ሃሳብ እናዋጣ!

40

ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ መገለጫ ናት፡፡ ከሁለት ሚሊኒየም ዓመታት በፊት የነበረችባቸው የስልጣኔ ማማዎችን ስንመለከት በመካከሉ የት ነበርን የሚል ጥያቄን እስከሚያጭር ድረስ ለብዙዎቻችን ግርምትን መፍጠሩ አይቀርም፡፡ አንዳንድ የስልጣኔ አሻራዎቻችን ዛሬም ቢሆን የማንሞክራቸው ምጡቅ የስልጣኔ ምስክሮች ናቸው፡፡

ያም ሆኖ ግን እነዚህ የኋላ ታሪኮቻችን ለቀጣይ ብርታት ሊሆኑን ይገባል፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ከጠንካራ የኋላ ታሪኮቻችን ቁጭትን፤ከውድቀቶቻችን ደግሞ ትምህርት ወስዶ ለቀጣዩ ትውልድ የኩራት ምንጭ ሆኖ ለማለፍ መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ያለንበት ወቅት ወሳኝ በመሆኑ ምን ላይ ማተኮር አለብኝ የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡

አሁን አገራችን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ በርካታ መልካም እድሎች ከፊት ለፊት የተደቀኑበት ሰፊ ምህዳር ያለው እንደሆነ መገንዘብ ያሻል፡፡ በተለይ አሁን በደረስንበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ለማደግ የሚያስችላት ሰፊ እድል በእጇ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ውስጥ አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ነው፡፡

አንድ አገር ለእድገቷም ሆነ ለውድቀቷ የህዝቦቿ የስራ ባህል፣ ሰዋዊና ቁሳዊ ሃብት እንዲሁም አጠቃላይ የመልከአ ምድራዊ አቀማመጧ ጭምር ወሳኝ እንደሆነ ቢታመንም ከሁሉ በላይ ግን እያስተዳደረ ያለው መንግስት ለእድገቱ የሚኖረው ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በአገራችን ያለውን የለውጥ ሂደት ስንመለከት ለእድገትም ሆነ ለለውጥ ያለው ቁርጠኝነት ሰፊና መልካም እድል የሰጠ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በፖለቲካው መስክ በሰላማዊ መንገድ ወደ ፖለቲካ ትግሉ ገብቶ ለመታገልና ለውጥ ለማምጣት እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት በእጁ ሰፊ እድል  ያለበት ሁኔታ ይታያል፡፡ አሁን ማሸነፍ የሚቻለው በያዝነው የሃሳብ ልዕልና ብቻ በመሆኑ የተሻለ ሃሳብ ያለው ሁሉ ወደፊት ወጥቶ የመሪነት ሚናውን ለመቆናጠጥ ሰፊ እድል ያገኘበት ወቅት ነው፡፡  ከዚህ አንጻር ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር መፈጠሩ እንደመልካም አጋጣሚ የሚወሰድ ነው፡፡

ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትም በተሻለ ሁኔታ በተግባር የተከበረበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ ደግሞ አሸናፊ የሚሆኑ ሃሳቦችን በነፃነት ለማንሸራሸርና ተመራጭ ለመሆን ወይም ለአገር የሚጠቅሙ ሃሳቦችን ለመስጠትና ለማስረጽ  እድል የሚሰጥ በመሆኑ ይህም ከሚታዩ እድሎች አንዱ ነው፡፡

በአንጻሩ ግን እነዚህን እድሎች ለማኮላሸት የሚያስችሉ እድሎችም እንዳሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ደግሞ በአንድም በመንግስት ሃይሎች ውስጥ ባለው የአሰራር፣ የአመለካከት፣ አደረጃጀት ወይም ሌላ ችግር፣ በሌላም በኩል በህብረተሰቡ ውስጥ በሚታዩ የቆዩ የተበላሹ አስተሳሰቦች ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ ሁሉም የሚመለከታቸው የመንግስት ሃይሎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሁም ህብረተሰቡ  ቆም ብሎ ማሰብና አገርን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሃሳቦችን ለማዳበር መጣር አለበት፡፡

