አካል ጉዳተኝነት ያልበገረው ወጣት

24

አካል ጉዳት ማለት ከመጠሪያው መረዳት እንደሚቻለው በሰዎች አዕምሮ ወይም አካል ላይ፤ አንዳንዴም በሁለቱም ላይ በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሠራሽ አደጋ ምክንያት የሚከሰት ነው። የአካል ጉዳት የሰውነት ተግባርና መዋቅር ላይ ችግር ሲያጋጥም የሚከሰት በመሆኑ በአካል ላይ በሚደርሰው ጉዳት መጠን ልክ ከእንቅስቃሴ መወሰንና ከተሳትፎ መገደብን ያስከትላል።

የአካል ጉዳተኛው እንቅስቃሴና ተሳትፎም ባለው ነባራዊ ሁኔታና በአካባቢው ምቹነት የሚወሰን እንደመሆኑ፤ አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ ለአካል ጉዳተኛ ዜጎቿ ምቹ አካባቢን አልፈጠረችም ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። ምክንያቱም በአንፃራዊነት የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ተሟልተውላታል በምንላት በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ እንኳን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ባለመሆኗ በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ውስጥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲገጥሟቸው ሰምተናል፤ ዓይተናል።

ከዚህም በላይ ማህበረሰባችን ለአካል ጉዳት የሚሰጠው ግምት በእጅጉ የተሳሳተ በመሆኑ ብዙዎች ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል፤ ታፍነዋል፤ ተረስተዋል። ይሁን እንጂ ጥቂት የማይባሉ አካል ጉዳተኞች ደግሞ ከቤተሰብና ከአካባቢው ማህበረሰብ ባገኙት ድጋፍ፤ ምቾት የማይሰጡ ጎርባጣዎችን ደግሞ በመታገል ተምረው ወደፊት በመውጣት ጥሩ ደረጃ ላይ የደረሱና ለሌሎች አካል ጉዳተኞችም አርአያ መሆን የቻሉ፤ አሁን በትምህርት ላይ ያሉና ወደፊት ደግሞ ከታላላቅ ሥራቸው ጋር ብቅ የሚሉ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ተስፈኛ ልጆችም አሉ።

ከእነዚህ ተስፈኛና ተጠባቂ የኢትዮጵያ ልጆች መካከል አንዱ ተማሪ አቤኔዘር ሕዝቅኤል ነው። አቤኔዘር ተወልዶ ያደገው በጋሞጎፋ ዞን አርባምንጭ ከተማ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ5ኛ ዓመት የህግ ተማሪ ሆኖ በዊልቸር የሚንቀሳቀስ አካል ጉዳተኛ ወጣት ነው።
በጣም የሚገርመውና አቤኔዘርን ከሌሎች የአካል ጉዳተኞች ለየት የሚያደርገው ለከፍተኛ ትምህርት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን እስከተቀላቀለበት ጊዜ ድረስ አልፎ አልፎ በቅዝቃዜ ሰዓት ከሚሰማው የእግር ህመም ውጪ ፍፁም ጤነኛ መሆኑ ነው። የአንደኛ ዓመት ተማሪ እያለ ችግሩ እንዳጋጠመው የሚናገረው አቤኔዘር፤ ወደዚህች ምድር ሲመጣ ሙሉ አካል ይዞ ጤናማ ነበር። እንደእኩዮቹም በሙሉ አካሉ ተጫውቶ፤ ቦርቆ፤ እነርሱ የሆኑትን ሁሉ ሆኖ አድጓል። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በአርባምንጭ ከተማ አጠናቅቋል።

