ዘመን ያልረታው የሥራ ፍቅር

40

 ቤተሰቦቻቸውን ለማገዝ ጨው፣ ዳቦቆሎና ሽንኩርት ይሸጡ ነበር። በተለያየ ጊዜ የባልትና ውጤቶችንም በማቅረብ ይታወቃሉ። ብዙ ጊዜ ኪሳራ ቢያጋጥማቸውም ተስፋ መቁረጥ የሚባልን አያውቁም። እንደውም በተደጋጋሚ ለምን ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ ራሳቸውን ይጠይቃሉ። «ይህ ያልተሳካልኝ፤ ሙከራዬ የተበላሸ ነገር ስላለው ነው» ብለው ያምናሉ። አካባቢን አጥንቶ ሥራ መጀመር በይበልጥ ይመቻቸዋል። ይህ ደግሞ ዛሬ ለደረሱበት ውጤት እንዳበቃቸው ይናገራሉ። የዛሬ የህይወት እንዲህ ናት እንግዳችን ወይዘሮ ማሜ በሻውረድ።

እንግዳችንን ያገኘኋቸው በአጋጣሚ ነበር። ሊያውም በሠርግ ላይ በተነሳ ወሬ አማካኝነት። በሃዋሳ ፒያሳ አካባቢ ይኖራሉ። ነዋሪዎቹ በሙሉ በሚባል ደረጃ «እያያ» ይሏቸዋል። ልክ እንደናታቸው ነው የሚወዷቸው።  ብዙ የህይወት ተሞክሮ እንዳላቸውም ይነገርላቸዋል። እኔም ጊዜ ሳላጠፋ ጉዞዬን ወደ እርሳቸው ቤት አደረኩና የህይወት ልምዳቸው ምን እንደሚመስል እንዲያጫውቱኝ ጠየኳቸው። እርሳቸውም እሽታቸውን ገለጹልኝና ብዙ ነገር አጫወቱኝ። ይሁንና የነገሩኝን ሁሉ ማቅረቡ አዳጋች ነውና በጣም ምርጥና ሰዎች ይማሩባቸዋል ያልኳቸውን መራርጬ እንዲህ ላቀርብላችሁ ወደድኩ። መልካም ንባብ።

ፍርኖዬ

እናታቸውም ሆኑ አባታቸው እንዲሁም የአካባቢው ሰው ሁሉ ፍርኖ እያለ ነው የሚጠራቸው። ዛሬ ላይ የሚጠቀሙበት ስማቸው የወጣላቸው ትምህርት ቤት ከገቡ በኋላ ነበር። ፍርኖ የተባሉበት ምክንያት በጣም ቆንጆና ዞማ የሆነ ጸጉር ስለነበራቸው እንደሆነ ነግረውኛል። በአካባቢው አጠራር «ጉድሮ» የሚባለውን የጸጉር አሠራር ዓይነት እንኳን ተሠርተው በተልባና መሰል ነገሮች የተጠቀለለው ጸጉር ኃይል ኖሮት ያድጋል። ይህ ደግሞ ውበታቸው ይበልጥ እንዲጎላ ያደርጋል። አያታቸውም ይህን ተመልክተው ፍርኖዬ ሲሉ ስም አወጡላቸው። ያንን ተከትሎም የአካባቢው ነዋሪ ሁሉ ፍርኖዬ ማለቱን ቀጠለ።

አንዳንድ ሰዎች ከዚህ አልፈው ፍርኖ በሻውረድ የሚለውን ስማቸውን «ፍርኖ በሻይ» ይሏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ የሆነውም እርሳቸው በተወለዱበት ሰዓት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ፍርኖ ዳቦ የማይገኝና ብርቅ በመሆኑ ነው። በእርግጥ ፍርኖ በሻይ ሲባሉ በጣም ይናደዳሉ። ለስማቸው መቀየርም መንስኤው ይህ መሆኑን ያስረዳሉ።

