ደግሰን ግራ ከምንጋባ …

15

የዘንድሮን ሰርግና ሰርገኛ ጠላሁት፤ ምክንያት ስላለኝም ኮነንኩት፡፡ ለምን ካላችሁ፣ ከውዴ አጋጨኝ፤ ከፍቅሬ ጋር ለየኝ፡፡ ታዲያ ብጠላው ምን ያንሰኛል? ከውዴ ጋር ከተዋወቅን ሶስት አመት ሞላን፤ ከተግባባን ግን ሶስተኛ ወራችን ነው፡፡ ግራ መጋባት ከጀመርን ደግሞ ሶስተኛ ሳምንታችን፤ ግራ መጋባታችን አድጎ ከተኳረፍን ሶስተኛ ቀናችን፡፡ እኔና ውዴ የማያግባባን ሶስት መሰረታዊ ነገር ነው፡፡ አንዱ እኔንም አሳምኖ፣ ባንዱ ላይ ደግሞ ተቻችሎ መቆየት ችለን ነበር፤ ሶስተኛው ጉዳይ ግን ልዩነታችንን አስፍቶ አቃረነን፡፡

ከባዱን ውሳኔ ወስነን ነበር ለመጋባት፡፡ ቀለል ያለው ጉዳይ ግን ግራ አጋባን፡፡ እንዴት መጋባት እንዳለብን ስላልተግባባን ተለያየን፡፡ ምክንያቱም ውዴ ውድ ነገሮችን አጥብቃ ትወዳለች፡፡ ምግብ ቤት ገብተን ከምግብ ዝርዝር እና ዋጋ ማሳያ ሰሌዳ /ሜኑ/ ውስጥ ውድ ምግብ ካልሆነ አታዝም፤ ልብስ ልንሸምት ከወጣን ከልብሶችም ውዱን እንጂ አትመርጥም፡፡ ይሄን ማድረግዋ አስከፍቶኝ አያውቅም ነበር፡፡ ውድ ነገር መምረጥዋ በምክንያት ወድጄው ነበር፤ እኔንም ውድ ስለሆንኩ ነው የመረጠችኝ ብዬ፡፡ ምን ዋጋ አለው ዛሬ አንተ ከሰርጉ የበለጥክ ውድ አይደለህም ብላ መሰለኝ ትታኝ ሄደች፡፡

ሰዎች ለምን አታገባም ብለው ሲያስጨንቁኝ፤ እኔም ቆሞ መቅረቴ ሲያሳስበኝ ያስቀመጥኩትን መስፈርት ሁሉ ንጄ ነበር ውዴን የቀረብኳት፡፡ እርግጥ ቀርባኝ መጣመር ለካስ ጥሩ ነገር አለው እንድል አስችለኝ፤ መስፈርቴንም ጭራሽ እንድተውም አድርጋኝ ነበር፡፡ ወድጃትም ልንጋባ ወሰንን፤ ለዚያም መዘጋጀት ጀምረን ነበር፡፡ ዝግጅት ማድረግ ካቆምኩ ሶስት ቀን ሞላኝ እንጂ፡፡ ሰርግ ካልደገስን አለች፤ እኔ ደግሞ ሰርግ ጥሩ ለኛ አለመሆኑን ተሟገትኩ፡፡

