በበጀት ዓመቱ ከ600 ሺህ በላይ የሥራ ዕድል መፈጠሩ ተገለፀ

32

አዲስ አበባ፡- በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት 635 ሺህ 89 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

በኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ፈረደ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ከተፈጠሩት የሥራ እድሎች 57 በመቶ በመደበኛና 43 በመቶ በግዙፍ ፕሮጀክቶች ሲሆን በግዙፍ ፕሮጀክቶችና በቅጥር ከተፈጠረው ውስጥ 48 በመቶ ቋሚ የሥራ እድል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በነዚህ የሥራ እድሎችም 1 ሺህ 147 አካል ጉዳተኞች፣ ሁለት ሺህ ከስደት ተመላሾች፣ 20 ሺህ 506 የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንና 24 ሺህ 615 የቴክኒክና ሙያ ያጠናቀቁ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡

በሦስት ዓመት ተኩል የሥራ አፈፃፀምም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በመደበኛና በመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለ8 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከታቀደው አንፃርም 61 በመቶ ማሳካት ያስቻለ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ በሥራውም አስፈላጊ መንግሥታዊ ድጋፎች ተደርገዋል ብለዋል:: በዚህም 4 ቢሊየን 6 ሚሊየን 331 ሺህ 387 ብር ቁጠባና 3 ቢሊየን 2 መቶ 32 ሚሊየን 146 ሺህ 148 ብር ብድር ማቅረብ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ብድር አመላለስ ላይ የሚነሱ ችግሮችን ለማቃለል በተሰራው ሥራ ከዘመኑና ከውዝፍ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ተመላሽ ማድረግ እንደተቻለም አቶ አሰፋ ገልፀዋል፡፡

መንግሥት ዜጎችን ከማደራጀት ባለፈ ከሚሰጣቸው ድጋፎች ውስጥ የገበያ ትስስር እንዲሁም የመሥሪያና መሸጫ ቦታዎችን ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ አንዱ እንደሆነ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ የመንግሥት አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ለእያንዳንዱ ተጠቃሚ ይህን አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ ማቅረብ ባይቻልም ዜጎች ከተደራጁ በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው ጭምር እንዲሰሩ ገበያውንም በራሳቸው አቅም እንዲፈልጉ እያበረታቱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ሆኖም አመለካከት ቀረፃ ላይ ቀሪ የቤት ሥራዎች በመኖራቸው በተጠቃሚዎች ያለው የጠባቂነት መንፈስ አሁንም ጎልቶ ይታያል ያሉት ዳይሬክተሩ በዚህም እያንዳንዱን ድጋፍ ከመንግሥት የመጠበቅና በራስ ጥረትም ወጤታማ ለመሆን አለመጣር ያልተሻገርናቸው ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡

በአመለካከትና በግብዓት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል ከሚሰራው ሥራ በተጨማሪ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ለ66 ሺህ 63 ኢንተርፕራይዞች 8 ቢሊየን 129 ሚሊየን 234 ሺህ 973 ብር የገበያ ትስስር መፍጠር መቻሉንም አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡

ከመሥሪያና መሸጫ ሼድ ጋር ተያይዞም ቀደም ሲል ግንባታቸው የተጠናቀቁትንና የዚህን ዓመት ጨምሮ 1 ሺህ 253 ሼዶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች እንዲተላለፉ መደረጉንና ከዚሁ ጋር ተያይዞ  ሼዶችን በተቀመጠው መመሪያ መሠረት በወቅቱ አለመልቀቅ  ማነቆ ነው ብለዋል፡፡

የኢንተርፕራይዞች ሽግግር አዲስ ለሚደራጁ ዜጎች አስፈላጊ በመሆኑ 59 ሺህ 871 ኢንተርፕራይዞችን በተለያዩ የዕድገት ደረጃዎች እንዲሸጋገሩ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም በዘርፉ የሚስተዋለው የሥራ ዕድል ፈጠራን ሥራ ለአንድ ዘርፍ ብቻ የመተው አመለካከት ሊቀረፍ እንደሚገባና ለዚህም በባለድርሻነት የሚሰሩ ሌሎች ዘርፎች እንዲሁም እያንዳንዱ ዜጋ የበኩሉን መወጣት እንደሚገባው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ለ5 ሚሊየን 78 ሺህ 438 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በዚህም 9 ሺህ 492 ሔክታር መሬት የለማ ሲሆን፤ የ19 ሺህ 841 ሼዶች ግንባታ ተከናውኗል፡፡ በተያያዘ 23 ቢሊየን 278 ሚሊየን 125 ሺህ 56 ብር ብድር ለተጠቃሚዎች መቅረቡ ታውቋል፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 27/2011

በፍዮሪ ተወልደ