የጎዳና ተዳዳሪዎቹን ማቋቋሙ በዘላቂ መፍትሔ ይታገዝ!

26

በቅርቡ ይፋ በተደረገው መረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቁጥራቸው እስከ50 ሺህ የሚደርስ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዳሉ ተገልጿል። በክልሎች ደረጃ ደግሞ ይህ ቁጥር እስከ 80 ሺህ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። እኒህ ሁሉ ቤት አልባ፤ ተንከባካቢ ያጡ ዜጎች የማህበራዊ ህይወት ሰለባዎች ናቸው።

በድህነት፣ በቤተሰብ መፈናቀል ወይም መለያየት፣ ወይም በወላጅ እጦት፣ በአጠቃላይ በአሳዳጊ ማጣት ከቤታቸው የሚወጡ፤ ወጥተውም ወደአቅራቢያ ከተሞች የሚጓዙ፤ ያገኙትንም አጋጣሚ ተጠቅመው በአዲስ አበባ የሚገኙ ታዳጊዎችም ሆኑ ሌሎች መገለጫቸው የጎዳና ተዳዳሪነት ቢሆንም፤ የአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች፤ እንዲሁም ውጥንቅጥ ማህበራዊ ህይወት ተጎጂዎች ናቸው። እንደነዚህ ዓይነት የማህበረሰብ ክፍሎችን መድረስና ማቋቋም የመንግስትና የማህበረሰብ ኃላፊነት ነው።

በእርግጥ በአገራችን የከተሞች ዘመናዊ ህይወት ከተስፋፋባቸው ከ1950ዎቹና 60ዎቹ ዓመታት ጀምሮ በርሀብ፣ በሥራ ፍለጋ ወይም በሌሎች ምክንያቶች አካባቢያቸውን ለቅቀው የሚወጡ የማህበረሰብ ክፍሎች በርካቶች ናቸው። ከነዚህ መካከል እድሜአቸው ለስራ የበቃው በየደረሱበት አካባቢ በመሰማራት የዕለት ጉርሳቸውን ሲያገኙ፤ ለሥራ ያልደረሱት ወይም በዕድሜ የገፉት እንዲሁም በህመም እጅ የሰጡት ደግሞ የግድ የሰው እጅ ወደማየት ይሰማራሉ። በዚያውም ያልፋሉ።

ምክንያቱና መንስኤው ይለያይ እንጂ አሁንም ከተጠቀሰው ጊዜ አንስቶ እነዚህን የጎዳና ተዳዳሪዎች ‹‹መልሶ ማቋቋም›› ወይም ‹‹ራሳቸውን ማስቻል›› የሚባሉ ማህበራዊ ተግባራት ባለፉት መንግስታትም ሲከናወኑ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ፤ የታሰበው ግብ ሳይሳካ ቀርቷል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ በየክልሉ ባሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች እንዲሁም በሰላምና በጸጥታ ችግሮች የተነሳ ተፈናቃዮች በዝተዋል። ይህንን ተከትሎም የጎዳና ህይወት የሚቀላቀለው ዜጋ ቁጥሩ ከፍ ብሏል። በእድሜ ደረጃም ህጻናት፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶች አሮጊትና ሽማግሌዎች ሁሉ ይገኙበታል።

የተጠቀሰውን ችግር ለመቀነስ የአዲስ አበባ መስተዳድር የማህበራዊ ጥበቃ ፈንድና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጄንሲ በከተማዋ በተለይ በአራት ክፍለ ከተሞች የሚገኙትን የጎዳና ተዳዳሪዎች ወደመደበኛ ህይወት ለመመለስ የሚያስችል ተሀድሶና ስልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ የመጀመሪያዎቹን ሰልጣኞች ወደመጠለያና ማሰልጠኛ ጣቢያዎች አጓጉዟል። በቀጣይም ተመሳሳይ ስራ እንደሚያከናውን ታውቋል፡፡

ይህ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከየአካባቢያቸው ተገፍተው ወደከተማ የገቡ/የሚገቡ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማቋቋም ሂደት በራሱ መልካም ነገር ቢሆንም ካለፉት ጊዜያት ተሞክሮዎች ግን በችግር የተሞላ መሆኑን ማንሳት ይቻላል። ከነዚህም መካከል የባለጉዳዮቹ ባህርይ፤ የሚሄዱባቸው ማዕከላት አያያዝና የፕሮግራሙ ቀጣይነት ማጣት በግንባር ቀደምትነት የሚነሱ ናቸው። በዚህም ምክንያት በርካታ በመንግስትም ይሁን በግብረሰናይ ድርጅቶች የተከናወኑ ተመሳሳይ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች የተጠበቀውን ፍሬ ማፍራት አልቻሉም።

