የወጣቶችን ገቢ ማሻሻል ያስቻለ የስራ ዕድል

35

ስራ ማጣት ሲያብሰለስላቸው የነበሩ ወጣቶች ለምን ስራ አንፈጥርም? በሚል ቁጭት አምስቱ ወጣቶች አንድ ላይ በመሆን ኮልፌ ክፍለ ከተማ የቤተል አካባቢ ከአዲስ ብድርና ተቋም 250ሺ ብር በመበደር የማስዋብ (ዲኮር) ስራ በመስራት ገቢ ማመንጨት መጀመራቸውን የሚገልፀው ወጣት ጥላሁን አብደታ ስራ አጣሁ በሚል እጃቸውን አጣጥፈው ከመቀመጥ ይልቅ የሰርግ ፣ የስብሰባ አዳራሾችን የማስዋብ ስራ በመስራት ስምንት ወራት ውስጥ ገቢያቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ይመሰክራል።

ለውጡንም ሲገልፅ «ዛሬ የእራሳችን ኑሮ የምናሸንፍበት ገቢ ከማግኘት ባለፈ ብድራችንን መልሰን 400 ሺህ ብር ሀብት አፍርተናል።ለ3 ሰዎችም የስራ ዕድል ፈጥረናል፡፡የሙሽራ ወንበር፣ አልባሳትና ሌሎች የማስዋቢያ ዕቃዎችን ተከራይተው ሲሰሩ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በራሳቸው ወጪ ገዝው እየሰሩ ነው›› ብሏል።

የወረዳ 6 ጥቃቅንና አነስተኛ ጽህፈት ቤትም 15 ካሬ ሜትር ቢሮ ሰጥቷቸዋል፡፡የበለጠ መስራትንና የተሻለ ዕድገትን እንሻለን የሚለው ወጣት ለዚህም ራሳቸውን ዝግጁ አድርገው እየሰሩ ይገኛሉ ።የማስዋብ ስራ ወቅታዊ ስለሆነም በቀጣይ ሆቴል የመክፈት ዕቅድ አለን ሲል ነግሮናል፡፡
ወጣቱ ገርበብ ያለ በር ሲያገኘ በደንብ በመክፈት ያገኘውን ዕድል ማስፋት አለበት የሚል ጽኑ እምነት ያለው ወጣት ጥላሁን ይህን ዕድል ከማስፋት ይልቅ የተሰጣቸውን ዕድል የሚያጨልሙ ወጣቶችን ወቅሷል፡፡ስለዚህ ወጣቱ ያለውን መልካም ዕድል በመጠቀም በትጋት መስራት ይኖርበታል ሲል መልዕክት አስተላልፏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ካሉት አስር ክፍለ ከተሞች በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ለውጥ ማምጣት የቻሉ ኢንተርፕራይዞች መካከል አንዱ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በከተማ ግብርና ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው አስኳል የመኖ ማቀነባበሪያ ተጠቃሽ ነው።
አስኳል የመኖ ማቀነባበሪያ ኢንተርፕራይዝ የከብቶችና የዶሮ መኖን በተሻለ ደረጃ አዘጋጅቶ ለገበያ የሚያቀርብ ነው። ማህበሩ በ50 ሺህ ብር መነሻ ካፒታልና በአምስት አባላት ስራውን የጀመረ ሲሆን፤ በአሁን ጊዜ አንዱ አባል በህመም ምክንያት ተሰናብቶ አንድ ሴትና ሶስት ወንዶች ሆነው በስራቸውም ለ16 ሰዎች የስራ ዕድል በመፍጠር ከአባላቱ ጋር በድምሩ 20 ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ።

ማህበሩ በዋናነት የተለያዩ የእንስሳት መኖን በማምረት የሚሸጥ መሆኑን የማህበሩ አባልና የንግድ መምሪያ ኃላፊ ወጣት ደረጄ ሀብታሙ ይናገራል። አባላቱም በእንስሳት መኖና በእንስሳት እርባታ የተማሩና ልምድ ያላቸው በመሆኑ እውቀታቸውን ተጠቅመው ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል።የመንግስት ድጋፍም ያልተለያቸው መሆኑን ያነሳል። ስልጠናዎችን ሰጥቶናል፣ንግድ ትርኢት እንድንሳተፍ አድርጎናል፣ በመስሪያ ቦታችን የነበሩ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ቀርፎልናል፡፡ ድጋፍና ክትትል አድርጎልናል።

