የእያንዳንዳችን እጅ እንዳለበት ምን ያህል ታውቃላችሁ?

24

አንድ መጥፎ ነገር ሁሌ ሲደጋገም ድርጊቱ ትክክል ነው ብሎ የማመን አመለካከት በጭንቅላታችን ውስጥ ሰርጾ ይሁን የችግሩን አስከፊነት ሳናስተውለው ቀርተን ባይገባኝም፤ በተለይ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ያለው ፆታዊ ጥቃት አሁን አሁን የሁሉም ሰው ቤት ችግር ነው ወደሚያስብል ደረጃ ደርሷል። ድሮ ድሮ እንዲህ ጠለፋ እንደዛሬው በወንጀለኝነት ሳይፈረጅ ወንዶች የሚፈልጓትን ሴት ለማግኘት ጥሩ ዘዴያቸው ነበር። ያኔ ጥፋቱ በሴቷ ፈቃድ ላይ አለመመስረቱ እንጂ ያንን ያህል ችግሩ ከፍቶ እንዲህ እንዳሁኑ መላ ቅጡ የጠፋ አልነበረም።

ብዙ እናቶች ከጠለፋ በኋላ ልጆች ወልደው፤ ወግ ማዕረግ አይተው ተደስተዋል። ያኔ በድሮዋ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሴት ልጅ የያዘችውን እንስራ ሰብሮ በእጁ ተሸክሞ ወደቤቱ የሚያስገባት ወንድ ዛሬ ዘመናዊ ሆነናል፤ ተምረናል በምንለው የኛ ትውልድ አሲድ በመድፋት ተለወጠ። በቃ ነገሩ የለየለት ከእንስራ ሰበራ ወደአሲድ መድፋቱ ሲለወጥ ነው። ነገሮች አሁንም ወደአስከፊ ደረጃ መሄዳቸው አልቀረም። አባት ልጁን ደፈረ፤ የሰባት ዓመት ህጻን ጥቃት ደረሶባት ሞተች የሚሉት ዜናዎች አሰቃቂነታቸው ቀርቶ ልክ እንደስፖርት ዜና በየእለቱ የሚዘገቡ ተራ ወሬዎች ሆኑ።

ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች አገግመው ወደህብረተሰቡ እስኪቀላቀሉ ድረስ ለአዕምሮ አቸው የሥነልቦና ባለሙያ፤ ለአካላቸው ጉዳት ህክምና የሚያገኙበት አንድ ማገገሚያ ተቋም አዲስ አበባ ውስጥ እንኳን ለመገንባት ያልተቻለው ገንዘብ ጠፍቶ ነው? መሬት ጠፍቶ ነው? ወይስ ጥናት አድርጎ ፕሮፖዛል የሚያዘጋጅ ጠፍቶ ነው? የሚሉት ጥያቄዎች የብዙዎች ናቸው። የእያንዳንዱን ሰው አዕምሮ ቀይሮ ጥቃትን ማስቆም ከባድ ጉዳይ ቢሆንም፤ ቀላሉ ነገር ግን የተጠቁ ሴቶች የሚያገግሙበት ማዕከል መገንባቱ ነበር። ቀላሉን ሳንሰራ ከባዱን ለመስራት መሞከር ሞኝነት ነውና የሚመለከተው ሁሉ ሊያስብበት ይገባል። ከአራት ዓመት በፊት በሰባት ወንዶች ጥቃት ደርሶባት ህይወቷ ያለፈውን የሀናን ታሪክ መቼም ሁሉም ያስታውሰዋል። ያኔ ተወራ፤ አገር ጉድ አለ፤ ስብሰባዎችና የፓናል ውይይቶች ተዘጋጁ፤ ከዚያ ቆመ። በቃ ቆመ። ያኔ ስብሰባዎቹ የእውነት የተዘጋጁት ለሀናና መሰል ጥቃት የደረሰባቸውን/ የሚደርስባቸውን ሴቶች ችግር ለመፍታት ሳይሆን፤ ለ50 እና ለ100 ብር አበል ብቻ አዳራሽ ለመሙላት የገቡ ሰዎችን ግርግር ለሚዲያ ፍጆታ ለማዋል ብቻ መሆኑ የሚታወቀው በዚህ ነው። እኛ ደግሞ ግርግሩን ከስር መሰረቱ ሳናጠና ችግሩ ተባብሶ የመጨረሻው ደረጃ ከደረሰ በኋላ ደረት እየመቱ የማልቀስ አባዜ አለብን።