ሆኖም ሰርግ ጥሩ ያልሆነው ለኔ ብጤ ነው፤ ወሩን ጠብቆ ጠብ የሚል ገቢ ላለው፡፡ ለደላውማ ሰርግ በየአመቱ ቢደጋገም ፍቅሩ ባይደምቅ ድግሱ መድመቁ አይቀር፡፡ ለኔ ግን ሰርግ መሰረግ አይደለም ስሙ ከባድ ነው፡፡ በሌለን ገንዘብ ሰርገን ግራ ከምንጋባ ተግባብተን እንጋባ ብያት ነበር፡፡ ብዙ ጎትጉቼም አሳምኛት ነበር፡፡ የሰሞኑ የሰርግ ግርግርና ሰርገኛ መልሶ ሃሳብዋን አስቀየራት፡፡ ማሳመኛ ምክንያች ደረደርኩ ወይ ፍንክች፡፡ ፍቅር እንጂ ሰርግ ጎጆን አያሞቅም ብዬ በአለም ላይ ትልቅ ወጪ ወጥቶባቸው በወራት ውስጥ የፈረሱ ሰርጎችን ታሪክ አወራኋት አልሰማህም አለችኝ፤ የባንክ ደብተሬን አሳየዋት አላምን አለች፡፡ ይሄኔ ተከፋው፤ ያን ጊዜ አመረርኩ፡፡ እርግጥ እወዳት ነበር ስንት ያስቀመጥኩትን መስፈርት ቀንሼ…ቀንሼ ኧረ እንደውም ትቼ ቀረብኳት፡፡ አንቺ ትሻይኛለሽ ብዬ ስለስዋ ሁሉንም ተውኩ፡፡

የኔ ነገር ለካስ ውዴን እንዴት እንደተዋወኳት አልነገርኳችሁም፡፡ ሳላገባና ሳልወልድ አንድ ምዕተ አመት ተጋመሰብኝ፡፡ ይሄኔ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ቆሜ እንዳልቀርም ሰጋሁ፡፡ ሰውም አስጨነቀኝ “ሚስት ለምን አታገባም?” ብሎ ደጋግሞ ሲወተውተኝ ፍላጎቴ ተባባሰና ውሃ አጣጬን መፈለግ ጀመርኩ፡፡ ታዲያ ያኔ እንደ ሚስት ስፈልግ እንደ መስፈርት የደረደርኳቸው ነገሮች ብዛት ዛሬ ሳስብ ይገርመኛል፡፡ ያን ሁሉ መስፈርትም ውዴ አስትታኝ ነበር፡፡ ዛሬ ትታኝ ልትሄድ ስቱን አስተወችኝ ወይ ነዶ፡፡

እኔ ሚስት ለማግባት ካስቀመጥኳቸው መስፈርቶች ውስጥ አንዱ ብዙ ልጅ ልትወልድልኝ ፍቃደኛ የሆነች ሚስት ማግኘት ነበር፡፡ አዎ መስፈርቴ በብዙ ሴቶች የማይሞከር ሆኖብኝ ተቸግሬ ነበር፡፡ ልጅ በጣም እወዳለሁ፤ በጣም ብዙ ልጅ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ ቢያንስ አንድ ደርዘን ሊኖሩኝ ግድ ይላል ብዬ አስብ ነበር፡፡ ከተቻለም ቁጥሩ ከፍ ቢል የኔም ደስታዬ ከፍ ይላል፤ ሚስቴንም ይበልጥ እወዳታለሁ ማለትን አዘውትሬያለሁ፡፡ እንደው ለሚስቴ ካዘንኩኝና ትንሽ ከራራሁ ከአስራ ሁለት አንድ ልቀንስላት እችላለሁ፡፡

ከ11 ግን ፈጽሞ አልቀንስም፡፡ በቃ መጨረሻዬ ነው፤ ዘጋሁት፣ 12 ካልተቻለ 11 ልጅ፡፡ ከዚያም 12 ወይም 11 እድሎችን በተለያየ አስር አቅጣጫ መጠበቅ፡፡ ህይወት የምትሰምረው በእድል ነው ብዬ አስብ ነበራ፡፡ በነገራችን ላይ እድልና እድለኝነት ዛሬ ድረስ አምንበታለሁ፡፡ በእስከዛሬ ተሞክሮዬ ጥረት እና ትጋት ምንም ስላልፈየዱልኝ በእድል ማመን ጀምሬያለሁ፡፡ በነገራችን ላይ በእድል አለማመን የሚያከብዱብን ሁኔታዎች ሲደጋገሙ እድል ላይ ያለን አተያይ ይለወጣል አይደል? እኔ ግን በእድል በጎ ተፅዕኖ ተፈጥሮብኝ በሱ ማመን ጀምሬያለሁ፡፡ እድል ባይኖር ኖሮ አንዳንዱ አንድም ቀን ሳይሰራ የሚቸረው የተትረፈረፈ ሀብትና የተሟላ ኑሮ ባልኖረ፤ ሌላው ደግሞ እድሜውን ሙሉ ሲማስን ኖሮ በወጉ ጠግቦ መብላት ብርቅ ባልሆነበት ነበር፡፡ እናም ህይወት እድል ናት፡፡