ፍርኖዬ በ1953ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን፤ ይህንንም ያወቁት የእነመንግሥቱ ነዋይ ግርግር ጊዜ ተወለድሽ በመባላቸው ነው። ያው እንደዛሬው የልደት ካርድ የለማ። በልጅነታቸው ቤተሰብን በሥራ በሚገባ ያግዛሉ። ይሁንና እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ከብት ጠብቀው አያውቁም። ለዚህ ምክንያቱ አባታቸው ነጋዴ ስለሆኑና እርሳቸውም በንግዱ ስለሚያግዙ ነው። ይህ ደግሞ በሂሳብ ሳይማሩ የተማሩ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። ብዙ ጊዜያቸውን በቤት ውስጥ ያሳልፋሉ። እናታቸውንም ቢሆን ቤት በማስተካከል፣ እንጀራ በመጋገርና ወጥ በመሥራት ያግዛሉ። ቡና ማፍላትና ልብስ ማጠብ ግን በጣም ይጠሉ እንደነበር ይናገራሉ።

በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ በጅሩ ወረዳ እንጠራ በምትባል የገጠር ከተማ ውስጥ የተወለዱት ባለታሪኳ፤ ልጅነታቸውን ሲያስቡት ከታናሽ ወንድማቸው ጋር የሚያደርጉት ነገር መቼም አይረሳቸውም። እርሱ ብልጥና ማንጎዳጎድ የሚወድ፤ የተለያዩ ነገሮችን ከቤተሰብ የሚሰርቅና ሁልጊዜ የሚያስደበድባቸው ነበር። እርሳቸው ደግሞ በባህሪያቸው መስረቅም ሆነ መዋሸት አይወዱም። ይህ ሲሆን ደግሞ ታናሽ ወንድማቸው እንዳያዩ ለማድረግ ከቤት በተለያየ ምክንያት ያስወጣቸዋል። ከዚያ በቤት ውስጥ የጠፋ ነገር መኖሩ ሲታወቅ መጀመሪያ ተጠያቂ የሚሆኑት እንግዳችን ናቸው። ያላዩትን መናገር ስለማይወዱም ከጥፋተኛው እኩል ይገረፉ እንደነበር አይረሱትም።

የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ ናቸው። በዚህም እናትም ሆነ አባታቸው በጣም ይሳሱላቸዋል። ሰው ሲቸገር ግን በፍጹም አይወዱም። ቸገረኝ ሲሉ ያለቅሱ እንደነበርና የማይወዱት ስርቆት ውስጥ ገብተው ከቤተሰብ ሽሮ በርበሬ ለተቸገሩት እንደሚሰጡም ይናገራሉ።

«የልጅነት ህልሜ ብዙ ጊዜ በትምህርቴ ውጤታማ ሆኜ በንግዱ ዘርፍም የተሻለ ደረጃ መድረስ ነበር። ሀብታምና የተማረ ነጋዴ መሆንን ሁልጊዜ አስባለሁ። ለዚህም መሰረቱ በቅርቤ ያለው አባቴ ነው። ከአባቴ ጋር መመሳሰልን እፈልጋለሁ። ግን የተማረ ነጋዴ መሆን ነው የማስበው። የተማረ ሰው በእውቀት የተመራ ንግድን ያካሂዳል፤ የተማረ ሰው ትርፋማነቱን በሚገባ ያውቃል። ኪሳራውንም ቢሆን በምን ማካካስ እንደሚችል ስለሚያውቅ የተማረ ነጋዴ መልካም ነው» ይላሉ።

ትምህርት በራስ ጥረት

በቤት ውስጥ ነው የሥራ ልምዳቸውን ያካበቱት። ስለዚህ ትምህርትም ሲጀምሩ በዚህ መልኩ ነው የሆነው። እናትና አባታቸው ተለያይተው ስለሚኖሩ እናታቸው ጋር በመሄድ ነበር ለመማር የቻሉት። ስለዚህም በማንም ጫንቃ ላይ ላለመሆን የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራሉ። ቆሎ፣ ሽንኩርትና ጨው መሸጥ የጀመሩትም ለዚህ ነው። በራስ ጥረት ለመማር ሲሉ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት እነዋሪ ከተማ ሲሆን፤ ትልቅ ከሆኑ በኋላ ማለትም በ12 ዓመታቸው እንዲገቡ ተደርጓል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እናታቸው በሥራ እንዲያግዟቸው በመፈለጋቸው የተነሳ ነው። አያት ግን ሁላችንም ሳንማር መቅረት የለብንም በሚል ተከራክረው በስንት ትግል እንዲገቡ አደረጓቸው። ለያውም መስከረም 18 የምዝገባ ጊዜ ካለፈ በኋላ።

