‹‹የፋይናንስ አቅርቦት ጉዳይ የህብረት ስራ ሴክተር ቁልፍ ማነቆ ነው››

22

በኢትዮጵያ የህብረት ስራ ማህበራት ዕውቀትን፣ ሀብትንና ጉልበትን በማቀናጀት ችግሮችን በተባበረ ጥረት መቋቋምን አላማ በማድረግ ላለፈው ግማሽ ምእተ ዓመት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ቁጥራቸውን በመጨመርና አደረጃጀታቸውን በማስፋት የፋይናንስን ተደራሽነት፤ በተለይም ለአባሎቻቸው በማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ማህበራቱ የተለያዩ ፈታኝ ችግሮችም ያሉባቸው በመሆኑ የአባሎቻቸውን ፍላጎት በሚፈለገው ልክ እያረኩ እንዳልሆነ ይገለፃል፡፡

በኢትዮጵያ የህብረት ስራ ማህበራት ስኬቶች፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የህብረት ስራ ማህበራት ህብረተሰቡን  በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ አድርገዋል?

አቶ ኡስማን ሱሩር፡-  በኢትዮጵያ ህብረት ስራ ማህበራት ከአርሶ አደር፣ አርብቶ አደርና በከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተነጣጥለው አይታዩም፡፡  በሀገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታ እነዚህን ክፍሎች የሚያካትቱ ስለሆነ ህብረት ስራ ማህበራት ለህብረተሰቡ ከፍተኛ  ጥቅም እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

በተለይም ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ አስፈላጊ  የግብርና ቴክኖሎጂዎችን፤ ለአብነትም ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና የሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን በማቅረብ ለግብርናው እድገትና መዘመን ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ በዚህም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት በማረጋገጥና ለሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገትም የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ናቸው፡፡

የህብረት ስራ ማህበራት የአርሶ አደሩን የግብርና ምርቶች በተደራጀ መልክ አሰባስበው ለሃገር ውስጥ ገበያ ፣ ለኢንዱስትሪዎች፣ ለምርት አቀናባሪዎችና ለውጪ  ገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ገቢ ከፍ እያሳደጉና ተጠቃሚነቱንም እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡

የህብረት ስራ ማህበራት በመኖራቸው በከተሞች አካባቢ ያሉ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በገጠር ካሉ የአርሶ አደር የግብርና ህብረት ስራ ማህበራት ጋር ቀጥተኛ የገበያ ትስስር ተፈጥሯል። በዚህም የግብይቱን ሰንሰለት በማሳጠር አርሶ አደሩ ያመረተው ምርት ለገበያ እንዲቀርብና ሸማቹ ህብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ አግዟል፡፡

ምርት በጥራት፣ በተፈለገው ጊዜና ቦታ እንዲገኝ በማድረግና በአንፃራዊነት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅርብ የከተማውን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት እያረጋገጡም ይገኛሉ፡፡ በምርቶች ላይ የሚታየውን ያልተገባ የዋጋ ንረት በመከላከልም ማህበራቱ የድርሻቸውን እየተወጡም ይገኛሉ፡፡  የገጠር ከተማ የኢኮኖሚ ትስስሩ እንዲጠናከርና ሊገነባ ለታሰበው አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ እውን መሆን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይም ይገኛሉ፡፡

ህብረት ስራ ማህበራቱ በሃገራዊ ኢኮኖሚ፣ ማህ በራዊ፣ ፖለቲካዊና የሰላም  ልማት ግንባታ እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ተኪ የለሽ ነው። ይሁን እንጂ፤ አሁን ያለው የማህበራቱ ቁጥርና መንግስት ማህበራቱ እንዲያበረክቱ ከሚፈልገው አስተዋፅኦ፤ እንዲሁም  አባላት ከማህበራቱ ከሚፈልጉት ውጤት አንፃርና ህብረተሰቡ ከሚፈልገው ውጤት አኳያ  አጠቃላይ ጥረታቸውና ስኬታቸው በቂ ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሆኖም፤ ማህበራቱ ከታገዙና ከተደገፉ ግን ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ይችላሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከ2003-2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ የመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ቁጥር እያደገ መምጣቱ ተጠቅሷል፡፡ በእርግጥም የእቅዱን ያህል ቁጥሩ በቂ ነው? እንዴትስ ይገመገማል?

