የኬንያውያን ተጫዋቾች የጨዋታ ማጭበርበር ቅሌት

16

በአትሌቲክሱ ዓለም አበረታች ንጥረነገር መጠቀም የስፖርቱ ነቀርሳ እንደሆነው ሁሉ በእግር ኳሱ የጨዋታን ውጤት ሆን ብሎ ማስቀየር ወይም የጨዋታ ማጭበርበር ቅሌት ከምንም በላይ ለተወዳጁ ስፖርት ጠንቅ ነው። የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋም ስፖርቱን ከዚህ አደጋ ለማፅዳት የተለያዩ ርምጃዎችን ይወስዳል።

ቢቢሲ ሰሞኑን ያስነበበው ሃተታም ፊፋ በዚሁ የጨዋታ ማጭበርበር ቅሌት ጋር በተያያዘ የተለያዩ አፍሪካ አገራትን እኤአ የ2010 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን መለስ ብሎ መመልከትና ምርመራ ማድረግ ጀምሯል የሚል ነው። በዚህም መሰረት ምስራቅ አፍሪካዊቷ የአትሌቲክስ አገር ኬንያ የእግር ኳስ ተጫዋቾች በ2010 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በዚሁ ቅሌት ሳይዘፈቁ እንዳልቀሩ ዘገባው አመላክቷል።


ፊፋ ያወጣው አስር ገፅ ሪፖርት እንደሚያመለክተው የቀድሞው ኬንያዊ ተጫዋች ጂዮርጅ ኦዊኖ እና እውቁ የጨዋታ ውጤት አስቀያሪ ራጅ ፔሩማል የበርካታ ጨዋታዎችን ውጤት ለመቀየር ግንኙነት እንደ ነበራቸው ተደርሶበታል። ሁለቱ ግለሰቦች በርካታ የኢሜል ልውውጦችን እንዳደረጉ የተደረሰበት ሲሆን ፊፋ ተጨማሪ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ አሳውቋል። እኤአ ከ2009 እስከ 2011 ድረስ ኬንያ ባደረገቻቸው ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ይህ ቅሌት እንደተከናወነ የሚገልፀው ፊፋ ኬንያ በ2010 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በቱኒዚያ አንድ ለዜሮ ተሸንፋ የተሰናበተችበት ጨዋታ ዋነኛው መሆኑን አሳውቋል።


የቀድሞው የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ኦዊኖ የጨዋታ ውጤቶችን ለመቀየር ከፔሩማል ጋር ድርድር ሲያደርግ እንደነበረም ሁለቱ ግለሰቦች ከተለዋወጡት ኢሜል መረጋገጡን የፊፋ ሪፖርት ያሳያል። እኤአ ከ2008 እስከ 2015 ድረስ ለብሔራዊ ቡድኑ ተሰልፎ የተጫወተው ኦዊኖ ምንም አይነት ስህተት እንዳልሰራ ቢያስተባብልም ፊፋ ቅሌቱን በማስረጃ አስደግፎ ይፋ አድርጎታል። ከዚህ ቀደም በተለያዩ የጨዋታ ማጭበርበር ቅሌቶች በተለይም ከፊንላንደና ሃንጋሪ ጋር በተያያዘ ስሙ ሲነሳ የነበረው ፔሩማል እስካሁን በይፋ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠም።


ፊፋ ከኬንያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በተያያዘ ኦዊኖና ፔሩማል እኤአ ከ ሰኔ 2009 እስከ መጋቢት 2011 ድረስ ሁለቱ ግለሰቦች ያደረጓቸውን የኢሜል ልውውጦች መነሻ በማድረግ የጨዋታን ውጤት ስለመቀየራቸው አስቀምጧል። ሲንጋፖራዊው ፔሩማል ኬንያ ለ2010 የዓለም ዋንጫ እኤአ ጥቅምት 2009ከቱኒዚያ ጋር ያደረገችውን ጨዋታ ብቻ በተመለከተ ኦዊኖን ጨምሮ ሌሎች ሁለት የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ከአቅማቸው በታች እንዲጫወቱ ወይም እንዲለቁ አነጋግሯል።


ፔሩማል በኢሜል መልዕክቱ «ልብ አድርጉ በቱኒዚያ አንድ ለዜሮ ከተሸነፋችሁ ምንም አታገኙም፤ እኔ የምፈልገው ሦስት ለዜሮ የሆነ ውጤት ነው» በማለት ለተጠቀሱት የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች እንዳሰጠነቀቀ ፊፋ በሪፖርቱ አያይዞ አቅርቧል። ከዚህ ጨዋታ በኋላም እኤአ ጥር 2011 ኬንያ ከደቡብ አፍሪካ ባደረገችው የወዳጅነት ጨዋታ ፔሩማል እጁን ስለማስገባቱ ፊፋ እያጣራ ይገኛል። ፔሩማልና ኦዊኖ የነበራቸው ግንኙነት ከኬንያ ብሔራዊ ቡድን በዘለለ እስከ አውስትራሊያ እንደሚዘልቅ ታውቋል።

ለዚህም ፔሩማል እኤአ 2010 መጋቢት ወር ላይ ለኦዊኖ «ወደ አውስትራሊያ የምወስድህ ለስራ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ታማኝ ልትሆንልኝ ይገባል፤ አድርግ ያልኩህን ከፈፀምክ በየወሩ ሰላሳ ሺ ዶላር ታገኛለህ» የሚል መልዕክት እንዳደረሰው ተረጋግጧል። ይህ መልዕክት ከተላከ ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ ኦዊኖ «ምንም ችግር የለውም ምክንያቱም ለእኔም ሆነ ለቤተሰቦቼ ጥሩ ህይወት እፈልጋለሁ፤ ስለዚህ አድርግ ያልከኝን አደርጋለሁ፤ ነገር ግን የክፍያው ጉዳይ በምን መልኩ ነው» የሚል ምላሽ በኢ ሜል አድራሻው ምላሽ እንደሰጠ ፊፋ ደርሶበታል።


ፊፋ ከዚህም በዘለለ ኦዊኖ ክፍያውን እንደተቀበለ የሚያረጋግጥ መልዕክት ደግሞ እንደላከ ደርሶበታል። ይህም መልዕክት «በጣም አመሰግናለሁ፤ ተባረክ» የሚል መሆኑ በተጨማሪ ማስረጃነት ቀርቧል። እኤአ 2011 ላይ በዚሁ የጨዋታ ማጭበርበር ቅሌት ተከሶ ወደ ማረሚያ ቤት የገባው ፔሩማል በበርካታ የአፍሪካ አገራት የጨዋታ ውጤቶችን በተሳካ ሁኔታ ሲያስቀይርና ሲያጭበረብር እንደነበር ራሱ ተናግሮ ነበር። ፊፋም ከኬንያ በተጨማሪ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ላይ የምርመራ ስራዎች እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ከ2010 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ጋር በተያያዘ እኤአ 2008 ላይ ሴራሊዮን ከ ደቡብ አፍሪካ ጋር ያደረገችው የማጣሪያ ጨዋታ ዋነኛው መሆኑ ታውቋል።

አዲስ ዘመን የካቲት 2/2011

ሶሎሞን በየነ