‹‹ክልሎች የሌሎች የሆነውን ለመመለስ የእነርሱን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለባቸው››    አቶ ሙልዬ ወለላው- በፌዴሬሽን ምክር ቤት የህግና የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ

108

ባለፉት ዓመታት ከአስተዳደራዊ ወሰን ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የበርካታ ሰዎች ህይወት አልፏል። በርካቶች  ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል። በዚህም ዜጎች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነልቦናዊና ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ወድቀዋል። የተለያዩ አካላት ስለመንስዔውና መፍትሔው ሃሳብ ይሰነዝራሉ። አገር እንደ አገር እንዲቀጥል ለችግሩ መድሃኒት መፈለግ ይገባል ይላሉ።

በዚህ ሁኔታ ከሚስማሙት አንዱ  አቶ ሙልዬ ወለላው ናቸው። በአሁኑ ወቅት በፌዴሬሽን ምክር ቤት የህግና የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ ናቸው። ቀደም ሲል በምክር ቤቱ በህገ መንግሥት ትርጉምና  በማንነት ጉዳዮች  በዳይሬክተርነት አገልግለዋል።  በአማራ ክልልም የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛና ፕሬዚዳንት ነበሩ። በገቢዎች ባለስልጣን የአቃቤ ህግ ኃላፊ፤ በኢትዮጵያ የህግና ስርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት የወንጀል ጥናት መምሪያ ኃላፊ፣ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን  የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርምራ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል።

አቶ ሙልዬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግና በሰብዓዊ መብት ሁለት ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። በማኔጅመንትም የመጀመሪያ ዲግሪ ባለቤት ናቸው። በሰብዓዊ መብት፣ በማንነትና ወሰን ጉዳዮች ላይም በርካታ ጥናቶችን አካሂደዋል። ከማንነትና በተለይም ከወሰን ጋር በተያያዘ በችግሮቹ መንስዔና መፍትሔዎች ላይ ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸዋል። እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፡- አሁን በኢትዮጵያ ያሉት ክልሎች በህገ መንግሥቱ መሰረትና ሳይንስዊ ጥናትን መሰረት አድርገው ተዋቅረዋል?

አቶ ሙልዬ፡- በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 46 የክልሎች አወቃቀር በቋንቋ፣ በባህል መቀራረብ፣ በማንነትና አሰፋፈርን መሰረት እንደሚያደርግ ይደነግጋል። በአንቀጽ 48 የአከላለል ለውጥ እንዴት መሆን እንዳለበትና የወሰን አለመስ ማማቶች እንዴት እንደሚፈቱ ያስቀምጣል። ከዚህ ባለፈ አሁን ያሉት ክልሎች እንዴት፤ ለምንና በምን ምክንያት እንደተካለሉ ግልጽ አይደለም። ለምን በዘጠኝ ክልል እንደተዋቀረም የሚያሳይ ሳይንሳዊና ምክንያታዊ ጥናት የለም። የወሰን አከላለልም በህዝቡ መተማመንና በህገ መንግሥቱ መሰረት አይደለም የተዋቀረው። አሁን በኢትዮጵያ ያለው ችግርም መነሻው 1983 ዓ.ም በኋላ ክልሎች በአግባቡ መዋቀር አለመቻላቸው ነው። በዚህም በኢትዮጵያ ከወሰንና ከማንነት ጋር ተይይዞ በርካታ ዜጎቻችንን ለህልፈት፣ ለአካል ጉዳትና መፈናቀል ገብረናል።

አዲስ ዘመን፡- ክልሎቹ ህገ መንግሥቱና ሳይሳንዊ ጥናትን መሰረት በማድረግ ካልተዋቀሩ በምን መንገድ ተካለሉ?