አቶ ኡስማን ሱሩር፡– በመጀመሪያ፤ የህብረት ስራ ማህበራት ውጤት የሚለካው በቁጥር ሳይሆን በሚፈጥሩት ተጽዕኖ ልክ ነው። የማህበራቱን የአገልግሎት ተዳራሽነት ማስፋት ግን ያስፈልጋል፡፡ በተለይም አገልግሎት አሰጣጣቸውን ቀልጣፋ፣ ፈጣን፣ ወጪ ቆጣቢና የአባሉን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ መሆን አለበት፡፡

ይህም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ ተካትቶ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ በመሆኑም የማህበራቱን ቁጥር ከማሳደግ ይልቅ ያሉትን በውጤታማነት ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ማህበራቱ ያሉባቸውን የአሰራር፣ የአመራር፣ የአደረጃጀትና የብቃት ችግሮች መፍታትም ይጠበቃል፡፡

ያለአግባብ ተደራጅተው ብዙም አገልግሎት የማይሰጡና እሴት የማይጨምሩ ማህበራትን ማዋሃድም ያስፈልጋል፡፡ ይህም ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማሳደግና  የመወዳደርና የመደራደር አቅማቸውንም ለማጎልበት ያስችላል፡፡ ወደኢንዱስትሪው ዘርፍ ሲገቡም የአባላቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስችላቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በግብርና ምርቶች ላይ 100% እሴት በመጨመር ለገበያ ለማቅረብ አቅጣጫ ተይዟል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ይህንንስ  ከአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር ለማገናኘት ምን ዝግጅት ተደርጓል?

አቶ ኡስማን ሱሩር፡- የህብረት ስራ ማህበራት ምርቶቻቸውን በጥሬው ወደገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምረው፤ ማለትም ከማበጠር ጀምረው ደረጃ አውጥተው፤ አቀነባብረው ለሃገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ፡፡ ይህም የሚሆነው በቅድሚያ ህብረት ስራ ማህበራቱ በሃገር ውስጥ ገበያ የሚኖራቸው ድርሻና የመደራደር አቅማቸውን  ሲያሳድጉ ነው፤ ከዚያም፤ ካፒታል እየጨመሩ ሲሄዱ ወደ እሴት መጨመር መግባት አለባቸው፡፡ ይህን ሲያደርጉም የአባላት ተጠቃሚነት እያደገ ይሄዳል፡፡

በሀገር ደረጃ ባጠቃላይ 878 የህብረት ስራ ማህበራት የገነቧቸው ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች አሉ፡፡ እነዚህ ማህበራት በቀጣይ መንግስት እየገነባቸው ባሉ የተቀናጁ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ አብዛኛውን ስራ ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ መጋቢ ለሆኑት የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማእከላት በዋናነት የሚሰሩት ህብረት ስራ ማህበራቱ ናቸው፡፡ መሰረታዊ ማህበራቱ ተጠናክረው፤ ምርቶቻቸውን እንደየአካባቢያቸው ሁኔታ አደራጅተው፣ የመጀመሪያ ደረጃ ማቀነባበር አካሂደው (እሴት ጨምረው) ለኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የሚያቀርቡበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

አቅም የፈጠሩ፣ ካፒታል ያላቸውና ልምድ ያካበቱ ማህበራት ደግሞ እንደማናቸውም የግል ዘርፍ/ባለሃብት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው የሼዶች ባለቤት ይሆናሉ፡፡  ለምሳሌ፤ በአማራ ክልል በቡሬ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ማህበራቱ የመግባት እድል አላቸው፡፡ ይህን ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ፤ በተለይም ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። የመጀመሪያው ስራም ማህበራቱ የባለቤትነት አስተሳሰብ እንዲፈጥሩና እንዲዘጋጁ ማድረግ ነው፡፡  በዚህ ላይ በተለይም በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል የነበረው ቅንጅታዊ አሰራር የላላ ስለነበር በቀጣይ ብዙ መስራት ይጠይቃል፡፡

