ሙገሳ በቆቦ የቃል ግጥሞች

9

የሙገሳና የውዳሴ ቃል ግጥሞች የማህበረሰቡን የመኖሪያ ቦታዎች፣ የአርሶ አደሩን የዕለት ተዕለት ተግባርና ግለሰቦችን ያወሳሉ። እንዲሁም በአርሶ አደሩ ህይወት ትልቅ ሀብት የሆኑትን እንስሳት በማሞገስ፣ የማህበረሰቡን አስተሳሰብ፣ ህይወትና ማህበራዊ ግንኙነት ማሳየት ይችላሉ፡፡ ጎበዙን ገበሬ ከበሬው ጋር አዛምደው ያነሳሉ። ገበሬው ደግሞ በማሳ ላይ የእርሻ ሥራውን ሲከውን በሬውን እያሞካሸ ይዘፍናል አሊያም ያቅራራል። እረኛው በከብት ጥበቃ ላሞቹን በግጥም ያሞካሻል፤ ሲለውም ይዘፍናል፡፡ እንዲሁም በተለያየ የማህበራዊ አጋጣሚ ማለትም በሰርግ፣ በጭፈራ፣ በመዝናኛ ቦታዎች እና በመንገድ የሙገሳ ቃል ግጥሞች ይከወናሉ፡፡ አስተዳዳሪዎች እና ጀግኖች ለአገር ተቆርቋሪ አድርጎ ማሞገስ፣ ወንዝና ተራራውን እየጠሩ ስለአካባቢው ተፍጥሮ እያነሱ ማወደስ በቃልግጥሞች የሚስተዋል ጉዳይ ነው።

የሙገሳ መነሻው ከበጎ አስተያየትና ስሜት የሚመነጭ ሲሆን፤ ማሞገስ አዎንታዊ በሆነ መንገድ አንድን ነገር ከፍ ከፍ አድርጎ ማቅረብ ነው። በቃል ግጥሞችም ቃላትን እየሰደሩ የነገሩን መልካም ገጽታ፣ ባህሪና ችሎታ አጉልቶ በማሳየት ይነገራል።  በሰሜን ወሎ ስለሚነገሩ የአማርኛ ቃልግጥሞች  ዶክተር አማረ ሞላ ጥናት ሠርተዋል። በጥናቱ መሰረት  በተለይ በሰሜን አካባቢዎች ቆቦ እና አፋር ወሰን ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች በሙገሳ የቃል ግጥም ህይወታቸው የተከበበ ነው። አካባቢንና ሰዎችን ከሚያሞግሱ የቃል ግጥሞች መካከል የሚከተለውን መመልከት ይቻላል።

ከልካይ አባ መሬ

የከልካይ ካቦ አገር

የቸኮለ አሊ አገር

ያነ ማድ፣ ተሮ በሩ

ያነ ማድ፣ ዞብሌ በሩ

እንኳን ሰው ቁሞበት ያስፈራል ግራሩ

ይህ የቃል ግጥም በማቅራራት የሚቀርብ ነው።

በግጥሙ ውስጥ ‹‹ያነ ማድ ተሮ በሩ ዞብሌ በሩ›› የሚለት ሀረጎች አሉ፡፡ ስሞቹ የአካባቢው መጠሪያ ናቸው።

     ‹‹ያነ ማድ›› የሚለውን ሀረግ በመጠቀሙ ክዋኔው ቆቦ ውስጥ መሆኑም ገጣሚው ያስረዳል። ጠብመንጃ ይዞ እያቅራራ ከወዲያ ወዲህ ሲመላለስ ታዲሚውንም ሆነ አድማጩን በዓይነ ህሊናው ወደ አካባቢው እንዲሄድና አካባቢውን እንዲያስታውስ በአገሩ የነበሩትን ታዋቂ ሰዎች እንዲያስባቸው ይቀሰቅሳል። በመጨረሻው ግጥሙ ስለአካባቢው አስፈሪነት እና ግርማ ሞገስ ያወሳል።