አቶ ሙልዬ፡-  የህገ መንግሥቱ  አርቃቂ ኮሚሽን የተነጋገረባቸው 52 ረቂቅ ጥራዞችን ተመልክቻለሁ። ዘጠኙ ክልሎች በምን ምክንያት እንደሚካለሉ፣ ለምን እንደተካለሉ፣ እንዴት እንደተካለሉ የሚገልጽ ነገር የለውም። የተለያዩ ባለሙያዎችም  ክልሎች በህገ መንግሥቱ መሰረት አልተካለሉም የሚሉት ለዚያ ነው። ይህ እውነት ነው፤ አሁን ያሉት ክልሎች በህገ መንግሥቱ መሰረት የተካለሉ አይደሉም። ሳይንሳዊ ጥናትም አልተደረገባቸውም። የዚህ ማረጋገጫ ቀላል ነው። አሁን ያሉት ክልሎች የተመሰረቱት ህገ መንግሥቱ ከመውጣቱ በፊት በ1984 እና 1985 ዓ.ም ነው። ህገ መንግሥቱ የወጣው በ1987 ዓ.ም ሲሆን፤ ክልሎች ሲመሰረቱ ህገ መንግሥቱም አልነበረም።  ህገ መንግሥቱ የወጣው ክልሎች ከተመሰረቱ በኋላ በመሆኑ ህገ መንግሥቱን መሰረት አድርገው የተካለሉ ናቸው ማለት አይቻልም።

አሁን ለተፈጠረው ምስቅልቅል ትልቁ መንስዔ ስለክልሎች አከላለል ህዝብ አልተወ ያየበትም። ህዝቡ ይህ ቦታ ወደዚህ ያኛው ወደዚያ ይሁን በማለት ከስምምነት አልተ ደረሰበትም። ክልሎች ሲዋቀሩ የነበረው የሽግግር ምክር ቤትም የህዝብ ወኪል የሌለውና ሁሉንም ህዝብ በአግባቡ የሚወክል ባለመሆኑ ህዝቡ በወኪሎቹ ወስኗል ለማለት አይቻልም። ክልሎቹ ሲፈጠሩ በሳይንሳዊ መንገድ አልተሠራም፤ ጥናትም ተደርጎበት አይደለም።

በሁሉም የአገሪቱ ክልሎችና አካባቢዎች ችግር የሚነሳው ለዚያ ነው። አሁን ላይ ችግር የሌለበት ክልል የለም። በአንድ አካባቢ የተፈጠረም አይደለም። በጋምቤላና በኦሮሚያ፣ በጋምቤላና በቢኒሻንጉል ጉምዝ፣ በአማራና በቢኒሻንጉል ጉምዝ፣  በትግራይና በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ፣ በአማራና በአፋር፣ በሶማሌና በአፋር፣ በሶማሌና በኦሮሚያ፣ በደቡብና በኦሮሚያ፣ በኦሮሚያና በሀረሪ በሁሉም ክልሎች መካከል ግጭት አለ። ግጭትና ችግር የሌለበት ክልል የለም። ወደ ዞን ወረዳ ሲወርድ ደግሞ ችግሩ በእጥፍ ያድጋል። የወሰን አከላለል የህዝብን ይሁንታን ያለገኘና ሳይንሳዊና ታሪካዊ ጥናትን ያላደረገ በመሆኑ አገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቷል።

አዲስ ዘመን፡- የክልሎች ወሰን ቀድሞ ቢካለልም፤ ህገ መንግሥቱ ሲወጣ እውቅና ከሰጣቸውና ፤ በህገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ስርዓት ካሟሉ በህገ መንግሥቱ መሰረት አልተካለሉም ማለት ይቻላል?