በቤተሰብ ትግባ አትግባ ንትርክ የምዝገባ ጊዜ አለፈ። በዚህ የተናደዱ አያትም አንድ ዘዴ ፈጠሩ። አባቷ ስለሞተ ለቅሶ ላይ ስለነበረች መመዝገብ አልቻለችም ሲሉ ዋሹ። ይህ ደግሞ ወይዘሮ ማሜን ትምህርት ቤት እንዲገቡ ረዳቸው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነበር የአባታቸው ስም በአያታቸው የተቀየረው። አባት በህይወት ስላሉ ቢገኝስ የሚል ፍራቻ ስላለባቸው በሞተው አያታቸው እንዲጠሩ እንዳደረጋቸው ያስታውሳሉ።

ትምህርቱ ቀጥሎ  ስድስተኛ ክፍል ሳሉ ግን  የሚያቋርጡበት ነገር ተፈጠረ። ልጅ ወለዱ። ይሁንና በዓመቱ መማርን ስለሚሹ ቀጥለዋል። እስከ ስምንት በዚህ ስፍራ ከተማሩ በኋላም ሁሉ ነገር አልመች ስላላቸው በዚህ ችግር ውስጥ ራሳቸውን ላለማሳለፍ ሲሉ ልጃቸውን ትተው ከአክስታቸው ዘንድ ሻኪሶ ሄዱ። በእርግጥ በዚህም ቢሆን ራሳቸውን ማስተዳደር እንዳለባቸው ያውቃሉ። ከአክስታቸው ምንም ገንዘብ ላለመጠየቅ ሲሉ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርተዋል። 

«ሥራ የለመደ ሰው ቁጭ ማለት ይጨንቀዋል» የሚሉት ወይዘሮ ማሜ፤ እናታቸው ጋር እያሉ  በሁለት ፈረቃ እየተማሩ ሽንኩርት፣ ጨው እየሸጡ ወጪያቸውን ይሸፍኑ ነበር። በተለይ ቅዳሜ ሲሆን ትምህርት ስለሌላቸው ሙሉ ቀናቸውን በሥራ ያሳልፋሉ። በዚህም ለቤተሰቡ ቡናና ሌሎች ነገሮችን የሚሸምቱት እርሳቸው ናቸው። ይህ ሁሉ ጫና ሲበዛባቸውና ልጅ ከወለዱ በኋላ ይበልጥ ራሳቸውን ማስተዳደር ስለነበረባቸው ከቤተሰቡ በቅርብ ርቀት ቤት ተከራይተው ራሳቸውንና ልጆቻቸውን እያስተዳደሩ ይማሩ ነበር። 

ቀን ባለቻቸው ሰዓት ራሳቸውን ለማሰተማር የሚያግዛቸውን ሥራ ይሠራሉ። እናታቸው አረቄና ጠላ ሲለሚሸጡ ለዚያ የሚሆን ውሃ የሚቀዱት እርሳቸው ናቸው። ብዙ ጊዜ ምሳ ሰዓት ላይ ያለቻቸውን ሰዓት የሚጠቀሙት ውሃ ለመቅዳት ነው። በእንስራ ከጉድጓድ የቻሉትን ያህል ይቀዳሉ። ማታ ሲመጡ ደግሞ ለእንጀራ መጋገሪያና ለሌሎች ነገሮች ማብሰያ የሚሆን ማገዶ ይለቅማሉ። እናት አባት እስኪያዛቸውም አይጠብቁም።

አክስታቸው ጋር ሻኪሶ ከሄዱም በኋላ ቢሆን እንዲሁ ነው የሚያደርጉት። በዚያ ዘጠነኛና አስረኛ ክፍልን ተከታትለዋል። ነገር ግን ንግዱ የተሻለ አማራጭን ስለሰጣቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው በቀጥታ ንግዱ ላይ ብቻ ትኩረታቸውን አደረጉ። ይህ ደግሞ የተማረ ነጋዴ በመጠኑ ሆኜበታለሁ። ብጨርስ የበለጠ የተማሪ ነጋዴ መሆን እችል ነበር። ይሁን እንጂ አሁንም ያልተማረ አይደለሁም ይላሉ።

