ዘመንና ፎቶግራፍ

17

«ፈገግ… አዎ… ሳቅ…ሳቅ» ወዲያው አጠገቤ ይደርስና ደግሞ «ከአንገትሽ ቀና በይ እንጂ» እያለ አገጬን በእጆቹ ቀና አድርጎ፤ ከፊት ለፊቴ ይቆማል። ከወገቡ ሰበር ከአንገቱ ወደ እኔ ሰደድ ብሎም የካሜራውን ጉጥ ይጫነዋል። እንደ መብረቅ ብልጭ ከሚለው ብርሃን ጋር «ቀጭ» የሚል ድምጽ ይወጣል። ከዚያ ደግሞ ለሌላ ዓይነት አነሳስ «ወዲያ ሂጂ…አዚያ ተቀመጪ… ይንን ያዢ… እንዲህ ሁኚ» ይለኛል።

አንዴ በርከክ፣ ሌላ ጊዜ ከወገቡ ሰበር፣ ደግሞ ወደኋላ ሰገግ እያለ ከካሜራው ጋር ሲጫወት ገጹም ከእንቅስቃሴው ጋር፤ ፈገግ ኮስተር ይላል። የእርሱን ስሜት ተከትሎ ፊቴ አብሮት ሳቅ፤ ቅጭም ይላል። እንዲህ ሳደርግ ወዲያው አጠገቤ ይደርስና «ለምን ትኮሳተሪያለሽ ሳቂ እንጂ… ደግሞ አንገትሽን አትቅበሪ» ከሚል ተግሳጽ ጋር እጁን ያሳርፍብኛል።

ይህንን ቅጽበት እወደዋለሁ፤ ፎቶው ቀርቶ ይህንኑ ቢደጋግመኝ እመኛለሁ። እርሱ ግን ወደስራው ይመለሳል… እኔም በንዴት እንደ ኤሊ ከአንገቴ እሰምጣለሁ። ደግሞ ከሌላ ተግሳጽ ጋር እጁን ከአንገቴ ያሳርፋል።

«አያቴ አንዴ ፎቶ እንነሳ» የከበቡኝ የልጅ ልጆቼ፤ ከትዝታዬ መለሱኝ፡፡ መቼ እንደተነሳን በውል ላውቅ አልቻልኩም፤ አንዷ እኔን ተደግፋ፣ ሌላኛዋ ከንፈሯን አሞጥሙጣ፣ ወንዱም ምላሱን አውጥቶ፣ ሌሎቹም ጣታቸውን አንጨፍርረው፣… «ተዘጋጁም…ሳቁም» ሳይባል ድንገት ተነሳን ብለው እንደ አመጣጣቸው ግር ብለው ከአጠገቤ ራቁ።

እንደ ድሮው በእድሜና በቁመታቸው ተሰድረው እንድንነሳ እጠብቅ ነበር፤ እነርሱ ግን በእንጨት መሳይ ነገር በወደሩት ስልካቸው በቅዕበት ውስጥ «ፎቶ ተነሳን አሉኝ»። ሌሎቹም በየተራ እኔን  እየከበቡና እንዳሻቸው ፊታቸውን እየቀያሩ ስልካቸውን ጠነቋቁለው ሲሄዱ የሚያደርጉት ግራ ገብቶኝ ነበር የማያቸው።

ዘመን ሄዶ ዘመን ሲተካ፤ እርሱን ፎቶ እኔን አያት አድርጎናል። «አሻ ገዳዎ በል አሻ ገዳዎ…» የሚለው የሰርግ ዘፈንማ ከግድግዳው ከተሰቀለው የሰርጌ ፎቶ ጋር አብሮ ወደኋላ ያኖረኝ ከያዘ ሳምንት አልፎኛል። ምድሪቷን ለመሰናበት እርሱ ቢቀድመኝም ትናንትን እንዳለ ከወረቀት ያተመው ፎቷችን ግን ትዝታዬን ቁልጭ አድርጎታል።

አንዴ ከዛፍ ላይ ሌላ ጊዜ ከአበቦች መሃል፣ ከዚያ ደግሞ ሳሩ ላይ ተንጋለን፣ ደግሞ እየተሯሯጥን፣… የተነሳናቸው የሰርጋችን ፎቶ ከዘመን ተሽለዋል። የተፈጥሮ ከሃዲነት ጥሎኝ ከሄደው መልኬና ባሌ ጋር ይመሳሰልብኛል፤ የፎቶግራፉ አዛኝነት ልቤን ሲነካውም እንባዬ ልውጣ አልውጣ እያለ ይታገለኛል።

