የዜግነት መብትና ፌዴራሊዝም

29

የፌዴራል ሥርዓት በአንድ አገር ውስጥ ያልተማከለ አስተዳደርን በመስፈንና አምባ ገነንነትን በማስወገድ ረገድ ትልቅ ሚና ያለው ስርዓት ስለመሆኑ በሰፊው ይነገራል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የተለያየ ማንነት ባላቸው አገራት ደግሞ ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩና የስልጣን ተካፋይ እንዲሆኑ ስለሚያስችል አማራጭ የሌለው ስለመሆኑም ይገለጻል፡፡

ይሁን እንጂ እንደየአገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ሊቃኝና አተገባበሩም ችግሮቹን ባማከለ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ከሰሞኑም “የፌዴራል ሥርዓት በኢትዮጵያ፤ አተገባበሩ፣ ተግዳሮቶቹና መጻኢ ዕድሉ” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አዘጋጅነት በተካሄደ የምሑራን የውይይት መድረክ ላይ የተነሳውም ይሄው ነው፡፡

በአንድ አገር የፌዴራል እውን ሲሆን አንባገነንነትን ለመቀነስና ስልጣንን በተለያየ ማዕከል መከፋፈልን ዓላማ አድርጎ እንደሆነ የሚናገሩት፣ በመድረኩ “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት አመሰራረት፣ ፋይዳውና ቀጣይ አቅጣጫዎቹ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶክተር አሰፋ ፍስሐ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ የፌዴራል ስርዓት በአንድ አገር ውስጥ ተመጣጣኝ የስልጣን ክፍፍልን ይፈጠራል፤ ራስን በራስ ለማስተዳደርም ያግዛል፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ አገር የሚመሰረተው የፌዴራል ስርዓት ይሄን አይነት እድል የሚሰጠው አንድም በህዝቦች ይሁንታ ሲኖረውና በፈቃዳቸው ላይ ተመስርቶ ሲደራጅ፤ አንድም በመርህ ላይ ተመስርቶ ሲተገበር ነው፡፡

በኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ሂደት የተለያዩ ሂደቶች ታልፈዋል፡፡ በሂደቱም የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ ከገበሬዎች አመጽ ጀምሮ የመሬት ላራሹና የብሄር ጥያቄ የደረሱ ጉዳዮችንም አሳልፏል፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ግን የፌዴራሊዝም ስርዓቱ የማዕከላዊነት ዴሞክራሲ ብሎም የአውራ ፓርቲ አመራር ሂደት መቃኘቱ በርካታ ችግሮች ይታዩበታል፡፡ ምክንያቱም የማንነት ጥያቄን የመለሰ ቢሆንም የዜግነት መብት ጉዳይን የዘነጋ ነውና፡፡ ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ ትቅደም ወደ ብሔር ይቅደም ፖለቲካ በሚደረገው ሽግግር ተገቢውን ሥራ ያለመስራት ውጤት ሲሆን፤ በተለይም የመንግሥት መዋቅሩና አካላት የብሔር ጉዳይ ላይ የተሰራውን ያክል በዜግነት መብት ላይ ለመስራት ፍላጎት ማጣት ጉልህ ድርሻ ይይዛል፡፡ በመሆኑም የብሔርም ሆነ የዜግነት መብት ጉዳይ በመርሆ ላይ ተመስርቶ የሚሰራበትን ሂደት መፈተሽና የዜግነት መብት ጉዳይ ተገቢው ከለላ ሊያገኝ ይገባል፡፡

“የፊስካል ፌዴራሊዝም አተገባበር በኢትዮጵያ፤ ስኬቱና ክፍተቱ” በሚል ርዕስ የጥናት ጽሑፍ ያቀረቡት ዶክተር ሰለሞን ንጉሤ የዶክተር አሰፋን ሀሳብ ይጋራሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ያለው የፌዴራሊዝም ስርዓት የሚፈጥረው የፖለቲካ ቀውስ በፊሲካል ሂደቱ ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ምክንያቱም አንድነትን የዘነጋ ብሔርተኝነት ስር እየሰደደና እየገነገነ በመጣ ቁጥር የጋራ የሆነ እሳቤን ስለሚሸረሽር የጋራ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስር ፈጥሮ በጋራ የመስራት ሂደቱን ይጎዳዋል፡፡ ይህ ደግሞ በፖለቲካው መስክ የተገነባውን የድንበር ግንብ በፋይናንሱም እንዲፈጠር በማድረግ ለጋራ የኢኮኖሚ ትስስር የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች የሚፈለገውን ውጤት እንዳያመጡ፤ ዜጎችም የዚህ መብት ተጠቃሚ የመሆን ሂደታቸው ላይም ገደብ  የሚያስቀምጡ ብቻ ሳይሆን የሚዘጉ ናቸው፡፡

እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለጻ፤ ጤናማ የፌዴራል ስርዓት ያለመኖር በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ክልሎች ፍትሃዊ የመሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ተደራሽነት ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ ባለፈ፤ በተሳታፊነት፣ በግልጸኝነትና በተጠያቂነት ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡ ይህ ተግሞ በተግባር እየተገለጸ ሲሆን፤ ፌዴራሊዝሙ መሬት ላይ ካልታየ በስተቀር ውጤት ሊመጣ ስለማይችልም ከራስ ባለፈ ለጋራ መስራት የሚያስችል አቅጣጫን መፍጠር በሚያስችል መልኩ በአግባቡ ተፈትሾ ሊታረም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን የዜግነት መብት ሊከበር፤ ብሔርተኝነትም በአንድነት ቅኝት ተዋዝቶ ውጤታማ የፊስካል ፌዴራሊዝም እንዲኖር ማድረግ ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት የብሔረሰቦችን ጥያቄ ለመመለስ የተነሳ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ፣ “የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት ሕገ መንግስታዊና የአተገባበር ክፍተቶችና ተግዳሮቶች” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶክተር አስናቀ ከፋለ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የፌዴራል ስርዓቱ ሲመሰረት የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች ያልተከራከሩበትና የህዝቦችም ተሳትፎ ያልነበረበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይልቁንም በተወሰኑ ሃይሎች ይሁንታና ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ እንጂ የህዝቦችን ሞራላዊና የጋራ አስማሚ የሆኑ ነጥቦች ያልተደረሰበት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ የፌዴራል ስርዓት ለብሔረሰባዊ ማንነት የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት፣ ዛሬ ላይ ለሚታዩ ችግሮች መሰረት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

ለምሳሌ፣ ከክሎች በብሔረሰብ ስም መቋቋም አንዱ በየክልሎች ያሉ ህዝቦች ላይ የሚያሳድረው ችግር ሲሆን፤ ክልል የማቋቋምና የመገንጠል መብቶችም ሌላው የክልሎችንም ሆነ የፌዴራል መንግሥትን የሚፈታተኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የፌዴራል ስርዓቱ የሚፈጥረው የብሔረሰባዊ ብሔርተኝነት ችግር ነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ያሉ ክልሎች በወሰን ሳይሆን በድንበር ራሳቸውን ያጠሩ ስለሆኑ የክልል ድንበሮች በራሳቸው የሰዎችን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመንቀሳቀስና የመስራት የዜግነት መብት የሚገድቡ ናቸው፡፡ በዚህም የዜግነት መብት በሕገ መንግሥቱ ያለ ቢሆንም በተግባር ችግር ሲገጥመው ታይቷል፡፡ ለዚህ መብት ጥበቃ የሚያደርግ ተቋማዊ አደረጃጀት ተፈጥሮ ሲሰራም አልታየም፡፡

እንደ ዶክተር አስናቀ ገለጻ፤ አሁን ያሉ ችግሮችን ለማረምና ለመፍታት የፌዴራል ስርዓቱን መፈተሽ ይገባል፡፡ በዚህም ብሔርተኝነት ከዜግነት ጋር እንዴት ተጣጥሞ መሄድ በሚችልበት ጉዳይ ላይ የተለያዩ አገራት ተሞክሮዎችን ወስዶ ለራስ በሚሆን መልኩ መስራት ሲሆን፤ በተመሳሳይ አሁን የሚነሱ ጥያቄዎችን በጥንቃቄ በማየት ምላሽ የሚሰጥበትን ሂደት መመልከት ነው፡፡ እስካሁን በኢህአዴግ የሚመራውን ከላይ ወደታችም ሆነ የጎንዮች የበይነ መንግሥታት ግንኑነቱንም መፈተሽና ተገቢውን እርምት ማድረግ ይገባል፡፡ የክልሎች የጸጥታ መዋቅር፣ ፖለቲካውን በጥርጣሬ ስሜት የሚያጦዘውን የመገንጠል መብት መፈተሽ፣ የወሰንና መሰል ጉዳዮችንም በጥንቃቄ መፍታት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግስት ትርጉም ሥራም ባለቤቱ ማን ይሁን የሚለውም ተፈትሾ ባለቤት ሊሰጠው ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 27/2011

በወንድወሰን ሽመልስ