የንግድ ሥራ ጅማሬ

ንግድን ሲጀምሩ እጥፍና ከዚያ በላይ እያተረፉ ነበር። ጅማሬያቸውም በጨውና ሽንኩርት ነው። ይህ ደግሞ ለበለጠ ውጤታማነትና ንግድ ወዳድነት አብቅቷቸዋል። ሁልጊዜ በሥራ የምባትልና ሀብታም መሆንን የምሻ ነኝ፤ ለዚህም ብዙ መልፋትና ውጤታማ የምሆንበትን መንገድ ቀይሻለሁ ይላሉ ወይዘሮ ማሜ። በየጊዜው እየተሳካልኝ የመምጣቱም ምስጢር ይህ ነው ይላሉ።

ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ መሸጋገሩ ለሁሉ ነገር አዲስ ቢሆንባቸውም ሻኪሶ ሲሄዱም  መሥራት ከተቻለ በወራት ውስጥ መለወጥ ይቻላል ብለው ስለሚያምኑ ችግርን ይረቱታል። ሻኪሶ ከወርቅ ምድርነቷ ጋር ተያይዞ እጅግ ተፈላጊ ከተማ መሆኗ ደግሞ ለእርሳቸው ልዩ አጋጣሚ የተፈጠረበት ጊዜ እንደነበር ያነሳሉ።  በአካባቢው ምን ቢነገድ ትርፋማ ያደርጋል የሚለውን ማጥናት ልምዳቸው ስለሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅል እያበቀሉ መሸጥን ተለማመዱት።

ወደ ስፍራው ካቀኑ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በሦስት ወራቸው ትዳር መስርተዋል።  ይህ ደግሞ ከቤተሰብ ጫንቃ ላይ እንዲወርዱና ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ዕድል ሰጣቸው። ብቅሉ ሲያበቅሉ ዕቃ ባይኖራቸውም ከጎረቤት እየተበደሩ ነበር። ሌላ ጥናት ሲያጠኑ ደግሞ በአካባቢው የሚቀርበው አረቄ ውሃ መሆኑን ተረዱ። ስለዚህ እጅ ላይ ሲቀጣጠል የሚንበለበለውን ጥሩ አረቄ ለማምረት ራሳቸውን ማዘጋጀቱን ተያያዙት። ግን በምን ዕቃ ሊሠሩት ይችላሉ። ስለዚህ ይህንን ሃሳብ ትተው ሌላ አማራጭ ፈለጉ።

ከመቀመጥ ተቀጥሮ መሥራት ይሻላል በሚል ምግብ አቅራቢ ለመሆን በአካባቢው ከሚገኝ ትልቅ ኮንስትራክሽን ጋር ተዋዋሉ። ድርጅቱ « ባቱ ኮንስትራክሽን» ይባላል። መጀመሪያ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት «ሻይ ከፈለጋችሁ እያፈላሁ ላቅርብ» በማለት ነው። እነርሱም በጣም በመቸገራቸው ማፍያ ቦታ ሠርቶ እስከመስጠት ድረስ አድርሰው በቋሚነት እንዲሠሩ ረዷቸው። ሥራ መፍታት የማይፈልጉት እንግዳችንም ቀጥታ ቦታው ድረስ በመሄድ ከሻይ አልፈው ጠቅላላ ትኩስ ነገሮችን፣ እርጎና ቁርስ እንዲሁም የተለያዩ ለስላሳ መጠጦችን ማቅረብ ጀመሩ።

    «ሥጋ አይጠግብ። ነገር ግን የተቻለኝን ያህል ሠርቼ ለዚህ በመድረሴ አምላኬን አመሰግነዋለሁ። ከዚህ የበለጠ በሥራ ሀብታም መሆንንም እፈልጋለሁ» የሚሉት ባለታሪኳ፤  ባለቤቴ ወታደር ነው፤ የመቶ ስልሳ ብር ደመወዝተኛ። ይሁንና አንድም ቀን የሰው ፊት ገርፎን አያውቅም። ምን ቸግሯቸው ያውቃል ነው የምንባለው። በርቀት ላሉ ለሁለት ልጆች ስልሳ ብር እየተቆረጠ በመቶ ብር መኖር እንችል ነበር። ይህ ደግሞ ይበልጥ እንድሠራ አበርትቶኛል። ካልተቸገሩ መሥራት እንደሌለ የተማርኩትም በዚህ ችግር ውስጥ በማለፌ ነው። አሁንም ብዙ ይቀረኛል። ምክንያቱም የማልመውን ያህል አልሠራሁም፤ አልሆንኩምም። እናም ብዙ ሠርቼ ከዚህ የበለጠ ህልሜ ላይ መድረስ አለብኝ ብዬ አምናለሁና ጠንክሬ እየሠራሁ ነው» ይላሉ ከጉዟቸው ጋር ምን ያህል እየታገሉ እንደነበር ሲያስታውሱ።