አቶ ሙልዬ፡- ህገ መንግሥቱ ድንበሩ ተካሎ ካለቀ በኋላ የወጣ ነው። ህገ መንግሥቱ ወደ ኋላ ሄዶ ህጋዊ ለማድረግ  አይችልም። ህግ የሚሠራው ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ወይም ደግሞ ህጉ ሲወጣ ወደ ኋላ ሄዶ ይሠራል ካልተባለ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ህገ መንግሥቱ በሌለበት ወቅት የተካለለን ወሰን በህገ መንግሥቱ መሰረት ነው የጸደቀው ሊባል አይችልም። ያልተወለደ ልጅ ያልኖረበት ዕድሜ እንደመቁጠር ነው። ልጅ ከተወለደበት ጊዜ በኋላ ዕድሜው እንደሚቆጠረው ሁሉ ህገ መንግሥቱም ዕድሜውም ሆነ ሥራው መቆጠር ያለበት ከወጣበት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡

በህገ መንግሥቱ መሰረት ክልል ለመሆን የተቀመጡ መስፈርቶች መሟላት አለባቸው። ይህን ለማድረግ ሳይንሳዊ ጥናት ማካሄድ ይገባል። ህዝቡንም አሳታፊ በሆነ መልኩ ማካሄድ ይገባል። በዚህ ሁኔታ አልተካሄደም። ይህ ባልሆነበት በህገ መንግሥቱ መሰረት ተመዝነው ክልል ሆነዋል ማለት አይቻልም።

ሌላው ለዚህ ማሳያ ከማንነት ጥያቄ ጋር የተያያዘው ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት 76  ብሄር ብሄርሰቦች እንዳሉ እውቅና ይሰጣል። ከዚህ ውስጥ ግን በህጉ መሰረት ተመዝነው እውቅና የተሰጣቸው  ስልጤ፣ አርጎባና ቅማንት ብቻ ናቸው። ሌሎቹ ግን ዝም ብሎ የተወሰዱ እንጂ በህገ መንግሥቱ መሰረት በተቀመጠው ተመዝነው አይደለም።

ከዚህ በላይም ለክልሎችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት 15 የሚሆኑ ጥያቄዎች ቀርበው ክልሎችም ሆኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገ መንግሥቱ መሰረት መልስ አልሰጡም። አንዳንዶች ተጠንተው ውሳኔ  የማይሰጥባቸው አሉ። ለምሳሌ የደንጣ ብሄረሰብ በአዲስ አበባና በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ተጠንቶ 80 በመቶ ቋንቋ  እንዳለው ቢረጋገጥም  እስከአሁንም ውሳኔ አለገኘም። በህገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሰረት የተጠኑም በፖለቲካ ጫና ተግባራዊ አልሆኑም። የህግ የበላይነት ቀርቶ የፖለቲካ የበላይነት ተግባራዊ ሲደረግ ነበር።

አዲስ ዘመን፡- በዚህ ችግር ህዝብና አገር ምን ያህል ጉዳት ደረሰባቸው?

አቶ ሙልዬ፡- ከአስተዳደራዊ ወሰንና ማንነት ጋር በተያያዘ የተከሰቱ  ግጭቶ  ጥናት ላይ ተሳትፌያለሁ። በሁሉም ቦታ አሳዛኝ ክስተቶች አጋጥመዋል።  ለምሳሌ በደቡብና በኦሮሚያ መካከል በተፈጠረው ግጭት ሰዎች ሞተዋል። በርካታ ዜጎች ቆስለዋል። በሚሊዮን የሚገመት ንብረት ወድሟል። በርካታ መኖሪያ ቤት ሲቃጠል፤ ከ800ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል። ከምንም በላይ በግጭቱ ሕፃናት፤ አካል ጉዳተኞችና ሴቶችን  ለከፋ ስቃይ ዳርጓል።

በቤኒሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ መካከል በተፈጠረው የአስተዳደራዊ ወሰን ግጭትም በተመሳሳይ 15 ሰዎች ሞተዋል። በርካታ ሰዎችም ለአካል ጉዳት ተደርገዋል። ከ700ሺ የማያንሱ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ከፍተኛ ንብረት ወድሟል። በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከልም በተፈጠረ ሰዎች ሞተዋል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