ከዚህ አንጻር አሁን ባለው ሁኔታ ከሚያጋጥሙ ችግሮች ውስጥ አንዱ የሃሳብ ጥራት አለመኖር  ነው፡፡ የሃሳብ ጥራት በተለያዩ ሃይሎች ውስጥ በየራሱ አውድ ሊገለፅ ይችላል፡፡

በአገራችን መንግስት እንሆናለን በሚል የሚታገሉ ከ70 በላይ የፖለቲካ ሃይሎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች አንዱ ከሌላው ያለው የሃሳብ አንድነትና ልዩነት በግልፅ አይታወቅም፡፡ እነዚህ ሃይሎች አገራዊ እድገትን ለማረጋገጥ የያዙት የሃሳብ አማራጭ ምን እንደሆነም በትክክል በህብረተሰቡ ውስጥ አልሰረፀም፡፡  አንዱ ድርጅት ከሌላው በተሻለ ሁኔታ እንዴት ነው ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለው ከሚለውም አንጻር የጠራ አመለካከት የለም፡፡ ይህ ደግሞ የፖለቲካ ሃይሎቻችን የሃሳብ የበላይነትን ይዞ መቅረብ ላይ ገና ብዙ መስራት እንዳለባቸው የሚያሳይ ነው፡፡

በሌላ በኩል በህብረተሰቡም ውስጥ ተመሳሳይ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ አንዱ በድንገት ተነስቶ የአንዱ የፖለቲካ ሃይል ደጋፊ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ለዚህ ፊት ፊት የሚታየው በአብዛኛው ከብሄር ማንነት እና ድርጅቱን የሚመሩ አካላት አልፎ አልፎ ከሚናገሩት የሃሳብ ልዕልና በመነጨ ብቻ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ጠንካራ አስተሳሰብ ላይ የተገነባ የፖለቲካ ድርጅት ለመገንባት አያስችልም፡፡ በዚህ የተነሳ በመንጋ የመነዳት ዝንባሌዎች እዚህም እዚያም ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሚዛናዊነትን የሚያስት ይሆናል፡፡

አለመደማመጥም ሌላው አሁን አሁን የመጣ ክፉ የሰላም ጠላት ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችን መንስኤ ስመለከት ቁጭ ብሎ በመነጋገር መፈታት የሚችሉ እንደሆኑ መገመት አያዳግትም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሃይል የራሱን ሃሳብ ከማቅረብ ውጭ የሌላውን ማድመጥ ላይ ድክመት ስለሚስተዋል ለመተማመንና በመግባባት ችግሮችን ለመፍታት የማያስችሉ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ለዚህም በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶችን ማየት ተገቢ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በአገራችን ከአስተዳደር ወሰንም ሆነ ክልል የመሆን ጥያቄ እስከ ከአካባቢያችን ውጡ ድረስ ያሉት ችግሮች ለግጭት የሚያበቁ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ግጭቶቹን የሚፈጥሩት ሃይሎች ለዘመናት አብረው የኖሩ፣ የተዋለዱና ርስበርስም መግባባት የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ችግሩ ያለው ካለመደማማጥ ነው፡፡

በአጠቃላይ አንድ ነገር ልብ ልንል ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በዘላቂነት አስተማማኝ ሊሆን የሚችለው የህዝቡ ኑሮ ከመሰረቱ ሲሻሻል ብቻ ነው። ከድህነትና ከስንዴ ልመና ሲላቀቅ ብቻ ነው። በአዲስ የዕድገት ጎዳና በአንድነት ተነሳስቶ አገሩን ለመገንባት ሲንቀሳቀስ ብቻ ነው። ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ ጠቃሚ ሃሳቦችን እናፍልቅ፤ እናካፍል፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 27/2011