ጥንካሬ የሠራው ቤት

ሻኪሶ ሳሉ በጣም ትልቅ ቤት የተባለ የሚሸጠው ሰባትና ስምንት መቶ ብር ነበር። ይሁንና መግዛት በሚችሉበት ወቅት እየተወደደ መጣ። ነገር ግን ይህም ጊዜ ቢሆን ከእርሳቸው ማምለጥ እንደሌለበት ስለሚያምኑ አምስት መቶ ካሬን በአራት ሺህ አምስት መቶ ብር ገዙ። ይህ ደግሞ ከየት አመጣችው እስከመባል አድርሷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ምክንያቱም በዚህ ዋጋ ቤት መግዛት አይደፈርም።

ወይዘሮ ማሜ ስድብና ሀሜቱን ወደ ጎን ትተው ሥራቸውን ማጧጧፉን ተያያዙት። በአንድ በኩል የሻይና ምግብ አቅርቦቱን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ የባልትና ውጤቶችን በማቅረብ አማራጫቸውን ማስፋት ላይ አተኮሩ። ይህም በምንም የተነሱበትን ቤት ሙሉ እንዲያደርጉ አስቻላቸው። ከቀበሌ ቤት ወደ ራስ ቤት እንዲዘዋወሩም ረዳቸው። መጀመሪያ ሲገዛ የነበረው ቤት  ከእንደገና ፈርሶ በጥራት እንዲሠራና የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩም አገዛቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሥራው እያለቀ በመሄዱ የድርጅቱ ተጠቃሚዎች በአብዛኛው በዱቤ የሚጠቀሙ ስለነበር ብራቸውን ይዘውባቸው ይሄዱ ጀመር። ከአስር ሺህ በላይ ብር ተወስዶባቸዋል። በዚያን ጊዜ ደግሞ ይህ ብር ስንት ቤት እንደሚገዛ ማሰብ ቀላል ነው። ይህ ብድር በዚህ ከቀጠለ ደግሞ ባዶ እጃቸውን መቅረታቸው መሆኑን አሰቡት። ስለዚህም ወደ ሌላ አማራጭ መግባት እንዳለባቸው አመኑ። በወቅቱ የቀሩ አንዳንድ ፈረንጆች በመኖራቸው ከእነርሱ ጋር በፍርኖ ዱቄት አቅርቦት ለመሥራት ተደራደሩ። ተፈቀደላቸውናም ሁለት ኩንታል ፍርኖ ዱቄትን በአንድ ኩንታል ስኳር እየቀየሩ ማትረፋቸውን ተያያዙት። ግን ይህም በቋሚነት ህይወት የሚለውጥ አለመሆኑን በመረዳታቸው ጎን ለጎን ሌላ ሥራ ምን ያዋጣኛል የሚለውን ማጥናታቸውን ቀጠሉ። በዚህም ይህንን አማራጭ በቀላሉ ሊተካላቸው የሚችል ዘዴ ቀየሱ።

ሻሸመኔ ሄደው በአካባቢው አጠራር «ጪጬ» የሚሉትን ምርጥ የሚባል አረቄ በማምጣት መሸጥ ለበለጠ ስኬት እንደሚያበቃቸው አስበው ገቡበት። ጪጬ የተባለው በለመዱት ውሃ አረቄ እኩል በመጠቀማቸው ምክንያት ራሳቸውን እስከመሳት ስለሚያደርሳቸውና ጭጭ ስለሚያደርጋቸው እንደሆነ ባለታሪኳ ይናገራሉ።  ከብዙ ነጋዴዎች ጋር በመሆን ሌሊቱን ሙሉ በጭነት መኪና እየተጓዙ ሴትነታቸው ሳይገድባቸው ይህንን ሥራ በመሥራት ውጤታማነታቸው ጎልቶ እንደነበር አይረሱትም።