በመሆኑም፤ ኤጀንሲው አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከክልሎች ጋርም ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ክልል በሚገነባው የቡልቡላ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአካባቢው በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ግብይት  የተሰማሩ ማህበራት የኢንዱስትሪው ባለቤት እንዲሆኑ፤ ሼድ እንዲያገኙ የዝግጅት ስራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ አስፈላጊው የፕሮጀክት ጥናትና መሰል ስራዎችም እየተከናወኑ ናቸው፡፡ የማህበራቱ በነዚህ ፓርኮች ውስጥ መሳተፍ የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነትና የኢንዱስትሪውን ውጤታማነት የበለጠ ያሳድጋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

 አዲስ ዘመን፡- በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ከሜካናይዜሽን ግብርናና መስኖ ልማት ጋር በተያያዘ ምን ለመስራት  ታቅዷል? ሃገሪቱ ከያዘችው እቅድ ጋርስ ምን ያህል የተጣጣመና አብሮ የሚሄድ ነው?

አቶ ኡስማን ሱሩር፡- ማህበራቱ ከትንሽ እስከ ከፍተኛ የሜካናይዜሸን አገልግሎት አቅርቦት ላይ ይሳተፋሉ፡፡ በቀጣይም አቅጣጫው ማህበራቱ በግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት አቅርቦት ላይ በቅድመ ምርትም ሆነ በድህረ ምርት በሰፊው እንዲሳተፉ ለማድረግ በመሆኑ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይም አርሲ ባሌ  ላይ የነበረውን የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መልካም ተሞክሮ በመቀመርና ሌሎቹም ማህበራት እንዲያውቁትና እንዲጠቀሙበት የማድርግ ስራ በአማራ፣ በትግራይ እና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ክልሎች ላይ ተጀምሯል፡፡ በቀጣይም ማህበራቱ  የአግሮ ሜካናይዜሽንን ሊመራ የሚችል አሰራር፣ አደረጃጃት ሊኖራቸው ይገባል፣ ብቃት ያለው ሞያተኛም መቅጥር ይኖርባቸዋል፡፡

የህብረት ስራ ማህበራቱ የመስኖ ልማት ዘርፉን በማዘመን፣ ውጤታማነቱና ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ በተለይም ለማምረት የሚያስፈልጉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ፣ ምርቱ ከተመረተ በኋላም ምርቱ ፍትሃዊ የገበያ ዋጋ እንዲያገኝ በማስቻል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበረክታሉ፡፡ በመስኖ ልማት የተመሩ ማህበራት ከከተሞች፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና  ከማረሚያ ቤት ተቋማት ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ቀጥታ ገበያው ውስጥ ገብተው ምርቱን ሸማቹ ህበረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምትና አርሶ አደሩም የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ሆኖም ማህበራቱ ከአደራጃጀት አንፃር፣ ብቃት ያለው ባለሙያ ቀጥሮ  ከማሰራት አንፃርና የአግሮ ኬሚካል ፋይናንስ ግብአት ከማቅረብ ጋር በተያያዘ ችግሮች ስላሉባቸው ስኬታቸው በቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም በቀጣይ ማህበራቱ በመስኖና በሜካናይዜሽን ግብርና  እያደረጉት ያለው አስታዋጽኦ መጠናከር ይኖርበታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለ20 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር የቀጣይ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ የሥራ እድሎቹ በምን መልኩ ነው የሚፈጠሩት?

አቶ ኡስማን ሱሩር፡– የሀገሪቱ የህብረት ስራ ማህበራት አሁን ካሉበትና በቀጣይ ሊደርሱበት ከሚገባው እድገት አንፃር የሚመጥን አዲስ ረቂቅ የህብረት ስራ ልማት ፖሊሲ ተቀርጿል፡፡ ፖሊሲው መሬት የሚያርፍበት የአስራ አምስት ዓመት የህብረት ስራ ልማት ፍኖተ ካርታም ተዘጋጅቷል፡፡ ፍኖተ ካርታው ከ2011 እስከ 2025 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ማህበራት በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚሳተፉና በምን ዘርፎች ላይ ምን ዓይነት የሥራ እድሎችን እንደሚፈጥሩ ይዘረዝራል፡፡ በዚህም መሰረት በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ፣ በሜካናይዜሽን አገልግሎት አቅርቦት፣ የፋይናነስ አገልግሎት ተደራሽነቱን በማስፋትና ለአባላት የብድር አገልግሎት በመስጠት ለሃያ ሚሊዮን ዜጎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የስራ እድል ይፈጠራል፡፡

 አዲስ ዘመን፡- የገበያ ትስስርን ለመፍጠር በፌዴራል ደረጃ ከሚዘጋጁ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች በተጨማሪ በክልሎችም በተመሳሳይ ለማስፋት ምን  ታቅዷል ? ቋሚ ኤግዚቢሽኖችስ ለምን አይኖሩም?

