የስኳር አቅርቦትና የስኳር ኮርፖሬሽን

14

በኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪው “ሀ” ብሎ ጉዞውን የጀመረው የዛሬ 65 አመት በኢትዮጵያ መንግስት እና ኤች.ቢ.ኤ በተባለው የሆላንድ ኩባንያ በሽርክና በተገነባው የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ነው። ይህንን ተከትለው ሸዋ እና የመተሀራ ስኳር ፋብሪካዎች ተገንብተው ለረጅም አመታት አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል።

እነዚህ ፋብሪካዎች ግን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት፣ እንዲሁም ስኳርን በግብአትነት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች መበራከት ጋር ተያይዞ የሚቀርበውን ጥያቄ ተቋቁመው መቀጠል አልቻሉም። መንግስት ችግሩን በመገንዘብ የተፈጠረውን የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ለማስተካከል በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መጀመሪያ በአራት ፕሮጀክቶች አስር የስኳር ፋብሪካዎችን ግንባታ ጀምሯል፡፡


በ2003 ዓ.ም የተጀመሩ እነዚህ ፋብሪካዎች ግን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ አልቻሉም፤ መንግስት የተጋነነ ወጪ እንዲያወጣ በማድረግም በርካታ ቅሬታዎችን ፈጥረዋል። የቅሬታዎቹን መበራከት ተከትሎም በፕሮጀክቶቹ ላይ በርካታ የማስተካከያ እርምጃዎች እየተወሰዱ ሲሆን፤ እኛም በፋብሪካዎቹ ላይ እየተወሰዱ ያሉ ማስተካከያዎችንና አጠቃላይ በሀገሪቱ ያለውን የስኳር ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ያገኘነውን መረጃ እንዲህ አሰናድተን አቅርበነዋል።


ለአገዳ ምርት ያለ ምቹ ሁኔታ
ኢትዮጵያ ለሸንኮራ አገዳ ልማት ተስማሚ የሆነ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ሔክታር ለም መሬት፣ በቂ ወንዝና ተስማሚ የአየር ንብረት አላት። ኢትዮጵያም በአገዳ ምርታማነት በአለም ቀዳሚ ከሚባሉት ሀገራት መካከል ትቀመጣለች። ምክንያቱም በኢትዮጵያ በአንድ ሔክታር መሬት በአንድ ወር ውስጥ 108 ኩንታል የአገዳ ምርት ማግኘት የሚቻል ሲሆን፤ በሌሎች አገራት ግን በአማካይ የሚገኘው ከ85 ኩንታል ያነሰ ነው።ይሄን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምም በመጀመሪያውና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 500 ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት እቅድ የተያዘ ሲሆን፤ እስካሁን 102 ሺ ሄክታር መሬት በአገዳ ለመሸፈን ተችሏል።


ፍላጎትና አቅርቦት
አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ በአመት ከ6ነጥብ5 ሚሊዮን ኩንታል እስከ 7ሚለዮን ኩንታል አመታዊ የስኳር ፍላጎት አለ። እስካሁን ያለው ከፍተኛው የምርት መጠን ግን ከሶስት ነጥብ አምስት እስከ አራት ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነው፡፡ ይህም በፍላጎትና አቅርቦቱ መካከል ከሁለት ነጥብ አምስት እስከ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ ሲሆን፤ ክፍተቱ የሚሞላውም ስኳርን ከውጪ በማስገባት ነው።


ይሄን መነሻ በማድረግም በተያዘው በጀት አመት 5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ለማምረት እቅድ የተያዘ ሲሆን፤ በ2012 ዓ.ም አሁን በስራ ላይ ያሉትን ስምንት ፋብሪካዎች በማጠናከር የስኳር ፍላጎቱን በሀገር ውስጥ ምርት ለማሟላት እቅድ ተይዟል። በሀገሪቱ ያሉት አስራ ሶስቱም ፋብሪካዎች ወደ ማምረት ሲገቡ ደግሞ 22 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል የማምረት አቅም ይኖራቸዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ሀገሪቱን ከአለም አስር ቀዳሚ የስኳር አምራች ሀገራት ተርታ የሚያሰልፋት ይሆናል።


