በትግራይ አንድ መቶ ሺ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው

መሰረት ገ/ዮሃንስ

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አንድ መቶ ሺ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ፅህፈት ቤት አስታወቀ። ባለፉት ሶስት አመታት በሃገራችን የተፈጠረው የስራ እድል የትግራይ ወጣት እንዳልተጠቀመበት ገለጸ።

የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ባርያጋብር አባይ ከወጋሕታ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለፁት ፤ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ለአንድ መቶ ሺ ወጣቶች ስልጠና በመስጠት የራሳቸው ቢዝነስ ፕላን አዘጋጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

ወጣቶቹ በመረጡት የስራ መስክ ስልጠናና ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ስራ እንዲገቡ በመቐለ ከተማ በሰባቱ ክፍለ ከተሞች ምዝገባ መጀመሩን ገልፀዋል። ይህ ወጣቶችን የስራ እድል ተጠቃሚ የማድረግ ስራ እስከ ወረዳዎች ድረስ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

በሰላም ሚኒስቴር ስር የተደራጀ ቡድን ወደ ትግራይ በመሄድ ወጣቶችን በማነጋገር ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እንዳከናወነ ያሳወቁት አቶ ባርያጋብር ፣ ከወጣቶቹ ጋር መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮችን ወደ ተግባር ለመቀየር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በትግራይ የስራ እድልን በሚመለከት ችግሩ ከዚህ በፊትም እንደነበረ የሚታወቅ ነው ያሉት አቶ ባርያጋብር፣ ባለፉት ጊዜያት ስራ ይገኝ የነበረው በቤተሰብ እና በወዳጅነት እንደነበረ አስታውቀዋል።

የኤፈርትድርጅቶችም ቢሆኑ ለራሳቸው ሰዎች በኔትዎርክ የስራ እድል ይፈጥሩ እንደነበር ጠቁመዋል።

የቀድሞው የትግራይ ክልል መንግስት ለወጣቶች ብዙ ትኩረት አይሰጥም ነበር ያሉት ኃላፊው፤ ትግራይ ከሌሎች ክልሎች በተፈጥሮ የተጎዳ አካባቢ ስለሆነ ለስራ ፈጠራ አስቸጋሪ በመሆኑ ከአራት መቶ ሺ በላይ ወጣት ስራ አጥቶ ቁጭ ብሏል። በዚህም የተነሳ ወጣቱ የስደት ህይወት በመምረጥ ህይወቱን አደጋ ውስጥ እየጣለ ይገኛል ብለዋል።

ስራ ፈጠራ በሚመለከት በጣም ብዙ ስራዎች ሊሰራ እንደሚገባ ያመለከቱት ኃላፊው፣ ችግሩ በክልል ደረጃ አደጋ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል። በሀገራችን ህዝብ ከሰባ በመቶ በላይ ወጣት ከመሆኑ አንፃር መንግስት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ያለው በስልጠና አቅም ለመፍጠር መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋርም በመነጋገር የስራ እድል ለመፍጠር በመስራት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

‹‹ባለፉት ሶስት አመታት በሃገራችን የተፈጠረው የስራ እድል የትግራይ ወጣት አልተጠቀመም፤በነበረው ውጥረት ህወሓት ይህ እድል እንዲዘጋ አድርጓል፤ በዚህ ሰአት በትግራይ ክልል ያለው ወጣት በተለየ ሁኔታ መታገዝ አለበት፤ ካልሆነ የወጣቱን አላማ ማስተካከል አይቻልም››ብለዋል።

አዲስ ዘመን የካቲት 26/2013

Ad Widget

Recommended For You

About the Author: wendimagegn

Leave a Reply