አለመረዳዳት ድህነትን ያበዛል!

15

“አምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለአምሳ ሰው ጌጡ” የሚል የአገራችን ብሂል አለ፡፡ ይህ አባባል በቀጥተኛ ትርጉሙ መተባበር ያለውን ከፍ ያለ ዋጋ ያሳየናል፡፡ ይህ ደግሞ የአገራችን ህዝብ ዋነኛ ማህበራዊ መገለጫ እንደሆነም ይነገራል፡፡ መረዳዳት በአገራችን የቆየ ባህላዊ ገፅታችን ነውና፡፡

ይህንን ሃሳብ ማንሳቴ ያለምክንያት አይደለም፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ትልቅ ትኩረት ስለተሰጠውና ስራው በዚህ ሳምንትም እንደሚቀጥል ስለሚጠበቀው የጎዳና ተዳዳሪዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ ጥቂት ለማለት ስለፈለኩ ነው፡፡

የጎዳና ተዳዳሪዎችን ህይወት ስንመለከት “እኛ ኢትዮጵያውያን ደግ ነን” የሚለውን በብዙዎች ልብ ውስጥ በእውነትም ሆነ በስህተት የታተመ ማህበረሰባዊ ባህርይ ዳግም እንድናጤነው ያስገድደናል፡፡ በኔ እምነት ደግነትን ራስን ከማሸነፍ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ደግነት ጥቂት ሳንቲም ለደሃ መስጠት ብቻ የሚመስለን ብዙዎች ነን፡፡ ደግነት ግን ራስን አሸንፎ ለሰው ልጅ ሁሉ መልካም ማድረግ መቻል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እጥረቶች እንዳሉብን ይሰማኛል፡፡ ከዚህ አንጻር የጎዳና ተዳዳሪዎችን የምንመለከትበትን መነፅር ማየቱ ተገቢ ነው፡፡

በአዲስ አበባ በእግር ሲጓዙ ህሊናን ሊረብሹ የሚችሉ በርካታ ነገሮችን ሊያዩ ይችላሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ደግሞ አንዱ የጎዳና ተዳዳሪዎች ህይወትና ትዕይንት ነው፡፡ በተለይ አሁን አሁን አዲስ አበባ የጎዳና ተዳዳሪዎቿ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ የመጣባት ከተማ ሆናለች፡፡ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከአንድ ወረዳ ህዝብ ቁጥር ለሚበልጡ ዜጎች የመኝታ ስፍራ በመሆን  ትልቅ “አስተዋፅኦ” እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ የአንዳንድ የአገራችን ከተሞች ጠቅላላ የህዝብ ቁጥር ያክል እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡

እኔም በየዕለቱ የምታዘበውን የጎዳና ትዕይንት በጥቂቱ ላካፍላችሁ፡፡ ጠዋት ጠዋት ወደ ስራ ስገባ በእግር የመጓዝ ልማድ አለኝ፡፡ በዚህም መሰረት አብዛኛውን ጊዜ ከቤት የምወጣው ከማለዳው 12 ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ቢያንስ ሶስት ኪሎ ሜትሮችን በእግር እጓዛለሁ፡፡ ቀሪውን ደግሞ በታክሲ ተሳፍሬ የምሰራበት ቦታ እደርሳለሁ፡፡

በዚህ የዘወትር እንቅስቃሴዬ ያለማቋረጥ ከሚያጋጥሙኝ ጉዳዮች አንዱ ልመና ነው፡፡ በተለይ ፒያሳ ደጎል አደባባይ አጠገብ ስደርስ እጃቸውን የሚዘረጉ የጎዳና ልጆች ማግኘት የዘወትር ገጠመኜ ነው፡፡ “ነብሴ፣ አንድ ብር ሙላልኝ፣ ዳቦ ግዛልኝ፣ እናትዬ፣ ሲስቱ፣ ፍሬንድ ሳንቲም ስጠኝ፣ ወዘተ”፡፡ እነዚህ ቃላት በአካባቢው ላይ ከሚያድሩ የጎዳና ልጆች የሚሰማ የዘወትር የልመና ድምፅ ነው፡፡