በስራ ላይ ያሉ ፋብሪካዎች
በአሁኑ ወቅት ባጠቃለይ ስምንት ፋብሪካዎች (ፊንጫአ፣ ወንጂ፣ መተሀራ፣ ከሰም፣ ተንዳሆ፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት እና ኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሶስት) በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ተንዳሆና አርጆ ዴዴሳ በውጪ ኩባንያዎች ተገንብተው በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ በሜቴክ ተይዘው ለረጅም ጊዜ የተጓተቱና በአሁኑ ወቅት ለቻይና ኩባንያዎች ተሰጥተው ወደ ስራ የገቡ ናቸው።


የፋብሪካዎቹ ወቅታዊ አፈጻጸም ደረጃቸው ሲታይም የከሰም ስኳር ፋብሪካ ግንባታው 99 ነጥብ አምስት በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ከ2007 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በማምረት ላይ ይገኛል። የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ግንባታም 96 ነጥብ አራት በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ከ2009 ጀምሮ ወደ ስራ ገብቷል። የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሶስት የግንባታም 92ነጥብ ሰባት በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በጥቅምት 2011 ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል። እነዚህ ፋብሪካዎች የቻይናው ኮም ፕላንት ኩባንያ የገነባቸው ሲሆኑ፤ በቀን ከስምንት ሺ እስከ አስር ሺ ኩንታል ስኳር ማምረት የሚችሉ ናቸው።


በግንባታ ላይ ያሉ ፋብሪካዎች
በግንባታ ላይ ያሉት ሁለት ሲሆኑ፤ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አምስት አንዱ ነው፡፡ ይህ ፋብሪካ አዲስ ሲሆን በሁለት ምእራፍ የሚገነባና 24 ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያለው ነው። ያለበት የግንባታ ደረጃም ምእራፍ አንድ 27ነጥብ ሶስት በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ምእራፍ ሁለት ግን አልተጀመረም፡፡ አጠቃላይ ግንባታው በ2013 ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህው ፋብሪካ ግንባታው የሚያካሂደው በቻይናው ጄ.ጄ.አይ.ኢ.ሲ ኩባንያ ነው።


ሁለተኛው፣ የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ሲሆን፤ በ2005 የተጀመረና 24 ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ያለው ነው፡፡ ግንባታውን የሚያከናውነው የቻይናው (ሲ.ኤ.ኤም.ሲ) ካምስ ኩባንያ ሲሆን፤ ምእራፍ አንድ 84 ነጥብ 32 በመድረሱ ግንባታው በዚህ አመት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ወልቃይት ምእራፍ ሁለትም ግንባታው 48 ነጥብ 64 ደርሷል። ነገር ግን ግድቡ ባለመድረሱና የአገዳም እጥረት ስላለ በ2012 ወደ ማምረት ላይገባ ይችላል። ለዚህም ግድቡ እስኪጠናቀቅ አንድ የእስራኤል ኩባንያ ሰባት ሺ ሄክታር መሬት ኮንትራት ወስዶ በጠብታ ውሃ የአገዳ ልማት እየሰራ ይገኛል።


የተቀሩት በቅርቡ ከሜቴክ የተነጠቁት ሶስት ኩባንያዎች ሲሆኑ፤ እነዚህም ጣና በለስ ቁጥር አንድ 65 በመቶ ደርሶ 2010 የቆመ ሲሆን፤ ግንባታውን በሌላ የውጭ ድርጅት ለማስቀጠል የመረጣ ስራ ተጠናቅቋል፤ ፋይናንስ ከተገኘም በዚህ አመት የሚጠናቀቅ ይሆናል። ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ በተመሳሳይ በ2010 የቆመና ግንባታው 80 በመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ስራውን በውጪ ተቋራጭ ለማስቀጠል እየተሰራ በመሆኑ ገንዘቡ ከተገኝ በስድስት ወር ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል። ጣና በለስ ቁጥር ሁለት በ2009 አ.ም የቆመና ግንባታው ከ 25 በመቶ ያልዘለለ ሲሆን፤ ይህንንም በአማራ ክልል የሚገኝ አንድ ሀገር በቀል የልማት ድርጅት ለመግዛት ጥያቄ በማቅረቡ የሀብት ግምታ እየተካሄደ ሲሆን ከስምምነት ላይ ከተደረሰ ለልማት ድርጅቱ የሚተላለፍ ይሆናል።


