የሞራልና ኢኮኖሚ ልእልና ማግኛ

15

የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል አገራዊ መግባባት እንዲጎለብት ያደረገ ፣ የሁሉንም ድጋፍ ያተረፈ ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ የፖለቲካ አመለካከት፣ የሃይማኖት ልዩነት፣ የመኖሪያ ቦታ (ከአገር ውስጥም ከውጭም) ርቀት ሳይገደበው፣ የብሄር፣ የዕድሜ ወይም የጾታ ልዩነት ሳይታይበት በአንድነት ድጋፉን የቸረው ነው።

አንድ አባት በአንድ መድረክ ላይ ለዚህ ግድብ ድጋፍ የማያደርጉት «በማህጸን ያሉ ሕፃናት እና በመቃብር ያሉ ሙታኖች ብቻ ናቸው» ሲሉ መግለጻቸውም ኢትዮጵያውያን በሙሉ ድጋፋቸውን ያደረጉለት ግድብ መሆኑን ያመለክታል።
ይህ የባለብዙ ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት የሲቪል ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ቢሆንም ፣በኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው ክፉኛ መጓተት ሳቢያ የሚጠበቅበት ደረጃ ላይ ሊደርስ አልቻለም፡፡የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራውን እንዲያከናውን ኮንትራት የወሰደው ሜቴክ ፈጽሟል በተባለው ብክነት እና በፈጠረው ማጓተት ሳቢያ ነው መጓተቱ የተከሰተው፡፡

ይህ ህዝብ እንደ ዓይኑ ብሌን የሚጠብቀው ፕሮጀክት ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ የተገነዘበው መንግሥት ሜትክ ሥራውን ለሌላ ተቋራጭ እንዲያስረክብ፣ ለግንባታው የተመደበው ሀብት እንዲባክን አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ አካላትም ለህግ እንዲቀርቡ እያረገ ይገኛል፡፡ ግንባታው ሊፋጠን የሚችልበትን መንገድ ሁሉ አመቻችቷል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከግድቡ ግንባታ መጓተት እንዲሁም የሀብት ብክነት ጋር በተያያዘ በህዝቡ ዘንድ የተፈጠረው መቀዛቀዝ እንዲወገድ በመንግሥት በኩል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ የህብረተሰቡን ስሜት ለማነቃቃት የግድቡ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የተለያዩ መድረኮችን እያዘጋጀ ይገኛል። ከመድረኮቹ መካከልም ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ፣ ከተለያዩ አደረጃጀቶችና የህዝብ ክንፎች ጋር ያደረጋቸው ሰፊ ውይይቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህም ጥሩ ገብረ መልሶች ተገኝተዋል።

ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ እንዳለውም፤ ግድቡ ከተጀመረበት ከ 2003 ዓ.ም ጀምሮ ከህዝብ ተሳትፎ ብቻ 12 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል፤ ከዚህ ውስጥ ዲያስፖራው ከ 49 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በቀጣይም ይህ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተጠየቀ ሲሆን፣ፖለቲካውንና የግድቡን ግንባታ ነጣጥሎ ማየት እንደሚገባም ተመልክቷል።

እስከአሁን ድረስ «ለግድቡ ግንባታ ገንዘብ አዋጡ» ከመባል ውጪ ግልጽነት የተላበሰ ወይይት አድርገው እንደማያውቁ የመድረኮቹ ተሳታፊዎች ጠቅሰው፣ ይህ ድብብቆሽ ደግሞ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል አድርጓልም ሲሉ ጠቁመዋል። ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ያለፈውን አንዳለፈ በመቁጠር አሁን በአዲስ መንፈስና ወኔ የጀመርነውን ከግብ ማድረስ አለብን የሚል መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ህዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን የሞት ወይም የሽረት ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በ 80 ቢሊዮን ብር የተጀመረው ፕሮጀክት በመጓተቱ ምክንያት በትንሹ ከ60 በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከቱሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰው ፤ አሁንም ሥራው የሚንከባለል ከሆነ ኪሳራው በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል ስጋታቸውን አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ኢንቨስት ከተደረገው ውስጥ አንድ አምስተኛው የባንክ ወለድ እየተከፈለበት መሆኑን በማስታወስ የመጠናቀቂያ ጊዜው እየጨመረ በሄደ መጠን ወለድ እየተከፈለ ፕሮጀክትን እየተሸከሙ መሄድ እንደሚከተል ይናገራሉ፡፡