የልጆች ቁጥር ብዙ ሲሆን ብዙ እድል ይገኛል ብዬ ማሰብ ያስጀመረኝም ጉዳይ የበረከተ ነበር፡፡ ኮንዶሚኒየም እጣ ሲወጣ በእጣ አወጣጡ ላይ ብዙ ቤተሰብ ያለው ቅድሚያ ተሰጥቶት ብዙ ክፍል ያለው ቤት ይሰጠዋል አሉ፡፡ ባለፈው የመምህራንን አለያችሁም? ብዙ ልጅ ያላቸው ብዙ ክፍል ያለው ቤት አግኝተዋል፡፡ እናም ልጅ ሲኖር እድል ይሰፋል ዝም ብላችሁ ውለዱ፡፡

አስቡት እስቲ ጥሩ ኑሮ የምትኖሩትና ጥሩ ምግብ የምትበሉት ልጅ ስለሌላችሁ ወይም ቁጥራቸው አነስተኛ ስለሆነ አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ የዚህ ተቃራኒ የሚሆነው ቁጥራቸው የበዛ ልጆችን ስለወለዳችሁ አይደለም፡፡ ይልቁንም የልጆቻችሁ ቁጥር መብዛት ለስኬት ያቃርባል፡፡ ልጆቻችንን ለማሳደግ ይበልጥ ስንጥር የኑሮ ሁኔታችንም ያድጋል፤ ይቀየራል፡፡ ደግሞ አምላክ ላንድ ሰው የፈጠረው የሰውየው ድርሻ ማንም ሊቀንስበት ወይም ሊጨምርለት አይችልም እንደው ለሰበቡ እንሮጣለን እንጂ፡፡

እሩጫችን ይጨምር ግድየለም በደንብ እንትጋ ለልጆቻችንም ወንድምና እህት እንጨምርላቸው፡፡ በአለም ላይ ተጽዕኖ ፈጥረው ካለፉ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ስለቤተሰባቸው ብታጠኑ የቤተሰባቸው 4 ወይም 5 ልጅ ሆነው ነው የምታገኙዋቸው፡፡ ታዲያ አለም ላይ በጎ ተፅዕኖ ፈጥረው ያለፉ ሰዎች ወላጆች አሁን የሚባለው የቤተሰብ ምጣኔ ቢኖር ስንት ነገር ይቀርብን ነበር፤ አስባችሁታል? ኧረ የምን ምጣኔ ነው? እሱን ለገጣሚዎች እንተውላቸው፡፡ የግጥም ቀለም ምጣኔ እንጂ የቤተሰብ ምጣኔ አይጥምም፡፡ ተፈጥሮን መጥኖ ደግሞ አይቻል ነገር መዘዙ ብዙ ነው፡፡ አለም ደግሞ የሚበላ ጠፍቶ ወይም አሁን ላለው ህዝብ የምትበቃ ስላልሆነች አይደለም ፍቅር ስለጠፋ፤ አንድነቱን ህብረቱን መተባበሩን አልፈልግም ስላልን እንጂ፡፡

