የማህበረሰቡና አመራሩ ጥምረት ለሶስቱ 90ዎች ስኬት ሚናው የጎላ ነው

5

ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው።
በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

መዲናችን አዲስ አበባ በፍጥነት እያደገች ያለች ከተማ እንደመሆኗ በከተማዋ በርካታ ሆቴሎች፣ የእንግዳ ማረፊያዎች፣ ፔኒሲዮኖች፣ የተለያዩ መዝናኛ ስፍራዎች እየሰፉና እየተበራከቱ የመጡበት ሁኔታዎች አሉ፡፡ የከተማዋ የህዝብ ቁጥርም ከሌሎች የሀገሪቷ ትላልቅ ከተሞች በራቀ ሁኔታ ከፍተኛ በመሆኑ ጫናውም በዚያው ልክ ነው፡፡

ከሃገራችን ከተለያዩ አካባቢዎች ስራ ፍለጋ እና የተሻለ ኑሮ በመሻት በየቀኑ ወደ ከተማዋ የሚገቡ ዜጎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ መገፋፋቶች ረጃጅም የታክሲ ሰልፎች የዚህ መገለጫዎች ናቸው፡፡ በከተማዋ ያለው የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭትም ባለው መዘናጋት ምክንያት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

  ይህንኑ አስመልክቶ ከጥር 19-20/2011 ዓ.ም ኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ላይ በአዳማ ከተማ በነበረው የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት መድረክ ተሳታፊ የነበሩት፤ በልደታ ክፍለ-ከተማ የወረዳ አንድ የምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አንተነህ ግርማዬ ሃሳባቸውን አካፍለውናል፡፡  አቶ አንተነህ በመድረኩ በርካታ ትምህርትና ግንዛቤ መገኘቱን እና የኤች አይ ቪ መከላከል እና መቆጣጠር ስራ እንደ አንድ ዋነኛ ጉዳይ ሊታይ እንደሚገባ መረዳታቸውን ገልጿል፡፡ ከተሰጡ መረጃዎች  ማወቅ እንደሚቻለው በአሁኑ ሰዓት በተለይ በአዲስ አበባ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ ስርጭትና የማህበረሰባችን ተጋላጭነት ከፍተኛ መሆን  አሳሳቢና አንገብጋቢ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ አድርጎታል፡፡ ይህም አስደንጋጭም ስለሆነ አሁን ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ ሲታይ አጠቃላይ በህብረተሰባችን ያለው ግንዛቤ ጥሩ ነው በሚባልበት ደረጃ፤ እየተከሰተ ያለው የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭትም አጠቃላይ አሁን ያለው ሁኔታ ስጋት ላይ ጥሎናል፡፡ ስለዚህ «ሁሉም የህብረተሰብ አካል እንዲሁም አስተዳደሩ እና አመራሩ በጥምረት እና በቅንጅት ሆነው በትኩረት መስራት እንዳለባቸው እና ሳይሰራ የቀረውም ቀጣይ ተግባርና የቤት ሥራ መሆን አለበት» ሲሉም ገልጸዋል፡፡

 በመሆኑም በከተማችን ከንቲባም ጭምር ትኩረት የተሰጠው እና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በጋራ ተቀራርበው በዘመቻ ለመስራት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አጠቃላይ አፈ-ጉባኤዎች እስከ ወረዳ ያለው ቃል የገቡበትና የአቋም መግለጫም ያወጡ ስለሆነ ቀጣይ ላይ የመቆጣጠሩን ስራ በሰፊው መስራት ይገባልም ብለዋል፡፡ ሚድያው፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ አጠቃላይ የሚመለከታቸው ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት፣ ቤተ-እምነቶች፣ የኃይማኖት መሪዎችና አስተማሪዎች በሙሉ ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