የልጄ ልጅ ሦስት ጉልቻዋን ስትመሰርት፤ አያት ነኝና እንደወጉ ጉልበቴን ተስሜ መርቄ ለመሸኘት ተሰይሜያለሁ። ከባለ ሦስት በአራቱ ጥቁርና ነጭ ጉርድ ፎቶ ግራፍ የጀመረው ዕውቅና ከፎቶ ቤቱ ማድመቂያነት አልፎ ዛሬ የልጅ ልጅን ወግ እስከማየት አድርሶናል።

ደጋሿ ልጄ ልጇን ልትድር ነውና ከቀልቧም አይደለች፤ ሌሎቹም ራሳቸውን አሰማምረው ወደ ጭፈራውና ጨዋታው ሄደዋል። እኔም የሚንቆረቆረው የሰርግ ዘፈን ይዞኝ ከትዝታ ባህር እያሰመጠኝ ከግድግዳው ላይ ከቀረው ወጣትነታችን ጋር ጨዋታዬን እይዛለሁ።

ከአምስት አሥርት ዓመታት በፊት ለ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ጉርድ ፎቶ ለመነሳት ከትንሿ ፎቶ ቤት ሄድኩ። በቀጠሮዬ መሰረትም በሦስተኛ ቀኑ ወደዚያው ሲመለስ ግን ባየሁት ግራ ተጋብቼ ነበር። ፎቶ አንሺውን ለመጀመሪያ ጊዜ ከንዴት ጋር አተኩሬ ያየሁትም የዚያኔ ነበር።

«ይሄ የማን ፎቶ ነው?» አልኩት ያየሁትን ወንዳወንድነት ከመጤፍ ሳልቆጥር። ግራ በተጋባ ገጽ «ያንቺው ነዋ እመቤት» አለኝ በትህትና፤ እኔ ግን «እኔ አይደለሁም» ነበር መልሴ። ክርክራችንም በተበላሸው ፎቶዬ ምትክ ሌላ በማንሳት ስምምነት ተቋጭቶ ተለያየን።

እንደተባባልነውም በሳምንቱ ከዚያች ፎቶ ቤት ተገኘሁ፤ በህይወቴ እንደዚያን ቀን ራሴን ለማሳመር የተጨነቅኩበትን ሁኔታ አላስታውስም። የማማሬ ምክንያት ሳምንት ሙሉ ሳሰላስል ለቆየሁት ለዚያ ፎቶ አንሺ ይሁን ለምነሳው ፎቶ አላውቅም። ብቻ በእርምጃዬ ሁሉ ስደነቃቀፍ፣ በንግግሬ ስርበተበት፣ በእይታዬም ስሽኮረመም ነበር ከቀጠሮዬ የደረስኩት።

ካሜራውን ከአንገቱ እንዳንጠለጠለ ባንኮኒውን ተደግፎ እየጠበቀኝ ነበር። ከቀድሞ ይልቅ ዛሬ እንዳማረበት ስመለከት እሱም እንደእኔው ሲያስበኝ ከርሞ ይሆናል ከሚል ተስፋ ላይ ደረስኩ። የመቀጫ ፎቶውንም በአቅራቢያ ካለ መናፈሻ ሊያነሳኝ እንዳሰበ ነግሮኝ እንድከተለው ጠቆመኝ።

አንድ ሁለት ፎቶ ካነሳኝ በኋላ ከቀዩ አበባ ቀጥፎ ጆሮዬ ላይ ሲሳካልኝ የተሰማኝ ስሜት ዛሬም እንደ አዲስ ይሰማኛል። ፍቅር ከፎቶ አንሺ ከጆሮ ተነስቶ እንደሚጠነሰስ ያወቅኩትም የዚያኔ ነበር። ከዚያማ ልባችን በፍቅር፣ ትንሿ ፎቶ ቤት በአንዲት ሴት ፎቶዎች፣ ግባችን በትዳር፣ ጎጇችንም በልጆች ተሞላች።

