የ«ሀድያ ጋራድ» ትንሣኤ

58

ከ1520 ዓ.ም በኋላ ነው ይባላል፤ የሀድያ ንጉሣዊ አስተዳደር ሥርዓት የተቀዛቀዘውና ኋላም የተቋረጠው። ይህም ከሀድያ ስርወ መንግሥት መዳከም በኋላ የተከሰተ ነው። ይሁንና ታዲያ የሀድያ ሕዝብ በየጎሳው «ጋራድ» እየሰየመ ሰላሙን ጠብቆና ባህሉን አቆይቶ ኖሯል። እንደው ችግር የተፈጠረ እንደሆነም፤ ማዕከል ሆኖ አቤት የሚባልለት ንጉሥ የለምና፤ የየጎሳው መሪ ጋራዶች ሰብሰብ ብለው ይመክሩና መፍትሔ ይሰጡ ነበር።

ሀድያዎች ጋራድ ወይም ንጉሥ የሚመርጡበት ሥርዓት «ሴራ» ይባላል። ይህ ሥርዓት መከናወን ካቆመ አሁን አምስት መቶ የሚጠጉ ዓመታት ተቆጥረዋል። ቢሆንም ሥርዓቱና ባህሉ ከልቡ ያልጠፋው የሀድያ ሕዝብ እንዲሁም የሀድያ አባቶች፤ ጊቾዎች ከአምስት ዓመታት በፊት የሥርዓቱን ትንሣኤ ለማስበሰር እንቅስቃሴ ጀመሩ።

ለመሰባሰብና እየተዘነጋ ያለውን የሕዝቡን ባህላዊ ሥርዓት ለማቆየት ተፈልጎ ነው። እናም በሀድያ የተለያየ ጎሳ መሪ የሆኑ ጋራዶች ተሰባሰቡ። በዛም ኅብረት የደበዘዘውን ባህል አድምቆ ለማሳየትና ለውጥ ለማምጣት ተባብረው ሊሠሩ ቃል ገቡ። ቸል አላሉም፤ ሃሳቡን እያሰላሰሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀመሩ። አንዱ ተግባርም እጩ ንጉሥ ወይም አሻን ጋራድ መሰየም ነበር፤ አደረጉት። ከዚህ በኋላ «አሻን ጋራድ ፋውንዴሽን» ተመሠረተ።

ተቋሙ ዓላማው የሀድያ ሁለንተናዊ ባህል ላይ ጥናትና ሰፊ ምርምር ማድረግ፤ አልፎም ባህሉንና ሥርዓቱን ማስተዋወቅና በዓለም ማሳየት ነው። ይህም የተሳካ ነበር። ለዚህም ምስክር በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በሚዘጋጁ ባህልን የተመለከቱ ክዋኔዎች ላይ የዚህ ፋውንዴሽንና የጋራዶች ላቅ ያለ ተሳትፎና በየጊዜውም ከባህልና ቱሪዝም ቢሮው ያገኙት ሽልማትና እውቅና ነው።

ከወራት በፊት የሀድያ ሽማግሌዎች «አሻን ጋራድ» ብለው የሰየሙትን ሰው ጠርተው «ለ”ሀድያ ጋራድ”ነት መርጠንሃል» አሉ። ይህም ልክ የዛሬ ሳምንት ጥር 19 ቀን 2011ዓ.ም ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ በሚገኘው የ«አሻን ጋራድ» መኖሪያ ቤት በደማቅ ሥነ ሥርዓትና በይፋ በዓለ ሲመቱ ወይም የንግሥናው ሥርዓት ተከናወነ። ተቋርጦ የነበረው የሹመት ሥርዓት «ሴራ» ዳግም ቀጥሎ፤ አምስት መቶ ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው «ሀድያ ጋራድ» ተሾመ።

«የሀድያ ሕዝቦች ባህላቸውን እንዲሁም ታሪካቸውን በጋራ መጠበቅ ስላለባቸው፤ ለዚህ ደግሞ የመጀመሪያው ጉዳይ መሰባሰብና አንድ መሆን ስለሆነ ለአምስት ዓመት ይህን ሠርተናል።» ያሉት፤ «አሻን ጋራድ» የነበሩትና ከአሁን ወዲያ «ሀድያ ጋራድ» ሆነው የተሾሙት አቶ ገብረኪዳን ቀልባቦ ናቸው።

ጋራዳዊ አስተዳደር
የሀድያ ጋራዳዊ ሥርዓት ወይም ንጉሣዊ አስተዳደር ሥርዓት እንደ ፌዴራላዊ መንግሥት ያለ አወቃቀር ያለው ነበር። በጋራድ የሚመሩ ጎሳዎች ሁሉ ተጠሪነታቸው ደግሞ ለዋናው «ሀድያ ጋራድ» በመሆኑ ነው። «ሀድያ ጋራድ» የመጨረሻ ባለሥልጣን ሲሆን፤ ሥልጣኑም ይግባኝ ሰሚና የዳኝነቱን ጥግ ያካትታል።

