ኢትዮጵያውያን በሳምንቱ የደመቁባቸው ውድድሮች

9

ያለፈው ሳምንት በአትሌቲክሱ ዓለም በርካታ ታላላቅ ውድድሮች የተስተናገዱበት ሆኖ አልፏል። ከቤት ውስጥ በርካታ ውድድሮች አንስቶ እስከተለያዩ የጎዳና ላይ ውድድሮችም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በድል ተንቆጥቁጠው ታይተዋል። ከጣፋጭ ድሎቻቸው ባሻገርም በተለያዩ ርቀቶች ፈጣን ሰዓቶችና ክብረወሰኖች ማስመዝገብ ችለዋል።


ትናንት ማለዳ በተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ በተካሄደው የራስ አል ኪማህ ግማሽ ማራቶን ውድድር ኢትዮጵያውያን ያስመዘገቡት ውጤት በጉልህ የሚጠቀስ ሲሆን በሁለቱም ፆታ ፈጣን ሰዓቶች ተመዝግቦበታል። በሴቶች መካከል በተካሄደው ውድድር ሰንበሬ ተፈሪ በርቀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፋ 1፡05፡45 በሆነ ሰዓት አሸናፊ ሆናለች። ይህም በታሪክ በርቀቱ የመጀመሪያ ተሳትፎ የተመዘገበ ፈጣን ሰዓት ሲሆን የኢትዮጵያ ክብረወሰን ሆኖ ሊመዘገብም ችሏል።


እጅግ ጠንካራ ፉክክር በታየበት ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ አራት ባለው ደረጃ ውስጥ ሲያጠናቅቁ የዓለም ግማሽ ማራቶን የክብረወሰን ባለቤት የሆነችው ነፃነት ጉደታ እስከ መጨረሻ ድረስ ታግላ ለጥቂት በመቀደሟ በተመሳሳይ ሰዓት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ዘይነባ ይመር 1:05:46 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆና ስትፈፅም ደጊቱ አዝመራው በ1:06:07 ሰዓት ተከታዩን ደረጃ ይዛ አጠናቃለች። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እስከ መጨረሻ ያደረጉት አጓጊ ፉክክር ከአንድ እስከ ሦስት ባለው ደረጃ ያጠናቀቁ አትሌቶች የገቡበት ሰዓት ልዩነት የአንድ ሰከንድ ብቻ እንዲሆን አድርጎታል።


በተመሳሳይ በወንዶች መካከል በተካሄደው ውድድር ለድል ሲጠበቁ የነበሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቀዳሚውን ደረጃ በኬንያዊው ስቲፈን ኪፕሮፕ ቢነጠቁም ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው አጠናቀዋል። የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቶት የነበረው አባዲ ሃዲስ ድንቅ ፉክክር ቢያሳይም በአጨራረስ ድክመት ኪፕሮፕ በሁለት ሰከንድ 58፡42 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ መሆን ችሏል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ፍቃዱ ሃፍቱ 59:08 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆኖ ውድድሩን ጨርሷል። ኪፕሮፕ ያስመዘገበው ሰዓት የውድድሩ ክብረወሰን ከነበረው ሰዓት ጋር እኩል ሲሆን በርቀቱም በታሪክ አምስተኛው ፈጣን ሰዓት መሆን ችሏል።


ካለፈው ረቡዕ አንስቶ በተለያዩ የዓለማችን ከተሞች ሲካሄድ በነበረው የቤት ውስጥ የዙር ውድድርም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አስደናቂ ውጤት አስመዝግበዋል። ፖላንድ ቶሩን በተካሄደው የቤት ውስጥ ውድድር የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮኑ ወጣት አትሌት ሳሙዔል ተፈራ የውድድር ዓመቱን መሪ ሰዓት3:35.57 በማስመዝገብ አሸናፊ ሆኗል። በዚህ ውድድር ልምድ ያለው ኢትዮጵያዊ አትሌት አማን ወጤ እልህ አስጨራሽ ፉክክር ቢያደርግም በመጨረሻዎቹ ሦስት መቶ ሜትሮች የአስራ ዘጠኝ ዓመቱ ሳሙዔል ተፈራ እጅ የሚሰጥ አልነበረም።


በተመሳሳይ ቀንና ቦታ በሴቶች ስምንት መቶ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሃብታም አለሙ በፈጣን ሰዓት ታጅባ ያሸነፈችበት ክስተትም ያልተጠበቀ ነበር። አትሌት ሃብታም አለሙ በርቀቱ ከፍተኛ ልምድና ችሎታ ያላትን እንግሊዛዊቷን አትሌት ላውራ ሙዒርን ቀድማ በመግባት የውድድር ዓመቱ መሪ የሆነውን1:59.49 ሰዓት ማስመዝገብ ችላለች።


በሳምንቱ ከተመዘገቡት ታላላቅ ውጤቶች አንዱ የሆነው በስፔን ሳባዴል በተካሄደው የቤት ውስጥ ውድድር ገንዘቤ ዲባባ ያስመዘገበችው ነው። የዓለም የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ቻምፒዮንና የርቀቱ የቤት ውስጥም ከቤት ውጪም ክብረወሰን ባለቤቷ ገንዘቤ ዲባባ አሁንም በርቀቱ ከዓለማችን ኮከብ አትሌቶች አንዷ መሆኗን እያሳየች ትገኛለች። ገንዘቤ ምንም እንኳን ወጣ ገባ የሆነ አቋም በማሳየት ያለፈውን የውድድር ዓመት ጎልታ ባትታይም ዘንድሮ 3:59.08 የሆነ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ሌላኛዋን ኢትዮጵያዊት አትሌት ለምለም ሃይሉን አስከትላ በመግባት ማሸነፍ ችላለች።

አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011

ቦጋለ አበበ