አቤኔዘር የመጀመሪያ ዓመት የህግ ትምህርቱን እየተከታተለ በነበረበት በ2007 ዓ.ም ሳያስበው ሁለቱም እግሮቹ አልታዘዝ ብለውት ዊልቸር ላይ ተቀመጠ። «አንዳዴ ስለራሴ ሳስብ ዊልቸር ላይ መቀመጤ በጣም ይገርመኛል፤ እንደዚህ እሆናለሁ ብዬ በፍፁም አስቤ አላውቅም ነበር፤ ነገር ግን ይኸው ዊልቸር ላይ ዋልኩ፤ ያለዊልቸር መንቀሳቀስ አልችልም። ይሁን እንጂ፤ አካል ጉዳተኝነት ለማንም ሰው ቢሆን የአጋጣሚ ጉዳይ እንጂ ሌላ ምንም ማለት አይደለም» ይላል።

አቤኔዘር ካጋጠመው የእግር ህመም ለመፈወስ የተለያዩ ህክምናዎች ተከታትሏል። ይሁን እንጂ፤ በሀገር ውስጥ ባደረገው ህክምና ሊድን እንደማይችልና በውጭ ሀገር በደቡብ አፍሪካ ሄዶ ቢታከም የመዳን ዕድሉ የሰፋ መሆኑ በሀኪሞች ተረጋግጦለታል። ታድያ አቤኔዘር የህግ ትምህርቱን አጠናቅቆ የመዳን ተስፋ የተጣለበትን የውጭ ሀገር ህክምና ለማድረግ ከፍተኛ ጉጉት አድሮበታል። ሆኖም የውጭ ሀገር ህክምናው ተሳክቶ ወደ ቀድሞው ጤንነቱ እንዲመለስ የሌሎች እገዛ እንደሚያስፈልገው ይናገራል።

ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ ዊልቸር ላይ መቀመጡን ከአባቱ በስተቀር ወላጅ እናቱም ሆኑ እህት ወንድሞቹ አለማወቃቸው ነው። የሰው ልጅ በተስፋ መኖር እንዳለበት አምናለሁ ስለሆነም ማንኛውም ሰው ነገን ተስፋ እንደሚያደርገው ሁሉ እኔም እንደማንኛውም ሰው ትልቅ ተስፋ አለኝ። ጠንክረን ከሠራንም ሁላችንም ያሰብንበት ቦታ መድረስ እንችላለን። እኔም ብዙ መሥራት የምፈልጋቸውና የማስባቸው ነገሮች አሉ ያሰብኩበት ደረጃ እንደምደርስም አምናለሁ ይላል።

አካል ጉዳተኛ መሆን ከምንም ነገር አያግድም፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጊዜ አካል ጉዳተኛ መሆን የምፅዋትና የተረጂነት ሰለባ ተደርጎ ይታሰባል። አካል ጉዳተኛ መሆን ከአካላችን አንድ ነገር ማጣት እንጂ፤ ሙሉ ለሙሉ ተስፋ ማጣትና ተረጂ መሆን አይደለምና ከዚያ ባሻገር ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር እንዲማሩ፤ እንዲሠሩና እንደ ማንኛውም ሰው መንቀሳቀስ እንዲችሉ ማድረግ ያስፈልጋል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ ማንኛውም ነገር ሲሠራ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ በማድረግ አይደለም። መንግሥት እዚህ ላይ ሊሠራ ይገባል። ምክንያቱም ጉዳዩ የተረጂነት ሳይሆን የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው የሚለው አቤኔዘር፤ ኢትዮጵያም የፈረመቻቸው የዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ህግ ማንኛውም ነገር ላይ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ እንድታደርግና ትኩረት እንድትሰጥ ያስገድዳል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ወስዶ ሊሠራ ይገባል፤ እንደሚሠራም እምነቴ ነው ይላል።

አቤኔዘር ሕዝቅኤል በቅርቡ ወደስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስለአካል ጉዳተኞች የተናገሩትን በማስታወስ ደስተኛና ተስፈኛ መሆኑን ይናገራል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን ከመጡ ወዲህ በአንድ ወቅት አካል ጉዳተኞች ትኩረት አላገኙም፤ በየትኛውም መንገድ ትኩረት የሚሹ ዜጎች ናቸውና ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል በማለት ተናግረዋል። ከዚህም በላይ ደግሞ አካል ጉዳተኞች ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱበት ዊልቸር ኢትዮጵያ ውስጥ ባለመሠራቱ ምክንያት ብዙ ቁጥር ያላቸው አካል ጉዳተኞች ለመንቀሳቀስ ተቸግረዋል፤ መብታቸውም ተገድቧል። ስለዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ የዊልቸር ፋብሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚከፈት ቃል በመግባት ለአካል ጉዳተኞች ትልቅ ዜና አብስረዋል።