ወይ እንዮ ቆቦ ልይ

ነጭ ጤፍ ማሽላ ወስደው ኻላቀኑ

ወይ እንደ ጨርጨር ልይ

ቡሻ ኸመዳፊያው ጊደር ኻላበሉ

ወይ እንደ ዞብል ልይ

እገጭ እገው ሲል ልብን ኻላመኑ

አሁን ወይት ይገኛል ወተት ሞይዘር ቢሉ

ይሄኛው ግጥም ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች የተገለጹበት ነው፡፡ አንደኛው የምርት ዓይነት ሲሆን፤ ሁለተኛው እርባታ፣ ሦስተኛው ደግሞ ጀግንነት ናቸው፡፡ ግጥሙ ላይ ‹‹ልይ›› ሲል ልጅ ለማለት የሚጠቀምበት የወሎ ቅላጼን የሚወክል ነው። ቆቦ ዙሪያውን ሜዳና ለእርሻ አመች ስለሆነ ብዙ ባመረተ ቁጥር ለገበያ የሚያቀርበው እህል ከፍተኛ ነው:: በጎተራ የተሰበሰበው ነጭ ጤፍ፣ በጉድጓድ የሞላው ማሽላ፣ ገበሬው የሚቀጥለውን የምርት ሁኔታ እያገናዘበ ለገበያ ያቀርባል፡፡ ስለዚህ ኻላቀኑ ሲል በግጥሙ ለገበያ ካላቀረቡ ለማለት ነው።  ገበያ ካላቀኑ ወይ እንደ ዞብል አካባቢ ልጅ ልብ ካላሸበሩ እያለ ያሞግሳል። በመጨረሻ ይህን ካላረጉ እህል ሸጠው ካልገበዩ ለወተት የሚሆን ላም ከየት ይገኛል? ሞይዘር የተባለው መሳሪያስ ከወዴት ይገኛል እያለ ያቅራራል።

ግጥሙ ‹‹ወይ እንደ ጨርጨር ልይ ቡሻ ኸመዳፊያው ጊደር ኻላበሉ›› ሲል ቡሻ ለራያ አካባቢዎች አጎራባች የሆነ የአፋር አካባቢ ነው፡፡ ከጨርጨር ወይም አዘቦ አካባቢ ያሉ አርሶአደሮች በተለይም ብዙ ከብት ያላቸው ከብቶቻቸውን ወደ አፋር አካባቢዎች ይዘው በመሄድ ማሰማራታቸውን ሲገልጽ ነው። ይህም የአካባቢዎቹ ተዛምዶ የቆየና አንዱ የአንዱን መስክ የሚጠቀም መሆኑንም ያሳያል።

አካባቢውንና የአካባቢውን ሰዎች የሚያሞግሱት ግጥሞች እንዳሉ ሁሉ ግለሰቦችን እያነሳሱ ማሞገሱም በግጥም ይከወናል። ከዚህ በታች ያሉት መንቶዎችና አርኬዎች ወይም የግጥም ክፍሎች ደግሞ ቆቦንና አካባቢውን እንዲሁም አፋር ውስጥ ስለነበሩ ባላባቶች የሚያስታውሱ ናቸው:፡

እንደምነው ቆቦ ያባ ዘበን አገር

እንዴነህ በሉልኝ በቀኑ ቁጥር 

ያባ ዘበን አገር የፈንታ ኩቢን

ቆቦን ያቀና ሰው ለምን ይኮነናል

እንኳን የሰው ልጁ ውሻው ጤፍ ይበላል

በጣሳ ቢሸመት ስስት የለብሽ

ያባ ዘበን አገር ቆቦ እንደምነሽ

እውር ያለመሪ የሚሄድብሽ

አረቂ በጠርሙስ ጠጅ በብርሌ የሚጠጣብሽ

ያባ ዘበን አገር ቆቦ እንደምነሽ

በዚህ ግጥም ውስጥ በስም የተጠቀሱት የአካባቢው ባላባት ፈንታ ኩቢ የሚባሉት የአባ ቦና ኩቢ ልጅ ናቸው፡፡ እርሳቸው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በግዞት ወደ ሀረር ተወስደው፤ በኋላ በማይጨው ጦርነት ወቅት ከሀረር ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው በጦርነቱ እንደተሳተፉ በታሪክ ይነገራል። የቃል ገጣሚው በዚህ መልክ ቀደም ሲል የነበሩትን የአካባቢ ባላባት በማስታወስ የአሁኑን ትውልድ ወደኋላ በታሪክ ትዝታ ይስበዋል።

ጠመንጃው ሞይዘር ነው ጥይቱ ዘጠና

የዳውዴ አደም አገር እንዴነሽ አሊይና

አትንኩት ያመኛል ጎመጅ አፋፉን

አትንኩት ያመኛል አራቱ ጋሪያን

ዱህኒኖየ ባቤ፣ቃሲሞየ ባቤ፣የቆዩበትን

የከፋው ወንድ ልጅ አሳዲጊውን

በረጅሙ ከርፎ የሚያጠጣውን

በግጥሞቹ ውስጥ የተጠቀሱት የሰውና የቦታ ስሞች የሚገኙት  አፋርም፣ አማራም ትግራይም ክልል ውስጥ ነው። ቡጢ ባቤ፣ ዱህኒኔ ባቤ፣ ቃሲም ባቤ፣ ወንድማማቾች የአፋር ጎሳ አባላት ሲሆኑ፣ ቡጢ ባቤ የጎሳው መሪ የነበሩ ናቸው፡፡ ዳውድ አደም የእነዚሁ ሰዎች የቅርብ ዘመድ ሲሆን፣ ‹‹ጥይት የማያስመታ›› መድሀኒት አለው እየተባለ የሚነገርለት ተዋጊ ነበር። ፍቂሳና አሊይና የአካባቢ ስሞች ሲሆኑ እነዚህ የጎሳ አለቆችና ባላባቶች ኖረውባቸዋል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው የአካባቢው የተለያየ ክልል ማህበረሰብ ምን ያህል በባህልና ታሪክ የተቆራኘ መሆኑን ነው። በግጥሙ መጨረሻ ‹‹ከርፍ›› የተባለው ደግሞ ከእንጨት ተጠርቦ የሚሠራ የወተት ማለቢያን ለመግለጽ ነው። ከርፍ እስከ አምስት ሊትር ወተት ሊይዝ ይችላል።