«በዚህ ጊዜ አሁን በተሰጠኝ ሹመት የምሠራው እርቅ፣ ሰላም እና ፍትህ እንዲኖር፤ ብሎም ሕዝቡ ባህሉንና ታሪኩን እንዲጠብቅ፤ በጥቅሉ ለአገራችንም ለራሳችንም በሚጠቅም መልክ ሕዝብን ማስተማርና መምራት ነው።» ይላሉ፤ ሀድያ ጋራድ ገብረኪዳን ቀልባቦ።

በነገራችን ላይ የጋራዳዊ ሥርዓት በኦሮሞ ባህል ካለው የገዳ ሥርዓት ጋር ተመሳሳይነት አለው። ምንም እንኳ በዚህ ላይ በንጽጽር የተደረጉ ጥናቶችን በቅርበት ለማግኘት ባልችልም፤ ሀድያ ጋራድ እንደሚናገሩት፤ በሁለቱ ሥርዓቶች መካከል ያለው አንዱ ልዩነት የሥልጣን ዘመን ነው። በገዳ ሥርዓት መሪ የሚሆነው ሰው ለስምንት ዓመት የሚቆይ ሲሆን፤ በሀድያ ጋራዳዊ ሥርዓት ግን ሥልጣኑን የሚሰጠው በዘር ሐረግ ከመሆኑ በተጨማሪ እድሜ ልክ የሚቆይ ነው።

«ሁሉም ብሔረሰብ ለሰላም የራሱ ባህላዊ ድርጅት አለው። ሕዝብም ሰላምን የሚያስከብርበትና ከመንግሥት መዋቅር ውጪ የሆነ ሥርዓት አለው» የሚሉት ሀድያ ጋራድ ገብረኪዳን፤ እነዚህን በየብሔረሰቡ ያሉ ባህሎችና ሥርዓቶች መጠበቅና ማውጣት እንዲሁም ማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አያይዘው ያነሳሉ። እናም ይህን የሀድያ ሥርዓት በተመለከተ፤ የኢትዮጵያ ሆኖ እንዲመዘገብና እውቅና እንዲሰጠው የበለጠ ይሠራልንም ብለዋል።

በነገራችን ላይ፤ «ሀድያ ጋራድ» ተብሎ የሚሾም ሰው የሀድያ አባቶች እንዲሁም የተለያዩ ጎሳ መሪ ጋራዶች የሚመርጡት ነው። ሀድያ ጋራድ እስከሕይወት ፍጻሜ በሚቆይ የሥልጣን ዘመኑም ምንአልባት ጥፋት አጥፍቶም ከሆነ ማዕረጉን ባይቀማም ሥልጣኑን ግን ይነጠቃል። «በሀድያ ባህል አንድ ጊዜ ማኀራኖ ተብሎ ሹመት የተሰጠው፤ ሹመቱን አይነጠቅም» የሚል ሥርዓት አለ። ይሁንና ጥፋት በተገኘ ጊዜ ሥልጣኑን መወሰንና መገደብ የየጎሳ ጋራዶች ኃላፊነትና ሥልጣንም ነው። ከዚህ በተጓዳኝ አንድ ሰው «ሀድያ ጋራድ» ለመሆን በእጩነት እንዴት ይቀርባል የሚለውም ሌላው ጥያቄ ነው።

«የሀድያ ማኅበረሰብ የዘር ሐረግ /የቅድመ አያቶች/ ታሪክ እና የአስተዳደር መዋቅር» /The Ancestral History and Traditional Administrative Structure of Hadiyya Society: An Ethnic Group in Ethiopia/ በሚል ርዕስ፤ በኤርጎጌ ተስፋዬ /ዶክተር/ የተዘጋጀ ጥናት በዚህ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ይዟል።

ጥናታዊ ወረቀቱ እንደሚያስረዳው፤ በጥንት የሀድያ ሥልጣኔ ዘመን፤ የሀድያ ሕዝብ ከወገኑና ከሌላ ብሔረሰብ ተወላጅ ጋር በጋራና አብሮነት እንዲኖር ይህ አስተዳደራዊ ሥርዓት በአያሌው ጠቅሞታል። አንድን ሰው ለጋራድነት በሕዝቡና በአባቶች ዐይን ውስጥ የሚያስገባው፤ የየእለት እንቅስቃሴውና አኗኗሩ ነው። ለምሳሌ የአካባቢውን ባህልና ሥርዓት ማወቅና መጠበቅ፤ ታማኝነት፣ አገልጋይነት፣ ለሕዝብ ያለው ተቆርቋሪነት፣ ጥሩ የንግግር ችሎታ፣ የተሻለ ሀብት ያለው፣ ቤተሰቡን በአግባቡ መምራት የቻለ፣ ጸብን ማብረድ የሚችል ሊሆን ይገባል።
በዓለ ሲመቱ እንዴት ነበር?