የፋብሪካዎች ግንባታና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው
በስኳር ልማት ዘርፍ 70 ማህበራት በሸንኮራ አገዳ አብቃይና አቅራቢ የታቀፉ ሲሆን፤ በዚህም 15ሺ 316 አባላት የስራ እድል አግኝተዋል። እያንዳንዱ ፋብሪካ ለስኳር ማሸጊያ ከረጢት/ጆንያ ፋብሪካዎች ስራ የሚፈጥር ሲሆን፤ ከፋብሪካዎቹ የሚወጣውም ተረፈ ምርትም የኢታኖል ምርት፣ ለአልኮል፣ ለእንስሳት መኖ፣ ለችፑድ፣ ለወረቀትና ለቀለም ማምረቻ ፋብሪካዎች ግብአት ይውላል።


የነበሩ ተግዳሮቶች
በኮርፖሬሽኑ በኩል አስር ፋብሪካዎችን ለማስገንባት የሚያስችል የአስተዳደር እውቀት አልነበረም። በተጨማሪም አስሩም የስኳር ፋብሪካዎች በሚገነቡባቸው ቦታዎች ምንም አይነት የመሰረተ ልማት አውታር አልነበረም፡፡ በወቅቱ መንገድ ባለመኖሩ ጥናቱ የተከናወነው በሄሊኮፕተር ነበር። በኮንትራክተሮች በኩልም አስሩንም ፋብሪካዎች መንግስት የሰጠው ለሜቴክ ሲሆን፤ ሜቴክ ደግሞ ፋብሪካ በመገንባት ልምድ ያለው ተቋም ስላልነበረው ለመዘግየቱ አንድ ምክንያት ነበር። በተጨማሪም የፋይናነስ፣ ከውጪ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ የማሽነሪዎችና የመለዋወጫ አቅርቦት መዘግየት ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።


በፋብሪካዎቹ መዘግየት የደረሰ ኪሳራ
ሜቴክ ይዟቸው ከነበሩት ጣና በለስ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ በኮንትራት በውሉ መሰረት በ18ወር ውስጥ በ2006 አጋማሽ መጠናቀቅ ነበረባቸው። በወቅቱ ፋብሪካውን ለመገንባት ከሜቴክ ጋር ስምምነት ላይ የተደረሰው ክፍያው በኢትዮጵያ ብር የሚከፈል ሆኖ ለእያንዳንዱ 235 ሚሊዮን 772 ሺ 160 የአሜሪካ ዶላር ነበር።


ሜቴክ የወሰደው ግን ለጣና በለስ ቁጥር አንድ 257 ሚሊዮን 34ሺ424 ዶላር። ለጣና በለስ ቁጥር ሁለት 192 ሚሊዮን 779 ሺ 336ዶላር አፈጻጸሙም ዝቅተኛ ነበር (25 በመቶ)። ለኦሞ ኩራዝ አንድ 236 ሚሊዮን 97 ሺ908 ዶላር ነው። ይህም ሆኖ ፋብሪካዎቹ ተጠናቀው ስራ ባለመጀመራቸው ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም ኮርፖሬሽኑ ሊያገኘው ይችል የነበረውንና በመዘግየቱ ኮርፖሬሽኑ ለወጪ በመዳረጉ ከ9 ነጥብ4 ቢሊዮን ብር በላይ ለኪሳራ ተዳርጓል።


ቀጣይ መፍትሄዎች
የበጀት ችግሩን ለመፍታት መንግስት እንደ አዲስ በጀት መመደብ አለበት፡፡ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቃል ገብተዋል፡፡በፕሮጀክቶቹ አስተዳደር ውስጥም ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ስለሚያስፈልግ የመንግስት የቅርብ ክትትል ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011

ራስወርቅ ሙሉጌታ