መጀመሪያ ላይ አረቄው አይሸጥም በማለት በሁለት ሺህ ብር እንኳን መግዛት ፈርተው ነበር። በኋላ ግን ትርፉና የፍላጎት መጠኑ በማየሉ በየቀኑ ከሻኪሶ ተለይተው መዋልን ለመዱት። ጎን ለጎንም የባልትና ውጤቶችን በድጋሚ መሥራት ጀመሩ። ሁለቱ ሥራዎች ይበልጥ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ሲመለከቱ ግሮሰሪ መክፈትን አሰቡ። ከፊት ቤታቸውን አስፈርሰው በሚገባ የግሮሰሪ መልክ እንዲይዝ አደረጉና መጠጦችን ያቀርቡ ጀመር። ይህ ሲሰፋ ደግሞ ምግብ ጨመሩበት። ከ30 በላይ ሠራተኞችንም ይዘው መሥራታቸውን ቀጠሉ። ይሁንና ልጆቻቸውም ሆኑ ሠራተኞቹ በሆነው ባልሆነው ገንዘቡን እያጠፉ አስቸገሯቸው። መቋቋም እስኪያቅታቸው ድረስ ብዙ ገንዘብ አጡ።

የቤቱ መታወቅና የገበያው ስፋት በስድስት ብር ቁርጥ እየተሸጠ በቀን ሦስት ሺህ ብር ይሸጥበት እንጂ እጃቸው ላይ የሚደርስ ብር ዋናው እንኳን አልሆን አለ። በዚያ ላይ ባለቤታቸው ጡረታ ወጥቷል። ከጊዜ ቆይታ በኋላ ደግሞ ታሞ አልጋ ያዘ። ይህ ይበልጥ ለወይዘሮ ማሜ ፈተናን ደራረበባቸው። መሥራት ቢወዱም ባለቤታቸውን ማን ይንከባከበው፤መቆጣጠር ቢሹም ቤቱን ማን ይጠብቀው። ስለዚህ በቅርብ ሳይርቁ የሚሠሩትን ሥራ ማሰላሰል ላይ ገቡ። 

ግሮሰሪውን ባወጣው ያውጣው ብለው ጭርሱኑ ቁጥጥሩን ተውትና ወደ ማስታመሙ ገቡ። ግን ይባስ ብሎ የለፉበትና ያስታመሙትን ባላቸውን በሞት ተነጠቁ። በዚህም ቅስማቸው ተሰበረ፤  ኀዘናቸው በረታ። ግን ቤቱን ማቆምና ስሙን ማስጠራት እንዳለባቸው ስለተረዱ ወዲያው ወደ ሥራ ገቡ። የዚያ ኪሳራ ሊያቋቁማቸው የሚችለውን ሥራ ለማከናወን አቀዱ። በእጃቸው ባለው ገንዘብ መሥራት የሚችሉት የባልትና ውጤቶችን ነውና ትኩረታቸውን ወደእርሱ አደረጉ። ይህ ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን ወደነበረ ማንነታቸው መለሳቸው። አሁን ልጆቹም አደጉ፤ ማሰብና ማገናዘብ ጀመሩ። ስለዚህም ወደ ሃዋሳ መጥተው እንዲሠሩ ይገፋፏቸው ጀመር። ግን እርሳቸው ሻኪሶ ሁሉ ነገሬ ናት ስለሚሉ ቦታውን ለመልቀቅ አልወደዱም። ሁለቱ ልጆቻቸው ግን ሊያስቀምጧቸው አልቻሉም። ቢያንስ ሃዋሳ ላይ ቤት ግዢ እያሉ ይጨቀጭቋቸው ጀመር። በተለይም አንደኛው ልጃቸው ሁሉን ነገር እኔ አግዝሻለሁ በማለት ያበረታቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

እርሳቸውም ፍላጎቱን ለማሳካት ሲሉ ብቻ ቦታ ገዙ። ይሁንና መኖሪያ ቤት ሳይኖረኝ ከሻኪሶ አለቅም የሚል እምነት ነበራቸው። ሆኖም እየተመላለሱ መሥራት ሲጀምሩ ሥራው ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርገው የሃዋሳው እንደሆነ አመኑበትና ሳያቅማሙ የልጆቻቸውን ሃሳብ ተቀብለው ወደ ሃዋሳ መጡ። በዚህም ሆቴሉን ቀጥ አድርገው ያዙት። ትርፋማነታቸው ከቀን ቀን ማየል ጀመረ።

