበኛ እርካታና ደስታን የሚያገኘው፤ ያቀረበው ሥራ ፍሬ ሲያፈራ አልፎም ተወዳጅ ሲሆንለት ነው። ለዛ ነው «ሕዝብ ነው ሀብቴ» የሚሉትን በርካቶችን የምንሰማው። አሁን ላይ ግን ከዛ በተቃራኒ ሩጫው ሁሉ የነጋዴ ዓይነት ሆኗል። ይህን በፈራጅ ሳይሆን በታዛቢ ዓይን የምንለው በመሆኑ ሁሉንም ይመለከታል ማለት አይደለም።

«ፍሪሊየነር» ናቸው ብለን የምናስባቸው የኪነጥበብ ሰዎች ንግድ የደራባትን አዲስ አበባን እንዲሁም ጥቂት ከተሞችን ማዕከል አድርገው ብቻ ይሠራሉ። ሁሉም በያለበት ፍሬ ሊያፈራ የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ከተለያዩ ክልል ከተሞች በሙያው ፍቅር በርትተው የሚመጡት ሳይቀሩ በአዲስ አበባ «የጥበብ ገበያ» ተውጠው ነው የሚገኙት። አገራዊ ተብለው የሚቋቋሙና «የኢትዮጵያ…» ብለው የሚጀምሩ በርካታ የሙያ ማኅበራት ሳይቀሩ፤ በውክልና ሁሉም ጋር ይደርስ ይመስል፤ ከዋና ከተማዪቱና ከጥቂት የተነቃቁ ከተሞች በዘለለ ሲንቀሳቀሱ አይታዩም። ከተንቀሳቀሱም አውሮፓና አረብ አገራት ናቸው መዳረሻቸው። ይህም በተለይ በሙዚቃው መስክ ጎልቶ የሚታይ ነው።

ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በእንግድነት ቆይታ አድርጎ የነበረው ጋዜጠኛና የኪነጥበብ ባለሙያ አባተ ማንደፍሮ ተከታዩን ሃሳብ አካፍሎን ነበር። እንዲህ ነው፤ በቀደመው ጊዜ ይልቁንም የኪነት ቡድኖች እንቅስቃሴ ጠንካራ በነበረበት ወቅት የነበረውን አስታውሷል። «እኛ በስድስት ብር አበል ከባሌ ፖሊስ ጋር ግማሽ ኢትዮጵያን ዞረናል። በተመሳሳይ ከወሎ ላሊበላ ኪነት ጋር በአሥራ አራት ብር አበል ነው በየስፍራው እየተንቀሳቀስን የሠራነው» ይላል አባተ።

ለምሳሌም ይጠቅሳል፤ «ለምሳሌ ንዋይ ደበበ ራስ ቴአትር የመጣው ራስ ቴአትር ወላይታ ሄዶ ባዛር ሲሠራ ነው። አንጋፋውና የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠን ስንመለከት፤ አገር ፍቅር ቴአትር ወሊሶ ሄዶ ሙዚቃ ባይሠራ፤ ጥላሁን ገሠሠ ኢዮኤል ዮሐንስን አያገኝም ነበር። ያኔ የኪነቱ እንቅስቃሴ ክፍለ ሀገር ላሉ ልጆች መነሻ ምክንያት ነበር» ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ አንጋፋውን ሙዚቀኛ ጥላሁን ገሠሠን በ«ፍሪሊየነሮች» ተርታ ጠርተዋል፤ በተረዳነው እሳቤ መሠረት ይህ እውነት ነው። ከዛም አልፎ የሚገርመውና የሚልቀው ደግሞ ጥላሁን ገሠሠ ራሱ የ«ፍሪሊየነሮች» ውጤት መሆኑ ነው። ሙያውን እንጂ ገንዘቡን ያላዩ፤ አሁንም የሀብታቸው ብዛት ሳይሆን ስማቸውና ክብራቸው እንዲሁም ሥራቸው የተረፈን «ፍሪሊየነሮች» ናቸው እነዛን ድንቅ ሰዎች የወለዱልን።

በጥቅሉ በጥበብ ይህን ሃሳብ ስናየው ገና ምንም ያልተሠራበት መሆኑን እንረዳለን። የኪነጥበብ ባለሙያዎች ቆሎ ቆርጥመው እያደሩ ተጎሳቁለው ይሥሩ ማለት አይደለም። ይሁንና የጥበብ ሰው ከአትራፊ ቢራ ፋብሪካና ድርጅት በላቀና በተሻለ ማኅበራዊ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል። ይህም በበጎ አድራጎትና ሰብዓዊ እርዳታ ብቻ አይደለም፤ በጥበብ ሥራቸው የተሻለ ሰው ማፍራት ቀላል ሥራ አይመስለኝም።
የሚከፍሉት ገንዘብ ባይኖራቸው፣ ምቹ ወንበሮች ባያዘጋጁም፣ መድረክ አስጊጠው ባይጠብቁና በመብራት የተንቆጠቆጠ እይታን ባያቀርቡ፤ ፈገግታ፣ ምርቃትና ምስጋናቸው ከልብ የሚገባ፤ ከአዲስ አበባ አልፈው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ማሰብ ይገባል። «ፍሪሊየነር» መሆን የተቀበሉትን መስጠትና በተቀበሉትም ብዙ ማትረፍ መሆኑ ላይ መስማማት ከተቻለ፤ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በውስጣቸው ያለውን ጸጋ በመጠቀም ብቻ ሳይሆን አትርፈውበትም ሊደምቁ ያስፈልጋል።

እንግዲህ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው አይሁንብኝና የኪነጥበብ ባለሙያዎች በዛ መልክ ቢንቀሳቀሱ እላለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ይህ እሳቤ ከመደመር ጋር ተጣምሮ ነውና የበለጠ ፍሬ የሚያፈራው፤ በዚህም አውድ የሚመለከታቸው ሁሉ ሁኔታዎችን በአቅማቸው እያመቻቹ የባለሙያውን በር ሊያንኳኩ ይገባል። ይሄኔ ብቻ ነው፤ ከሚሊኒየም አዳራሽና ከጋዝ ላይት፤ ከአዲስ አበባና ባህርዳር ወይም ከአዳማና ከሃዋሳ በዘለለ፤ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የኪነጥበብ ባለሙያን ጥበባዊ ሥራ ሊቋደሱ የሚችሉት። ሰላም!

አዲስ ዘመን ጥር26/2011

ሊድያ ተስፋዬ