በዚህ አካባቢ በርካታ የጎዳና ተዳዳሪ ወጣቶች ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ህጻናትና ሴቶች ናቸው፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ እድሜያቸው ለመውለድ መድረሳቸው የሚያጠራጥር ህጻናት ራሳቸው የህፃናት እናት ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ አብዛኞቹ እዚህ አካባቢ የሚገኙት ህፃናት ሴቶች የልጅ እናት ሆነዋል፡፡ በዚያ የማለዳ ሰዓት ህጻናቱ ጭምር በዚያ አይነት ሁኔታ አድረው ሲታዩ የሰው ልጅ ምን ያህል የኑሮ ልዩነት ውስጥ እንዳለ እንዲገነዘብ ያደርጋል፡፡

እነዚህ የጎዳና ተዳዳሪዎች ደግሞ የሚያዳብሩት ሱስ ለነገ ህይወታቸውም ሆነ ለሌላው ትውልድ ከፍተኛ የስጋት ምንጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ በጎዳና ህይወት ማስቲሽን፣ ቤንዚን መሳብ፣ ሃሺሽ ማጨስ፣ ጫትና ሲጋራ  መጠቀም ወዘተ ገና በለጋ እድሜ የሚለመዱና በስፋትም አገልግሎት ላይ የሚውሉ ሱሶች ናቸው፡፡ በጎዳና ላይ ገና ባለ ሁለት አሃዝ እድሜ ያላስቆጠረ ጨቅላ ህጻን ሲጃራ ሲያጨስ መመልከት የተለመደ ነው፡፡  በዚህ እድሜ የሚለመድ ሲጋራ በጤንነትም ሆነ የወደፊት ህይወት ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ጫና መገመት ደግሞ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

በጎዳና ህይወት የሴቶች ያለእድሜያቸው መደፈርም እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በርግጥ በዚህ መልኩ በመንገድ ላይ ያውም ቁጥጥር በሌለበትና ኃላፊነት የሚሰማው አካል በማይገኝበት ሁኔታ የሴቶቹ መደፈር አዲስ ነገር ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ዜጎች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ መብት ያላቸው መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ህገመንግስትም ሆነ ሌሎች ህጎችና ማህበራዊ እሴቶች ሁሉ ለነዚህ ዜጎችም ሊሰራ ይገባል፡፡ ከሃገራቸው ሃብትም የሚገባቸውን ጥምቅ ማግኘት ይገባቸዋል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ስናስብ ለነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች የተደረገው ትኩረት አናሳ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

ከከተማ ገፅታም አንጻር ቢሆን የጎዳና ህይወት የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል እንዳልሆነ እንመለከታለን፡፡ በተለይ አዲስ አበባ በርካታ ቱሪስቶችና ዲፕሎማቶች የሚመላለሱባት ከተማ ከመሆኗ አንጻር በዚህ መልኩ የከተማዋ ጎዳናዎች የሰው ልጅ ማደሪያ ሆነው መገኘታቸው ትልቅ የገፅታ መጠልሸት እንደሚያስከትል አያጠራጥርም፡፡

ሌላው ደግሞ የጎዳና ተዳዳሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ውሾችን የማሳደግ ባህል አዳብረዋል፡፡ እነዚህ ውሾች ደግሞ አንድም በአግባቡ ስለማይያዙና የምግብም እጥረት ስሚያጋጥማቸው በቀላሉ ለበሽታ የመጋለጥ እድል ይኖራቸዋል፡፡ በዚህ መካከልም የውሾች በሽታ ቢከሰት በቀላሉ ወደ ወረርሽኝ የመቀየር እድል ስለሚኖረው ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው፡፡

ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ በአዲስ አበባ ያለውን ቅዝቃዜ እያንዳንዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሚገነዘበው ነው፡፡ በተለይ ከጥቅምት ወር ጀምሮ በመንገድ ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች እንኳን ተጉዘን የሚሰማን ቅዝቃዜ መቋቋም እስከሚያቅተን ድረስ ከባድ በሆነበት ሁኔታ እነዚያ ህጻናትና ገና በልጅነታቸው የልጅ እናት የሆኑ ታዳጊዎች በዚያ ውርጭ ውስጥ በዚህ መልኩ መኖራቸው የአዲስ አበባ የኑሮ ደረጃ ምን ያህል በከፍተኛ የልዩነት አጣብቂኝ ውስጥ እንዳለች የሚያሳየን ነው፡፡ አንዱ ሌሊቱን ሙሉ በአልኮልና በሱስ ሲናውዝና በሴሰኛ ባህሪው ገንዘብ ሲረጭ፤ ሌላው ደግሞ የሚቀምሰውና የሚልሰው አጥቶ በዚህ መልኩ ለችግር ይዳረጋል፡፡ ሃገራዊ ኃላፊነቱን የዘነጋውም በሌብነት ውስጥ ተዘፍቆ እንዲህ የብዙዎችን ስራ እድል የሚፈጥር ሃብት እየዘረፈና እያባከነ ይኖራል፡፡