በሶማሌና በአፋር መካከል በተለያየ ጊዜ የወሰን ግጭት እየተነሳ በርካታ ጉዳቶች ደርሰዋል። በአማራና በአፋር፤ በትግራይና በአፋር መካከልም በተለያየ ጊዜ ግጭት አየተነሳ የዜጎች ሞት፤ መፈናቀልና ንብረት ውድመት በተለያየ ጊዜ ደርሷል። በአማራና በትግራይ መካከል በወሰን ምክንያት ከአማራ ክልል በርካታ ዜጎች ተፈናቅለዋል። በአማራና በቤኒሻንጉል ጉምዝ መካከልም በወሰን  ምክንያት በርካታ ዜጎች ሞተዋል፤ ተፈናቅለዋልም።

በአጠቃላይ በሁሉም የአገሪቱ ጫፎች ከወሰንና ከማንነት ጋር በተያያዘ ሞት፣ መፈናቀል፤ የአካል ጉዳትና ሌሎችም ጉዳቶች ደርሰዋል። በዚህ የተነሳ በአገሪቱ ግጭት የሌለበት ቦታ የለም። ዜጎቸ ያልሞቱበት ያልተፈናቀሉበት ክልል የለም። በአስተዳደራዊ ወሰንና በማንነት ምክንያት በአገሪቱ በአጠቃላይ ችግር ውስጥ ናት። በዚሁ ከቀጠለ አገር መፍረሱ አይቀርም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ኮሚሸን አቋቁመው ወደ ማስጠናት የገቡት አገር እንዳይፈርስ የማስቆም ኃላፈነት ስላለባቸው ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ያሉት የአገሪቱ ክልሎች አወቃቀር በህገ መንግሥቱ መሰረት የተከናወነ  እንዳልሆነ አንስተዋል። በህገ መንግሥቱ መሰረት የአስተዳደራዊ ወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ቢፈቱ በአገሪቱ ያለውን ችግር ያስወግዳል?

አቶ ሙልዬ፡- ህገ መንግሥቱ ችግሮችን ፈትቷል ወይም አልፈታም ብሎ ሁለት ጫፎች መረገጥ ተገቢ አይደለም። ህገ መንግሥቱ ችግር ፈጥሯል ዋጋ የለውም ማለት አይቻልም። ብሄር ብሄርሰቦች እርስ በእራሳቸው ተከባብረውና መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ አድርጓል። ከጥቅሙና ከጉዳቱ ግን ሲታይ አሁን ላይ ያለው ሁኔታ ታፍኖ ተይዞ እንጂ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ነው የሚያሳየው። ሌሎቹን እንኳን ትተን ፖለቲካውን እናሽከረክረዋለን የሚሉት የአራቱ ትላልቅ የኢህአዴግ ድርጅቶች ክልሎች በወሰን ምክንያት  ተጎጂ ናቸው።

አማራውም፣ ደቡብም፣ ትግሬውም ሆነ ኦሮሞው ከእራሳቸው ወይም ከሌሎች ክልሎች ተፈናቅለዋል። የትኛውም ክልል ተጠቃሚ አልሆነም። ሁሉም እየተጎዳ መቀጠል አይቻልም። ይህ የሚያሳየው ችግር እንዳለ ነው። በመሆኑም ህገ መንግሥቱ ይፈታዋል ከማለት ይልቅ የችግሩን መንስዔ አጥንቶ መፍትሔ መስጠት ይገባል። ለዚህ አገር ፌዴራልዝም  አስፈላጊነቱ የማያጠያይቅ ቢሆንም ከአስተዳደራዊ ወሰንና ከማንነት ጋር የተያያዘ ግን መጠናት ያለበት ጉዳይ እንዳለ ነው የማስበው። ምክንያቱም  ፌዴራሊዝም ውጤታማ ሆኖ ሳለ እኛ ጋር የማይሳከበት ሁኔታ የለም።  በሂደቱ ያጋጠመንን ችግር ለመፍታት መሪዎች ቁጭ ብለው መነጋገር አለባቸው። ለህዝብም ቢሆን እኔ አውቅልሀለሁ ሳይሆን ቁጭ ብሎ በመወያየት በጋራ ሆኖ የመሰለውንና የሚያምንበትን እንዲወስን ዕድል መስጠት ይገባል። መንግሥት ህዝቡ ሲወስን አደራውን ተቀብሎ ማስተዳደር ብቻ ነው የሚገባው።

አዲስ ዘመን፡- ከአስተዳደራዊ ወሰን ጋር በተያያዘ አገሪቱ የገጠማትን ችግር ለመፍታት ምን ዕርምጃ መወስድ አለበት?