ፆታዊ ጥቃትና ትንኮሳ ከምንም ሳይነሳ እዚህ ደረጃ አልደረሰም። ቀላል የሚመስለውንና ለነገሮች ሁሉ መነሻ የሆነውን ምሳሌ፤ “ለከፋ”ን እንውሰድ፤ ሲጀመር መልከፍ ለሰው ልጅ የተሰጠ ባህርይ አይደለም። ግድየለም ይሁን፤ ሰዎች ተስማምተው ያወጡት መግባቢያ ወይም ቃል ነው እንበል፤ እናም ለከፋው “እናትዬ ቅርጽሽ ያምራል፤ እንትና አለባበስሽ ካንቺ ጋር አይሄድም” በሚሉ አስጸያፊ፤ አንዳንዴም ማሞገሻ በሚመስሉ ቃላት ይጀመራል። መንገድ ላይ የሚያገኛት አንድ ወንድ እንዲህ ለማለት ምን ስልጣን አለው? የመጀመሪያ ቀን በሩቅ እንዲህ ያላት ወንድ በቀጣዩ ቀን በድፍረት አጠገቧ ቆሞ “ስልክሽን ካልሰጠሽኝ፤ አንቺ ማን ስለሆንሽ ነው?” በሚል ማሳበቢያ መግቢያ መውጫ ያሳጣታል። ነገሩ ሲቆይ፤ ሲቆይ ደግሞ “አንዲት ወጣት በስለት ተወግታ ህይወቷ አለፈ፤ ወንጀለኛውም በሁለት ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ” የሚል ዜና ሆኖ በቴሌቪዥን መስኮት ይመጣል።

አያችሁ የትናንት ለከፋ ዛሬ ምን ደረጃ እንደ ደረሰ? ከሁሉም በላይ የሚገርመውና አስተሳሰባችን ምን ያህል እንደወረደ የሚያሳየው የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ተጠያቂ ማድረጉ ሲጨመርበት ነው። የሰው ህይወት ያጠፋው ወይም ምስቅልቅል ያወጣው ወንጀልና እኩይ ተግባር ከፊት ለፊት እየታየ “ማን አጭር ቀሚስ ለብሰሽ ውጭ አላት? ማን ተሽኮርመሚ አላት?” የሚሉ አሉባልታዎች ከጥቃቱ ሰለባዎች ጀርባ ይነሳሉ፤ አያናድድም? ሴቶች የተጠቁት ወይም የሚጠቁት በፍጹም በአለባበሳቸው እንዳልሆነ ለማየትም ሆነ ለማመን ባለፈው ጊዜ መስቀል አደባባይ በሚገኘው ሙዚየም “ምን ለብሳ ነበር?” “What she wore” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን አውደ ርዕይ ያየ ካለ እሱን ማስታወስ በቂ ነው። አውደ ርዕዩ ከ7-20 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሴቶች ሲደፈሩ ለብሰው የነበረውን ልብስ ከነታሪካቸው የሚያሳይ ነበር። እሺ! ልክ ነው! ሴቶች እስከዛሬ በአለባበሳቸው ጥቃት ደርሶባቸዋል እንበል፤ ወንዶቹስ? ወንዶችም የሚደፈሩትና ጥቃት የሚደርስባቸው አጭር… ስለለበሱ ነው? ወይስ ስለተሽኮረመሙ ነው? በፍፁም አይደለም። ጥቃት ሲባል ያልገባን ነገር ስላለ ነው።

በሌላ በኩል አብዛኞቻችን አስገድዶ ከመድፈርና ከመደባደብ ውጭ ጥቃት ያለ አይመስለንም። መስደብ፣ ማንጓጠጥ፣ ማዋረድ፣ ክብርንና ሰብዕናን የሚነካ ማንኛውንም ነገር ማድረግ ሁሉ ከአካላዊ ጥቃት ባልተናነሰ በወንጀለኝነት የሚጠቀሱ ድርጊቶች ናቸው። ነገር ግን ምን ያህሎቹ የፍትህ ተቋማት ናቸው በስድብ፤ በማንጓጠጥ ክስ ያቀረበችን ሴት ጉዳዬ ብለው አይተው በወንጀለኛው ላይ ቅጣት ያሳለፉት?

