በከተማዋ ከ1ሺ330 በላይ የሸማቾች  ሱቆች ግንባታ ሊጀመር ነው

37

አዲስ አበባ ፡- በአዲስ አበባ የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ  ማኅበራትን ለማጠናከርና ለነዋሪዎቹና ለአባላቱ የቅርብ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል 1ሺ 332 የሸማቾች ሱቆችን ለመገንባት ቦታዎች ተለይተው ወደ ግንባታ እየተገባ መሆኑን የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አረጋ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ ሱቆቹ የሚገነቡት በ243 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ሲሆን፤ የግንባታውን ወጪ  የሚሸፍኑት የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ይሆናሉ፡፡

ተጨማሪ የሸማቾች ሱቆች የሚገነቡት ለ1ሺህ 500 አባወራዎች ቢያንስ አንድ የሸማቾች ኅብረት ሥራማኅበር ሱቅ ያስፈልጋል በሚል የከተማው መስተዳድር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት መሆኑን አቶ ሲሳይ አስታውቀዋል፡፡ ሱቆቹ እያንዳንዳቸው 50 ካሬ ሜትር ስፋት እንዲኖራቸው እንደሚደረግ  የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ኮንስትራክሽን ቢሮ ያደረገውን ጥናት ዋቢ አድርገው የጠቀሱት አቶ ሲሲይ፤   ከነመደርደሪያቸው እስከ 183 ሺ ብር ድረስ ወጪ እንደሚደረግባቸውም ገልጸዋል።

በከተማው 143 መሠረታዊ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንደሚገኙና 325ሺህ ነዋሪዎችን በአባልነት አቅፈው እንደሚንቀሳቀሱ ተጠቁሟል፡፡ ካፒታላቸውም ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ታውቋል።

አዲስ ዘመን ጥር 28/2011

በኃይለማርያም ወንድሙ