አቶ ሙልዬ፡- ችግሩን ለመፍታት ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ዜጎችና ሌሎች አካላት በሰከነና በእውነት ችግሮቹን ነቅሶ ለማውጣት መወያየት አለባቸው። ችግሮቹን ነቅሶ ለማውጣትና መፍትሔ ለመስጠት ሁሉም ክልሎችና ዜጎችም ተባባሪ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደ አጥቂና ተጠቂ ማሰብ አይገባም፡፡ የሁሉም የጋራ ችግር መሆኑን በማመን የጋራ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል።

በውይይቱ የእውነት ታሪክን፣ መረጃዎችን፣ የህዝብ አሰፋፈርና  ህዝቡ የሚያምነውን ይዞ በመግባት በእውነት የጋራ መፍትሔ ማምጣት ይገባል። ሁሉም ክልሎች የእራሳቸው የሚሉትን ቦታ በእውቀትና በማስረጃ አስደግፈው በማቅረብ የማያዳግም መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን በጉልበት መውሰድም ማስቀረትም አይቻልም። አንዳንዶች በህገ መንግሥቱ ያገኘነው ሲሉ አንዳንዶች ደግሞ በህገ መንግሥቱ  የተወሰነ አይደልም ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ህገ መንግሥት ከመውጣቱ በፊት የእኔ ነበር በማለት በአገሪቱ ወስብሰብ ችግረ ፈጥረዋል። ይህን ውስብስብ ጉዳይ በመነጋገር መፍታት ይገባል።

ክልሎች የሌሎች የሆነውን  መመለስ የእነሱ የሆነውን መቀበልና በጋራ ተቻችሎ ለመኖር ዝግጁ መሆን አለባቸው። ይህ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ብትከስም በአገር ሽማግሌም፤ በዘመድ ሽግሌዎች ብትነጋገር አይለወጥም። መሆን ያለበት እውነት የሆነውን ማንም ሊለውጠው የማይችለውን ጉዳይ በመፍታት ወደ ልማት መግባት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ይህ ችግር መፍትሔ  ካለገኘ አገሪቱ ወዴት ታመራለች?

አቶ ሙልዬ፡- ሁሉም  ክልሎች ወደ መፍትሔ መሄዳቸው የግድ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ኮሚሽን ያቋቋሙት ለዚያ ነው። በህገ መንግሥቱ ክልሎች እንዲህ ዓይነት ችግሮች እንዲፈቱ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ግን መፍታት አልቻሉም። ይህ ሁኔታ በቶሎ ካልተፈታ አገር ወደ መፍረስ ነው የሚሸጋገረው።

አገር እንዳይፈርስ በህገ መንግሥቱ ስልጣን የተሰጣቸው አካላት  ችግሩን በመገንዘብ አገር እንዳይፈርስ ኃላፊነት ለመወጣት ወደ ሥራ ገብተዋል። ጥናት የሚያደርግ ተቋም በአዋጅ አቋቁመዋል። ችግሩን ለመፍታት ቢያንስ መፍትሔ ያገኛሉ። ከዚያ በኋላ የሚመለከታቸው አካላት ወደ መፍትሔ ይገባሉ። በሂደቱ ሁሉም ተሳታፊና የመፍትሔ አካል መሆንና መደራደር ነው የሚገባው። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በከፍተኛ ድምፅ የጸደቀን አዋጅ ከህገ መንግሥቱ አስካልቀረ ማንም ሊያስቀረው አይችልም።

አዲስ ዘመን፡- የትግራይ ክልል የኮሚሽኑን መመስረት ተቃውሟል። በዚህ ሁኔታ በትግራይ ጥናት ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ይኖራል ብለው ያስባሉ?