አቶ ኡስማን ሱሩር፡- ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች ዋነኛ የገበያ ስልቶች ናቸው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመሩና በየአመቱ ከጥር እስከ የካቲት ለአንድ ወር የሚካሄዱ ቋሚ የህብረት ስራ ማህበራት ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች አሉ፡፡  በኤግዚቢሽኖቹና በባዛሮቹ ላይ ከሚሰሩ ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሲምፖዚየም ሲሆን፤ ይህም የሀገር አቀፍ የህብረት ስራ ማህበራት ስኬቶች የሚዘከሩበት፣ በዘርፉ ማነቆዎች ላይ ምክክር የሚደረግበት፣ ማህበራቱ የልምድ ልውውጥ የሚያካሂዱበት፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች የሚቀርቡበት፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የተለያዩ የዘርፉ ምሁራን የሚሳተፉበት መድረክ ነው፡፡

ኤግዚቢሽኖች ህብረት ስራ ማህበራቱ አገልግሎትና ምርቶቻቸውን ለህብረተሰቡ የሚያስተዋውቁባቸው ሁነኛ መድረኮችም ናቸው:፡ ሌሎችንም የሚያነሳሱበትና የምርትና የአገልግሎት የገበያ ትስስርም የሚፈጥሩባቸው መንገዶች ናቸው:: ባዛሮች ደግሞ ሁሉም የህብረት ስራ ማህበራት ምርቶቻቸውን ለህብረተሰቡ የሚሸጡባቸውና በዋጋ፣ በጥራትና በብዛት ተወዳዳሪ መሆናቸውን የሚያሳዩባቸው ናቸው፡፡ ህብረተሰቡ በህብረት ስራ ማህበራት ላይ እምነት እንዲያሳድር የሚያድርጉበትና ዘላቂ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ  የሚያስችል መንገድም ነው፡፡

ኤግዚቢሽኖች፣ ባዛሮችና ሲምፖዚየሞች በክል ሎችም እንዲተገበሩ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በዚሁ መሰረት አንዳንድ ክልሎች ለምሳሌ፤ አማራ ክልል ኤግዚቢሽኖችንና ባዛሮችን በክልል ደረጃ ጀምረው ወደዞንና የዞን ከተሞች በማውረድ መተግበር ጀምረዋል፡፡  በተመሳሳይ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎችም ተጀምረዋል፡፡ በደቡብ ክልልም መጠነኛ እንቅስቃሴዎች ይታያሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቀጣይም በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች እንዲተገበሩ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ለህብረት ስራ ማህበራት ቋሚ የኤግዚቢሽን ቦታ እንዲኖር፤ በተለይም በአዲስ አበባ በአራቱ መግቢያዎች ትላልቅ የህብረት ስራ ማህበራት የጅምላና የችርቻሮ የገበያ ማእከላት ለመገንባት እቅድ ተይዟል፡፡ ማእከላቱን የመገንባቱ ዕቅድ ከተሳካ ወደሌሎች የክልል ከተሞችም የማስፋት እድል ይኖራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ አብዛኞቹ (36 %) የሚሆኑት የህብረት ስራ ማህበራት በገንዘብ ቁጠባና ብድር ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ ሀገሪቱ ከምትከተለው ግብርና መር ኢኮኖሚ አኳያ የግብርና ህብረት ስራ ማህበራትን ቁጥር ማብዛት ለምን አልተፈለገም? በቀጣይስ ምን ታስቧል?

