ወደ ድጋፉ እንመለስ !

17

ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ያስተሳሰረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ተቀዛቅዞ ቆይቶ ከቅርብ  ጊዜ ወዲህ ወደ መድረክ እየመጣ ነው፡፡ የግድቡ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተለያዩ  መድኮችን እያደረገ ነው፡፡ በቅርቡም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ከዲያስፓራው ጋር መክሯል፡፡

ግንባታው ህብረተሰቡ በሚጠበቀው ልክ አለመሆኑ ይታወቃል፡፡ ግንባታው ደረሰ እየተባለ ለህብረተሰቡ ይደርስ የነበረውም መረጃ የተሳሳተ ነበር፡፡ ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን ለመገንባት የተዋዋለው ሜቴክ የወሰደው ገንዘብና ግንባታው የደረሰበት ደረጃ በጣም የተራራቀ መሆኑ ነው፡፡

መንግሥት ለግንባታው የተመደበው ገንዘብ አባክነዋል በመባል የተጠረጠሩትን  የቀድሞ የሜቴክ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ በማጣራት ክስም እየመሰረተባቸው ይገኛል፡፡ ሜቴክ እንዲያካናውን ተሰጥቶት የነበረው የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራም ለሌሎች ተቋራጮች ተሰጥቷል፡፡

አሁን ሥራ የሚፈልገው በግንባታው መጓተት እና በባከነው የሀገር ሀብት ሳቢያ የተቀዛቀዘውን የህብረተሰቡን ተሳትፎ ወደ ቀድሞ መስመሩ መመለስ ነው፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት  የህዝቡን የድጋፍ ስሜት መልሶ ለማምጣት የውይይት መድረኮችን እያዘጋጀ የሚገኘውም ለእዚሀ ነው። ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው፣ እስከ አሁን አራት መድረኮች ተዘጋጅተዋል፤ መጠይቆች ተበትነው ግብረ መለስ እየተሰበሰበ ይገኛል።

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት፣ ለዲያስፖራው ማህበረሰብ፣ ለተለያዩ አደረጃጀቶችና የህዝብ ክንፎች እንዲሁም ለሌሎች በተዘጋጀው መጠይቅ 98 በመቶ የሚሆኑት  የውይይት መድረኮቹ  አስፈላጊና ህዝባዊ ተሳተፎውንም ለመመለስ የሚያግዙ ናቸው ተብሏል።

ከመድረኮቹ መረዳት የተቻለው ህብረተሰቡ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ አሉታዊ አስተሳሰብ እንደተፈጠረበትና ተስፋ መቁረጥ እንደታየበት ነው፡፡ ይህንንም ለማስተካከል ጽህፈት ቤቱ  ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ግንባታው እየተካሄደ መሆኑን ለማሳየት ሞክሯል፡፡ አሁን ለውጥ እየመጣ መሆኑንም ነው የሚገልጸው፡፡

እንደሚታወቀው የግድቡ ችግር ያለው ሲቪል ሥራው ላይ አይደለም፡፡ ሜቴክ ይዞት የነበረው ኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አሁን ለሌላ ተቋራጭ ተሰጥቷል፡፡ በእዚህ ላይ መንግሥት ወሳኝ ዕርምጃ ወስዷል፡፡

ከተፈጠረው ችግር አኳያ  የህብረተሰቡ ተሳትፎ መቀዛቀዙ የሚጠበቅም ነው፡፡ አሁን መንግሥት የተፈጠረውን ችግር ግልጥልጥ አድርጎ ማውጣቱን እና ግንባታው ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ሊሸጋገር የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠሩን ትልቅ ስፍራ መስጠት ይገባል፡፡ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም ግድቡ ብዙ ዋጋ  የከፈልንበት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ግንባታው ለማጠናቀቅ ከመቼውም ጊዜ ባለቀ በመልኩ በትኩረት መሥራት ያስፋልጋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት  በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ህዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን የሞት ወይም የሽረት ጉዳይ መሆኑን  አስገንዝበዋል። ግንባታውን ፈጥነን ካላጠናቀቅን እና ሥራው የሚንከባለል ከሆነ  ኪሳራው በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችልም ስጋታቸውን አስገንዝበዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰቢያ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ ስናደርግ የቆየውን ድጋፍ መልሰን እንድናጠናክር የሚያደርግ ነው፡፡ ግንባታውን የለውጡ ሥራ አካል ማድረግም ይገባል፡፡ይህንንም በማድረግ ለውጡን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የጀመረውን የህብረተሰቡን የተቀዛቀዘ የድጋፍ ስሜት መልሶ ለማምጣት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ የጀመራቸውን መድረኮች በየደረጃው ማውረድም ያስፈልጋል፡፡

መገናኝ ብዙሃንን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን፣ ታላላቅ ሰዎችን በመጠቀም ማስታወቂያዎችን መሥራት፣ የውይይት መድረኮችን ማካሄድ ይኖርበታል፡፡ ይህንንም በመገናኛ ብዙሃን ማስተላለፍ ይኖርበታል፡፡

ግድቡን ማስጎኘቱንም እንደገና መጀመር ይኖርበታል፡፡ ሰው በሰማው ልክ ብቻም ሳይሆን ባየው ልክም የሚናገር እንደመሆኑ ግድቡን የማስጎብኘቱ ሥራ መጀመር ይኖርበታል፡፡ ለዓይን መግለጫ እንዲሆንም የመገናኛ ብዙሃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ፣ አርቲስቶች ግንድቡን በአስቸኳይ እንዲገነቡ ማድረግ ይገባል፡፡

ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ለማስባሰብ የተዘጋጁ ዋንጫዎች እና ችቦም ወደ ሥራቸው እንደሚለሱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ ዋንጫዎችና ችቦዎች ምን ያህል ገንዘብ መሰብሰብ እንደተቻለ ይታወቃል፡፡ ምን ያህል ግንባታውን በህዝቡ ልብ ውስጥ ይበልጥ ማሳደር እንደታቸለም ይታወቃል፡፡

መንግሥት የግድቡ ግንባታ የኢኮኖምም የሞራልም ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጿል፡፡ ለመንግሥት ያለንን አጋርነት ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ራእያችን አርገን ይዘነው ለቆየነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ማድረግ የሚጠበቅብንን ድጋፍ ለማድረግ ጊዜ መውሰድ አይኖርብንም፡፡በቆየን ቁጥር ግንባታው እንዲጓተት እንዳደረግን አርገን ማሰብ ይኖርብናል፡፡  በመሆኑም ግንባታው የሞት የሽረት ጉዳይ መሆኑን አውቀን ወደ ድጋፉ መመለስ ይኖርብናል፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 28/2011