ዛሬ በአገራችን ያለውን የሃብት መጠን በአግባቡ ብንጠቀምበት እና የሰው ልጅ  የመረዳዳት ባህል ቢጠናከር ማንም ለችግር የማይዳረግባት ሃገር መፍጠር እንደምንችል መገመት እችላለን፡፡ በተለይ የቢራ ፋብሪካዎቻችንን ብዛትና ምርት፣ በየዕለቱ ለሽያጭ የሚቀርበውን የጫት መጠን ወዘተ ስንመለከት አገራችን ከመሰረታዊ ፍላጎቷ በላይ ለሌሎች የሱስና የቅንጦት ተግባራት ምን ያህል ሃብቷን እያዋለች እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ይህንን ስል ግን መዝናናት አያስፈልግም ከሚል እሳቤ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የሰው ልጅ ከመሰረታዊ ፍላጎቱ በተጨማሪ መዝናናት ይገባዋል፡፡ ይህ ባይሆን አሁን የደረሰበት የእድገት ደረጃ ላይም ለመድረስ በተቸገረ ነበር፡፡ ነገር ግን ከልክ ያለፈ የቅንጦት እና ከዚያም አልፎ ደግሞ ራስን በሚጎዱ ሌሎች ሱሶች የሚወጣው ወጪ በዚህ ልክ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያድግ ከሆነ ጤናማ የማህበራዊ ህይወት አለ ለማለት አይቻልም፡፡

በሌላ በኩል የአገራችን ህዝብ በመስጠት የሚታማ እንዳልሆነም ይነገራል፡፡ በተለይ ዘወትር በበዓላት ወቅት እና ሰሞን ለደሃ ለመመፅወት ሳንቲም ዘርዝሮ በየጎዳናው ላይ እያንጠባጠበ ጎንበስ ቀና እያለ የሚውል በርካታ ኢትዮጵያዊ እንመለከታለን፡፡ ያም ሆኖ ግን የጎዳና ተዳዳሪዎች በዚህ መልኩ የመረዳት እድላቸው አናሳ ነው፡፡ በዚህ የተነሳም አብዛኞቹም በሌብነት ተግባራት ይሰማራሉ፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ከየሆቴሎችና ግለሰቦች ቤት የሚሰባሰብ ትርፍራፊ ምግብ በመለቃቀም ህይወታቸውን ይገፋሉ፡፡

በአጠቃላይ የጎዳና ህይወት ቀላል የማይባል የማህበራዊ ቀውስ እየሆነ ይገኛል፡፡ በተለይ ከ80 ሺህ በላይ ዜጎች በጎዳና በሚገኙባት የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ለነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ትኩረት ካልተሰጠ በቀጣይ ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአዲስ አበባ ብቻ ከ50 ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ለነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ለሁለንተናዊ እድገት አስተዋፅኦ የሚኖረው በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

በርግጥ በአዲስ አበባ ከዚህ ቀደም የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማሰባሰብና በአንድ ማዕከል በማስገባት ለማደራጀት የተሞከረበት ሁኔታ እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ ሆኖም ችግሩ በዘላቂነት ሊፈታ አልቻለም፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያች ይነሳሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የችግሩን ባለቤቶች ህይወት በዘላቂነት ሊለውጥ የሚችል ዘላቂ የስራ እድል ከመስጠት ይልቅ ጊዜያዊ እርዳታ ላይ የተመሰረተ ድጋፍ መደረጉ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች ፍልሰት በየጊዜው እየጨመረ መሄድና አንዱ ሲሄድ ሌላው እየተተካ ችግሩ ሊቆም አለመቻሉ፣ በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ የተደረገላቸውም የጎዳና ተዳዳሪዎች ከማገገሚያ ማእከላት እየጠፉ መልሰው ወደ ጎዳና ህይወት መግባት፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ለሱስ የተጋለጡ በመሆኑ ከዚህ ለመላቀቅ አስቸጋሪ ስለሚሆንባቸው፣ የጎዳና ተዳዳሪዎቹ በትናንሽ ስራዎች ላይ ለመሰማራት አለመፈለግ የሚሉት ዋና ዋና ምክንያችም ተደርገው ይቀርባሉ፡፡