ከአዲስ ብድርና ቁጠባም ተቋም 400 ሺህ ብር ተበድረን በአንድ ዓመት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ብድሩን መመለስ ችለናል የሚለው ወጣት ደረጄ ለስኬት ያበቃን ዋናው ነገር አባላቱ በሙሉ በእንስሳት እርባታና መኖ የተማሩና ዕውቀት ያላቸው መሆናቸው ነው ይላል። ስለዚህ ሰዎች በማህበር ሲደራጁ በፍላጎታቸውና ያላቸውን እውቀት መሰረት አድርገው ቢደራጁ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ከአስኳል ማህበር ሊማሩ ይገባል ባይ ነው። ማህበራቸውም በ2009 ዓ.ም በአንድ ዓመት ውስጥ ጥሩ አፈፃፀም ያስመዘገበ በሚል ጎንደር ላይ በተደረገው የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ውድድር ተሸላሚ ነበረ፡፡በዘርፉ ለተሰማሩት ማህበራትም ስልጠና ይሰጣል፡፡

አቶ ወንድሜነህ ዓለም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት የኢንተርፕራይዞች ድጋፍና ሽግግር ቡድን መሪ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በበኩላቸው መንግስት ያመቻቸውን ብድር የመመለስ ሁኔታና የመስሪያ ቦታን ተረክቦ በወቅቱ ያለመልቀቅ ችግሮች በስፋት የሚታዩ ናቸው፡፡ ይህን በሚያደርጉት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ለአብነትም ያህል በጉለሌ ክፍለ ከተማ እግዚአብሔር አብ አካባቢ ከተሰጠው ቦታ በላይ አስፋፍቶ የያዘ ኢንተርፕራይዝ ቦታውን ለሌሎች ኢንተርፕራይዞች ከፍሎ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡እንዲሁም የመስሪያ ቦታውን ለሁለተኛና ለሶስተኛ ወገን አሳልፈው የሰጡ ኢንተርፕራይዞች ሙሉ በሙሉ ቦታውን በማስለቀቅ ለሌሎች ተሰጥቷል ብለዋል።

የፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በመደበኛና በግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች ስምንት ነጥብ አራት ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ይዞ እየሰራ ነው። አንድ ዓመት ከመንፈቅ ጊዜ በቀረው የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ለአምስት ሚሊዮን 163ሺ926 ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ፈረደ ይገልጻሉ።

የስራ ዕድል ፈጠራ የሚያተኩርባቸው መስኮች በመደበኛና በግዙፍ የመንግስት ልማት ፕሮጀክቶች፤ እንዲሁም በቅጥር የሚፈጠሩ መሆናቸውን የገለፁት አቶ አሰፋ ፈረደ፤ መደበኛ የስራ መስኮች የሚባሉት በአምስት ዋና ዋና የስራ ዘርፎች ማለትም ማኑፋክቸ ሪንግ፣ የከተማ ግብርና፣ ኮንስትራክሽን፣ ንግድና አገልግሎት ናቸው፡፡ በ2011 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በእነዚህ የሥራ ዘርፎች ለ325ሺ139 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ እንዲሁም በግዙፍ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶችና በቅጥር ማለትም በቤቶች ግንባታ፣ በመንገድ ስራ፤ በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና በማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታዎችና በመሰል የስራ መስኮች ደግሞ ለ309ሺ 950 በድምሩ ለ635ሺ089 ሥራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል።

መንግስታዊ ድጋፎች
በስራ ዕድሉ ምንም አይነት ገቢ የሌላቸው ማንኛውም ዜጋ ተሳታፊ መሆን እንደሚችል የሚናገሩት አቶ አሰፋ፤ በሁሉም ክልሎች በዓመት ሁለት ጊዜ የስራ አጥ ዜጎች ምዝገባ ይካሄዳል ይላሉ። አብዛኛዎቹ ሥራ ፈላጊዎች ወጣቶች ናቸው። በመሆኑም ወጣቶቹን እንዲደራጁ በማድረግ በቅድሚያ የስራ ክቡርነትንና የስራ ፍቅርን እንዲያዳብሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይሰጣል፡፡ ለሥራ ፈጠራ ዝግጁ እንዲሆኑም ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

