“ፓርቲዎች የማይታረቁ ህልሞችን ለማጣጣም የሚያስችሉ አጀንዳዎችን ይዘው ወደ ምርጫ መግባት አለባቸው” አቶ ሀሳቡ ተስፋ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነምግባር ትምህርት መምህር

መላኩ ኤሮሴ

አዲስ አበባ፡- በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የማይታረቁ ህልሞችን ማጣጣምን ዋነኛ መሰረት ያደረገ አጀንዳ መቅረጽና ያንን አጀንዳ አንግበው ወደ ምርጫው ሂደት ሊገቡ እንደሚገባ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የስነ ዜጋና ስነምግባር ትምህርት መምህር አቶ ሀሳቡ ተስፋ ጠቆሙ።

አቶ ሀሳቡ ተስፋ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የማይታረቁ ፍላጎቶችና ህልሞችን አንግበው ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል። የማይታረቁ ፍላጎቶችና ህልሞችን ለማስታረቅ፣ ለማቀራረብ እንዲሁም ለማጣጣም የሚያስችሉ አጀንዳዎችን ሳያነግቡ በምርጫ ሜዳ መንቀሳቀስ ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚፈለገውን አስተዋጽኦ ሊያበረክት አይችልም።

ፓርቲዎች የማይታረቁ ህልሞችን ለማጣጣም የሚያስችሉ አጀንዳዎችን ሳይዙ ወደ ምርጫ ሂደት መግባት ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለሀገር ዘላቂ ሰላም እጦት ከሚኖረው አሉታዊ አስተዋጽኦ ባሻገር ወደ ስልጣን የሚመጡ ፓርቲዎችንም አደጋ ውስጥ ይከታል ብለዋል።

“የህዝቡን ፍላጎት አጣጥሞ ለመሄድ የሚያስችል አጀንዳ ሳይዙ ስልጣን ላይ መውጣት እሳት ላይ እንደመቀመጥ ነው” ያሉት መምህር ሀሳቡ፤ ፓርቲዎች ለራሳቸው ሲሉ አጀንዳዎቻቸውን ደጋግመው ማየት እንደሚኖርባቸው አስታውቀዋል።

የህዝብን ፍላጎቶች ለማጣጣም የማይጣጣሙ ህልሞችን እና ፍላጎቶችን ለማጣጣምና ህዝቡን ወደ አንድ ለማምጣት የሚያስችል፣ ህዝባዊ አንድነትን ዋነኛ መሰረት ያደረገ ፕሮግራሞችን መቅረጽ፣ በፕሮግራሞቹም መሰረት የፖለቲካ ሜዳው ላይ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

 “ስልጣን የሚያስፈልገው ሀገር ለማስተዳደር ነው። በመሆኑም ስልጣን ለመያዝ ሀገር መኖር አለበት። ሀገር እንዲኖር የህዝብ አንድነት አስፈላጊ ነው። ስለዚህ

 ፓርቲዎች በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና በድህረ ምርጫ ወቅት ስልጣንን ብቻ በማማተር የህዝብን አንድነት ሊከፋፍሉ ከሚችሉ ሀሳቦችና ድርጊቶች መቆጠብ አለባቸው” ብለዋል።

እንደ አቶ ሀሳቡ ማብራሪያ፤ ፓርቲዎች የህዝቡን አንድነት ሊከፋፍሉ ከሚችሉ ተግባር እንዲቆጠቡ የሚያደርጋቸው አንድም የሞራል ልዕልና፤ ሁለትም የሀገሪቱ ህጎች ናቸው። አንዳንድ ፓርቲዎች የሞራል ልዕልናን በማጣት የሀገርን እና የህዝብን አንድነት ሊጎዳ የሚችል ተግባር ሲፈጽሙ ይታያል።

እንዴት የሞራል ልዕልናን አጡ ተብለው ባይከሰሱ እንኳ የሀገሪቱን ህጎች አክብረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ያመለከቱት አቶ ሀሳቡ፣ ፓርቲዎች የሞራል ልዕልናን ቢያጡ እንኳ ህግን አክብረው ቢንቀሳቀሱ ለምርጫው ስኬታማነት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ፓርቲዎች እንዴት ስልጣን ላይ እንወጣለን የሚለውን ብቻ ሳይሆን ወደ ስልጣን ከወጣን በኋላ እንዴት አድርገን የተባበረች እና አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር እናስተዳድራን የሚለው ትልቅ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ሀሳቡ ማብራሪያ፤ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ ፍጆታ በማለት ህዝቡን አንድ የማያደርጉ እና በተግባር ሊፈጽሙ የማይችሉትን ነገሮች ቃል መግባት የለባቸውም። ሊሳኩ የማይችሉ አማላይ ነገሮችን ቃል በመግባት ህዝቡን ስሜታዊ በማድረግ ስልጣን ላይ መውጣት ሌላ ቀውስ ሊያስከትል ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።

ፓርቲዎች ለህዝቡ የሚያቀርቡት አጀንዳ ሀገሪቱን ከነአንድነቷ፣ ከነህዝቡ፣ ከነጥንካሬዋ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

በምርጫ ወቅት የሚነሱ አጀንዳዎች በተለያዩ ምክንያቶች ፈተና ላይ የወደቀውን ህዝባዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችል መፍትሄ ይዞ መቅረብ ወሳኝ የምርጫ አጀንዳ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

አዲስ ዘመን የካቲት 26/2013

Ad Widget

Recommended For You

About the Author: wendimagegn

Leave a Reply