ሰሞኑን መንግስት የጀመረው እነዚህን የጎዳና ተዳዳሪዎች በዘላቂነት የማደራጀትና ምርታማ የሚሆኑበትን መንገድ የማመቻቸት እንቅስቃሴ ግን ትልቅ ተስፋ ያለው ይመስላል፡፡ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ክብርት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት እነዚህን የጎዳና ተዳዳሪዎች በአዲስ መልኩ ለማደራጀት የሚያስችል ትረስት ፈንድ መቋቋሙም ይፋ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመነሻ የሚሆን አንድ መቶ ሚሊየን ብር በመመደብ ሌሎች የገቢ ምንጮችንም ለማጠናከርና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የጎዳና ተዳዳሪነት ችግርን ለመፍታት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማም የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይ ወጣቶች፣ ክልሎችና የፖለቲካ አመራሩም ለዚህ ስራ ቁርጠኛ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡ በከተማዋም ስድስት ማዕከላት መለየታቸው ታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የጤና ባለሙያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮም የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደማዕከላቱ መግባት ጀምረዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶች የተነደፉ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድም በአመት እስከ 450 ሚሊየን ብር በመሰብሰብ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ድጋፍ ለማበርከት የራሱን ድርሻ ወስዷል፡፡ ከዚህም ባሻገር አርቲስቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም የሚሳተፉበት ኮንሰርት እንደሚዘጋጅ ታውቋል፡፡ መላው ህብረተሰብም ድጋፍ የሚያደርግባቸው የባንክ ሂሳብ ቁጥርና የኤስ ኤም ኤስ መልዕክት ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ መሰረት በኤስ ኤም ኤስ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ዜጎች ሁሉ በ 6400 ላይ “A” ብሎ በመላክ  ችግሩን የራስን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚቻል የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ገልፀዋል፡፡

እንግዲህ ኢትዮጵያዊነት ወይም አገርን መውደድ ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱ አሁን የተጀመረው የድጋፍ መንገድ ነው፡፡ በየመንገዱ ጥቂት ሳንቲሞችን ከመስጠት በዘለለ ዘላቂ ድጋፍን ለማድረግ እንዲያግዝ አሁን እነዚህን የጎዳና ተዳዳሪዎች ከመንገድ ላይ አንስቶ ዘላቂና የተረጋጋ ህይወት እንዲመሰርቱ ለማድረግ እያንዳንዱ ዜጋ እጁን መዘርጋት አለበት፡፡

የምንሰጠው ነገ ከምናመልከው ፈጣሪ አገኛለሁ በሚል ሃይማኖታዊ መንፈስ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው” በሚለው የመቄዶንያ መርህ ተመስርተን ሰዎችን ለመርዳት መነሳት ተገቢ ነው፡፡  የሰው ደግነት የሚለካው ያለንን ስላካፈልን ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያም በዘለለ ለሰዎች በጎ መስራትን መለማመድ ይገባል፡፡ እነዚህ የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎች “የኔም ወንድሞችና እህቶች ናቸው” ብሎ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ እናም “እኔ ዛሬ ባልበላም ነገ አገኛለሁና ይህንን ለነሱ ባደርግ ይህ ለኔ ይበቃል” የሚል የበጎነት አስተሳሰብ ልናዳብር ይገባል፡፡

“አምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ፣ ለአምሳ ሰው ጌጡ” እንደሚባለው ሁላችንም ያለንን ከወረወርን ነገ እኛም በወጣንበት ስፍራ ሁሉ አይናችን ጉስቁልናን እና የሰው ልጅ ችግርን አይመለከትም፣ ህሊናችንን የሚያደፈርስ የሰው ልጅ የአኗኗር ገጽታም አናይም፡፡ በመሆኑም ባለን አቅም ሁሉ እነዚህን የጎዳና ልጆች ለመደገፍ ከልብ እንነሳ፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 27/2011

ውቤ ከልደታ