ስራ ፈጣሪው ወጣት ወደ ስራ ለመሰማራት በቅድሚያ 20 በመቶ ሲቆጥብ መንግስት ደግሞ 80 በመቶ ብድር ያመቻቻል። ነገር ግን ኢንተርፕራይዞቹ ብድራቸውን በወቅቱ መመለስ ባለመቻላቸው ከፍተኛ ችግር እንደገጠማቸው የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ባለፉት ሶስት ዓመት ከመንፈቅ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ብድር የተሰጠ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ተመላሽ ሁኗል። ስራ ፈጣሪዎቹ ብድር በወቅቱ አለመክፈላቸውም ገንዘቡን ለሌሎች ስራ ፈላጊ ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ መሰናክል መፍጠሩን ይጠቅሳሉ፡፡

የገበያ ትስስር በተመለከትም ኢንተርፕራይዞቹ ለሚያመርቷቸው ምርቶች ገበያ የማፈላለግ ሥራም ይሰራል። ይህ ማለት መንግስት ሁልጊዜ ሥራ ያፈልጋል ማለት ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ ወጣት ወይም ኢንተርፕራይዞቹ ራሳቸው አካባቢያቸውን በማጥናት ገበያው የሚፈልገውን ምርት በማምረት ገበያውን ሰብረው እንዲገቡ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ነው የሚናገሩት።

የፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በዓመት ሁለት ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ የንግድ ትርኢት ያዘጋጃል፡፡በዚህም ጥራት ያለውን ምርት የሚያመርቱ የተለያዩ ኢንተርፕራይዞች ምርታቸውን የሚያስተዋውቁበት ነው። በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ዘጠኝ ነጥብ አንድ ቢሊዮን የገበያ ትስስር ለመፍጠር ታቅዶ ስምንት ቢሊዮን 129 ሚሊዮን 234ሺ 973 የገበያ ትስስር ተፈጥሯል። የገበያ ትስስሩ የተፈጠረባቸው መስኮችም ለውጭ ገበያ በማቅረብ፣ ኤግዚቢሽንና ባዛር በማዘጋጀት፣ በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር፣ በጨረታና በተለያዩ የግብይት ስርዓቶች መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ኢንተርፕራይዞች ስራ ሲጀምሩ ምርታቸውን የሚያመርቱበትና የሚሸጡበት ቦታ ያስፈልጋቸዋል። ይህን ቦታ ደግሞ ለሁሉም ኢንተርፕራይዞች መስጠት ስለማይቻል በቤተሰቦቻቸው ቤትና በሚኖሩበት አካባቢ ስራውን እንዲጀምሩት ይደረጋል። ስራው እየሰፋ ሲሄድ መንግስት የተወሰኑትን ኢንተርፕራይዞች በተሻለ አቅም እንዲያመርቱ የመስሪያ ቦታ (ሼዶችን) እየገነባ ይሰጣል። ለከተማ ግብርናም እንደ ዶሮና ከብት እርባታ ለመሳሰሉት ቦታ በጊዜያዊነት ይሰጣል። በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ በአጠቃላይ አንድ ሺ163 ሄክታር መሬት ዝግጁ ሆኖ ለከተማ ግብርና እና ለሼድ ተጠቃሚዎች ተላልፏል።

በ2011 ዓ.ም ስድስት ሺ 163 ሼዶችን ገንብቶ ለማስተላለፍ የታቀደ ቢሆንም ማስተላለፍ የተቻለው አንድ ሺ 253 ሼዶችን ብቻ ነው። በእነዚህ ሼዶችም 84ሺ 367 አንቀሳቃሾችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ 30ሺ 743 አንቀሳቃሾችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

አዲስ ዘመን ጥር29/2011

ፍሬህይወት አወቀ