ይህ አሁን የከተማ መስተዳድሩ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የጀመረው መልሶ የማቋቋም ስራ ግን የእንዲህ አይነቱ ችግር ሰለባ መሆን የለበትም። ምክንያቱም ፕሮግራሙ ሲጀመር ኤጀንሲው ቀዳሚ የሚያደርገው ጥናት አለና ነው።  ይህ ጥናት ደግሞ የከተማዋን የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን እኒህ በእድሜ፣ በጾታና በፍላጎት የተለያዩ ዜጎች ምን ተምረው፣ በምን ታድሰው ወደህብረተሰቡ ቢቀላቀሉ ለራሳቸውና ለማህበረሰቡ፤ አልፈውም ለአገር እንደሚጠቅሙ የታሰበበት ነው ብለን እናምናለን።

በመሰረቱ እንዲህ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማቋቋሙ ሂደት ቅድሚያ የሚሰጠው የባህሪይ ተሃድሶ በማድረግ ነው። ዜጎች ከነበሩበት የጎዳና ቆይታቸው የሚወርሷቸው በርካታ ባህሪያት አሉና እነርሱን ማረቅና ወደሚፈለገው አቅጣጫ መመለስ ከባድ ስራ ይጠይቃል። ከዚያም አልፎ ኃላፊነት የሚሸከም፣ ተስፋ የሚሰንቅና ነገን አስቦ የሚሰራ ሰብዕና መትከል ደግሞ ትልቅ ስራና ፈተና ነው። እናም ኤጀንሲው በተናጠል፤ መንግስት በድምር እነዚህ ኃላፊነቶች ይጠበቁባቸዋል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁልጊዜም እንዲህ አይነቱ የመልሶ ማቋቋም ስራ ሲታሰብ ከጀርባው ይዞት የሚመጣው የአዲስ መጤዎች መበራከትም የሚጠቀስ ችግር ነው። እና ጥናቱ ይህንን ችግር ሊያየውና አስቀድሞ የመመከቻ ዘዴ ሊቀይስ ይገባል።

እናም የሄዱት ተስፋ ቆርጠው እንዳይመሰሉ፤ ወይም ጥለውት የሄዱትን የስሜት ኑሮ ናፍቀው እንዳያስቸግሩ መስራት ያስፈልጋል። ቀደም ሲል የተጀመሩ ፍፃሜ ሳይደርሱ የቀሩ ተመሳሳይ መርሃ ግብሮችም ለምን ሳይቋጩ ቀሩ የሚለውን ጉድለታቸውን አይቶ ትምህርት መቅሰምና ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ መጣር የግድ ይሆናል።

ከሁሉም በላይ ከሚመለከታቸው የፌዴራልም ሆነ የክልል መስተዳድር አባላት ጋር ተቀራርቦና ተመካክሮ መስራት ቁልፍ ጉዳይ ነው እንላለን። ምክንያቱም እነዚህ  ዜጎች አብዛኞች ምንጫቸው ከክልል ነውና ሲመለሱም ወደ ክልል ስለሚሆን የጋራ ኃላፊነት መውሰድ የመርሃ ግብሩን ውጤታማነት ያጠናክረዋል።

ህብረተሰብን የሚመለከተው ድርሻም ከቤተሰብና ከቤተዘመድ ይጀምራል። እነዚህ ዜጎች ሲሆኑ ቤተሰብ (በሙሉም ይሁን በከፊል) እልፍ ሲል ቤተዘመድ ከዚያ ሲያልፍም የነበሩበት አካባቢ ማህበረሰብ መልሶ ሊያቅፋቸው ይገባል።  እናም ሲወጡ የተገፉበት ማህበራዊ ህይወት መልሶ ሊገጥማቸው አይገባም።

በአጠቃላይ ይህ የጎዳና ተዳዳሪዎች መልሶ የማቋቋምና ወደመደበኛ ህይወት የመመለስ ተግባር የመንግስት፣ የህብረተሰብና የቤተሰብ ቀዳሚ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። መንግስት በየደረጃው አቅሙን አሰባስቦ የጀመረውን ይህንን ተግባር ከዳር እንዲያደርሰው ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ የድርሻውን ያበርክት እንላለን።

አዲስ ዘመን ጥር 29/2011

ለተጨማሪ ንባብ ሊንኩን ይጫኑ