አቶ ኡስማን ሱሩር፡- በኢትዮጵያ ህብረት ስራ ማህበራት በማምረት፣ በአገልግሎትና በጥምር /በማምረትና በአገልግሎት/ ዘርፎች ይደራጃሉ፡፡ ሙሉ በሙሉ በግብርና ዘርፍ ላይ ብቻ አተኩረው የተደራጁ የህብረት ስራ ማህበራት 32 በመቶ ይጠጋሉ፡፡  ከ65 በመቶ በላይ የሚሆኑት ማህበራት ግብርና ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተሰማርተዋል፡፡  ግብርና ነክ የሆኑትን የህብረት ስራ ማህበራት አንጥሮ በሰነድ የማስቀመጥ ችግር ካልሆነ በስተቀር በሀገሪቱ አብዛኛዎቹ የህብረት ስራ ማህበራት ግብርና ነክ ናቸው፡፡ ቀጥለው የሚመጡት ደግሞ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ሲሆኑ፤ እነዚህም ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እድገት የማይተካ ሚና አላቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት የወቅቱ ፈተናቸው የፋይናንስ አቅርቦት ችግር መሆኑ ይታወቃል:: ምክንያቱ ምንድን ነው? ችግሩን  ለመፍታት ምን ታቅዷል?

አቶ ኡስማን ሱሩር፡- ቀደም ሲል በከተማም ሆነ በገጠር ህብረተሰብ አካባቢ መበደር እምብዛም የተለመደ አልነበረም፡፡ ሆኖም የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ፋይዳቸውና ተፅእኗቸው እየጎላ መምጣቱን ተከትሎ፤ እንዲሁም ከማህበራቱ ብድር ወስደው ህይወታቸውን የቀየሩ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ በመጨመሩ ምክንያት በርካታ ሰዎች የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት አባል ሆነዋል፡፡ በዛው ልክ የቁጣባ መጠንም እያደገ መጥቷል፡፡ ሆኖም፤ የአባላትን የብድር ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ስርዓት ባለመኖሩ የቁጠባ መጠንና የብድር ፍላጎት ሊመጣጠን አልቻለም፡፡  እንደ ሀገር የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራትን በፋይናነስ የሚደግፍ ተቋምም የለም፡፡ ባንኮች ለባለሀብቶች እንጂ ለህብረት ስራ ማህበራት ብድር የማያመቻቹ በመሆኑ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት የለም፡፡

መንግስት በፖሊሲ ደረጃ አይቶ ይህን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ሊፈታ ይገባል፡፡ ኤጀንሲው ካረቀቀው የህብረት ስራ ፖሊሲ ውስጥ አንዱ የህብረት ስራ ባንክ ማቋቋም ነው፡፡ ይህ የህብረት ስራ ባንክ እንዲህ ዓይነቱን ችግር ይፈታል፤ ሌሎች ግብርና ነክ ጉዳዮችን በፋይናንስ ይደግፋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

የፋይናንስ አቅርቦት ችግር የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የህብረት ስራ ሴክተሩ ማነቆ ነው፡፡  ይህም በመሆኑ የግብርናውን ዘርፍ ለማገዝ የህብረት ስራ ማህበራትን በፋይናንስ መደገፍ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኦዲትና የሀብት ምዝበራ አንዱ የማህበራቱ ተግዳሮት ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው? ከዚህ ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ የገቡ ማህበራትስ የሉም ወይ?

አቶ ኡስማን ሱሩር፡- ባለፉት አምስት ዓመታት ከአስተሳሰብ ጀምሮ በህብረት ስራ ማህበራት ውስጥ ያሉ ብዥታዎችን ሊፈቱ የሚችሉ በርካታ ንቅናቄዎች ተካሂደዋል፡፡ በንቅናቄዎችም ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ የአባላትን ቁጥር ማሳደግ፣ አባላት በህብረት ስራ ማህበራቱ ውስጥ ተጨማሪ እጣዎችን እንዲገዙና ካፒታል እንዲያሳድጉ ማድረግና ሌሎችም መሰል ተግባራት  የውጤቱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ የማህበራት ቁጥር ከነበረበት 38 ሺህ ወደ 88 ሺህ መድረሱ፣ የአባላት ቁጥር ከ6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ወደ 20 ሚሊዮን ከፍ ማለቱ፣ የካፒታላቸው መጠን ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን  ወደ 23 ቢሊዮን ማደጉ ንቅናቄው የፈጠረው ስኬት ነው፡፡

በንቅናቄ ስራዎች እነዚህ ሁሉ ስኬቶች ቢኖሩም፤ የህብረት ስራ ማህበራት ህግና ህጋዊነታቸው፤ እንዲሁም ደህንነታቸውና ግልፀኝነታቸው ገና ያልተፈታና ውጤት ያልታየበት ጉዳይ ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ የኦዲት ጉድለትና ኢንስፔክሽን ችግሮች ዋናዎቹ ናቸው፡፡  በተለይም፤ የህብረት ስራ ማህበራት  አመታዊ የኦዲት ሽፋን ከ30 በመቶ በታች መሆኑ ከፍተኛ የኦዲት ጉድለት እንዳለ ያሳያል፡፡  ከዚህ ጋር በተያያዘ ጉድለቱን ለመሙላት እየተሰራ ነው፡፡

