ባንኩ ከስጋት ተላቆ ሥራውን እንዲጀምር ዞኑ ጥሪ አቀረበ

45

አዲስ አበባ፡- በአሁኑ ወቅት የተረጋጋ ሰላም እየተፈጠረ ባለበት በምዕራብ ወለጋ ዞን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራውን ያለምንም ስጋት በአግባቡ እንዲጀምር የዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ዘሪሁን ተክሌ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ በዞኑ ውስጥ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ያስቸገረው የባንኮች ሥራ አለመጀመር ነው፡፡  በአሁኑ ወቅት ሰላምና መረጋጋት የተፈጠረ በመሆኑ ቀድሞ የነበረው ዘረፋና የመንገድ መዘጋት አይስተዋልም፡፡ አንዳች የሚያሰጋ ነገር ባለመኖሩም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለምንም ስጋት የገንዘብ እንቅስቃሴውን ማድረግ ይችላል፡፡

እንደ አቶ ዘሪሁን ገለጻ፤ የመንግሥት ሠራተኛውም በአሁኑ ወቅት በሥራ ገበታው ላይ የተገኘ ሲሆን፣ ህብረተሰቡም በሰላም ወጥቶ እየገባ ነው፡፡ አዳዲስ አመራሮችም በዞንና በወረዳ ደረጃ ተመድበው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

‹‹ሌሎች እንደ አዋሽና መሰል የግል ባንኮች ምንም እንኳ በቂ ገንዘብ ባይዙም ሥራ ላይ ናቸው፡፡››ያሉት ኃላፊው፣ በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ የሌለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ነው›› ብለዋል፡፡ በዚህ የተነሳም ለሠራተኛው የወር ደመወዝ መክፈል እንዳልተቻለ ጠቅሰው ባንኩ ስጋቱን ወደ ጎን በመተውና ገንዘብ ወደ ባንክ በማስገባት ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ሊያደርግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

‹‹የመንግሥት የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ  አስከፊ በሆነ ችግር ወቅት ህብረተሰቡን ማገልገል ካልቻለ ወደፊት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚኖረው አመኔታ ይቀንሳል፡፡›› ያሉት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ፣ የባንኩ አመራሮች በአስቸኳይ ዕርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

እርሳቸው እንደተናገሩት፣ መምህራን አሁን የዕረፍት ጊዜያቸው እንደመሆኑ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ወዳጅ ዘመዶቻቸውን መጠየቅ ይፈልጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ የጥር ወር ደመወዛቸውን ካላገኙ ወደየትም መንቀሳቀስ አይችሉም፤ ይህ ደግሞ ሌላ የጸጥታ ችግር ሊያስነሳ ይችላል፡፡

በተመሳሳይ ዞኑ ቡና አብቃይ ወረዳዎች ያሉት እንደመሆኑ በኦሮሚያም የታወቀ እንዲሁም ቡናውን በማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ግንባር ቀደሙ ነው፤ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የቡና ግብይት ጊዜ ነው፡፡ ይሁንና ነጋዴው ከባንክ የሚያወጣው ገንዘብ የለም፡፡ በመሆኑም አርሶ አደሩ ደግሞ ቡናውን ወደ ገበያ አውጥቶ በተመጣጣኝ ዋጋ መሸጥ አይችልም ማለት ነው፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ ካልሸጠ ደግሞ የመንግሥትን ግብር ለመክፈል ይቸገራልና ይህ ሁኔታ ሊፈታ ይገባል፡፡

‹‹መንግሥት በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል፤ ህብረተሰቡ እንዳይቸገርና የንግድ እንቅስቃሴውም እንዳይቆም በጥቂት ቀናት ውስጥ ይስተካከልልን፡፡›› በማለትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በምዕራብ ወለጋ ዞን የህዝብ ትራንስፖርት እንደልብ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉ ይታወሳል፡፡ በዚህ የተነሳም የህብረተሰቡም እንቅስቃሴ የተገደበ ከመሆኑም በተጨማሪ በዞኑ ከሚገኙ ስድስት ያህል ባንኮችም መዘረፋቸው ይታወቃል፡፡

በአካባቢው ከተፈጠረው የሰላም መናጋት ጋር በተያያዘ ከዞኑ አዋሳኝ ቦታዎችና ጎረቤት ከሆነው ከማሺ ዞን በርካታ ተፈናቃዮች ወደ ዞኑ ገብተው በመጠለያ ውስጥ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት ግን ሰላም መስፈኑን ከዞኑ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡

የዞኑን ጥያቄ መሰረት በማድረግ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በልሁ ታከለን የጠየቅናቸው ቢሆንም፤ ለጥያቄው በምላሽ ማግኘት የሚቻለው ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 28/2011

በአስቴር ኤልያስ