ቋሚ መታሰቢያ ለአፍሪካ አንድነት አባት

51

የአፍሪካ አባት ኃይለሥላሴ ግርማዊነትዎ የህዝብ እንደራሴ

    ብሎ ቴዎድሮስ ካሳሁን የዘፈነላቸው ያለምክንያት አልነበረም። የአፍሪካውያን መሪዎችን አሰባሳቢ ብሎም ለመብቶቻቸው እንዲታገሉ ጥሪ ያቀረቡ ብርቱ ሰው በመሆናቸውም ጭምር ነበር።

አፍሪካውያን ሙሉ ለሙሉ አሁን መዋሃድ አለባቸው በሚለው የካዛብላንካው እና ቀስ ብሎ ውህደቱ ይመጣል እስከዚያው ግን የአንድነት ማህበር ያስፈልጋል በሚለው የሞኖሮቪያው ቡድን መካከል ፍጭት ነበር። አፄ ኃይለሥላሴ ደግሞ  ለሁለት የተከፈለውን የአፍሪካ አገራት መሪዎች ቡድን አንድ ለማድረግ ወጥነዋል። ውጥናቸው ሰምሮ ከሦስት ቀናት ጉባኤ በኋላም ሌሊቱን ጭምር በተደረገ ውይይት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ  እውነ ሆነ። የዛሬ 56 ዓመት ወርሐ ግንቦት ላይ ነበር በአዲስ አበባ የአፍሪካ አገራትን መሪዎች በአንድ አዳራሽ ሰብስበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ጉልህ ሚና ያበረከቱት።

አፄ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያ መሪ በሆኑበት ወቅት የአፍሪካ አንድነት መመስረቻ ንግግር እንዲያደርጉ ተጋብዘዋል። በወቅቱም ሙሉ ሱፋቸውን ከነከረባታቸው እንዳደረጉ ለንግግር ወደመድረክ ሲወጡ ሁሉም በአንክሮ ይመለከታቸው እንደነበር የምስልና ድምፅ መረጃዎች እማኝ ናቸው።

እርሳቸውም እንዲህ አሉ ‹‹በዛሬው ቀን መላው ዓለም አተኩሮ ይመለከተናል። አካባቢያችን  በተጠራጣሪዎች እና ተስፋ በሚያስቆርጡ የተሞላ ነው። አፍሪካውያን እርስ በርሳቸው በመጣላት የተለያዩና የተከፋፈሉ ናቸው የሚሉ አሉ። እውነትም አንዳንድ አለ። ቢሆንም ይህ መጥፎ አስተያየት ያላቸውን ሁሉ ከንቱ መሆኑን በሥራችን እናሳያቸው። ሌሎች ደግሞ አፍሪካውያን ባለፉት ዘመናት የደረሰባቸውን ጭቆና በማሰብ የህዝቦቻቸው የወደፊት ዕድል የተቃና እንዲሆን ተጣጥረው ለመሥራት ቆርጠው ተነስተዋል የሚሉ አሉ። እነዚህ ለኛ ለአፍሪካውያን በጎነት የሚያስቡ ደግሞ ያልተሳሳቱ መሆናቸውንና በእኛም ላይ የጣሉት እምነት የሚገባ መሆኑን በተግባራችን እናስመስክር።››

ረጅሙ ንግግራቸው ቀጥሏል። የነገዪቱ አፍሪካ፣ ቂም መያዝ አይገባም፣ የመሸጋገሪያ ጊዜ ያስፈልጋል በሚሉና በሌሎችም አርዕስቶች ተከፋፍሎ በንባብ የሚቀርበው ንግግራቸው በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ነበር። በአስተርጓሚ የሚቀርብላቸውን የንጉሡን መልዕክት የሚያዳምጡ መሪዎችም በመሃል በመሃሉ አድናቆታቸውን ለመግለጽ ማጨብጨባቸው አልቀረም። ከዚያ ስብሰባ በኋላ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በየጊዜው እየተገናኙ ስለጉዳዮቻቸው በጋራ መምከሩን ተያይዘውታል።

የንጉሡ አስተዋጽኦ ግን የተረሳ ቢመስልም ጊዜውን ጠብቆ መወደሱ አልቀረም። የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች ለሆኑት ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው የቀድሞው የደቡብ አፍሪካው መሪ ታቦ ምቤኪ እና ሌሎችም ሲጠይቁ ነበር፡፡ የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በህብረቱ ስብሰባ ላይ ሐውልቱ እንዲቆም ጠይቀዋል። ታሪክ አስታዋሽ ነውና የአፄ ኃይለሥላሴ ሥራ ከንቱ አልቀረም። በመሆኑም በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ሕንፃ ፊት ለፊት ሐውልታቸው ተቀርጾ ለዕይታ የሚበቃበት ቀን ዛሬ ሆኗል።