ይሁንና ሠራተኞቹ በጣም ብልጦችና መስረቅ የሚወዱ በመሆናቸው አሁንም ዳግመኛ ለኪሳራ ተዳረጉ። በይበልጥ ደግሞ ቫት የሚል ነገር በመምጣቱ ከጎረቤቶቻቸው ጋር መወዳደር ተሳናቸው። ስለዚህ ሌላ አማራጭ መፈለግ እንዳለባቸው አሰቡ። በስምንት መቶ ብር ሰፊ ቤት ተከራይተውም የሚወዱትን የባልትና ሥራ ጀመሩ። ግን እስኪለምድ ድረስ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለውበታል።

   ከፍተኛ የሸጡት 700 ብር እንደነበርም ያስታውሳሉ። በዚህ ጊዜ ልዩ ውይይት በቤተሰቡ ዘንድ መደረጉንም አይረሱትም። ስለዚህም መጀመሪያ ይሠሩበት የነበረውን ባርና ሬስቶራንት አከራይተው በተከራዩዋት ቤት ውስጥ ከባልትና ሱቁ ጎን ለጎን ትንሽ ሽሮ ቤት ከፈቱ። በዚህም የተሻለ ገቢ ማግኘት በመቻላቸውና የሻኪሶውን ቤታቸውን ሸጠው  ለመኖሪያ የሚሆን ቦታ ገዙ። ይህ ሁሉ የሆነው ግን ሻኪሶ በሚሠሩት የባልትና ሥራ መሆኑን የነገሩኝ ወይዘሮ ማሜ፤ የባርና ሬስቶራንቱ ሙሉ ዕቃ የተሟላውም በዚሁ ሥራ ነው።

ባልትናውም ቀስ እያለ ለመደና አሁን ውጤታማ እየሆነላቸው መሆኑን ይናገራሉ። ለዚህ ሁሉ ያበቃቸው ደግሞ ሥራ ወዳድነታቸውና በተለያየ ጊዜ ሁኔታዎችን እያዩ የሥራ አማራጮችን በዘዴ በመቀየሳቸው መሆኑን ይገልጻሉ። ዛሬ በዚህ ትጋት የተገነባው ቤት በብዙ ነገሮች እየሞላ እንደሆነ የሚያነሱት ባለታሪኳ፤ የቤተሰብ ማህበር መስርተው በመንግሥት እገዛ ቦታ ተሰጥቷቸው የተለያዩ የማምረቻ ዕቃዎችን ገዝተው እየሠሩ ይገኛሉ። ግን አሁንም ችግር እንዳለባቸው ያስረዳሉ። በተለይም የቦታ ጥበትና የገንዘብ ድጋፍ ፈተና እንደሆነባቸውና ለበለጠ ሥራ እንዳይተጉ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።

«ገንዘብ በልጅነት እውቀት ደግሞ በአርባ ዓመት» እንደሚባለው የልጅነት ጉዳይ ተጫጭኗቸው ትርፋማ ነጋዴም ቢሆኑ ብዙ ሳይጠቀሙበት እንደባከነባቸው ያነሳሉ። በተለይም በዱቤና በአልባሌ ነገር የሚጠፋው ብር ቁጥር ስፍር እንደሌለውና ይህ ደግሞ ዳግኛ ብዙ እንዲለፉ እንዳስገደዳቸው ይናገራሉ። «እንዳሰራሬ ዛሬ ላይ ቁጭ ብዬ እበላ ነበር» የሚሉት ወይዘሮ ማሜ፤ ዛሬ ላይ ለሁሉም ልጆች የራሳቸው ቤት እንዲኖራቸው እንኳን እንዳላደረጉ፤ በብድር እንደሚሠሩ። ለማህበራት የሚደረገው እገዛ ለእርሳቸው ብዙም እንዳልሆነ ያነሳሉ።