ለሹመቱ ብዙ መንገድ አቋርጠው ብዙ እንግዶች አዲስ አበባ ተገኝተዋል። ከአፋር፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያና ሌሎችም በርካታ በርቀት የሚገኙ አባቶችና ወጣቶች ታድመዋል። አዲስ አበባ መገኘታቸው የሹመት ሥርዓቱ ላይ ለመሳተፍና እንደ ሥርዓቱ ተመራርቆ መልካም ምኞት ለመቀባበል ነው። የሀድያ ተወላጆች ብቻ አይደሉም፤ ከአፋርና ከሶማሌ ጥግ የተገኙም ነበሩ።

ምነው አዲስ አበባ ድረስ መጡ የተባለ እንደሆነ እንዲህ ነው። ሀድያ ጋራድ የረገጠው የተባረከ ነውና ሹመቱ በመኖሪያ ቤቱ እንዲፈጸም ባህሉ ያዝዛል። እናም በሀድያ ባህላዊ አስተዳደር፤ የሀድያ ንጉሥ መኖሪያቸው አዲስ አበባ ሆኖ ተገኘ። ታዲያ ከየክልሉ የተጠሩ አባቶች ብቻ አይደሉም፤ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ምሑራንም ተገኝተዋል። ለዚህም ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌታሁን፣ ዶክተር በቀለ ገርባና ጁነዲን ሳዶ ልንጠቅስ እንችላለን።

ረፋድ አራት ሰዓት ላይ የጀመረው መርሃ ግብር፤ በቤቱ የተገኙ እንግዶችን ቁርስ በማብላት ተከፍቷል። ቀጥሎም ሀድያ ጋራድ ሆነው የተሾሙት አባት፤ ካባቸውን ለብሰው ወደ መድረክ ወጡ። በትህትና በአባቶችም ፊት ተቀመጡ፤ ከየክልሉ የመጡ አባቶችና እናቶችም ምርቃታቸውን አቀረቡ። «ደስ ትላላችሁ፤ ባህሉን ይጠብቅላችሁ፤ ይጠብቅልን» ብለውም መልካም ምኞታቸውን ተገላለጹ። ከዚህ በኋላም በስፍራው የነበሩ ጋራዶች ባህላዊ ሥርዓቱን ከውነው ለሀድያ ጋራድ ኃላፊነቱን አስረከቡ። አያይዘውም አሻን ጋራድ ፋውንዴሽን ሀድያን የሚወክል እንዲሆን አደራቸውን ሰጡ።

ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምን ይላል?
«እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ይህ እንዲለማና እንዲቀጥል ነው የምንፈልገው» ያሉት በቢሮው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መክብብ ገብረማርያም ናቸው። በተለይም የሀድያ ጋራድ መኖሪያ ቤት አዲስ አበባ ላይ መሆኑ፤ ስፍራው የቱሪዝም መዳረሻና የብሔረሰብ ማዕከል መሆን ይችላል ብለዋል። ከዚህም በተጓዳኝ ተመራማሪዎችም ለጥናትና ምርምር ሁኔታዎች ምቹ እንደሚሆንላቸው ገልጸዋል።

የሀድያ ጋራድ ፋውንዴሽን አሁን ላይ የሀድያን ባህልና ሥርዓት በሚያስተዋውቅ መልኩ ይሠራል። አቶ መክብብ እንዳሉት፤ ፋውንዴሽኑ ላለፉት ሦስት ዓመታት በባህልና ቱሪዝም በሚዘጋጁ ክዋኔዎች ላይ ተሳትፈው ባህላቸውን ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል። ከቢሮው ጋር በጋራ ሲሠሩ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል። ይህን በማስቀጠል የሰላምና የእርቅ አካሄዶችን ለወጣቶች በማስተዋወቅና በማሳየት፤ ለመንግሥትም አቅም መሆን ይችላሉ ሲሉም ተናግረዋል።

በዚህ ላይ ሁሉም ርብርብ ማደረግ ግን ይጠበቅባቸዋል። ይህም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ያጠቃልላል። ሚኒስቴሩ ምንም እንኳ በአዲስ መስመርና አካሄድ ላይ እንደሚገኝ የሚታሰብ ቢሆንም፤ ከባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር ያለውን ግንኙነትና ትስስር መመልከትና ማጠናከር ይጠበቅበታል። እንደ አገር ከማይዳሰሱ ቅርሶች መደብ ሊያዝ ይገባል የሚሉት አቶ መክብብም፤ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል። ሰላም!

አዲስ ዘመን ጥር26/2011

ሊድያ ተስፋዬ