  በከተማዋ በርካታ ተቋማቶችና መዝናኛ ስፍራዎች ፔኒሲዮኖችና ልዩ ልዩ ቦታዎች ለአገልግሎት ይዘጋጃሉ፤ መኖሪያ የነበሩ ሰፈርና መንደር አካባቢ ያሉ ቤቶችም በተመሳሳይ አገልግሎቶች ውስጥ እየተስፋፉ ይገኛሉ፡፡ አንዱ የቫይረሱን ስርጭት በመከላከል ረገድ እየተፈጠረ ያለው መዘናጋት መጨመር ትልቅ እድል እየሰጠ ያለው ይሄ በመሆኑ፤ በዚህ ውስጥ የመጡ የተለያዩ መጤ ባህሎች ከከተማዋ እድገት ጋር ማስተካከልና ማስታረቅ ይገባል፡፡ በተቋሞቻቸው ሰዎች እንዴት እራሳቸውን ከቫይረሱ መጠበቅ እንዳለባቸው እና እንዳይዘናጉ በግልጽ ማስታወቂያም ጭምር በየክፍሉና በየበራፎቻቸው፣ በመዝናኛ ስፍራና ቦታዎች ላይ የሚያስተዋውቁበት ሰፊ ስራ መስራት ይገባል፡፡

  በአሁን ሰዓት የአዲስ አበባ የኤች አይ ቪ መቆጣጠሪያና መከላከያ ጽ/ቤት ዋናው ዓላማው አድርጎ የተነሳው እ.ኤ.አ በ2030 ሃገራችን ኤድስን ማቆም፣ ሀገሪቷን ከስርጭትና መተላለፍ ነፃ ማድረግ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ከሃገራችን እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወቅታዊ የቫይረሱ አሳሳቢነት አንፃር ሶስቱ ዘጠናዎች በሚለው እቅድ በመመራት እየተሰራበት ይገኛል፡፡ አንደኛው ዘጠና የሚባለው 90 በመቶው ዜጎች ተመርምረው የራሱን ሁኔታ የሚያውቅ ህብረተሰብ መፍጠር ነው፤ ሁለተኛው ዘጠና መድረስ ያለበት እቅድ ደግሞ ጠቅላላ ራሱን ካወቀው የፀረ ኤች አይ ቪ ህክምናውን የሚጀምርና ሳያቋርጥ የሚቀጥል ክትትል  የሚያደርገውን 90 በመቶ ማድረስ ነው፡፡ እንዲሁም ሶስተኛው ዘጠና መድሃኒቱን በአግባቡ እየወሰደ ያለው 90 በመቶው በደሙ ውስጥ ያለውን የቫይረሱን የጉዳት መጠን በምርመራ በማይታይበት ደረጃ መቀነስ መቻል የሚል ነው፡፡

 ከዚህ ጋር በተያያዘም ወቅታዊ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምርመራ ማድረግ ያለውን የዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ለሶስቱ ዘጠና እቅዶች ተግባራዊነት በየደረጃው ያሉ አመራሮችና የሚዲያው ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው።

  በዚህም አንድ ሰው ከቫይረሱ ጋር መኖሩን በጊዜ ቀድሞ ካወቀ ህይወቱን ለመታደግ የሚያስችለውን ህክምና ቀድሞ ይጀምራል ማለት ነው፡፡ ውጤቱም የተሻለ ይሆናል፤ በህይወትና በጤና ለመቆየትም ያስችላል፡፡ በተመሳሳይ ሌሎች በሽታዎችንም በጊዜ ለማወቅ እድል ይከፍታል፡፡ በመሆኑም እንደ ሳንባ ነቀርሳ /ቲቢ፣ የጉበት ብግነት/ሄፓቲቲስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊት እና የስኳር በሽታ የመሳሰሉትን ችግሮች በጊዜ ለማወቅም ያስችላል፡፡

 እንዲሁም በወቅቱ ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ራስን በማወቅ ቫይረሱን ከእናት ወደ ህፃን እንዳይተላለፍም ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ ከቫይረሱ ጋር እያለች በእርግዝና ላይ የሆነች ወይም እያጠባች ያለች እናት ከቫይረሱ ነፃ የሆነና ጤነኛ ሆኖ እንዲቆይ የሚችል ልጅ እንዲኖራት ማረጋገጥ ስለሚያስችላት ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው፡፡