ቤተሰብ

ባለቤታቸው ለእርሳቸው ያለው ክብር በወቅቱ ካሉት ወንዶች ሁሉ የሚለይ እንደነበር የሚያነሱት ወይዘሮ ማሜ፤ የፈለጉትን እንዲያደርጉ ያበረቷቸው እንደነበር፣ በተቻላቸው መጠን ደግሞ ይደግፏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። እርሳቸው ቢያልፉም አጋዥ ልጆችን ስለሰጧቸው አልሞተም ይሏቸዋል። ምክንያቱም ከጎናቸው የሚያግዟቸውን ልጆች ሰጥተዋቸዋልና ነው። በቤት ውስጥ አምስት ልጆች ያላቸው ሲሆን፤ አራት የልጅ ልጆችንም አይተዋል። ስለዚህም በእነዚህ ልጆች ሁሉ እየተደገፉ ይበልጥ እየሠሩ ይገኛሉ።

 ከዚህ በላይ ግን የአካባቢው ነዋሪዎች ይበልጥ ይወዷቸዋልና ድጋፉ ይበልጥ ያበረታቸዋል። በእርግጥ እርሳቸውም ቢሆኑ ለተቸገረ ደራሽ፤ አለሁ ባይ በመሆናቸው ነው ሁሉም ሰው የሚወዳቸው። በተለይ ተቸገርኩ ላለ እጃቸው አልሰጥም አይልም። በዚህም በአካባቢው ያለ ሰው ሁሉ በርሷ ቆሜያለሁ ነው የሚለው። ሕፃናት ከፍቅራቸው የተነሳ ትልቅ ሰው ቢሆኑም አንቺ እያሉ ነው የሚጠሯቸው። ይህ ሰብሳቢነታቸው ደግሞ ለታላቅ ክብር አሳጭቷቸዋል። ማለትም ሰው ወዳድና አስታራቂ ከእርሳቸው የበለጠ የለም የሚል ስምን ሰጥቷቸዋል።

መልክተ ማሜ

ከተማ አስተዳደሩ ሁለት ዋንጫና በርካታ ጊዜ በውጤታማነታቸው የምስክር ወረቀቶችን ሰጥቷቸዋል። በየጊዜውም የሞራል ግንባታ እንደሚያደርግላቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ማሜ፤ «ማሜ ባልትና የህብረት ሥራ ማህበር» በሚል የምንሠራው ሥራ ብዙዎች እንዲወዱት የሆነው ያለምክንያት አይደለም ይላሉ። ሁልጊዜ ትርፋማነትን ማሰብና ለሌሎች አለመኖር ኪሳራ  ውስጥ ይከታል። ከዚያ ይልቅ ለሰው ጥራት ያለው ነገር አቅርቦ በአቅሙ ልክ እንዲገዛ ማድረግ የብልህ ነጋዴ ባህሪ ሊሆን እንደሚገባ ይመክራሉ። በተጨማሪም አንድን ሥራ ሞክሮ አልሳካ ሲል ተስፋ መቁረጥ ተገቢ እንዳልሆነ ሰዎች ሊያውቁ ይገባል። በባልትና ዙሪያ ብቻ ከአምስት ጊዜ በላይ በተደጋጋሚ ከስሬ ጀምሬዋለሁ። አሁን ግን ጥሩ እንጀራ እንዳገኝ የረዳኝ እርሱ ብቻ ነው። ስለዚህ ከእኔ መውሰድ ያለባቸው ተስፋ አለመቁረጥን ነው ይላሉ። ሰዎች በንግድ ውስጥ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ትዕግስትንና ደጋግሞ መሞከርን ገንዘብ ሊያደርጉ ይገባል።

አንድ አካባቢ የንግድ ሥራን ለመሥራት በአካባቢው የሚፈለገው ምን እንደሆነ ሳይለዩ መግባት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል የሚሉት ወይዘሮ ማሜ፤ የደንበኛ አያያዝ ከምንም በላይ ዋጋው ላቅ ያለ ነው። ከውጭ ዜጎችም ኢትዮጵያውያን መማር ያለብን ይህንን ነው። በትንሹ ሰጥቶ በብዙ መቀበል የሚቻለው ደንበኛን አክብሮ ማስተናገድ ሲቻል እንደሆነ መማር በንግዱ ዓለም ለሚኖር ሰው ይጠቅማል ባይ ናቸው።

አዲስ ዘመን የካቲት 3/2011

ጽጌረዳ ጫንያለው