የጃን ሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ነገ ይካሄዳል

20

ታዋቂና ስመ ጥር የአገራችን አትሌቶች የሚሳተፉበትና ለ36ኛ ጊዜ የሚካሄደው የጃን ሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ነገ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይህንን ውድድር በተመለከተ ባለፈው ረቡዕ በጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የጎረቤት አገራት አትሌቶች ተጋባዥ ሆነው እንደሚወዳደሩ አሳውቋል። ከስድስት ያላነሱ አጋር የመንግስት መስሪያ ቤት ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በርካታ ውጤታማ፣ ታዋቂና ስመ ጥር አትሌቶች፣ የአትሌት ማናጀሮችና ተወካዮቻቸው እንደሚገኙም ተገልጿል።


ከውድድሩም ኢትዮጵያን የፊታችን መጋቢት ወር ዴንማርክ በሚካሄደው 43ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና የሚወክሉ አትሌቶች የሚመረጡ ሲሆን በወጣቶች ከ1ኛእስከ6ኛ የሚጨርሱ አትሌቶች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል። በአዋቂዎች ደግሞ ከ1እስከ5 ያሉት በቀጥታ ያልፉና 6ኛ ተመራጮች ደግሞ ባስመዘገቡት የተሻለ ሰዓት ተለይተው የሚካተቱ ይሆናል።


የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር በ1976 ዓ. ም በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ «የጃን ሜዳ አገር አቋራጭ ውድድር» በሚል ስያሜ የተጀመረ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ክፍል መረጃ ያመለክታል። ውድደሩ ሲጀመር ዋነኛ አላማውን አድርጎ የተነሳው ለዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ብቃት ያላቸውን አትሌቶች መምረጥ፣ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራትና ለአትሌቶች አገር አቀፍ የውድድር እድል መፍጠር የሚል ነበር።


የጃን ሜዳ አገር አቋራጭ ውድድር ቀደም ሲል በ9 ኪሎ ሜትር ወጣት ወንድና ሴቶች ላይ ብቻ ያተኩር የነበረ ሲሆን ቀስ በቀስ በ4፣ በ6፣ በ9 እና በ12 ኪሎ ሜትር ሲካሄድ ቆይቶ በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፉ የአገር አቋራጭ ሩጫ ውድድር ስታንዳርድ መሰረት አዋቂ ወንድና ሴቶች፣ እንዲሁም ወጣት ወንድና ሴቶች በሚል የ12፣ የ8 እና የ6 ኪሎ ሜትር ውድድሮች በሚል በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡


ቀደም ባሉት ዓመታት ከ5 ያልበለጡ ክለቦች ብቻ ይሳተፉበት ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ግን ከአርባ የማያንሱ ክለቦች የሚሳተፉበት ውድድር ሆኗል። የተወዳዳሪዎች ቁጥርም በየዓመቱ እየጨመረ መሄዱ ይነገርለታል። የጃንሜዳ አገር አቋራጭ ውድድርን ቀደም ባሉት ዓመታት በአሸናፊነት ካጠናቀቁ አትሌቶች መካከል ፤ ወዳጆ ቡልቲ፣ ደረጀ ነዲ፣ መሃመድ ከድር፣ አልማዝ ለማ፣ በላይነሽ በቀለና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ። ሶስት የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያጠለቀውና የዓለም የአምስትና የአስር ሺ ሜትር የክብረወሰን ባለቤቱ ቀነኒሳ በቀለም በመካከለኛው የውድድሩ ዘመን ካሸነፉ አትሌቶች አንዱ ነው። ከቀነኒሳ በቀለ ተጨማሪ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም፣ የሲቪያ ዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የ10 ሺ ሜትር አሸናፊዋ ጌጤ ዋሚ፣ አብዮት አባተ፣ ሃይሉ መኮንን እንዲሁም የሲዲኒ ኦሊምፒክ የአምስት ሺ ሜትር አሸናፊው ሚሊዮን ወልዴ ይገኙበታል።


በቅርብ ጊዜያት የውድድሩን የአሸናፊነት ዘውድ መድፋት ከቻሉት አትሌቶች መካከል እጅጋየሁ ዲባባ፣ አየለ አብሽሮ፣ መሰለች መልካሙ፣ ገነት ያለው፣ ሙክታር እንድሪስ፣ ህይወት አያሌው፣ ሃጎስ ገብረህይወት እና ሌሎችም ስመጥርና ውጤታማ አትሌቶች ናቸው።

አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011

ቦጋለ አበበ