የኬንያ ናይሮቢ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምምህሩ ፕሮፌሰር ሚካኤል ቼጌ እንደሚናገሩት፤ ንጉሡ ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገሮች ካዛብላንካ እና ሞኖሮቪያ በሚባሉ ሁለት ቡድኖች በተከፋፈሉበት ወቅት መሪዎቹን በማቀራረብ ወደ አንድነት ያመጡ ባለውለታ ናቸው። በጉባዔው ወቅት አፄ ኃይለሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሳይመሠረት እና የድርጅቱን ቻርተር ሳያፀድቅ መጠናቀቅ እንደሌለበት አጥብቀው በማሳሰብ ሌሊቱንም ጭምር በመሥራት ቁርጠኝነታቸውን እንዳሳዩ ታሪክ ያስረዳል። በዚህም የአፄ ኃይለሥላሴ ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

ፕሮፌሰር ሚካኤል እንደሚሉት፤ 32 አገራት የመሰረቱት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ብቻ ሳይሆኑ ነፃ ያልወጡ አገራትም ቀስ በቀስ ድርጅቱን እንዲቀላቀሉ የሚያደርጉት ጥረት ቀላል አልነበረም። በዚህም የአህጉሪቷን መሪዎች በዓለም መድረክ ላይ የበለጠ ተሰሚነት እንዲኖራቸው እና የአገራቸውን መብት እንዲያስከብሩ በር የከፈቱ ሰው ናቸው። አፍሪካውያኖቹ የሚሰበሰቡበት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ጉዳይ እና አህጉራዊ ውሳኔዎች መነጋገሪያ ጽህፈት ቤት ማሰሪያ መሬት እና ገንዘብ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም አበርክተዋል። በመሆኑም ለእርሳቸው ሐውልት ማቆሙ የሚያስመሰግን ተግባር ነው።

የአፍሪካ እርስ በእርስ መገማገሚያ መድረክ ባለሙያ የሆኑት ማላዊው ፕሮፌሰር ጆናታን ካውንዳ እንደሚገልጹት ደግሞ፤ አፄ ኃይለሥላሴ ባለራዕይ አፍሪካዊ መሪ ነበሩ። አፍሪካ ከነበረችበት የባርነት ሰቆቃ ወጥታ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣላት ይናገሩ ነበር። ነገ ብሩህ ጊዜ እንደሚኖር በማሳየት ለአፍሪካውያን የተሻለ ዘመን እንዲመጣ መነሳሳትን ፈጥረዋል። ማንኛውም አፍሪካዊ አገር በሚያጋጥመው ችግር ውስጥ የእርስ በእርስ ትብብር መኖር እንዳለበት ያስተማሩ አባት ነበሩ።

እንደ ፕሮፌሰር ጆናታን ከሆነ፣ አፍሪካውያንን ከጭቆና ቀንበር ለማውጣት ወንድማማችነቱ መጠናከር እንዳለበት በየመደረኩ ሰብከዋል። አገራት ሲተባበሩ በዓለም ላይ ያላቸው ተቀባይነት እና ተሰሚነት እንደሚጨምር ቀድመው የተገነዘቡ ባለራዕይ መሪ ናቸው።  የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ትብብር በአገራት መካከል እንዲጠናከር ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

መቀመጫውን ሩዋንዳ ኪጋሊ ያደረገው የአፍሪከ ዘላቂ ልማት ግቦች የአፍሪካ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይ እጅጉ ደግሞ ስለአፄ ኃይለሥላሴ የማይረሳ የነፃ አውጪነት ድጋፍ ያወሳሉ። እንደ እርሳቸው፤ ከህብረቱ ምስረታ በተጨማሪ ንጉሡ በቅኝ ግዛት ስር ወድቀው ለነበሩ አገራት ጠንካራ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር። የተለያዩ የነፃነት ታጋዮችን በማበረታታት እና ስልጠና በመስጠት እንዲሁም ኢትዮጵያ ነፃ በመውጣቷ ጥቁሮች ነፃ መሆን እንደሚችሉ በማሳየት ታሪክ የማይረሳው አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰው ናቸው።

በአፍሪካ ውስጥ አንድ አገር እንኳ ነፃ ሳይወጣ ቢቀር የኛም ነፃነት የተሟላ ሊሆን አይችልም ብለው የተናገሩት የንጉሡን ታላቅነት ያሳያል የሚሉት ዶክተር በላይ፤ በወቅቱ ቅኝ ግዛት ስር ለነበሩት ለሮዴሺያ፣ ለደቡብ አፍሪካ፣ ለአንጐላ፣ ለሞዛምቢክና ሌሎች የአፍሪካ አገራት ወንድሞቻችን ሙሉ ዕርዳታ መስጠት አለብን ብለው መሪዎችን በመወትወታቸው ሁልጊዜም ታሪክ ሲያወሳቸው ይኖራል። ዶክተር በላይ እንደሚናገሩት፤ ለአፄ ኃይለሥላሴ  ውለታ ሐውልት ማቆም ቢያንስባቸው እንጂ አይበዛባቸውም። ንጉሠን መዘከሩም ለመጪው ትውልድ ምሳሌ አድረጎ ለማቅረብ ይረዳል።  

አዲስ ዘመን የካቲት 3/2011

በጌትነት ተሰፋማርያም