አቶ ሙልዬ፡- የኮሚሽኑን ሥራ ላስቀር የሚል አካል ካለም በህገ መንግሥቱ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወሰዱ ስልጣን የተሰጣቸው አካላት ችግሩን ይፈቱታል። ነገር ግን አገሪቱ የምትከተለው የፌዴራል ስርዓት እንደመሆኑ ከምንም በፊት ቅድሚያ መስጠት የሚገባው በውይይት ለመፍታት መሆን ይገባል። በአብዛኛው ክልል ተቀባይነት ስላለው ተፈፃሚነት ይኖረዋል። የኮሚሽኑን አዋጅ ተግባራዊ አይሆንም ማለት ጨዋታው ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ እንደማለት ስለሆነ ተባባሪ መሆን ይገባል። ሌላው መገንዘብ የሚገባው ዛሬ ላይ በሃሳብ መቃወም ሳይሆን ወደ ተግባር ሲገባ የሚያሰናክል አካል ካለ ህገ መንግሥቱን ወደ ማስጠበቅ  ዕርምጃ ይገባል። አሁን ላይ በአዋጁ ላይ ሃሳብ መስጠትና ማንሸራሸር መቃወም ጭምር ዴሞክራሲያዊ ነው።

የትግራይ ክልል ውሳኔን በሚመለከት የተምታታ ነገር አለ። አንዳንዶች ህገ መንግሥቱ የሚቃረን ስለሆነ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይቅረብ የሚል ውሳኔ ነው የተላለፈው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በትግራይ ክልል አዋጁ ተግባራዊ አይሆንም  የሚሉ አሉ። የተምታታ ነገር አለው። ክልሉ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ አያስፈልገውም። ውሳኔ ማስተላለፍም ጥቅም የለውም። ምክር ቤቱ ሳይወስን ማቅረብ ይቻላል።

ከዚህ በላይ አከራካሪ የሚሆነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔና ሌሎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጨምሮ በውሳኔው ላይ መሳተፋቸው ነው። ምክንያቱም በክልሉ  ምክር ቤት ውሳኔ አሳልፈው አፈጉባዔዋ በዚህ ጉዳይ በድጋሚ ለፌዴሬሽን የህገ መንግሥት ማጣራቱ ቢመጣ ስብሰባውን ይመራሉ የሚለው አጠያያቂ ጉዳይ ነው። አንድ ሰው በአንድ ጉዳይ ላይ በአንድ ምክር ቤት የወሰነው ጉዳይ በሌላ ምክር ቤት ላይ በውሳኔ መሳተፍ አለበት ወይስ የለበትም የሚለው አጠያያቂና ለቀጣይም መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም አንዴ ካየ በሁለተኛ ምክር ቤት ላይ በንጹህ ህሊና  አያያውም፤ ያሳለፈው ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ተጽዕኖ ከማድረግ ባለፈ። በፌዴራል መንግሥት ተቋማት የሚሠራ ኃላፊ በዚህ ሁኔታ መሳተፍ በሌሎች ክልሎች እምነት የሚያሳጣ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የኮሚሽኑ መቋቋም የትግራይን ክልል ከሌሎች በተለየ ሊጎዳ የሚችልበት  ሁኔታ አለ?