 ከዚህም በተጨማሪ ተመርምሮ ራስን ማወቅ ተገቢውን እንክብካቤ ለማግኘት ትልቁ ኤች አይቪን የመከላከል መሳሪያ ነው፡፡ ህይወትን ማዳን እና ስርጭቱን መከላከል በመሆኑ  የኤች.አይ.ቪ ህክምና የቫይረሱን የጉዳት መጠን እንዲሁም ቫይረሱ በደሙ ያለ ከሆነም ያለውን  የቫይረስ መጠን በምርመራ በማይገኘበት ደረጃ ያደርሰዋል፡፡ በዚህም የሶስቱን ዘጠና ግቦች ለማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች መስራት ይቻላል፡፡

  ስለዚህ የሶስቱ ዘጠና ግቦች ለማሳካት ሁሉም የህብረተሰባችን አካል በመጀመሪያ ከቤቱ በመጀመር በትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡ በወረዳ ደረጃ ያለው መዋቅራዊ አደረጃጀትም የኤች አይ ቪን መከላከልና መቆጣጠር ስራን የእቅዱ አካል አድርጎ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል፡፡ በሌሎች ተቋማትና የስራ እድል ፈጠራዎች፥ የህብረተሰብ ተጠቃሚነትን እና ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስራዎችን በምንሰራው ልክ ለኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠርም  አብሮ በማስኬድ የበኩሉን መስራት ይጠበቃል፡፡

 ከሴቶች ጉዳይና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር የምንሰራቸውን ስራዎችም ከኤች.አይ.ቪ ጋር በትኩረት ለመስራት በእቅዶች ላይ ተካተው አስፈጻሚውም አካል ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርግበት ይገባል፡፡ የየወረዳውን አመራር መከታተልና መቆጣጠር በጋራ በመነጋገርና በመመካከር በተለይ የወጣቶችን መድረክ በመፍጠር ክበባትን በማጠናከር፣ የወጣት ማዕከላትን በማጠናከር፣ ሰፊ ስራ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ  ሴቶች ላይ ያለውን ተጋላጭነት ትኩረት ተሰቶት ሊሰራበት እንደሚገባ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከዚህም ውጪ ከ15-49 ዓመት ያለው አምራች የሆነው ህብረተሰብ ተጋላጭነቱ ከፍተኛ ስለሆነ በሃገራችን ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ተፅእኖ ይፈጥራልና በትኩረት መታየት አለበት፡፡ ስለዚህ በተለይ ወጣቶች ላይ በትኩረት መስራት አለብን፤ ወጣት ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣  እድሮች እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ ቡድኖችና ተቋማቶች ላይ በስፋት መሰራት አለበት ብለዋል፡፡

  በመሆኑም በተለይ በመዲናችን በአዲስ አበባ አንዳንድ ስፍራዎች ጭምር ተለይተው በጥናት ስለተቀመጡ በእነዚህ አካባቢዎች ከህብረተሰቡ ጋር በየጊዜው ፕሮግራሞች ተዘጋጅተው፥ የመመካከሪያ መድረኮች ተፈጥረው ከዚህ ቀደም በልማዳዊ መልክ ይደረጉ የነበሩትን በጎ ምክክሮች ሳይረሱ በየሲኒማ ቤቱ በየሚድያውም ተከታታይ ትምህርቶች በቀጣይነት ሽፋን ቢሰጠውም መልካም ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማት ኦርቶዶክሱ፣ ሙስሊሙ፣  ካቶሊኩ እንዲሁም ፕሮቴስታንቱ እና ሌሎችም ቤተ እምነቶችን በማሳተፍ  ከመሪዎች፣ ከአባቶች ከኃላፊዎች ጋር በመነጋገር እና በመመካከር የጋራ እቅድና አጀንዳ ተደርጎ ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል፡፡ 

አዲስ ዘመን የካቲት 3/2011

በኃይሉ አበራ