በሌላ በኩል በሬን እና እንስሳቱን የሚያሞግሱ የቃል ግጥሞችም በአካባቢ እንዳሉ አጥኚው ያስረዳሉ። ለአብነት፦

በሬው አመለኛ ያገኘ አይጠምደው

ጧት የተጠመደ ማታ እሚፈታው

ፋሚሌው ሸጋ ነው የሚተኛበቱ

በሬው ጆቢራ ነው ጆቢራ በብርቱ

አለው ሸጋ በሬ ቀዲም የማይፈራ

አለው ወደል ግመሌ ሸክም የማይፈራ

የለኝ ብሎ አይለምን አለኝ ብሎ አይኮራ

ሲጫወት ይውላል ከእኩዮቹ ጋራ

ኧረ በሬው ንጉሥ፤ኧረ በሬው ሌዶ፤ እንህድ 

ቦይ ለቦይ

ኻረባው ደጃማይ እኛ አንሻልም ወይ

ኸጠጅ ቤት ገብቶ ያለው ቅጅ ቅጅ

የበሬውን ጫንቃ ተማምኖ ነው እንጅ

እያለ ያቅራራል አንዱ ተነስቶ። በቃል ግጥሙ በሬው ብቻ ሳይሆን የሚሞካሸው በበሬው ጉልበት የሚተማመነው ገበሬው ጭምር ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የጭነት አገልግሎት የሚሰጠው የበረሃው መረከብ ግመልም አብሮ ይሞገሳል።

የእነዚህ ግጥሞች ዋና ሃሳብ የበሬውን ኃያልነት ብርቱነት አይደክሜነት ማረጋገጥ ነው፡፡ በግጥሙ ፋሚሌው ሲል አልጋ ለማለት ፈልጎ ነው። በሬው ጆቢራ ነው ጆቢራ በብርቱ ሲል ደግሞ ጆቢራ ማለት ቁመቱ ረጅም ቀንደ ረጃጅም መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡፡ በዘይቤኛው ግን ኃይለኛና ጉልበተኛ የሚለውን ይወክላል። ጆቢራ በብርቱ ሲል ከጠዋት እስከማታ ተጠምዶ እየታረሰ ቢውልም እንደማይዳከም ይገልጸዋል።  ‹‹ቀዲም የማይፈራ›› ሲለው ደግሞ ገበሬው ሲያርስ ወይም ሲያርምና ሲያጭድ በተወሰነ ርቀት ለክቶ የሚሠራበት ርቀትን እያመላከተ ያንን የማይፈራ ሲለው ነው።

ኧረ በሬው ንጉሥ፤ኧረ በሬው ሌዶ ሲለው ደግሞ ምርጥነቱን ሲገልጽ ነው። ‹‹ሌዶ›› በአካባቢው የሚገኝ የዛፍ ዓይነት ሆኖ ከዛፉ የሚቆረጥ በትር አባጣ ጎባጣ የማይገኝበትና ጠንካራ ዱላ ነው። እናም በሬውን የበሬውን ውበት ከበትሩ ጋር እያነጻጸረ ያደንቀዋል።

በእነዚህ በቀረርቶ እና ፉከራ መልክ ከሚቀርቡ የቃል ግጥሞች ማስተዋል እንደሚቻለው የግጥሞቹ ዋና ሃሳብ በሬውን በማሞገስ ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ ገበሬውም አብሮ ተወድሷል፤ ተሞግሷል። እንግዲህ በአካባቢው ሙገሳ የስነግጥም አንዱ አካል ተደርጎ ለዘመናት ቆይቷል። ስነግጥሞቹ በአግባቡ ተሰንደው ባለመያዛቸው አዲሱ ትውልድ በአግባቡ ሊጠቀምባቸው ባይችልም በአጋጣሚ የሰማውን ለየበዓላቱ ያውላቸዋል። እኛም እንደዚህ ዓይነት ታሪክና ባህልን የሚያስተላልፉ የቃል ግጥሞች ተሰንደው ቢዳረሱ መልካም ነው እንላለን። ቸር እንሰንብት!

አዲስ ዘመን የካቲት 3/2011

ጌትነት ተስፋማርያም