ሥራው ላይ ጠንካራ የሆነ ግምገማና ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ያብራራሉ። ‹‹ግንባታውን ማጠናቀቅ ለእኛ ኢትዮጵያውያን የሞት ወይም የሽረት ጉዳይ ነው» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ «የግድቡን የተዳከሙ ፕሮጀክቶች ለሌሎች በመስጠት ሙሉ ጊዜን ለሥራው በማዋል በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ለማጠናቀቅ እንደሚሠራ ነው ያረጋገጡት፡፡

ኢትዮጵያውያን ሀብታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና እውቀታቸውን ለግድቡ ሲያውሉ መቆየታቸውን ጠቅሰው፣ ግንባታው መጠናቀቅ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ሁለቱን ተርባይኖች በ2013 ዓ.ም አጋማሽ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረገም አመልክተዋል፡፡
መንግሥት በግንባታው ላይ የያዘውን ራእይ ከግብ በማድረስ እንደሚያሳካ አረጋግጠዋል፡፡የምክር ቤት አባላትም ግንባታው ላይ የተጠናከረ ክትትል ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹የህዳሴ ግድብን መጨረሳችን የኢኮኖሚና የሞራል ልዕልናን እናገኛለን›› ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በህዳሴው ግደብ ግንባታ ደረጃና የወደፊት የህዝብ ተሳትፎ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ይህንኑ የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱን ሃሳብ ያጠናክራሉ።
የመንግሥት ሠራተኛዋ ወይዘሮ ማሜ ለማ ለግድቡ ግንባታ ከሦስት ጊዜ ያላነሰ የወር ደመወዛቸውን ሰጥተዋል። «ከዛሬ ነገ አልቆ የማደግ ተስፋችን ይለመልማል ስንል በሥራው ላይ የገጠመው ችግርና ሌብነት በጣም ያሳዝናል›› ያሉት ወይዘሮ ማሜ፣ ሥራው የመንግሥት አልያም የሆኑ ግለሰቦች እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ የአገር ፕሮጀክት መሆኑን በመጥቀስም፣ ‹‹በተፈጠረው ሁሉ ብንናደድም ብንቆጭም የወደፊቱን ለማሳመር ተሳትፏችንን ለማጠናከር እንሠራለን » ብለዋል።

መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፋችሁን ቀጥሉ ከማለት ጎን ለጎን በተጨባጭና አሳማኝ መረጃ ላይ የተመሰረቱ ወቅታዊ ሪፖርቶችን በየጊዜው ይፋ ማድረግ እንዳላባቸውም ያስገነዝባሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ላይ የተጠናከረ ክትትል ማድረግ እንደሚገባም ይናገራሉ።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ እንደሚናገሩት፤ አስቀድሞም እንደሚታወቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሊሠራ የታቀደው በመንግሥት፣ በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ይሁንና ግድቡ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ጫፍ የደረሰ የህዝቡ ጉጉት ቢኖርም በተፈለገው ልክ መጓዝ አለመቻሉ ይታወቃል፡፡ ትልቅም እክል ያጋጠመው መሆኑ እውን ነው፡፡

ይህን እክል ለማስወገድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስቀመጡት አቅጣጫ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን በመጥቀስም በአዲስ መልክና አሠራር እንዲሁም በተገቢው ቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች መከናወን ይጠበቅባቸዋል ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር ኡጁሉ ገለጻ፤ አስፈላጊው ክትትልና ቁጥጥር ከተጠናከረ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በአራት ዓመት ውስጥ ግድቡን በማጠናቀቅ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ማዋል ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ አሁንም ቢሆን ህዝቡ ተባባሪ እንደሚሆን ጥርጥር አይኖርም፡፡ ምክንያቱም ፕሮጀክቱ ትልቅና አገራዊ ከመሆኑም በተጨማሪ የአገሪቱንም ገጽታ ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በተጨማሪም አገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ሊያሰልፋት የሚችል እንደሆኑም እምነት የሚጣልበት ነው፡፡
‹‹ይሁንና›› የሚሉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት፣ ‹‹ቀደም ሲል ህዝቡ ሳያሰልስ ከወር ደመወዙ እየተቆረጠ ሲከፍል የነበረው ገንዘብ በመኖሩ ለመክፈሉ ማረጋገጫ የሆነውን ቦንድ ማግኘት ይኖርበታል›› ይላሉ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚያስቀምጡት እርሳቸውም ለሦስት ጊዜ ያህል የከፈሉ ቢሆንም የአንዱን ቦንድ ያለማግኘታቸውን ነው የሚያስረዱት፡፡ በመሆኑም ህዝቡ መክፈሉን የሚያረጋገጥ ቦንዱን ሲያገኝ አሁንም ለተጨማሪ ክፍያ ይነሳሳልና ይህ ቸል መባል እንደሌለበት ያመለክታሉ፡፡