የማህበረሰብ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ኤሲዲዮ የሚሳተፉበት ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም አለ። እርሳቸውም በአንዱ ዝግጅት ላይ የሰጡት አንድ ምሳሌ ነበር። አንዲት ሴት በሌሊት ብቻዋን ከቤት ወጥታ ብትሄድ መፍራት ያለባት እንደጅብ ያሉ አውሬዎችን እንጂ ሰው አይደለም። ምክንያቱም እንስሳት አያስቡም፤ አያገናዝቡምና ጥቃት ቢደርስባት ጥፋተኛዋ በዚያን ሰአት ብቻዋን ከቤት የወጣችው ሴት ራሷ ትሆናለች። ሰዎች ግን አዕምሮ አላቸው ያስባሉ፤ ያገናዝባሉና ሴቷ በዚያን ሰአት በሰዎች ጥቃት ቢደርስባት በየትኛውም መስፈርት ጥፋተኛ ልትሆን አትችልም።ይልቁንም ሊረዷትና ሊደግፏት ሲችሉ የጎዷት ወይም ጥቃት ያደረሱባት ሰዎች ናቸው ጥፋተኛ የሚባሉት፤
ይህንን ጽሁፍ እያነበባችሁ ያላችሁ ወላጆች፤ መምህራን፤ የሚዲያ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች፤ ባለስልጣናት፤ ታዳጊ ወንዶችና ሴቶች ምን እያሰባችሁ ነው? ከአቅማችን በላይ ሆኖ አልቆም ያለው የሴቶች ጥቃት የእያንዳንዳችን እጅ እንዳለበት ምን ያህል ታውቃላችሁ?

ወላጆች ወንዶች ልጆቻችሁ ከትንሿ ለከፋ ጀምሮ በሴት ልጅ ላይ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠቡ መምከራችሁን ደግማችሁ አስታውሱ እስቲ፤ መምህራን በክፍል ውስጥ ገብታችሁ ከምታስተምሩት የሂሳብ፤ የኬሚስትሪና መሰል ትምህርት ላይ የደቂቃዎች ጊዜ ሸርፋችሁ ስንት ቀን ለተማሪዎቻችሁ ስለሴቶች ጥቃት ግንዛቤ ሰጥታችኋል? ተሽከርካሪ ወንበር ላይ የተቀመጣችሁ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያላችሁ ባለስልጣናት ድርጅታችሁ ተራ የመዝናኛ ፕሮግራም ስፖንሰር ከማድረግ ይልቅ በዚህ ጉዳይ ላይ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ምን ያህል ጥረት አድርጋችኋል? በሚዲያ አካባቢ ያላችሁ፤ የህዝብ ጆሮ ናችሁ የምትባሉ ጋዜጠኞች በዓመት አንዴ በወርሀ ህዳር የሚከበረው የ“ሴቶችን ከጥቃት እንጠብቅ” አሊያም የሴቶች ቀን (March 8) ሲደርስ ብቻ ለዝግጅታችሁ ወይም ለጽሑፋችሁ ድምቀት ከምታቀርቡት ፕሮግራም የዘለለ ስለሴቶች ጥቃት መንስኤዎች፤ ውጤቶችና መፍትሄዎች ምን ያህል ጊዜ ለታዳሚዎቻችሁ ቁምነገር አካፍላችኋል? ወጣትና ታዳጊ ወንዶች ስሜታችሁ አዕምሯችሁን ሳይሆን አዕምሯችሁ ስሜታችሁን እንዲመራው ማድረጋችሁን ምን ያህል እርግጠኞች ናችሁ? የችግሩ ዋነኞቹ ተጠቂዎች የሆናችሁ ሴቶችስ ለመብታችሁ ዘብ ቋሚ እንደሆናችሁ፤ በራስ መተማመናችሁን በዕውቀትና በልምድ እያሳደጋችሁ እንደሆነ፤ ከሚደርስባችሁ ጥቃት በደል ጀምሮ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ያገባኛል ብላችሁ ትኩረት እንደምትሰጡ ምን ያህል እርግጠኞች ናችሁ? ሁላችሁም ወደልቦናችሁ ተመለሱና ይህንን ጉዳይ አብላሉት።

ባልዲው የሞላው ሁላችንም ባንጠባጠብነው ውሃ ጥርቅም መሆኑ ግልፅ ከሆነ፤ ባልዲውን ማጉደል ወይም ባዶ ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ውሃ በመቀነስ ነው። ለዚህ ደግሞ እያንዳንዳችን ያዋጣነውን ውሃ መቀነስ እንዳለብን ግልጽ ነው። እናም ሁላችንም ራሳችንን ቆም ብለን እንመልከት!

አዲስ ዘመን ጥር29/2011

ህሊና ተስፋዬ