አለም ዛሬ ላይ ሰቆቃዋ እጅግ በርክቶ ዋይዋይታዋ ከምንግዜውም በላይ ጎልቷል፡፡ ግን ደግሞ የአለም እዚህ መድረስ ምክንያት የአለም ህዝብ ቁጥር መጨመር ነው ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም አለም ላይ ያልተነካና ገና ያልተደረሰበት በጣም ብዙ ሀብት አለ፡፡ ግን ደግሞ ህዝቦችዋ በፍቅር ሳያድሩ ቀሩና እርስ በእርስ መተሳሰቡን ትተወና መነጣጠቁ በዛና ጭካኔው አየለና ሰብዓዊነት ራቀ፡፡
እናም አንዱ ረሀብ ሌላው ቁንጣን ምቾት አሳጣው፡፡ አንዱ ዘለቂ ሰላምን ሲያረጋግጥ ሌላው እሳት ውስጥ በማያውቀው ይማገዳል፡፡ ለዚህ ሁሉ ሰበብ ፍቅር መጥፋት ነውና ለዚህ ሰቆቃና እልቂት መፍትሄው ፍቅር ማስተማር አይመስላችሁም? ታዲያ ምቾትን ያገኘው ፈልጎ ስቃይን የሚያስተናግደው ፈቅዶ አይደለም፤ እድል ባስገኘው ቦታ የተገኘ እንጂ፡፡ እድልማ ወሳኝ ነው፡፡ ይሄማ የትናንት ብቻ ሳይሆን የዛሬም አቋሜ ይመስለኛል፡፡

ከውዴ ጋር እንዴት እንደተገናኘን እያወጋ ኋችሁ ነበር አይደል ቀጠልኩ፡፡ ውዴን ከማግኘቴ በፊት እኔን ለማግባት ከቀረብኳቸውና ከቀረቡኝ ሴቶች ኡ! ይቅርታ ሴቶች አልኩኝ ለካስ “ሴት” ያልሆኑም ነበሩ እናም “ልወልድልህ የምችለው አንድ ልጅ ብቻ ነው፡፡” ካለችኝ አንስቶ በከፍተኛ ጉትጎታ፣ ድርድርና ማግባባት “ሰባት ልጅ እወልድልሀለሁ፡፡” ያለችኝ ሴት ድረስ ገጥማኝ ነበር፡፡ ውዴ መጥታ ቁጥሩን በአንድ ከፍ አድርጋ ሰባትዬን አስተወችኝ እንጂ፡፡ በነገራችን ላይ ከተቀራረብን በኋላ ስምንት እወልዳለሁ ያለችኝ ቁጥሩን ሶስት አድርሳው ነበር፡፡ እኔም ፉክራዬን ትቼ እሺ ብያት የልጆች ፍላጎቴ ከ12 ሁለት ሶስት እጥፍ ቀንሼ ሶስት አደረኩት፡፡ ኧረ ብንቆይ ኖሮ ሶስቱም ይቅር ሳትለኝ እኔም እሺ ሳልል ይቀር ነበር ብላችሁ ነው፡፡

ያኔ ትዳር ለመያዝ ሚስት ስፈልግ ብዙ ልጅ የምትወልድ እንደ ዋንኛ መስፈርት አስቀምጬ አልነበር የምፈልግ እናም አንድ ልጅ ያለችኝ ነበረች እስዋን ከአንድ ጊዜ በላይ አላገኘኋትም፡፡ አንድ ልጅ ላለ አንድ እድል ብቻ ነዋ መስጠት የሚገባው፡፡ ሰባት ያለችኝ ግን ውዴን እስካገኛት ስወዳት ቆይቻለሁ፡፡
ምን አልባትም የአንድ ደርዘን መስፈርቴን የምታሟላ ካልተገኘች በኋላ እንደገና ለትዳር የምትሆነኝን ለማግኘት ስቀርብ ውሃ አጣጪዬ እስዋ ልትሆን ትችላለች፤ የልጆቼ እናት፡፡ ጠበቅ ማድረግ አለብኝ ብዬ ሰባት ጊዜ አግኝቻታለሁ፡፡ “በቃ ሰባት ልጅ ብቻ ነው መውለድ የምፈልገው” የሚለውን የመጨረሻ ቃልዋ መሆኑን እስክሰማ ሰባት ሙከራ አድርጌያለሁ፡፡ እንደው ጥሩ ልጅና ከአራት ነው በብዙ ጉትጎታ ሰባት የደረሰችው፡፡