ይህ ደግሞ ለአካል ጉዳተኞች ትልቅ ተስፋ ነው። ምክንያቱም፤ እስከአሁን ለአካል ጉዳተኞች ዊልቸር የሚመጣው ከውጭ ሀገር በመሆኑና ሀገር ውስጥ ዋጋውም ውድ በመሆኑ ችግሩን የበለጠ አወሳስቦታል። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገቡት ቃል መሰረት ዊልቸር በሀገር ውስጥ መመረት ከጀመረ ማንኛውም አካል ጉዳተኛ በቀላሉ ገዝቶ መጠቀምና ሲበላሽም በቀላሉ ማስጠገን ስለሚቻል የችግሩን መጠን በብዙ እጥፍ መቀነስ ይቻላል።

ለምሳሌም፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉት አካል ጉዳተኞች የሚጠቀሙበት ዊልቸር ሲበላሽ ለማስጠገን የሚፈጀው ጊዜ እጅግ ረጅም በመሆኑ ለከፋ ችግር እንደሚጋለጡና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውም በዚያው ልክ እንደሚገደብ አቤኔዘር ይናገራል። በአንድ ወቅት አቤኔዘር የዊልቸሩ ጎማ ተበላሽቶ ለማስቀየር ከሁለት ወራት በላይ እንደጠበቀና በዚህ ጊዜ ውስጥም ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የጓደኞቹን ዕርዳታ ይጠብቅ ስለነበር ሁኔታው በጣም አስቸጋሪና ከባድ እንደሆነ ይናገራል።

በተለይም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያለው መንገድ የአካል ጉዳተኞችን ችግርና ፍላጎት ያላገናዘበ በመሆኑ በዊልቸር እንኳን ለመንቀሳቀስ በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ ነው። ወደካፌም ሆነ ወደላይብረሪ፤ እንዲሁም ወደማደሪያ ክፍሎች ለመንቀሳቀስ ያለው ፈተና ቀላለ አይደለም። አብዛኛው አካል ጉዳተኛም በግቢ ውስጥ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የሌሎች እገዛና ዕርዳታ የግድ ይለዋል፤ በእርግጥ፤ ማንኛውም ሰው በህይወት ሲኖር ብዙ ውጣውረዶች ይገጥሙታል፤ የሚለው አቤኔዘር አካል ጉዳተኛ ስንሆን ደግሞ ተጨማሪ ችግርና ተጨማሪ ትግል ይጠበቅብናል። ይሁን እንጂ፤ ከኛ ጥረት በላይ ለሆነው ነገር ሁሉ ተቋሙም ሆነ መንግሥት እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ፤ ማህበረሰቡም ጭምር የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ጉዳዬ ብሎ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላል።

በመጨረሻም፤ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ፖለቲካ ምክንያት የማይቻሉ የማይነኩና የማይደፈሩ የሚመስሉ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መንግሥት ተችለው፤ ተነክተውና ተደፍረው ዓይተናል። አሁንም መልካም ሥራቸውንና አመራራቸውን ወደፊት በማስቀጠል ለአካል ጉዳተኞች የገቡትን ቃል ተግባራዊ አድርገው ነገ ከነገ ወዲያ ሰላሟ የተጠበቀ፤ የበለጸገችና ለአካል ጉዳተኛ ዜጎቿ ምቹ የሆነች ኢትዮጵያን እንደሚያሳዩን እምነታችን ነው እያልን አሁንም ትኩረት ለአካል ጉዳተኞች ይሁን እንላለን።

አዲስ ዘመን ጥር29/2011