ከሀብት ምዝበራ ጋር በተያያዘ፤ የምዝበራ ምልክቶች በህብረት ስራ ማህበራቱ ውስጥ እዚህም እዚያም ይታያሉ፡፡ የህብረት ስራ ማህበራቱ በአግባቡ ኦዲትና ኢንስፔክት ባለመደረጋቸው፣ ኦዲት ያደረጉ ባለሙያዎችም የመፈፀም አቅማቸው ደካማ በመሆኑና የማህበራቱ መሪዎቹ ከተመሪዎቹ በታች አቅማቸው እያነሰ በመሄዱ ምዝበራ ታይቷል፡፡  በአንዳንድ በህብረት ስራ ማህበራት ውስጥ የተከሰቱ ጉድለቶችና ኪሳራዎችም የዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ የወረቀት ማጭበርበር ስራዎችም ይካሄዳሉ፡፡

በቀጣይ ይህ ችግር ካልተፈታ ለህብረት ስራ ማህበራቱ ትልቅ አዳጋ ሊሆን ስለሚችል፤ ማህበራቱ ህግ አክብረው እየሰሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በዓመት አንድ ጊዜ ኦዲትና ኢንስፔክት መደረግ አለባቸው፡፡ በተለይም በዞን፣ በከተማና በወረዳ ደረጃ ያሉ የኦዲት መዋቅሮች ላይ ያሉ ችግሮች መፈታት ይገባቸዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኅብረት ሥራ ማህበራት  አሰራር ውስጥ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት መኖርም ሌላኛው የህብረት ስራ ማህበራት  ተግዳሮት ሆኗል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ጣልቃ ገብነቱንስ እንዴት  ለማስቆም ታስቧል?

አቶ ኡስማን ሱሩር፡- በየደረጃው በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባለው አመራር አማካኝነት በማህበራቱ ውስጥ የሚታየው ጣልቃገብነት በመልካምና በመጥፎ ጎን ይታያል፡፡  ማህበራቱ የተደራጁበትን ተልእኮ መሰረት አድርገውና የህብረት ስራ ማህበራትን ህግና የአሰራር መርሆዎች ተከትለው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሆኖም ግን፤ ከዚህ አሰራር ውጪ ማህበራቱን የሚመሩ አመራሮች ልክ እንደነጋዴ ሆነው በምርቶች ላይ አላስፈላጊ ዋጋ በመጨመር ምርቶችን በመሸጥና በማከማቸት የመጠበቅ ድርጊቶች ይታያሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የሴክተሩ አመራር ይህ ትክክል አለመሆኑን በመረዳት ማህበራቱ እንዲያስተካክሉ በተገቢ መንገድ ጣልቃ ይገባል፡፡ ሆኖም፤ አንዳንድ ብልጣብልጥ የህብረት ስራ አመራሮችና ሙያተኞች እንዲህ አይነቱን ጣልቃገብነት ሲኮንኑት ይታያሉ። ይሁን እንጂ፤  ጣልቃገብነቱ ተገቢ በመሆኑ ሊያስተካክሉት ይገባል::

በሌላ በኩል፤ በአንዳንድ ማህበራት ውስጥ እነዚሁ አመራሮች ይህን መነሻ በማድረግ  በሀብት ላይ ከማህበራቱ ጋር በመሞዳሞድ የሚሰሩ አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር ለማስቀረት ማህበራት ለአባሎቻቸው ግልፅ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በተገቢው መንገድ ኦዲትና ኢንስፔክት መደረግም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግልፀኝነት እየተፈጠረ በሄደ ቁጥርም ምዝበራው እየከሰመ ይሄዳል፡፡ ለዚህም አሰራሮችን በመዝርጋት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በዋናነት የቁጥጥር ስርዓቱ በሚገባ ከጠነከረ ጣልቃ ገብነቶቹን መቀነስ ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን

አቶ ኡስማን ሱሩር፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አዲስ ዘመን ጥር 30/2011

አስናቀ ፀጋዬ