ብዙ ልጅ የመውለዴን ሃሳብ ለእሷ ብዬ የሰረዝኩላት ውዴ ጋር ከተጋጨው ሶስት ቀን ሞልቶኝ የለ ትንሽ አይቼ ከጨከነች ሰባትዬን ፍለጋ መመለሴ አይቀርም፡፡ እንደውም ብዙ ልጆች የመውለድ ጉጉቴን መቀነሴንና አስተያየት ማድረጌን ብታውቅ ከውዴ ጋር ተጣልታ ሁላ የራስዋ ታደርገኝ ነበር፡፡ እራስሽን ጠብቂልኝ ሰባቱም ቀን በሰላም ወጥተሸ ግቢልኝ የኔ ቆንጆ፡፡ ውዴ እንድትጨክን ፀሎት እንዳታደርጊ ግን እወዳታለ፡፡
ሰባትዬ ያስጣለችኝ ውዴን መጀመሪያ ቀን ተቀጣጥረን ሳገኛት ካፌ ውስጥ ቀድማኝ ተገኝታ ቁጭ ብላ ነበር፡፡ እናም ከፊትዋ ምንም ነገር ሳጣ ደነገጥኩ እንዳታውቅብኝ ብቻ ፈገግ ብዬ ፊትዋ ላይ የጠፋው ፈገግታ እንድታስታውስ ደጋግሜ ብስቅላትም ወይ ፍንክች፡፡ በቃ ኮስተር፤ ቆፍጠ፤ ኦ! አምላኬ መኮሳተርዋ ሲያስፈራ፡፡ አብረን ስንቆይ ግን ጨዋታዋ ጥሞኝ መኮሳተርዋን ተላመድኩትና ተጋብተን የምንወል ዳቸው ልጆች ብዛት ላይ ድርድር ማድረግ ጀመርን፤ መታገስ ጥቅም አለው፡፡

ምን አገባኝ ልጆቼ ቆንጆም ባይሆኑ ችግር የለውም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ለእኔ ብዙ መሆናቸው ነው ዋናው መስፈርቴ፡፡ እንደውም በዚህ እሳት ዘመን ልጆቼ ቆንጆ መሆናቸው አደጋ አለው አስሩ “የኔቆንጆ” እያለ ከሚያስቆ ማቸው፡፡ በአስፈሪ መልካቸው ዘመኑን አልፍው እኔም የምፈልገው ቦታ ይደርሱልኛል፡፡ በኔ ወጥተው ጉድ እንዳያደርጉኝ እንጂ…. እንዴ! የምንሳቅ ነው? እውነት እኔ ቆንጆ ነኝ ግን ከውዴ ጋር ስሆን ነው ከእናንተ ጋር ስወዳደር አላልኩም፡፡

ብቻ ከውዴ ጋር እየተግባባን መጥተን ይበልጥ ስቀርባት ውስጥዋ የተዋበ ነበርና ወደድኳት ለመጋባትም ወስነን ነበር፤ ካለሰርግ ማለትዋ ግን አለያየን፡፡ አቅማችንን እንወቅ ዋናው የኔና አንቺ እውነተኛ ጥምረት ነው ህጋዊ ማድረጉ ላይ እንጂ መደገሱ ላይ አይደለም ወሳኙ ጉዳይ ማለቴ አቀያየመን፡፡ ስንት መስፈርቴን አስትታኝ የቀረበችኝ ውዴ እራስዋ ትታኝ ሄደች፡፡ ሰርግ ከሌለው ጋብቻ ይልቅ ፍቅር የሌለው ሰርግ ይሻላል ብላ ትታኝ ሄደች፡፡ እናንተዬ ተግባብቶ መጋባት ነው ወይስ ሰርጎ ግራ መጋባት ነው የሚሻለው? እኔ ግራ ላለመጋባት ጋብቻዬን ትቻለው፤ እናንተስ?

አዲስ ዘመን ጥር29/2011

ተገኝ ብሩ