አቶ ሙልዬ፡- የማይወስን ኮሚሽን ምን ብሎ ሊጎዳ ይችላል። አንድ ዩኒቨርሲቲ ሊሠራ የሚገባውን ሥራ እኮ ነው ኮሚሽን ተብሎ የተቋቋመው። የሚኒስቴር ምክር ቤት ለምን ኮሚሽን እንዳለው ባይገባኝም ኮሚቴ ከሚሠራው የተለየ ነገር የለም።

የትግራይ ክልልም ሆነ የአማራ ክልል ዝምብለው አንነካም ባይ ሆነው እንጂ ምንም የሚያመጣው ነገር የለም። ይህ አንነካም ባይነታቸው በህግ መስመር መሄድ አለበት። የህግ የበላይነትን ማክበር አለባቸው። አናከብርም ካሉ ደግሞ በህጉ መሰረት በመጠየቅ መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል። ህግን በአግባቡ የሚያስከበር ስርዓት ካለ ምንም የሚመጣ ነገር የለም።

ህገ መንግሥቱን የሚጣረስ ከሆነ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ከመወሰን ይልቅ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራት ይችላል። ግን ያን ያላደረገው ህጉን  ስለማይጥስ ነው። ዛሬም ቢሆንም ይህን አንቀጽ ይጥሳል ብሎ አስወስኖ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያስተካክል ማድረግ ይችላል። ግን ስለማይጥስና ስለማያዋጣ ነው። ትግራይም ይሁን አማራ ወይም ሌሎች ክልሎች ቁጭ ብለው መነጋገርና መፍታት አለባቸው።  በውይይት ችግርን ለመፍታት መሥራት በጣም አስፈላጊ ነው። ወደዱም ጠሉም ትግራይና አማራ ክልል አንድ ሆነው ችግራቸውን መፍታት የግድ ነው። ካልፈቱ ሁለቱም ተጎጂዎች ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- ኮሚሽኑ ምን ያህል በአገሪቱ ያለውን ችግር ይፈታዋል?

አቶ ሙልዬ፡- ኮሚሽኑ ወሳኝ ስላልሆነ  አስተያየት ነው የሚያቀርበው። የፌዴሬሽን ምክር ኮሚሸኑ ካጠና በኋላ ሲቀርብ አልቀበለውም ማለት ይችላል። ምክር ቤት የተሻለ አማራጭ ካለው መፍታት ይችላል።  ችግሩን የተፈጠረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ኃላፊነቱን ስላልተወጣ ነው። ክልሎች ካልፈቱት በሁለት ዓመት ገብቶ መፍታት ሲገባው ለበርካታ ዓመታት አልፈታም። በዚህም ለዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። መንግሥት ኮሚሽን ያቋቋመው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ኃላፊነቱን ስላልተወጣ ለማገዝ ነው።

አዲስ ዘመን፡- የአስተዳደር ወሰን ግጭቱ እንዲባባስ ምክንያት የሆነው በህገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 በተፈጠረው አለመተማመን እንደሆነ ይነገራል። በእርሰዎ እይታ እውነትነት አለው?

አቶ ሙልዬ፡- በእኔ እይታ አንቀጽ 39 ግቡን መትቷል። የአንቀጹ  ዋና ዓለማ የነበረው ሁሉም ብሄረሰቦች እንዲገነጣጠሉ አልነበረም። ዓለማው በብሄር ብሄረሰቦች መካከል መተማመን ለመፍጠር ነው። ሁሉም ብሄሮች በእራሳቸው ቋንቋ መማር፣ መዳኘት፣ ባህላቸውን ማሳደግ፣ ውክልና ማግኘት እና እራሳቸውን በእራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ ነበር። አሁን ይህን ሁሉ አግኝተዋል። ከዚህ በኋላ መቀመጡ ፋይዳው አይታየኝም።  ለእኔ ዓለማው ግቡን መቷል።   ከዚህ በኋላም መቀጥል የለበትም። በሃሳብ ደረጃ ለአስተዳደር ወሰን ግጭቱ አንዱ መንስዔ ሊሆን ይችላል። በተግባር ግን በፍጹም መሆን የማይችል ነው።

አዲስ ዘመን፡-  ለሰጠኙ ማብራሪያ አመሰግናለሁ!

አቶ ሙልዬ፡- እኔም አመሰግናለሁ!

አጎናፍር ገዛኸኝ