እርሳቸው እንደሚገልጹት፤ ህዝቡ አሁንም ቢሆን ተባባሪ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የጋምባሌን ክልል መጥቀስ ይቻላል፡፡ የበለጠ ደግሞ ህዝቡን በድጋሚ ለማነቃቃት ያስችል ዘንድ ቦንዱን መስጠት አንዱ መተግበር ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ግዴታውን ግን አጠናክሮ በመቀጠሉ ረገድ መንግሥት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ሀይሉ አብረሃም እንዳሉት፤ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ የህዝቡን የድጋፍ ስሜት መልሶ ለማምጣትና ሥራው እንዳይቆም ለማድረግ የውይይት መድረኮችን እያዘጋጀ ነው። እስከአሁን አራት መድረኮች ተዘጋጅተዋል፤ መጠይቆች ተበትነው ግብረ መለስ እየተሰበሰበ ይገኛል።

እንደ አቶ ሀይሉ ገለጻ ፤መንግሥታዊና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት፣ ለዲያስፖራው ማህበረሰብ፣ ለተለያዩ አደረጃጀቶችና የህዝብ ክንፎች እንዲሁም ለሌሎች በተዘጋጀው መጠይቅ 98 በመቶ የሚሆኑት የውይይት መድረኮቹ አስፈላጊና ህዝባዊ ተሳተፎውንም ለመመለስ የሚያግዙ ናቸው።

ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱም ከመድረኮቹ የተረዳው ህብረተሰቡ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ አሉታዊ አስተሳሰብ እንደተፈጠረበትና ተስፋ መቁረጥ እንደታየበት ነው ያሉት አቶ ሀይሉ፣ አንዳንዶቹም ግንባታው የለም እስከማለት መድረሳቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይህንንም ለማስተካከል ጽህፈት ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ ግንባታው እየተካሄደ መሆኑን ለማሳየት መቻሉንም አብራርተዋል። ከዚህ አንጻርም አሁን ለውጥ እየመጣ ነው ማለት እንደሚቻልም ይናገራሉ።

በቀጣይም በየክልሉ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን የማዘጋጀት ሃሳብ እንዳለ ጠቅሰው፣ ከመገናኛ ብዙሃን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመነጋገር የጠራ ግንዛቤ ይዘው ሌሎችንም እንዲቀሰቅሱ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት መታቀዱን ተናግረዋል።
እንደሚታወቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት ከሚከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው። ግድቡ ከዓድዋ ጦርነት በመቀጠል ኢትዮጵያውያንን አንድ በማድረግ የሚጠቀስም ነው። በአድዋ ጦርነት ወቅት አባቶቻችን ልዩነታቸውን ወደ ጎን ብለው አንድነታቸውን አጠናክረው የውጭ ወራሪን በመመከት ጊዜ የማይሽረው ታሪክ ሠርተዋል። ይህን ድል የተቀዳጁት ግን ነገሮች አልጋ ባልጋ ሆነውላቸው አይደለም፡፡

የተቀዛቀዘው ህዝባዊ ተሳትፎ እንዲያንሰራራ በሚል እየተካሄዱ ከሚገኙ መድረኮች በአንዱ ግንባታው ልጅን ከማሳደግ ጋር ተመሳስሏል፡፡ ልጅ ሲያድግ እየተነሳ እየወደቀ እንደመሆኑ ግንባታውም ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም ግንባታውን ማጠናቀቅ የኢትዮጵያውያን ግዴታ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። ብዙ በቢሊዮኖች ብር የወጣበትና ለማጠናቀቅም ከአራት ዓመት በላይ የማይዘል እንደመሆኑ የተቀዛቀዘውን ተሳትፎ እንዲነቃቀ በማድረግ ግንባታውን እውን ማድረግ ይገባል፡፡ እንደተባለው የግድቡን ግንባታ መጨረስ የሞራልም የኢኮኖሚ ልእልና ማግኛ ነው፡፡ ለእዚህ ደግሞ ተሳትፎው መነቃቃት ይኖርበታል፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 28/2011

እፀገነት አክሊሉ