ስደተኞች ተገቢውን ድጋፍና ክብካቤ ማግኘት አለባቸው

16

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ነዳያንን ማየት የተለመደ ቢሆንም፤ ሶሪያውያን ምፅዋት እንዲሰጣቸው ሲማፀኑ ማየት ግን እንግዳ ነገር ነው። በተረጂነት ብዙም የማይታወቁት አረቦች በየመንገዱ ምጽዋት መጠየቃቸውን ማስተዋላችንም በአገራቸው የተነሳው ጦርነት ሰለባ ስላደረጋቸው እንጂ ሶሪያውያን ስደተኞች የሰው ፊት ለማየት ፍላጎት ኖሯቸው አይደለም።

ኢትዮጵያ እንግዳ ተቀባይ አገር ናት ሲባል በዜጎቿና በመንግሥት በተግባርም በአሀዝም ተደግፎ የሚታይ ሀቅ ነው። አገሪቱ ምንም እንኳ በማደግ ላይ ከሚገኙ አገሮች ተርታ ብትመደብም በዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን በማስጠለል ከኡጋንዳ ቀጥላ ቀዳሚ ከሆኑት አገራት ጋር በመሰለፏ « የስደተኞች ቤት » የሚል መጠሪያ አሰጥቷታል።

እ.አ.አ. በጥር 17/2019 ቶምሰን ሬውተርስ ፋውንዴሽን የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅትን በመጥቀስ ከኬንያ ናይሮቢ እንደዘገበው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ  ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞች አሉ። ይህ ቁጥርም ስደተኞችን በመቀበል አገሪቱን በአፍሪካ ሁለተኛ እንደሚያደርጋት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያሳያል። እነዚህ ስደተኞች አብዛኛውን ጊዜ ግጭትና አለመረጋጋት ካለባቸው እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ሶሪያ ካሉ19 አገራት መጥተው        በትግራይ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በሶማሌ ክልሎች ተጠልለው የሚገኙ ናቸው።

ባለፉት ዓመታት በሱዳኑ የብሉ ናይል ግዛት በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት የሱዳን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠሩን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር)ማስታወቁ ይጠቀሳል ።

አብዛኞቹ ሀብታም ሃያላን አገራት ስደተኞችን አንቀበልም በማለት ወደአገራቸው እንዳይገቡ እገዳ በጣሉበት ወቅት ኢትዮጵያ የየትኛውንም አገር ስደተኞችን በቀናነት ተቀብላ ማስተናገድዋ ከበሬታን ያሰጣት ቢሆንም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ጉዳዩን በማጤን ለአገሪቱ ሊደረግ የሚገባውን ድጋፍ ሊያሻሽል ግድ ይለዋል፡፡

ባለፈው ወር በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን የተመለከተ የሕግ ረቂቅ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መፅደቁ ይታወሳል፡፡ በዚህ የህግ ማዕቀፍ በአገሪቱ ለሚፈጠረው 100ሺህ የስራ ዘርፍ ከሚመደበው 500 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 30 በመቶው ለስደተኞች ስራ ፈጠራ የሚውል መሆኑ ተገልጿል፡፡ይህም የሚያሳየው ሃገራችን ስደተኞችን ለማገዝና ለመንከባከብ ያላት ቁርጠኝነት ማሳያ ነው፡፡ ስለሆነም ሌሎች የአፍሪካ ሆነ የዓለም ሃገራት ሊከተሉት ይገባል፡፡

ሃገራችን ከነብዩ መሃመድ ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ጀምሮ ስደተኞችን ተቀብላና ተንከባክባ ያስተናገደች ናት፡፡ የራስዋ ዜጎችም በተለያዩ ምክንያቶች አገራቸውን እየለቀቁ ለስደት መዳረጋቸውም ይታወቃል፡፡ ባለፉት ጊዜያት በአረብ አገር በኮንትራት ስም የሚሰደዱ እህቶቻችንን ለማገድ አሸጋጋሪ ደላላዎችን ከመቆጣጠሩ ጎን ለጎን ስለ ስደት አስከፊነት በበቂ ሁኔታ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስራ ባለመሰራቱ በርካቶች ለሞትና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡

በየትኛውም ሃገር የሚኖሩ ስደተኞች ድጋፍና ክብካቤ ሊያገኙ የሚገባቸው በመሆኑ ሃገራት ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን በመቆጣጠርና ስደተኞችን በመንከባከብ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

በየትኛውም የአፍሪካ አገር ዜጎች« በሃገሬ ተቸገርኩ ፣ ተምሬ ስራ አጣሁ !» በሚሉበት ሁኔታ ስደትን መከላከል ቢከብድም፤ በህገ ወጥ ደላላ ተታልለው በህገ ወጥ መንገድ የሚሰደዱትን ለማስቆም መንግስታት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል፡፡

ምንም እንኳ ስደትን ማስቆም ባይቻልም አማራጩ ዜጎች ስለሚሄዱበት አገርና ሊሰሩት ስለሚችሉት ስራ ትክክለኛ መረጃና ቅድመ ዝግጅት ማድረግ በአማራጭ በመታየቱ በአገራት መካከል በሚደረግ የሰራተኛ ውል መሰረት በህጋዊ ኮንትራት ስራ ዜጎችን መላክና ከተላኩም በኋላ መብትን ማስከበር ከመንግስታት ይጠበቃል፡፡

በዚህ ሳምንት የአፍሪካ ህብረት ‹‹በአፍሪካ ስደትን፣ከስደት ተመላሾችንና በሃይል መፈናቀልን ዘላቂ መፍትሄ ማስገኘት›› በሚል መሪ ቃል 32ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሂዳል፡፡ይህ የሚያሳየው ችግሩ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ነው፡፡ መሪዎቹ ከውይይት ባሻገር የሚቀመጡ የመፍትሄ ሃሳቦችንና አቅጣጫዎችን በሚገባ በመተግበር አፍሪካውያን ስደተኞችን መታደግ አለባቸው፡፡

መሪዎቹ ኢትዮጵያ ለስደተኞች ምቹ በመሆን ለሰዎች ኑሮ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን ከማሟላት ባሻገር የትምህርትና የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ ያደረገችውን ተግባር መከተልና መተግበር እንደሚጠበቅ አፅንኦት ሊሰጡት ይገባል፡፡ ስደተኞች በየትኛውም አገር ቢኖሩ ሰዎች ናቸውና ተገቢውን ድጋፍና ክብካቤ ማግኘት አለባቸው፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011