እየተንጫጩ ፎቶ ለመነሳትና ሰላም ሊሉኝ የሚመጡት ፍሬዎቼ ደግመው ከሰመመኔ መለሱኝ። አፍታም ሳይቆዩ ደግሞ ለትዝታዬ ጥለውኝ ሄዱ። ዓይኔም ቀልቤ ከተሰቀለበት ፎቶ መልሶ አደረሰኝ። ከእኛ ፎቶግራፍ አጠገብ የልጄ እና የባለቤቷ ከዚያ ደግሞ የአዲሲቷ ሙሽራ ፎቶ፤ እንደየ ትውልዱ ከግድግዳው ተሰድሯል።

በሚዜዎቿ ታጅባ በአብሮ አደጎቿ እየተኳለች ያለችውን ሙሽራ ፎቶ ሳይ ተገረምኩ፤ በእኛ ጊዜ ፎቶ በሰርጉ ስነ-ስርዓት ከታደሙ ወዳጅ ዘመድ ጋር እንነሳ ይሆናል እንጂ ቀድሞ መነሳቱን አናውቅም ነበር። አሁን የማየው ፎቶ ግን ሙሽሮቹ ከሰርጉ ቀደም ብለው የተነሱት ነው። «የመስክ ፎቶ ልንነሳ ነው» ሲሉኝ ወደየትኛው ክፍለ ሃገር እንደሚሄዱ ጠይቄያቸው ስቀውብኛል።

ለካስ እንደኛ ጊዜ ለመስክ ፎቶ ከተማ መልቀቅ ቀርቷል። በመንገድ ላይ እንደ ቀልድ የተነሱት ፎቶ ጣጣውን ጨርሶ ሲታይ፤ ቤተ-መንግሥት ከመሰለ ያማረ ቤት ውስጥ፣ ከደን መሃል፣ ከሚፈስ ወንዝ አጠገብ፣ ከእንጨት ድልድይ ላይ፣… የሚገርም ነው። ትዳር ከሁሉ ቀድሞ በፎቶ ከመጀመሩም በላይ አንድ ቦታ የተነሱት ፎቶ በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ እንዲህ ማማሩ ግርም ይለኛል።

ፎቶ አንሺው ባለበቴ በሰርጋችን ዕለት በባልደረቦቹ ከመነሳቱ ባሻገር፤ ያ ሁሉ መልክና መዘናከት በእርጅና እስኪተካ የዘመኑን ግማሽ ያሳለፈው እኔን ፎቶ ሲያነሳ ነበር። አኳዃኔን ለፎቶው እንደሚሆን እንዳደርግ የሚነግረኝ ድምጹ፤ ደግሞ ፎቶው እንዲያምር ሲንበረከክ፣ ሲቆም፣ በደረቱ መሬት ላይ ሲተኛ፣ ወዳለሁበት ሲንጠራራ፣ ከዚያ ደግሞ ከጨለማው ክፍል ፊልሙን ለማጠብ ያለው ቁም ስቅል ዛሬም ያለ ያህል በምናቤ ይታየኛል።

የዛሬዎቹ ፎቶ አንሺዎችማ መቆም መቀመጡንም አያውቁትም። ጊዜ ደጉ የፈለጉትን በእጃቸው እንደ ስዕል ጨማምረው ማበጃጀቱን አድሏቸዋል። የሚጫኑት የካሜራው ማንሻም ብርሃኑን አያፈልቅም። «ተዘጋጁ… ሳቁ… ቀና በሉ…» ማለቱም አያስፈልግም።

ልጆቼና የልጆቼ ልጆችም በዘመናቸው ቆመው የእኛን ዘመን ፎቶ እና አነሳስ እያዩ ይስቃሉ። እኔ ግን ዛሬን ከትናንት ዘመንንም ከዘመን የማዛምድበት ድልድዬ፤ ጥሎኝ የሄደውንም የምመለከትበት መነጽር ነውና እንደ ዓይኔ ብሌን ያሳሳኛል። ጊዜን ከጉዞው መግታት አጋጣሚንም ቆም አድርጎ እስኪበቃ የማጣጣም ስልጣን ባይኖረንም ትዝታውን አትሞ ለዘለዓለም ማቆየት በራሱ ማጽናኛ ይሆናል። ትዝታዬ ከደከመው ዓይኔ ጋር ሊያስነባኝ ትግል ይዟል፤ ውስጤም ምድር ላይ ከመኖር የሚቀረው ፎቶ ብቻ ነው ይለኛል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

በብርሃን ፈይሳ